ቢትኮይን ዝርፊያ የተሳተፈው አሜሪካዊ በእስራት ተቀጣ

በዓለም ግዙፍ ከተባለው የምናባዊ መገበያያ (ክሪፕቶከረንሲ) ዝርፊያ የተሳተፈው አሜሪካዊ በአምስት ዓመት እስራት ተቀጣ። በፈጸመው ድርጊት መጸጸቱን ገለጸ።

ቢቢሲ እንደዘገበው ፤ኢልያ ሊችተንስታይን የተባለው ግለሰብ በ2016 ቢትፊኔክስ በተሰኘው የክሪፕቶከረንሲ ዝርፊያ የተገኘውን ገንዘብ በማዘዋወር ተከሶ ባለፈው ዓመት ጥፋተኛ ተብሎ ነበር ።

በወቅቱ የተሰረቀውን 120 ሺህ የሚጠጋ ቢትኮይን ከባለቤቱ ሄዘር ሞርጋን ጋር በመሆን ማዘዋወሩ የተገለጸ ሲሆን፤ ዝርፊያው ሲፈጸም የተዘረፈው ቢትኮይን የገበያ ዋጋ 70 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነበር።

በየካቲት ወር 2022 ሊችተንስታይን እና ባለቤቱ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ፣የቢትኮይኑ ዋጋ ወደ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አድጎ እንደነበርም አመልክቷል ። በአሁኑ ወቅት የቢትኮይን ዋጋ ከዚህ በብዙ እጥፍ የሚልቅ እንደሆነም ቢቢሲ አስታውቋል ።

ዘራፊዎቹ ሲያዙ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ቢትኮይን መገኘቱን ያመለከተው ቢቢሲ፣ ይህም በአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ታሪክ ከፍተኛው መጠን ያለው ገንዘብ ነው መባሉን አስታውሷል ።

ከሁለት ዓመት በፊት በቁጥጥር ስር ውሎ በእስር የሚገኘው ኢልያ ሊችተንስታይን በፈጸመው ድርጊት መጸጸቱን ተናግሯል።

የተላለፈበትን እስራት ካጠናቀቀ በኋላም የኮምፒውተር ክህሎቱን የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል እንደሚያውለው ለችሎት አስረድቷል።

የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ አቀንቃኟ ባለቤቱ ሄዘር ሞርጋንም ባለፈው ዓመት በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጥፋተኛ የተባለች ሲሆን ከቀናት በኋላ የቅጣት ውሳኔ ይተላለፍባታል።

የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያመላክቱት ሊችተንስታይን በ2016 የተፈጸመውን የቢትፊኒክስ ዝርፊያ ለማከናወን እጅግ የዘመኑ የጠለፋ መሣሪያዎች እና ቴክኒኮች ተጠቅሟል።

የተጠለፈውን ቢትኮይን ለማዘዋወርም ከባለቤቱ ሞርጋን ጋር በመሆን በርካታ አካውንቶችን መክፈቱንና የወርቅ ሳንቲሞችን መግዛቱንም ነው ሰነዶቹ የጠቆሙት።

በሩሲያ ተወልዶ በአሜሪካ ያደገው ሊችተንስታይን ከቤተሰቦቹ ጋር ለጉብኝት ወደ ሩሲያ ባቀናበት ወቅት ገንዘቡን የሚያዘዋውርበት መንገድ እያፈላለገ እንደነበርም ተገልጿል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You