አዲስ አበባ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት በማስተናገድ የሰላምና የዲፕሎማሲ መዲናነቷን አስመስክራለች!

ከተመሰረተች ከ130 ዓመት በላይ የሆናት አዲስ አበባ የብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ፤ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲና እና የተለያዩ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ነች:: ከ90 በላይ ኤምባሲዎችን በማቀፍም በዓለም ላይ ካሉት ጥቂት የዲፕሎማቲክ ማዕከል ከሆኑት ከተሞች ውስጥ ግንባር ቀደሟ ነች::

አዲስ አበባ ከአሜሪካዋ ኒውዮርክና ከስዊዘርላንዷ ጄኔቫ በመቀጠል ልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉባት፤ የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ከተማ ሆና በባለብዙ የትብብር መስኮች አገልግሎት እየሰጠች ነው:: ሆኖም ከተማዋ የዕድሜዋን ያህል ባለማደጓ እና ጭራሹንም ልማቷ የኋሊት ሲጓዝ የቆየ በመሆኑ ከአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷ ጭምር ለማንሳት በርካታ ሙከራዎች ነበሩ::

ከተማዋ ከምስረታዋ ጀምሮ በዘመናዊ ማስተር ፕላን የተቆረቆረች ባለመሆኗ እና ለዘመናትም አስታዋሽ አጥታ በመቆየቷ በእርጅና ብዛት ለመፍረስ ተቃርባ ነበር:: የመሠረተ- ልማት ዝርጋታዋም ሆነ አረንጓዴ ሽፋኗ አንድ ከተማ ሊያሟላ ከሚገባው ዝቅተኛ መስፈርት በእጅጉ የራቀ ሆኖ ቆይቷል:: በሂደትም ስምና ግብሯ የማይገናኙባት ከተማ እስከመሆን ደርሳለች::

ሆኖም የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ ከተማዋ ባገኘችው ትኩረት አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ አበባ የመሆን እድል አግኝታለች:: የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ የሆኑ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑባት ነው:: ከተማዋ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት የሚያበቋት የተለያዩ መሠረተ ልማቶችና የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተከናወኑባት ይገኛሉ:: የአንድነት ፓርክ፤ የወዳጅነት አደባባይ፤ እንጦጦ ፓርክ የመሳሰሉት የቱሪስት መዳረሻዎች ከተማዋ እንደገና እንድታንሰራራ አድርገዋታል::

በመጀመሪያው ዙር የአዲስ አበባን ገጽታ ከመሠረቱ የሚለውጥ የኮሪደር ልማት በአምስት አቅጣጫዎች ተተግብሮ አዲስ አበባን ውበት አላብሷታል::በአሁኑ ወቅትም ሁለተኛው ዙር ኮሪደር ልማት በመፋጠን ላይ ይገኛል:: የኮሪደር ልማቱ የተጎሳቆለውን አዲስ አበባ ገጽታ ለመቀየር ከማስቻሉም በላይ አዲስ አበባ ከአቻ ከተሞች ጋር መሳ ለመሳ እንድትቆምና የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ማዕከል የመሆን እድል አግኝታለች::አስገራሚ በሆነ መልኩም የኮንፈረንስ ቱሪዝም መናኸሪያ ለመሆን በቅታለች::

የኮሪደር ልማቱ ትሩፋቶች የሆኑት የዓድዋ ሙዚየም፣ልዩ ልዩ የመስህብ ቦታዎች እና ማራኪ እይታዎች እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ለስብሰባ የምትመረጥ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል::

ከዚሁ ጎን ለጎንም የመንገድ ዳርቻዎች ኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻዎች አዋሳኝ የተፋሰስ ልማት ፣ የብስክሌትና ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ልማት ፣ ዘመናዊ የትራንስፖርት ተርሚናሎች ግንባታ፣ አገናኝ የኮሪደር ልማት ድልድዮች፣ ማሳለጫዎችና የመጋቢ መንገዶች ልማት፣ የመንገድ ዳር የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ፣ ፋውንቴኖች እና የሕዝብ መናፈሻ ስፍራዎች፣ ወጥ የህንጻ ቀለምና የከተማ መብራት ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ፓርኪንጎች፣ የመኪና መጫኛና ማውረጃ አገልግሎቶችን ጨምሮ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የአዲስ አበባ መለያዎች ሆነዋል::ይህ የአዲስ አበባ ውበት እና ምቹነት ብዙዎችን ወደ ከተማዋ እንዲሳቡ እያደረጋቸው ነው::

ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ ከወዲሁ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነቷን አስመስክራለች:: ባለፉት ሶስት ወራትም ከረሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤ፣ የካፍ ጉባኤ፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የአፍሪካ ንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤና ሌሎች ጉባኤዎችን በስኬት ማስተናገድ ችላለች:: ይህም የሆነው አዲስ አበባ ባላት ሰላም፣ የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ በማደጉና ሆቴል እና አየር መንገድን ጨምሮ በዘመኑት የመሠረተ ልማት ግንባታዎቿ ምክንያት ነው:: ከአፍሪካ አልፎ የዓለም የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ የመሆን አቅም ያላት ከተማ መሆኗን አስመስክራለች::

በአጠቃላይ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አዲስ ለማድረግና አልፎ ተርፎም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያሟላች ከተማ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው:: የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ መለወጥም የአፍሪካ መዲናነቷን ለማጽናት ከማስቻሉም ባሻገር ከተማዋን የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃት የማይተካ ሚና እንድትጫወት ያደርጋል!

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You