– ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ጉባኤ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት አራት ወራት ከጥራጥሬና ቅባት እህሎች ከ156 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ። 13ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ጉባኤ ከህዳር 10 ቀን እስከ ህዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
የጉባኤው (ኮንፈረንሱ) አዘጋጆች የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ጉባኤውን አስመልክተው ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከጥራጥሬና ቅባት እህሎች ካላት የምርት አቅም አንጻር ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ባይሆንም በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው አራት ወራት የተገኘው የገቢ አፈጻጸም ካለፉት ጊዜያት መሻሻል አሳይቷል።
በ2017 በጀት ዓመት አራት ወራት ከቅባት እህል 66 ሚሊዮን ከጥራጥሬ ደግሞ 90 ሚሊዮን በድምሩ ከ156 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን አስታውቀዋል።
በአራት ወራት ወደ ውጭ ለመላክ ከታቀደው የምርት መጠንና የውጭ ምንዛሬ ገቢ አንጻር በአማካኝ የእቅዱን ከ95 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን አመልክተው፤ባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ወደ ውጭ ተልኮ 675 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግድ ገቢ እንዲያድግ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ኢትዮጵያ በጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ያላትን አቅም በማስተዋወቅ አሁን ከሚገኘው ገቢ በላይ ለማግኘት በትብብር መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል 13ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ጉባኤ ከህዳር 10 ቀን እስከ ህዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አመላክተዋል።
በጉባኤው ከ22 እስከ 25 የሚደርሱ የዓለም ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ እስካሁን ከ110 በላይ ተሳታፊዎች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያም ከ430 በላይ ላኪዎች፣ አምራቾች፣ ጥናት አቅራቢዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ብለዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት እና ወጪ ንግድ ያላትን እምቅ ሀብት ለዓለም በማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸው፤ምርትን ከማስተዋወቅ ባለፈም የገበያ ትስስርን ለመፍጠር እና የገበያ መዳረሻ ሀገራትን ለማስፋፋት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ኤዳኦ አብዲ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የግብርና ምርቶች ለኢትዮጵያ ወሳኝ የኢኮኖሚ አውታር ናቸው። እነዚህን ሰብሎች በሚፈለገው ደረጃ በማልማት ትርፋማ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መስራት ይገባል።
ሀገር አቀፍ ላኪዎች፣ አምራቾች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምርትን በጥራት ለዓለም ገበያ ለማዳረስና ለማስተዋወቅ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ጉባኤ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ጉባኤው የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጣና እና የዓለም ንግድ ድርጅት ለሚያመጧቸው የመወዳደሪያ መስፈርቶች የኢትዮጵያ ላኪዎች ልምድ እንዲቀስሙ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በጉባኤው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ገዢ ኩባንያዎች ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ለኢኮኖሚውና ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም