24ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር መነሻና መድረሻውን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አድርጎ ሲካሄድ 50 ሺህ ሰው እንደሚሳተፍ ታውቋል:: ዘንድሮ 50 ሺህ ሰዎች በውድድሩ የሚሳተፉት ሉሲ (ድንቅ ነሽ) የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር እንደሆነ ተገልጿል::
የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ‘’የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ህጻናት’’ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን፣ የተመጣጠነ ምግብ ለህጻናት አካላዊ እና አዕምሯዊ ዕድገት ያለውን የላቀ ፋይዳ ለስፖርት ቤተሰቡ ለማስገንዘብ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል::
የውድድሩ አዘጋጆች ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሩጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ ለ 6 ወራት ያህል ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል:: በዓመታዊው ውድድር ዘንድሮ 50 ሺ ሰዎች ሲሳተፉ ፤ ይህም ከአፍሪካ ተሻግሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ በማሳተፍ ከጥቂት ውድድሮች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል።
ከ20 በላይ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ከ500 የሚበልጡ የጤና ሯጮች እና ታዋቂ አትሌቶች በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ የተጠቆመ ሲሆን፣ ትልቅ ስም ካላቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንስቶ የረጅም ርቀት ውድድር ከዋክብት የሆኑ የዩጋንዳ እና ኬንያ አትሌቶች የውድድሩ ተፎካካሪ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል በወንዶች የሶስት ጊዜ የመድረኩ አሸናፊ አትሌት አቤ ጋሻው እና የአምና ባለድል አትሌት ቢኒያም መሃሪ፣ ይስማው ድሉና ኤርሚያስ ግርማ በውድድሩ ይሳተፋሉ ተብሏል:: ቢንያም አምና ውድድሩን ሲያሸንፍ፣ በ1999 ዓ.ም አሸናፊ የነበረው አትሌት ዲሪባ መርጊያ ካስመዘገበው ሰዓት በአንድ ሰከንድ ብቻ ዘግይቶ ነበር ያጠናቀቀው::
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ፉክክር የአምስተርዳም 10 ማይል ውድድር አሸናፊዋ አትሌት አሳየች አይቸው፣ የ2016 ዓ.ም ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር አሸናፊ ጉተኒ ሻንቆ እንዲሁም ብርነሽ ደሴና መቅደስ ሽመልስ ተሳታፊዎች እንደሚሆኑ ተጠቁሟል::
የውድድሩ መነሻዎች ሁለት ሲሆኑ፣ ይህም 10ሺ የሚሆኑ ፈጣን ሯጮች መነሻቸውን ከጊዮን ሆቴል የሚያደርጉ በመሆኑ ከ1 ሰዓት በፊት ሥፍራው ላይ መገኘት እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል። የተቀረው ለመዝናናት የሚሮጡት ደግሞ በተለመደው ሥፍራ መነሻቸውን ያደርጋሉ። የአዋቂ አትሌቶች ውድድር ከሌሎች ተሳታፊዎች ውድድር በአምስት ደቂቃዎች ቀድሞ እንደሚጀምር አዘጋጆቹ ጠቁመዋል::
የውድድሩ መሥራች እና ባለቤት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በጋዜጣዊ መግለጫው ባስተላለፈው መልዕክት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሃይማኖት፣ ፖለቲካና ብሔር የሌለው በመሆኑ ተሳታፊዎች ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብተው ወደ ውድድር ቦታው መምጣት ይጠበቅባቸዋል ብሏል::
ኃይሌ አክሎም ውድድሩ በዓለማችን እንደሚካሄዱት ታላላቅ የጎዳና ላይ ውድድሮች እንዲያድግ በተጠናከረ መልኩ እንደሚሠራ ጠቁሟል:: የሚያሸንፉ አትሌቶችም በዓለም አትሌቲክስ ማህበር እንደሚመዘገቡ ተናግሯል::
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፣ “ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ የአትሌቶች መፍለቂያ መሆኗን ለዓለም የምናስመሰክርበት የተግባር ማሳያ” ነው ብለዋል:: በዓለም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ያውለበለቡ አትሌቶቻችን የሚከበሩበትም መድረክ መሆኑን አስታውሰው፤ የአትሌቲክስ ዘርፍ ለቱሪዝም ትልቅ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ ከተሠራ ኢትዮጵያንና አፍሪካን ማሳደግ እንደሚቻል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል:: አትሌቲክሱ ኢትዮጵያ ድንቅ አትሌቶች መፍለቂያ ብቻ ሳትሆን የዓለም አትሌቶች መዳረሻ ማድረግ የሚችል አቅም መኖሩንም ጠቁመዋል::
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ የውድደሩ ዋና መሥራች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ማሸነፉ ይታወቃል:: የዓለም አትሌቲክስ የ2017 ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ሩጫን የሌብል (Label Road Race) ያለው ውድድር ብሎ ዕውቅና መስጠቱ ይታወቃል::
ዘንድሮ በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የሽልማት ገንዘብ መጠንም መጨመሩ የተገለጸ ሲሆን፤ ለዚህም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር መዘጋጀቱ ታውቋል። የውድድሩን ክብረወሰን የሚያሻሽሉ አትሌቶች ከዋናው ሽልማት በተጨማሪ 50ሺ ብር ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል:: በቅርቡ በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን የዓለም ክብረወሰንን ያሻሻለችው ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕንገቲች እና አየርላንዳዊው የቀድሞ አትሌት ኤሞን ኮግላን በክብር እንግድነት በውድድሩ ይታደማሉ።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም