ሁሉንም- በጊዜው …

ልጅነትን በትውስታ…

ልጅነቷን ስታስታውስ አስቀድሞ ውል የሚላት የድህነቷ ታሪክ ነው:: ድህነት አንገት ያስደፋል፣ ከሰው በታች ያውላል:: እሷም ብትሆን ስለቤተሰቡ የከፋ ኑሮ ስትናገር አንዳች ስሜት ይይዛታል:: ችግሩ ቢያልፍም ትዝታውን የምታወሳው ያለአንዳች እፍረት አፏን ሞልታ ነው:: እናት አባቷን ጨምሮ እህት ወንድሞቿ ኑሯቸው ችግር የሞላው፣ ድህነት የፈተነው ነበር::

ታደለች ሀብቴ/ስሟ በእሷ ይሁንታ የተቀየረ/ድህነት በሚፈትነው ቤተሰብ መሀል ማደጓ ብዙ አሳይቷታል:: በእነሱ ቤት በወጉ በልቶ መኖር፣ ለብሶ ማደር ይሉት ብርቅ ነበር:: አካል ጉዳተኛው አባቷ ቤተሰቡን በወጉ ማስተዳደር አይችሉም:: የጉዳታቸው ምክንያት በሆነው ካንሰር አንድ እጃቸው ከተቆረጠ ቆይቷል:: እናቷ የቤትእመቤት ናቸው:: ልጆች ከማሳደግ ያለፈ የገቢ ምንጭ የላቸውም::

ለቤቱ የመጀመሪያ የሆነችው ታደለች በዕድሜዋ ገና ልጅ ነች:: እንዲያም ሆኖ የታናሾቿ ኃላፊነት ወድቆባታል:: እነሱ ቀምሰው እንዲያድሩ፣ ትምህርት ውለው እንዲመለሱ ዋጋ መክፈል አለባት:: እንደ እኩዮቿ ትምህርት ቤት ብትገባም እንደእነሱ የመሆን ዕድል ከእሷ አይደለም::

ምን ቢርባት ከሞሰብ እንጀራ የሚቆርስላት፣ ችግሯን አውቆ የሚረዳላት የለም:: ይህ እውነት ደግሞ የእሷ ብቻ አይደለም:: የእናት አባቷ፣ የእህት ወንድሞቿ፣ የመላው ቤተሰብ እንጂ:: ታደለች ከትምህርት መልስ ቆሎ ይዛ በየቦታው ትዞራለች:: አይቶ የሚገዛት፣ ፈልጎ የሚከፍላት ካለ ‹‹እሰየው›› ነው:: ለእጇ ጥቂት አታጣም:: የያዘችውን ጥሬ በሳንቲም ለውጣ ቤቷ ትደርሳለች:: የተገኘው ትርፍ ቤተሰቡን አይመግብም:: በነሱ ቤት ሲገኝ ተቀምሶ፤ ሲጠፋ አንገት ደፍቶ ማ ደር ተለምዷል::

ውሳኔ …

አንዳንዴ ታደለች ከቤት ከሰፈሩ ብን ብሎ መጥፋት ያምራታል:: ጥቂት ሰርታ ያገኘችውን ብታመጣ ለቤተሰቡ እንደሚበጅ ታውቃለች:: በዕድሜዋ ልጅ ብትሆንም ይህን ማድረግ መሞከሩ ፍላጎቷ ነው:: እንዲህ ማሰቧ ወዳ አልነበረም:: እየተያዩ በችግር ከመሞት ሰርቶ ማግኘትን ታምናለች::

ታደለች ስድስተኛ ክፍል እንደገባች አብሯት የኖረውን ሀሳብ ዕውን ልታደርገው ቆረጠች:: ሚኒስትሪ ከተፈተነች በኋላ በነበሩት ግዚያት ቆሎ መሸጧን አልተወችም:: ጥቂት ቆይታ ግን ሰው ቤት ተቀጥሮ መስራቱን ፈለገችው:: የፈተናዋ ውጤት እስኪመጣ አልጠበቀችም:: ከአካባቢዋ ራቅ ወዳለ አገር ተጉዛ የቤት ሰራተኛ ሆነች::

ታደለች የልጅነት አቅሟ ቢፈትናትም ለድካም ፊት አልሰጠችም:: ርቆ የመውጣቷ ዓላማ ለቁምነገር መሆኑን ታውቃለች:: አንድ ሁለት ብላ የጀመረችው ግዜ ለስምንት ወራት ያህል ተቆጠረ:: አሁን የላብ፣ የድካሟን ደሞዝ ቋጥራ ይዛለች:: ያገኘችው ገንዘብ ለግዜውም ቢሆን ችግር ይፈታል:: ፈተናን ያሻግራል::

እንዳሰበችው ሆኖ ወደ ቤተሰቦቿ ተመለሰች:: ይህ ግዜ ለታደለች የወጣትነቷ ጅማሬ ነበር:: ሰውነቷ አምሮ ተለውጧል፤ ዕድገቷ ጨምሯል:: ለአቅመ- ሔዋን መድረሷ ዓይኖች በተለየ እንዲያይዋት ምክንያት ሆነ:: ለትዳር ታጨች:: ጥያቄው ሲመጣ አልተቃወመችም:: ጎጆ ይዛ ወይዘሮ ለመባል ፈቀደች::

አሁን ታደለች ከልጅነት ወደ አዋቂነት ዕድሜ አልፋለች:: እንደ ትናንቱ ለእናት አባቷ ቤት አታስብም:: የራሷ ጉልቻና ጎጆ አላት:: ጥቂት ግዚያት የዘለቀው ትዳር እንደታሰበው አልሆነም:: ለታደለች ሳይመች ቢቀር በአጭሩ ሊቀጭ ግድ ሆነ:: ወይዘሮዋ ጎጆዋን አፈረሰች፣ ትዳሯን ፈታች::

ከፍቺው በኋላ እንደቀድሞው ወላጆቿ ቤት አልሄደችም፣ ትምህርትቤት አልገባችም:: ሀዋሳ ከተማ ተቀምጣ ልባሽ ጨርቆችን መሸጥ ጀመረች:: በዚህ መሀል ከብቸኝነት ትዳር ይሻል ስትል የሞከረቻቸው ጎጆዎች አልተሳኩም:: ለብቻዋ ልጆች እያሳደገች፣ የእናትነት ኃላፊነቷን ስትወጣ ቆየች::

አሁን ግን ከአንድ ሰው ጋር ትዳር ይዛለች:: ጠዋት ማታ የምትለፋለት ሕይወት ድካም ቢኖረውም ኑሮዋ ቀጥሏል:: አራት ልጆቿ የአንድ አባት ፍሬዎች አይደሉም:: እሷ ግን ለእነሱ አንድዬና ብቸኛ እናታቸው ነች:: የወይዘሮዋ ሕይወት ሩጫ የበዛበት የኑሮ ትግል ያለበት ነው:: ይህ እውነት ደግሞ ለራሷ ግዜ እንዳትሰጥ ለጤናዋ እንዳታስብ አድርጓታል::

የታሸገው ፖስታ …

አንድ ቀን ታደለች እጆቿን ወደገላዋ ሰዳ ሰውነቷን ዳበሰች:: ጣቶቿ የተለየ ዕብጠት ያገኙ ቢመስላት ውስጧ ጥርጣሬ ገባው:: ይህ ስሜት በልቧ ውሎ አላደረም:: ለቅርብ ጓደኛዋ ሁኔታውን አማከረቻት:: ባልንጀራዋ ነገሩን ችላ አላለችም:: ሀኪም እንዲያያት ገፋፍታት ወደ ሆስፒታል አመራች::

የሄደችበት ሀኪም ወደ ሌላ ሆስፒታል ልኮ የምርመራ ውጤቷን ጠበቀ:: በፖስታ ስለመጣው ሚስጥር ወይዘሮዋ ያወቀችው አልነበረም:: በቀጠሮዋ ዕለት ፖስታውን ከሀኪሟ እጅ አድርሳ የሚሆነውን ጠበቀች:: ቀናት የፈጀው የጤና ምርመራ የዋዛ አልሆነም:: በርከት ያሉ ሀኪሞች ከበው ስለእሷ ዕጣ ፈንታ ይወያዩ ይነጋገሩ ያዙ::

ከቀናት በኋላ ለታደለች የማህጸን ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልጋት ተነገራት:: ጉዳዩን በዝርዝር ለመጠየቅ ሞከረች:: ሕክምናው ከበድ ያለ በመሆኑ ማህጸኗ በቀዶ ሕክምና እንደሚወገድ አወቀች:: ይህ አይነቱ ውሳኔ ለእሷ አስደንጋጭና ከባድ ነበር:: በወቅቱ ባለትዳር ስለነበረች ይሁንታዋን ፈጥና ለመስጠት ከበዳት::

በሕክምናው የታሰበው ከመሆን አላለፈም:: ለሕመሟ ከመፍትሄው ለመድረስ ሁሉም በግዜው ተከወነ:: ታደለች በወቅቱ ስለመታመሟ እንጂ ውስጧ ተገኘ ስለተባለው ችግር ያወቀችው አልነበረም:: ውሎ አድሮ ግን ‹‹ካንሰር›› ስለሚባለው ሕመም ምንነት ተረዳች:: እሷ ከዚህ ቀድሞ ይህን ቃል ሲጠራ እንኳን ሰምታ አታውቅም:: ስለሚያደርሰው ጉዳትም መረጃው የላትም::

ሕክምናው ከተጠናቀቀ በኋላ ወይዘሮዋ ስለማህጸን ካንሰር ጉዳቶች የማወቅ ዕድል አገኘች:: እሷ በወቅቱ በመታከሟ የከፋ ስቃይ አላገኛትም:: እንዲያም ሆኖ ግን በስኳር በሽታዋ ምክንያት ቁስሉ ቶሎ ባለመዳኑ ዋጋ ከፍላለች:: አልፎ አልፎ የሚሰማት ሕመም ደግሞ ሰላም የሚሰጣት አልሆነም::

ውሎ አድሮ ግን በሕክምናው እፎይታ ተሰማት:: ቀድሞ የነበራት ሕመም ለቋት የሄደ እስኪመስላት ጤንነቷን አዳመጠች:: ይህ እውነት ካለፈ ጥቂት ግዚያት በኋላ ታደለች ለቀጣዩ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ መምጣት ነበረባት:: አዲስ አበባን ከስም በቀር የማታውቀው ወይዘሮ ስለሚሆነው ሁሉ ሀሳብ ገባት::

ዛሬ ጤናዋ ሙሉ አይደለም:: ማረፊያ ዘመድ ቢገኝ እንኳን ሕመም፣ ችግሯን ይዛ ሰው ፊት መቅረብ ከማስቸገር በላይ ይሆንባታል:: ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለእሷ አዲስና እንግዳ ነው:: ይህ ሁሉ ተግባር ሆኖ ሲመጣ ላትቋቋመው ትችላለች:: እንዲያም ሆኖ የታሰበው አልቀረም:: ስለመኖር ሁሉም ሆነ:: ታደለች ሀዋሳን ርቃ አዲስ አበባ ደረሰች::

አዲስ አበባ…

አዲስ አበባ ለመቆየት ችግሮች ቢኖሩም መታከሟን አልተወችም:: ሕመሙ ጥቂት የማይባል ስቃይ አለው:: ከሀያ ሰባት በላይ የውስጥና የውጭ ጨረር ማድረግና የማስታገሻ መድሀኒቶችን መውሰድ አለባት:: ታደለች ይህን ሁሉ በጥንካሬ ተወጣችው:: የታዘዘላትን ሕክምና ጥርሷን ነክሳ ጀመረች:: ከጨረር ሕክምና ግዜ በድካም መቸገር፣ ራስን ስቶ መውደቅ ያጋጥማል::

በግዜው አብሯት የነበረው ባለቤቷ የቻለውን ሊያግዛት ሞክሯል:: በኋላ ግን መራራቅ ግድ ሆኖ በፍቺ ተለያዩ:: ታደለች በሕመሟ ግዜ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁማ አልፋለች:: ሕክምናው አግዟት ዛሬን ለመቆም ብትበቃም የተራመደችባቸው መንገዶች ሁሉ ሜዳማ አልነበሩም::

ስለ ልጆች…

ወይዘሮዋ ከስድስት ዓመት በፊት በጀመረችው ሕክምና ዛሬን በሕይወት ለመኖር በቅታለች:: ወደቀድሞ ኑሮዋ ለመመለስ ደግሞ በወጉ መስራትና በቂ ገቢ ማግኘት አለባት:: ይህ ግድ የሆነባት ታደለች ሕይወትን ካቆመችበት ቀጥላለች:: ከአራት ልጆቿ ሁለቱ ራሳቸውን ችለዋል:: የተቀሩት ደግሞ በትኩረት ማጣት ጎዳና እንዳይወድቁባት ኃላፊነቱ የእሷ ብቻ ሆኗል::

ዛሬ ላይ ታደለች ወደቀድሞ ንግዷ ተመልሳለች:: ልባሽ ጨርቆችን እያመጣች ለሚገዟት ሁሉ ትሸጣለች:: ይህን ስታደርግ እገዛ የሚያሻቸውን ልጆቿን ከዓይኗ አታርቅም:: ስራው ደግሞ አንዳንዴ እንደታሰበው አይሆንም:: ገበያው ቀንቶ በቂ ገቢ ላይገኝ ይችላል::

ታደለች እንደፊት ሕይወቷ ባለትዳር ባለመሆኗ የቤት ኪራዩን የሚከፍል፣ ኑሮዋን የሚካፈል አጋር የላትም:: ዛሬም እንደልጅነቷ ከአባቷ ቤት ተመልሳ ኑሮ ጀምራለች:: አባት በካንሰር ምክንያት አንድ እጃቸውን ካጡ ወዲህ መተዳደሪያ የላቸውም:: ዕድሜ ከሕመም ተዳምሮ አቅም ቢያሳጣቸው ከቤት ከዋሉ ቆይተዋል::

የታደለች አባት ዛሬም ለልጃቸው ጥላ ከለላ ሆነዋል:: ቤታቸው የቀበሌ ቢሆንም ኩሽናቸውን አድሳ እንድትኖርበት ፈቅደዋል:: ችግሯን የተረዱ የቅርብ ጓደኞቿም መኖሪያዋን በወጉ አስተካክለው ማረፊያዋን አዘጋጅተዋል::

ዛሬ ታደለች ከቤት ኪራይ ወጪና እንግልት መዳኗን ስታስብ ከፈጣሪ ቀጥሎ አባቷን አብዝታ ታመሰግናለች:: ይህ ባይሆን ኖሮ እሷን ጨምሮ ልጆቿ ጎዳና ከመውደቅ አያመልጡም:: ታደለች አሁን ላይ ስለማህጸን ካንሰር ስታስብ ብዙ ነጥቦችን አመዛዝና ነው:: እሷ ስለህመሟ በግዜ መንቃቷን ከፍ ያለ ዋጋ ትሰጠዋለች::

አይረሴ ትዝታዎች…

እሷ ሕክምና ላይ በነበረች ግዜ ያስተዋለችው ብዙ ነው:: አብዛኞቹ ሴቶች ወደ ሆስፒታል የሚመጡት ውስጣቸው ተጎድቶና ችግራቸው ከመድሀኒት አቅም በላይ ሆ ኖ ነ ው:: በ ርካቶቹ ጉ ዳታቸው የ ከፋ በ መሆኑ ስቃያቸው ያይላል:: እንዲህ አይነቶቹ ሕሙማን ሕይወታቸውን ሲያጡ አይዘገዩም:: ታደለች ከእሷ ጋር የነበሩትን ታካሚዎች ዛሬም ድረስ በሀዘኔታ ታስታውሳለች:: የዛኔ ታደለች በዓይን ያስተዋለቻቸው ሴቶች በአቅም ከእሷ የበረቱና የጠነከሩ ነበሩ:: በግዜው ሕክምናውን ባለመድረጋቸው ግን ሕመሙ ከፍቶባቸዋል::

በተለይ ወይዘሮዋ ገነት የተባለችው የቅርብ ባልንጀራዋን መቼም አትረሳትም:: ከእሷ ጋር በተመሳሳይ ቀናት ሲታከሙ ቆይተዋል:: ቀጠሮ በነበራቸው ግዜ በናፍቆት ተገናኝተው ያወጋሉ፣ ያሉበትን የጤንነት አቋም እየለኩ የወደፊት ኑሮና ተስፋቸውን ያልማሉ:: ታደለችና ይህች የልብ ሰው ከቀናት በአንዱ የተለመደውን የሕክምና ቀጠሮ ይዘዋል::

ቀጠሯቸው እየደረሰ ነው:: በዚህ ቀን ሁለቱም እንደቀድሞው ተገናኝተው የልብ ልባቸውን ያወጋሉ፣ ስለኑሯቸው፣ ስለነገ ተስፋቸው እያቀዱ ያልማሉ:: የቀጠሮው ቀን ጥቂት ቀናት እንደቀሩት ለታደለች ጆሮን ጭው የሚያደርግ ዜና ደረሳት:: ወሬው የገነትን ድንገቴ ሞት የሚያረዳ ነበር:: ውስጧን የምታይባት መስታወቷ፣ ነገን የምታልምባት ተስፋዋ፣ ዛሬ እንደልምዷ ቀጠሮዋን አላከበረችም:: እንደትናንቱ ከእሷ ተቀምጣ ላታወጋ፣ ዳግም ነገን እያለመች ፈገግ ላትል ርቃት ሄዳለች::

ለታደለች ይህ ግዜ ልቧን የሰበራት፣ ስለነገው መኖር ተስፋ ያስቆረጣት ነበር:: የገነት ሞት ርምጃዋን እስክትፈራ፣ ተኝታ መንቃቷ እስክትሰጋ አጠራጠራት:: ውስጧ ደጋግሞ አነባ፣ ዕንቅልፏን ተነጠቀች፣ ሰውነቷ ከስቶ ኪሎዋ ቀነሰ:: ጠዋት ማታ ያደረባት ጭንቀት ያለፈችበትን የሕመም ጉዞ አስታወሳት:: ‹‹እኖራለሁ›› ብላ ያደረገችው ቀዶ ሕክምና፣ የወሰደችው ጨረር፣ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ታያት:: በዚህ መሀል ቁምነገር ያልደረሱ ልጆቿ ውል እያሏት ተከዘች፣ ተጨነቀች::

የምክር ኃይል …

ከገነት ሞት በኋላ ቀናት ተቆጠሩ:: ታደለች አሁንም እሷን መርሳት አልቻለችም:: አንድ ቀን ግን ለአንዲት ባልንጀራዋ ቁጣና ምክር ጆሮዋን ሰጠች:: ሰው ሆኖ የማይሞት፣ በሥጋ የማይለይ እንደሌለ ገባት:: ወይዘሮዋ መለስ ብላ ስለራሷ አሰበች:: ጤናዋ በመልካም ሁኔታ ላይ ነው::

በየቀኑ ያለባት ጭንቀት ግን በአንድ ወር ውስጥ አስር ኪሎ እንድትቀንስ አስገድዷታል:: ታደለች ይህን ሁሉ አመዛዝና አሰበች:: የሕይወቷ ትርፍና ኪሳራ አልጠፋትም:: ፈጥና ከጀመረችው አጉል መንገድ መመለስ እንዳለባት ወሰነች:: አደረገችው:: ሁሉን ትታ ፈጣሪዋን አመሰገነች:: የቀድሞ ማንነቷን ለማግኘት አልቸገራትም::

አንዳንዶች ታደለችን ባገኟት ግዜ በገጽታቸው ብዙ ይነበባል:: በሰላምታቸው፣ በዓይናቸው ሀዘናቸውን የሚያሣይዋት ጥቂት አይደሉም:: አብዛኞቹ ካንሰር ታክሞ ይድን አይመስላቸውም:: እሷን ባዩ ግዜ ወዲያውኑ የምትሞት ይመስላቸዋል:: አንድ ቀን ቤቷን ትታ፣ ልጆቿን በትና ስለማለፏ በሹክሹክታ ያወራሉ:: ሁሌም ከጀርባዋ ከንፈራቸውን ሲመጡላት ይሰማታል::

አንዳንዶች ደግሞ ስለታደለች ብርታት ይደነቃሉ:: ከሕመሟ ታግላ፣ ከስራ ውላ መግባቷ ያስገርማቸዋል:: ሕይወት ለመምራት፣ ልጆች ለማሳደግ በምታልፍባቸው መንገዶች ጥንካሬዋን ያያሉ:: ታደለች በእሷ ማንነት ውስጥ የሚገለጸው እውነት ዛሬም ለሌሎች ምሳሌ ሆኖ ቀጥሏል:: አሁንም ስለመኖር እየተጋች፣ ልጆቿን እያሳደገች ነው::

የእሷ አንደበት…

ወይዘሮዋ ሆስፒታል በነበረች ግዜ ብዙ አጋጥሟታል:: እንደእሷ ለሕክምና ስፍራው የደረሱ አንዳንዶች ከሕመማቸው ቶሎ ድነው ለመሄድ ሲጣደፉ አይታለች:: ለመታከም እጅ አጥሯቸው በተስፋ መቁረጥ የሞቱትን ቆጥራለች:: ከምንም በላይ ግን በሕጻናት ሕሙማን ላይ ያየችውን ስቃይ አትዘነጋውም:: ካንሰር ለሁሉም ቀላል የሚባል አይደለም በእነሱ ላይ ሲሆን ደግሞ ሁኔታዎች ይከፋሉ:: በርካቶቹ የሚሰጣቸውን የኬሞ ሕክምና አይቋቋሙም፣ የሚወስዷቸው መድሀኒቶችም ይከብዷቸዋል::

ታደለች ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ዝም አትልም:: ማንም እሷ ባለፈችበት መንገድ እንዲጓዝ አትሻምና ሁሌም ምክሯን ትለግሳለች:: በየግዜው ቃል አንደበቷ አይለወጥም:: ማንኛውንም ሴት ስታገኝ ስለ ካንሰር ታስረዳለች:: በወቅቱና በግዜው ምርመራ የማድረግን ጠቀሜታ ከራሷ ልምድ በመነሳት ታካፍላለ ች::

ወይዘሮዋ ምክሯን ስታደርስ ካለመመርመር የሚመጣውን ጉዳት አትደብቅም:: የካንሰርን አስከፊነት ትገልፃለች:: ይህን የሚሰሙ በርካቶች በድንጋጤ፣ በፍርሀት ይረበሻሉ:: ይህን መስመር አልፈው በግዜ ለምርመራ እጅ የሰጡ ዛሬ እንድሷ በሕይወት ቆመዋል::

ታደለች ምክሯን ችላ ብለው በመዘናጋት የቀሩትን የአንዳንዶች ታሪክ ታውቃለች:: ከነዚህ መሀል የተወሰኑት ዛሬ በሕይወት የሉም:: ይህ በመሆኑ ሀዘኗ ከባድ ነው:: ማድረግ እየተተቻለ፣ የዝምታ ችላ ባይነት ዋጋ ማስከፈሉ ከልብ ያስቆጫታል::

‹‹በካንስር መታመም እንዳለ ሁሉ በግዜ ታክሞ መዳንም ይቻላል›› የምትለው ታደለች በአሁኑ ግዜ ከአፍላነት ዕድሜ ጀምሮ የሚደረገውን የካንሰር መከላከል ክትባት ከልብ ታደንቃለች:: ስለሕይወት ብዙ የሆነችው ወይዘሮ የግዜን ጠቃሜታ የምታሳየው በራሷ ሕይወት መስላ ነው:: ጊዜ ለእሷ ጤናዋ ነው:: ጊዜ ለእሷ ዛሬን ለመቆሟ መሰረት ነው:: ትናንት በወጉ የተጠቀመችው ጊዜ ዛሬ የልጆቿ እስትንፋስ፣ የመኖር ተስፋዋ ሆኗልና::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You