ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ

አዲስ አበባን ለዜጎቿ ምቹ እና ስማርት ዓለም አቀፍ ከተማ ለማድረግ ታቅዶ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ አንደኛውን ምዕራፍ በማጠናቀቅ ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ ሥራ ተገብቷል። የኮሪደር ልማቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅጣጫ ሰጪነት የመዲናዋን የመሠረተ ልማትና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያለመ ነው።

የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በዋናነት በከተማዋ ፋይናንስ የሚሸፈን እና የሚተዳደር ነው፡፡ በፌዴራል ተቋማት በቅንጅት የሚሠራ በመሆኑ በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ይገመታል፡፡ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባሉት ተቋማት ከፍተኛ ድጋፍ ያለው መሆኑን መረጃዎች አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ የሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት አስመልክተው ባለፈው ረቡዕ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት፤ ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት እየተሠራ ነው።

በከተማዋ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በተመረጡ አምስት የኮሪደር ልማት መስመሮች በዋነኛነት ከመንገድ ጋር የተያያዙ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ የተጀመረ መሆኑን ይገልጻሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ስድስት ኮሪደሮች ተመርጠው እንደነበር ምክትል ከንቲባው አስታውሰው፣ ይህን በማሰፋት ስምንት ኮሪደሮች መመረጣቸውን አስታውቃል፡፡ በእነዚህ ኮሪደሮችም 135 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከሁለት ሺህ ስምንት መቶ ሄክታር በላይ ስፋት የሚሸፍኑ ትልልቅ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባው እንደተናገሩት፤ ከሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አንዱ ከሳውዝ ጌት /ደቡብ በር/ ነው፡፡ ይህም ዲያስፖራ አደባባይ መገናኛ ፣መስቀል አደባባይ ፣ ከመስቀል አደባባይ ወደ ሜክሲኮ ከዚያም ቸርችር ጎዳና እንዲሁም ወደ አራት ኪሎ ዞሮ ካዛንቺስን መልሶ ማልማት ይዞ ሰፊውን አካባቢ የሚሸፍን ነው።

ሌላው ደግሞ ከአራት ኪሎ ሽሮ ሜዳ እንጦጦ የኮሪደር ልማት ነው። በሌላ መንገድ ደግሞ (በተለምዶ ሲኤምሲ አካባቢ የሚገኘው አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል ይዞ በሰሚት በቀጥታ ወደ ጎሮ) ከዚያ ደግሞ የቪአይፒ መግቢያ ወደ ሆነው ቦሌ አየር ማረፊያ የሚደርሰው ኮሪደር ነው። በተጨማሪም ቀደም ሲል ከተጀመረው ከሳር ቤት በቀጥታ ወደ ለቡ እና ላፍቶ ፉሪ የሚታጠፈው አንዱ ትልቁ የኮሪደር ልማት ነው።

በልማቱ ትልልቅ የወንዝ ዳር ልማት ሥራዎች ይካሄዳሉ። ይህም ከእንጦጦ በቀጥታ እስከ ፒኮክ የሚደርስ ወደ 21 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚሸፍን ትልቅ የወንዝ ዳር ልማት ይካሄዳል። ከጉለሌ፣ ከየካ ጫፍ በመነሳት በቀጥታ በቀበና ግንፍሌ፣ ወደ ፒኮክ የሚገጥሙ የወንዝ ዳር ልማትን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 135 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የመንገድ ርዝመት ያለው አካባቢን ይሸፍናል።

ከላይ በተገለጹት ሥራዎች መካከል የአስፋልት መንገድ አለ፤ በዚህም መካከል 237 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የእግረኛ መንገድ፣ የልጆች መጫወቻ ቦታዎች፣ 79 ያህል የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ይገነባሉ። 111 ኪሎሜትር የሚሸፍን የብስክሌት መስመር እንዲሁም 114 የሚደርሱ የፓርኪንግ እና ተርሚናል አገልግሎት መስጫዎች በዚህ ኮሪደር ሥራ እንደሚለሙ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

ከምድር በታች የሚሠሩትን ጨምሮ 50 የሚደርሱ የእግረኛ ማቋረጫዎች እና ድልድዮች በግንባታው መካተታቸውን ጠቅሰው፣ የእግረኛ እና የመኪና ማቋረጫዎች የትራፊክ አደጋ በማያደርሱ ሁኔታ የከተማዋን ደረጃ በሚያሳድግ መንገድ ፕላን ተደርገው እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ የስፖርት ቦታዎች፣ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓቶች፣ የከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ መብራቶች፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች እና የደኅንነት ቴክኖሎጂዎች በልማቱ መካተታቸውንም አብራርተዋል።

አቶ ጃንጥራር በአጠቃላይ የኮሪደር ልማቱ የልማት ተነሺ ነዋሪዎች የማስተናገዱ ሥራ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህም የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን በማሻሻል፣ በማስተካከል፣ መሠረተ ልማት በማሟላት እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ።

የካሳ ክፍያ እና የመሳሰሉ ጉዳዮችን የማስተናገዱ ሥራም እንዲሁ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተቀሩትንም በፍጥነት ለማስተናገድ ከተማዋ ሌት ተቀን ፕሮጀክቱን እያካሄደች መሆኗን ተናግረዋል። ሁሉም አመራሮች በተመደቡበት እየሠሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ የሚገኙ ሰነድ አልባ ቤቶችን ጉዳይም በመመሪያው መሠረት እንዲሁም የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለመፍታት እየተሠራ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ሰነድ አልባ ሆነው የቆዩ ነገር ግን ሰነድ ሊሰጣቸው የሚገባቸው በርካታ ቤቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ሰነድ አልባ ሲባል በሕገወጥ መንገድ የተገነባውን ሁሉ ማለት አይደለም፡፡ ሰነድ አልባ ሊያስብሉ የሚችሉ መመዘኛዎች አሉ፡፡ በእነዚያ መመዘኛዎች አማካይነት ሰነድ አልባ ለሆኑት ቦታ ተዘጋጅቶ ይሰጣቸዋል። ይህ መልካም አጋጣሚ ለእነዚህ ባለሰነድ አልባዎች ዘላቂ ሕይወት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣ መብታቸውን የሚያረጋግጡበትና በራሳቸው ይዞታ ላይ ዘላቂ በሆነ መንገድ ማልማት የሚችሉበት ዕድል ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከካሣ ክፍያ ጋር ተያይዞ ስለሚነሳው ጉዳይ ምክትል ከንቲባው እንደተናገሩት፤ ለግል ባለይዞታዎች ካሣ ይከፈላል። ካሣ መክፈል ብቻ ሳይሆን በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የግድ ቤት ተከራይተው መኖር ስለሚገባቸው ለሁለት ዓመት የሚሆን የቤት ኪራይ የሚሆን ክፍያን ጨምሮ የማጓጓዣ አቅርቦት በማድረግ በካሣ ሕጉ መሠረት የማንቀሳቀስ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ይህ ግን ለግል ባለይዞታዎች ብቻ የሚፈጸም ነው። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚገልፁት ሳይሆን ግምት የሚሠራው ለቤቱ እንጂ ለመሬቱ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ጃንጥራር እንዳመላከቱት፤ ለመሬት ዋጋ ተብሎ የሚሠራ የካሣ ስሌት የለም። አንድ ሰው የካሣ ክፍያውን ቤቱን ከመሬቱ ጋር የሚሸጥበትን ዋጋ አስቦ ካየው የዚህ አይነት ጥያቄዎች በትክክል ሊመጡ አይችሉም። መሬት በመስጠት ከዚያ ባሻገር ግምት ነው የሚሰጠው። ቦታ ስለሚስተናገድ እና ስለሚሰጥ ካሣ የሚሠራው ለቤቱ ግምት ነው። የቤቱ ግምት ደግሞ በወቅታዊ ዋጋው ታሳቢ ተደርጎ የሚሠራ ነው። አሁን ባለው ወቅታዊ ዋጋ በየጊዜው የዲዛይንና የግንባታ ቢሮ የዋጋ ጥናት ክለሳ ያደርጋል። በዚያ ጥናት መነሻነት አንድ ግንባታ የሚያወጣው ዋጋ ተሰልቶ የካሣ ክፍያ የሚስተናገድ መሆኑን አስረድተዋል።

የካሣ ክፍያ ከቀበሌ ቤት ጋር መገናኘት እንደሌለበት ጠቁመው፣ የቀበሌ ቤትና ኮንደሚኒየም በመንግሥት በኪራይ እየቀረበ ነው ብለዋል። ይህም በባሕሪው የተለየ መሆኑን ጠቁመው፤ ማጓጓዝ ከመክፈል ውጪ የቀበሌ ቤቱ የመንግሥት ቢሆንም ዜጎች መኖር ስላለባቸው ምትክ ቤት የመስጠት ጉዳይ ነው። በዚያ መንገድ ማየት እንደሚገባው አመላክተዋል።

ምክትል ከንቲባው እንዳብራሩት፤ ወደ ፊት ገና እየጠሩ የሚሄዱ መረጃዎች ቢኖሩም እስካሁን በተደረሰበት ወደ ሁለት ሺህ 74 የሚሆኑ የግል ባለይዞታዎች በልማቱ ተነሺ ናቸው። ከእነዚህ የልማት ተነሺዎች መካከል እስካሁን ከ500 በላይ የሆኑት ተስተናግደዋል፤ እስካሁን ባለው ግምት ደግሞ ወደ ስምንት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የካሣ ክፍያ ግምት ተሠርቷል። ከዚህም ውስጥ አራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል።

ይህም ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ለቀሪዎቹም ካሣና ማጓጓዣ ሳይከፈል እንዲሁም የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ ክፍያ ሳይፈፀም የሚቀር አይሆንም ሲሉ ምክትል ከንቲባው አስታውቀው:: ቦታቸው ላይ መሬት ተሸንሽኖ ሳይቀርብ የሚቋረጥበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ መሬት ተሸንሽኖ ቀርቦ በኪራይ ቤት የሚቆዩበት ሁኔታ ላይ መተማመኛ በመስጠት ልማቱም መቆም ስለሌለበት በመተማመን የሚከናወኑ ሥራዎች ምናልባት ሊኖሩ ይችላሉ። በመሠረተ ልማቱ ሂደት ከሁለት ሺህ 74 ቤቶች ውጪ ካሣ የሚገባቸው እና የሚነሱ ካሉ በየጊዜው ቁጥሩ እየተሻሻለ የሚሄድ ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ በትክክለኛ መረጃ ላይ በተመሠረተ ሁኔታ የሚስተናገዱበት ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ መሆኑ አቶ ጃንጥራር አስገንዝበዋል።

የመሠረተ ልማት አልተሟላም ጥያቄዎች በየጊዜው እየተፈቱ መሆናቸውን ጠቁመው፣ መጀመሪያ አካባቢ በተለይ በቦሌ አራብሳ ከመንገድ፣ ከውሃ፣ ከመፀዳጃ ቤት፣ ፍሳሽ ማስወገጃና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በዘመቻ እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከውሃም፣ ከመንገድም ለዚህ ተብሎ ቡድን ተቋቁሞ እየተሠራ ነው። በዚህም ሁሉንም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። ሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶችንም የማልማት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ገበያ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የፋርማሲ አገልግሎት በተለይ ገላን ጉራ፣ አቃቂ አካባቢ ለነዋሪዎች በሚመች ሁኔታ የማሟላት ሥራ በከፍተኛ ዘመቻ እየተከናወነ ነው። በሌሎችም አካባቢዎች ጉድለት ባለባቸው ሁሉ የከተማ አመራሩ በንቃት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ አሁን አብዛኛዎቹ ችግሮች የተፈቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሰፋ ችግር የለም፤ የሚጎድሉ ካሉም እየታዩ ይሞላሉ ብለዋል።

የሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ጠቅሰው፣ የመጀመሪያው ጉዳይ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቅ ይሆናል ብለዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ይህንንም ለማድረግ ቅድሚያ ዜጎችን ማንሳት፣ ቤት መስጠት፣ ምትክ ቦታ መስጠት፣ የመስተንግዶ ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ይሠራል። ከዚያም ተያያዥ የመሠረተ ልማት ሥራዎች፣ የሕዝብ ፕላዛዎች፣ ፓርኮች እና የመሳሰሉ ሥራዎች ይሠራሉ።

አሁን በስፋት የተገባበት የካዛንቺስ መልሶ ማልማት ሥራ በስፋት እየተሠራ መሆኑ ጠቅሰው፣ ቦታው ነፃ ተደርጎ የግንባታ ሥራው ተጀምሯል፡፡ ሌሎችም ኮሪደሮች ላይ በተወሰነ ደረጃ ሳይቶች ነፃ እየተደረጉ ናቸው። የኮንስትራክሽን ሥራው ተቋራጭ ምደባ ተደርጓል። አማካሪ ተመድቦ ወደ ሥራ ተገብቷል። ልማቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚቻል መሆኑን አብራርተዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የቴሌ፣ የውሃና የመሳሰሉት በሙሉ አንድ ቡድን እንዲመራቸው እንዲሁም ራሳቸውን የቻሉ አንድ ዲዛይን እንዲኖራቸው ተደርገዋል። በዚያም ሁሉም መሠረተ ልማት እና አገልግሎት የሚዘረጉ ተቋማት አብረው የሚሠሩበት እና አመራሩም ሥራውን በቅደም ተከተል መከናወኑን የሚከታተልበት ሁኔታም ተመቻችቷል ሲሉ አስታወቀዋል።

የውሃ፣ የቴሌ፣ የመብራት መስመሮች ተቋማት በጋራ ሆነው ሥራዎችን የሚያሳኩበት ሁኔታ ዲዛይን ተደርጎ እየተተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል። በግንባታ ሂደት የሚያጋጠሙ እክሎች ካልሆኑ በስተቀር የቅንጅቱን ችግር ለመፍታት መቻሉን ጠቁመዋል። የፌዴራል ተቋማትም አብረው እየሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ትምህርት የሚወሰድበት እና ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ከአንደኛው ምዕራፍ የተወሰዱ ልምዶችን በመቀመር በተሻለ እና ረጅም ጊዜ ማገልገል እንዲችሉ ታሳቢ በማድረግ ሥራዎች በጥራት እንደሚሠሩ አመላክተዋል። በተለይም ከአራት ኪሎ ቦሌ፣ ከጫካ ፕሮጀክት እስከ ቦሌ በተዘረጉ መንገዶች የሚሠሩት የእግረኛ መንገድ የኮንክሪት ሥራዎች ከውበትና ከዘለቄታዊነት አኳያ ማሻሻያ የተደረገባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሁለተኛውም የኮሪደር ልማት የተሻለ ወጪ ቆጣቢና ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል የእግረኛ መንገድ ታሳቢ ተደርጎ በኮንክሪት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል። በተለይ በዋና ዋና መንገድ፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው ትላልቅ አደባባዮች ባለባቸው ቅድሚያ ይሠራል። በቀጣይም ለሁሉም አካባቢ ደረጃው የጠበቀ የእግረኛ መንገድ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ የሚሠሩ ሥራዎች ሰው ተኮር መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በሁለተኛው ኮሪደር ልማት ማሳካት ከተቻለው አንዱም የልማት ተነሺዎችን ማኅበራዊ ትስስር በጠበቀ እንዲሁም የትምህርት፣ የጤና እንዲሁም የግብይት አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ በተለይ በተቀራረበ መንገድ ያሉ በአንድ ቀጠና ዕጣ እንዲወጣላቸው በማድረግ እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ጃንጥራር አመልክተዋል።

በኃይሉ አበራ

 አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You