ሀገራችን የዜጎቿን ሕይወት ሊቀይሩ፣ ኢኮኖሚዋን ሊያበለጽጉ፣ ገጽታዋንም በእጅጉ ሊለውጡ የሚችሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለጸጋ መሆኗ ሀቅ ነው:: ሊታረስ የሚችል ሰፊ ለም መሬት፣ ለመስኖ ሊውል የሚችል የገጸ እና የከርሰ ምድር ውሃ በአያሌው አላት፤ ዓባይን ያህል ወንዝ ከእነ ትላልቅ ገባሮቹ ይዛ እንዴት የተፈጥሮ ሀብት ባለጸጋ አትሆን !
ግሩም አየር ንብረት፣ በቂ ዝናብ ያላት ሀገር ናት:: በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ ከዓለምም ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ እንደሆነችም ይታወቃል:: በማእድን ሀብቷም እንደዚያው ናት፤ ወርቋን፣ በከርሰ ምድር አጭቃ የያዘቻቸውን ሌሎች ማእድናቶቿን የማያውቅ የለም፤ በግብርና ምርቷ በተለይ በቡናና ቅባት እህሎቿ ዓለም ያውቃታል:: በቱሪዝም ሀብቷ፣ በሕዝብ ብዛቷ፣ በቃ በብዙ ነገር ባለጸጋ ነች:: የማልጨርሰ ውን ጀምሬ ….
ይህ ሁሉ እምቅ አቅም ግን ሕዝብን፣ ሀገርን ቀና ሳያደርግ ነው የኖረው:: ለማልማት ፍላጎቱ ሳይኖር፣ ከፍላጎት አልፎም ሳይሞካከር ቀርቶ አይደለም:: ሲሞከር ሲከሽፍ ተኖሮ እንጂ:: እንደው የቅርብ የቅርቡን እንኳን ብጠቅስ ከለውጡ በፊት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ስኳር በስኳር ልንሆን በየቦታው ያልወጠነው አልነበረም፤ ምን አገኝን? ምንም::
ባለማዳበሪያ ፋብሪካ ልንሆን አውርተን አውርተን ብዙ ቢሊዮን ብሮችን አፍሰን የብዙ ቢሊዮን ብር እዳ እንጂ ማዳበሪያ አላየንም:: በቆዳው ዘርፍ ልንደርስ የታቀደበት ቦታም ይታወሰኛል፤ ያ ሁሉ ህልም ሆኖ ቆዳ መጣል ውስጥ ገብተናል፤ ዱሮ ያልጣልነውን በዚህ ዘመን ጣልነው፤ ዱሮ ዋጋ ነበረው::
በዓባይ ግድብ ግን ተሳክቶልናል፤ የዓባይ ግድብ ለእኔ የብዙ ፕሮጀክቶች ግምት ነው:: በሌሎች ያልተሳካልንን በዓባይ ተከስናል:: በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ተዋጥቶልናል፤ በውሃ ኃይሉም በንፋስ ኃይሉም በጸሀይ ኃይሉም ብዙ ብዙ ሰርተናል:: በእርግጥ ትልቅ ነገር ነው::
ስንዴ በሀገራችን ብዙ ታሪክ አለው:: በተለይ በእነዚያ በድርቅ ወቅቶች የካናዳ ስንዴ ብዙ ተብሎለታል:: እርዳታ ሲታሰብ ስንዴ ነው በኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ ቀድሞ የሚመጣው:: በእነዚያ ወቅቶች ብቻም ሳይሆን ብዙም ሩቅ ባልነበሩት ከዓመታት በፊትም የእርዳታ ስንዴ ይጠቀስ ነበር::
ስንዴ በእርዳታው ብቻ አይደለም ይጠቀስ የነበረው፤ ለዳቦ፣ ለፓስታም ሆነ ለመኮሮኒ ፋብሪካዎች ሀገሪቱ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮችን በማውጣት ስንዴ ከውጭ ታስመጣ እንደነበር ይታወቃል:: ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሸማቾች በኩል ስንዴ ሲቀርብ አስታውሳለሁ:: የስንዴው ጥራት አጠያያቂ ሆኖ ሲያወያይም እንደነበርም ይታወቃል:: በዚህ ላይ ሀገሪቱ በውጭ ኃይሎች ይደርስባት በነበረው ጫና ሳቢያ የውጭ ምንዛሬው እያላት ስንዴ የምትገዛበት ቦታ እንድታጣም ተደርጋ ነበር::
ይህ ሁሉ ግን ለደግ ሆነ፤ ጠንካራ አደረገን:: ጥቃቱ የገባው የለውጡ መንግሥት ይህን ታሪክ ገለበጠው፤ ሀገሪቱ በቁጭት ወደ ስንዴ ልማት ገባች:: በክረምት ወቅት ዝናብ/ በመኸር ግብርና/ ላይ ተመስርቶ የሚካሄደው የስንዴ ልማት ይበልጥ እንዲጠናከር ተደረገ፤ መንግሥት የበጋ መስኖ ልማት ውስጥ እንዲገባ አደረገ፤ የስንዴ ልማቱ ውጤት ይዞ ከተፍ አለ:: የሀገሪቱ የግብርና ሥራ በእዚህ ልማት እምርታ ተመዘገበበት::
በመኸር እርሻውም የሚመረተው የስንዴ መጠን እየጨመረ በመስኖ የሚለማውም በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ ሀገራዊ የስንዴ ፍላጎትን መመለስ ተቻለ:: ሀገሪቱን ስንዴ ከውጭ ከመግዛት አወጣት:: ለስንዴ ግዥ የሚውለው የውጭ ምንዛሬ ለሌላ ልማት የሚውልበት ሁኔታ ተፈጠረ፤ ስንዴ ለጎረቤት ሀገሮች ገበያ እስከማቅረብ ተደረሰ::
ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር በስንዴ ልማቷ በአርአያነት መጠቀስ ጀምራለች:: ገና ብዙ ታምር ይሰራል:: ሀገሪቱ ዘንድሮ 300 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደምታመርት ይጠበቃል:: ትልቅ ስኬት::
ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገው የድንጋይ ከሰል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከውጭ ነበር የሚገዛው:: ጥሬ እቃው ሀገር ውስጥ እያለ ነው ይሄ ሁሉ ያለፉትን ዘመናት ሁሉ ከውጭ እንዲመጣ ሲደረግ የኖረው:: ገቢ ምርትን ለመተካት የተጀመረው ሥራ የድንጋይ ከሰል ፍላጎትም በሀገር ውስጥ ምርት የተተካበትን ሁኔታ ፈጠረ::
በኢንዱስትሪውም መስከ እንዲሁ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ዘመናትን ከኖሩበት የአገልግሎት ዘርፍ ወደ በአምራች ዘርፉ እየመጡ ናቸው:: ለውጭ ባለሀብቶች ብቻ ይፈቀዱ የነበሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በስፋት እያስገቡ ናቸው። የኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረት አቅም እየጨመረ ነው:: በተለይ ተኪ ምርት ላይ በስፋት መስራት ጀምረዋል:: ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፤ ገና ብዙ ለውጥ ግን ያስፈልጋል::
በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን እንደ ስሟ አበባ ማድረግ ጀምሯል፤ ልማቱ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች የተዘረጋው ሰፊ ዘመኑን የዋጀ መሰረተ ልማት፣ በቀጣይ የሚፈጠሩ ኢንቨስትመንቶች፣ ወንዞቿን ለማልማት የተጀመሩ ሥራዎች ከተማን መለወጥ እንደሚቻል ያመላከቱ ናቸው::
በፕሮጀክቶች መጓተት ብዙ የተፈነች ሀገር ፕሮጀክትን ለሰባት ቀናት ለ24 ሰአት በመስራት በተባለው ጊዜ የሚጠናቀቅባት አንዳንዴም አስቀድሞ የሚጠናቀቅባት ማድረግ እየተቻለ ነው:: በተለይ በአዲስ አበባ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በገበታ ለሸገር በገበታ ለሀገር የተመዘገቡ የፕሮጀክት አፈጻጸሞች እየታየ ያለው ለውጥ ፕሮጀክት እንዳይጓተት ማድረግ እንደሚቻል በሚገባ ማመላከት ያስቻሉ ናቸው::
ገቢ የመሰብሰብ አቅም በየዓመቱ በብዙ መቶ ቢሊዮኖች እየጨመረ ይገኛል፤ በአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እድገት ከእቅድ በላይ እየተመዘገበም ይገኛል:: እድገቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የመሰከሩለት ይህ እድገት እንደሚቀጥል ይጠበቃል::
የወጪ ንግድ ገቢ እየጨመረ ሲሆን በተለይ ቡና እያሰገኘ ያለው የውጭ ምንዛሬ በየዓመቱ እምርታ እየታየበት ነው:: በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በችግኝ ተከላ እየተከናወነ ያለው ተግባር ስኬታማነት ሀገርንና ዜጎችን ከፍ ብለው እንዲታዩ ያደረጉ ናቸው:: በሌሎች በርካታ ዘርፎችም ተመሳሳይ ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው::
እነዚህ የተመዘገቡ ስኬቶች በእርግጥም በሚገባ ያጣጣምናቸው ስኬቶች ናቸው:: በሥራ በጥረት የተመዘገቡ ናቸውና ልንኮራባቸው ይገባል:: በኩራት ስሜት በእርካታ ስሜት ግን ልንዝናና አይገባም:: ስኬቶቹን ለማስመዝገብ ያስቻሉ አሠራሮችንና የመሳሰሉትን ልምድ ቀስመንባቸው ለቀጣይ ሥራዎች ስንቅ የምንቋጥርባቸው ናቸው::
ይቺ ሀገር ወባንና ኤችአይቪአድስን በመቆጣጠርና በመከላከል ብዙ ርቀት መጓዟ ይታወቃል:: የኤችአይቪን ስርጭት መግታት ተችሎም ነበር:: በወባም እንዲሁ ብዙ ውጤት ተመዝግቦ ነበር:: ድሉ ግን መዘናጋትን አስከትሏል፤ ይህም ሁኔታ ችግሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራበት እያስገደደ ነው::
አሁንም በልማቱ መስክ በተገኙ ስኬቶች ረክቶ መኩራራት አይገባም እላለሁ:: ሀገርና ሕዝብ ከሚጠብቁት አኳያ ብዙ መሰራት እንዳለበት መንግሥት በተደጋጋሚ ያስገነዝባል:: ስኬቶቹ የበለጠ ቢሰራ የበለጠ ውጤታማ መሆንን ያመላክታሉ:: ስኬታማ መሆን ተጀመረ፤ አልፎም ተርፎ ስኬቱን በተደጋጋሚ ማስመዝገብ ተቻለ እንጂ የሚፈለገው ግብ ዘንድ ለመድረስ ገና በብዙ መስራት ያስፈልጋል::
በስንዴ ልማት ታሪክ ተሰርቷል፤ ለእዚያውም በተደጋጋሚ:: ሀገር የምግብ ዋስትናዋን በሚገባ ማረጋገጥ አልፎም ተርፎ ለውጭ ገበያ በስፋት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እስከ አለባት ድረስ በሰፊው መስራት ያስፈልጋል:: በሌሎች ዘርፎችም እንደዚያው ነው:: ገና ብዙ መስራት ብዙ ማምረት ብዙ መገንባት ይኖርብናል:: የልማት ውጤቶች ሊያበረቱን ለበለጠ ስኬት ሊያንቀሳቅሱን እንጂ በፍጹም እርካታ እየተሰማን ተኩራርተን ልናያቸው አይገባም::
ረክተን ከተቀመጥን ያኔ በገዛ ፈቃዳችን ወደኋላ መመለስ እንደጀመርን አድርገን መቁጠር አለብን:: ለእርካታ እጅ ሳንሰጥ የተገኘውን ስኬት እያጣጣምነው በድል ድል ለመደረብ ተግተን መስራት ይኖርብናል:: አብረውን የኖሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታትም መጪውን ዘመን በአሸናፊነት ለመወጣትም ከእርካታ ባሻገር አስበን መስራት ያለብን ወቅት ላይ ነን!
እስመለአለም
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም