የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም የአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች በብዛት እንዲመረቱ አዘዙ

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሀገራቸው የአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን በስፋት እንደታመርት ትእዛዝ መስጠታቸው ተነግሯል። በወታደራዊ ንድፈ ሃሳቦች ላይ አስቸኳይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የመንግሥት የዜና ወኪል ኬ.ሲ.ኤን.ኤ እንደዘገበው ፣ኪም ጆንግ ኡን በሰሜን ኮሪያ መመረት የጀመሩ የአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች ሙከራ ላይ በመታደም ፤ ሀገራቸው የአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን በስፋት እንደታመርት ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡

እንደዚህ አይነት ድሮኖች መምጣታቸው የወታደራዊ ንድፈ ሃሳቦች ላይ አስቸኳይ ማሻሻያ ማድረግ ይጠይቃል ሲሉ የተደመጡት መሪው ፣ በተቻለ ፍጥነት ዘላቂነት ያለው የምርት ሥርዓት መገንባት እና ወደ ሙሉ የጅምላ ምርት መግባት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል ።

ኪም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ለወታደራዊ አገልግሎት የመጠቀም ፉክክር በዓለም ዙሪያ እየተፋጠነ መሆኑንም ገልጸዋል። “እንዲህ ዓይነቱ ተጨባጭ ለውጥ ብዙ የውትድርና ንድፈ ሃሳብ፣ ልምምድ እና ትምህርት ክፍሎችን ማዘመን ይጠይቃል” ብለዋል፡፡

“ሎይትሪንግ ጥይቶች” በመባል የሚታወቁት እነዚህ አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች በዩክሬን እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ በጦርነት ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን ፣ ሀገሪቱ ድሮኖቹን በፍጥነትና በስፋት ማምረት የጀመረችው ከሩሲያ ቴክኒካዊ ድጋፍ አግኝታ ሳይሆን እንዳልቀረም ይነገራል ።

ከሚሳዔልና ኒኩሌር ጋር ተያይዞ ስሟ በስፋት የሚነሳው ሰሜን ኮሪያ ድሮኖችንም የምትጠቀም ሲሆን፤ የደቡብ ኮሪያን ድንበር በመጣስ የላከቻቸው ድሮኖች በደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንታዊ ጽህፈት ቤት ዙሪያ እንዲሁም በረራ ክልክል የሆነባቸው ቁልፍ ቦታዎች ላይ ሲበሩ መታየታቸው ይታወሳል።

 

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You