አዲስ አበባ፡- ምሁራን ለጋራ ሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ እንዲያገኙ መስራት እንዳለባቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከ50 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራንና የተማሪ ተወካዮች ጋር በትናትናው ዕለት ውይይት አካሂዷል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ምሁራን ለጋራ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ የጋራ መፍትሔ እንዲያገኙ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለውን አንኳር ችግር ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ እንዲያገኙ መስራት ትልቅ ሚናና ኃላፊነት አለባቸው ።
የሀገሪቱ ዋነኛ ከሆኑ ተቋማት መካከል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኙበታል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ምሁራን ሀገሪቱ እየገጠማት ያለውን አለመግባባትና ግጭት ለመፍታት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በምክክር ሰላምንና መግባባትን ለማምጣት እየሰራ ነው፤ እየሰራ ያለውን ስራ አጠናክሮ በማስቀጠል የተቋቋመበትን ዓላማ እውን ለማድረግ የምሁራን ሃሳብና መፍትሔ አስፈላጊ ነው። ከምሁራን ጋር ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትሔ ለመስጠት እንወያያለን፤ እንመካከራለን ሲሉ ጠቁመዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት በዘጠኝ ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ ማሰባሰብና የመወያየት ስራ ተሰርቷል፤በቀጣይ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ተሳታፊዎችን የመለየት፤ አጀንዳ የማሰባሰብና የመመካከር ስራ ይሰራል ብለዋል።
ግጭትና ጦርነት ላይ የነበሩ ሀገራት ችግራቸውን በምክክር ፈትተው ሰላምና እድገታቸውን እያሳለጡ ይገኛሉ ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ችግርን በጦር መሳሪያ መፍታት አይቻልም፤ መፍትሔው መመካከር ነው።የምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት እየሰራ ነው፤ እየሰራ ባለውም ስራም ስለምክክር ግንዛቤ የማስጨበጥና አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እየሰራ ነው ።
ምክክሩን አካታች ለማድረግ እየተሰራ ባለው ስራ ኮሚሽኑ ስራ ሲጀምር ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች አብረው ሲሰሩ እንደነበር አውስተው፤ በአሁኑ ጊዜም ከኮሚሽኑ ጋር አብረው የሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች 50 መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ምሁራን ሀገራዊ መግባባት እንዲመጣ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ ቢሆንም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ኮሚሽነር አባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አስከፊ ግጭት አስተናግዳለች፤ ልዩነቶችንና ግጭቶችን ለመፍታት የምሁራን ሚና ትልቅ ነው ብለዋል።
ምሁራን ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል እውቀትና አቅም አላቸው።
ችግሮቻችንን በጠመንጃ ሳይሆን በምክክር መፍታት ባህል በማድረግ ረገድ ምሁራን ትልቅ ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም