ወላይታ ሶዶ፡- የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና የሚወስዱ 3 ሺህ 600 ተማሪዎችን እያዘጋጀ መሆኑን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው የመውጫ ፈተና በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም ይሰጣል።
የመውጫ ፈተና አዲስ አሠራር በመሆኑ በተማሪዎች ዘንድ መደናገጥና ፍርሃት እንዳይፈጠር ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን በሥነልቦና የማዘጋጀትና በትምህርታቸው ብቁ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በመደበኛ፣ በርቀትና በክረምት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ተማሪዎች ለመውጫ ፈተናው ይቀመጣሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው ለመውጫ ፈተናው ሂደት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል።
ለፈተናው ውጤታማነት እንዲረዳ የተማሪዎችን የኮምፒዩተር ችሎታ የሚያሳድጉ ሥልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸው፤ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች በሚገኙ የኮምፒዩተር ማዕከላት መሠረታዊ ሥልጠና በመሰጠት ላይ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ኮርሶችን የመከለስና የመማሪያ ሞጁሎችን የማዘጋጀት፣ የፈተና አካባቢዎችን በመለየት ሞዴል ፈተናዎች መሰጠታቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ተማሪ የሆነው ብሩክ አክሊሉ በበኩሉ፤ ለመውጫ ፈተናው አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግሯል።
በዩኒቨርሲቲው አማካኝነት ለፈተና የሚያዘጋጁ ሞዴል ፈተናዎችና የትምህርት ግብዓቶች ተማሪዎች እጅ ላይ ናቸው። በመምህራንና በዩኒቨርሲቲው አመራሮች አማካኝነት የገጽ ለገጽና በድረገጽ የታዘገ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነን ብሏል።
በተጨማሪም ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተጨማሪ ለፈተና ማዘጋጃ የሚሆን የትምህርት ክፍለ ጊዜ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ተማሪው አስረድቷል።
በሰባት የትምህርት ዓይነቶች ላይ ለመውጫ ፈተና እንድንዘጋጅ እየተደረገ ይገኛል ያለው ተማሪው፤ በጥሩ የሥነልቦና ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል።
የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪ የሆነችው አበሩ መኳንንት በበኩሏ፤ የመውጫ ፈተናው አዲስና የመጀመሪያ እንደመሆኑ በአንዳንድ ተማሪዎች ፍርሃት ሊፈጠር ይችላል፤ ይህን ቀድመው የተረዱ መምህራን አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ብላለች።
በዩኒቨርሲቲው መምህራን ከሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ባለፈ ተማሪው በእራሱ ለፈተናው ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በበቂ ሁኔታ በማጥናትና የተለያዩ የፈተና ጥያቄዎች በመሥራት ላይ እንገኛለን ስትል ተናግራለች።
በአሁኑ ወቅት የመመረቂያ ጽሑፍ ከማዘጋጀት በተጓዳኝነት ለአገር አቀፍ የመውጫ ፈተናውም ዝግጅት በማድረጋችን የጊዜ መጨናነቅ ፈጥሮብናል ያለችው ተማሪዋ፤ ካደረግነው በቂ ዝግጅት አንጻር ግን ጥሩ ውጤት እንደምናመጣ እንጠብቃለን ብላለች።
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በ2015 ዓ.ም በሁሉም የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ላይ የመውጫ ፈተና መስጠት እንደሚጀምር ማሳወቁ የሚታወስ ነው።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015