ሰሞኑን ከማህበራዊ ገጾች እና በአቅራቢያዬ ካሉ ወላጆች የግል ትምህርት ቤቶች ዋጋ ለመጨመር ከወላጆች ጋር እየተወያዩ እንደነበር አስተዋልኩ:: አንዳንዶቹም ‹‹ትምህርት ቤቱን ወደ ኮሌጅ ልናሳድግ ነውና….›› በማለት ወላጆች ዋጋ መጨመር እንዳለባቸው የሚናገሩ አሉ::
ይሄ ነገር ግን ‹‹አግዙኝ›› እንደማለት ነው ወይስ ግዴታችሁ ነው እንደማለት ይሆን? ባለቤቱ ኮሌጅ ለማድረግ ካሰበ ወላጆች የግድ የተለየ ክፍያ መክፈል አለባቸው?
የክፍያው መጠን በወላጆች ፍላጎት፣ በትምህርት ቤቱ ባለቤትና በወላጆች ስምምነት ስለሆነ መጠኑን እንተወው:: ዳሩ ግን በግሌ አንድ የምታዘበው ነገር አለ:: ስለግል ትምህርት ቤቶች በስፋት የሚወራው ከይዘቱ ይልቅ ክፍያው ላይ ነው:: የግል ትምህርት ቤቶች ስመ ጥርነት እና ገናናነት የሚታወቀው በክፍያው ነው:: ‹‹እገሌ ትምህርት ቤት እኮ ይህን ያህል ነው የሚያስከፍል›› እንጂ ‹‹እነ እገሌ የወጡበት ነው›› ሲባል አንሰማም::
ወላጆችም የሚፎካከሩት ‹‹የእኔ ልጅ እኮ ይህን ያህል ከፍዬ ነው የማስተምረው›› በማለት እንጂ ይህን ሠርቷል በማለት አይደለም:: በየጊዜው ሚዲያ ላይ አጀንዳ ሲሆን የሚታየው የክፍያው ነገር እንጂ ከግል ትምህርት ቤት ስለሚገኙ የፈጠራ ውጤቶች አይደለም:: ትምህርት እንዲህ ንግድ ሲሆን ብቁ ዜጋ ሊፈጥር አይችልም::
የግል ትምህርት ቤቶችን ጉዳይ ያደረኩት ከክፍያው ጋር ተያይዞ እንጂ ከመንግሥት ትምህርት ቤት ተመራማሪ ተማሪዎች እየወጡ ነው ማለቴ አይደለም:: ደፈር ብለን እንናገር ከተባለ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሥነ ምግባር እና ከአገር ወግና ባህል ጋር ተያይዞ ብዙ ሀሜት ነው ያለው::
ሀሜቱን እንኳን እንተወው ቢባል በግልጽ የሚታዩት አፈንጋጭ ነገሮች ቀላል አይደሉም:: የግል ትምህርት ቤቶች ከስያሜያቸው ጀምሮ አገራዊ ነገሮች ላይ ደካማ ናቸው:: የዕውቀት ጣሪያ ተደርጎ የሚታየው እንግሊዝኛ ቋንቋ ነው:: ቋንቋ ደግሞ ከመግባቢያነት ያለፈ ሚና የለውም::
እርግጥ ነው የግል ትምህርት ቤት እና ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት የሚማሩ ልጆች ሳይንቲስትም ሆነ በየትኛውም ዘርፍ ስኬታማ የመሆን ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው። እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ አቀላጥፈው ስለሚናገሩ ዓለም አቀፍ ገበያው ላይ ተመራጭ ይሆናሉ። እንደሚጎብዙባቸው የትምህርት ዓይነቶች ወደፈለጉት የትምህርት ዘርፍ ቀጥ ብለው ይገባሉ። የተሻለ ወቅታዊ መረጃ (በዓለም አቀፍ ደረጃ ማለት ነው) ተደራሽነት ስላላቸው ዓለምን የመዞር ዕድልን ያገኛሉ:: አዋጪ የሕይወት መስመራቸውን በልጅነት ዕድሜያቸው ያገኛሉ ማለት ነው::
ችግሩ ግን የምንታዘባቸው ነገሮች ለዚህ የሚያበቁ አይመስሉም:: ሲቀጥል ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች የሚያፈሩት ዜጋ ሁሉ ውጭ አገር ለማልማት መሆን የለበትም:: የአገሩን፣ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ካላወቀ የአገሩ የተፈጥሮ ሀብት ሁሉ ተመራማሪ ያጣል ማለት ነው:: እያስተማሩ ለሰለጠነ አገር ብቻ መገበር መሆን የለበትም:: የተማረና የሰለጠነ ዜጋ ብንፈጥር እኮ ከሰለጠኑ አገራት ይገኛል የሚባለውን ነገር ሁሉ ከአገራችን ማግኘት ይቻል ነበር::
ሌላው በቅንጦት ትምህርት ቤቶች የምንታዘበው ነገር ልጆች ከተፈጥሮና ማህበራዊ መስተጋብር የራቁ መሆናቸው ነው:: የሀብታም ልጆች ስለሆኑ እንኳን ወላጆች ልጆቹ ራሳቸው መኪና ያላቸው ናቸው:: አካባቢያቸውን የሚያዩት ምናልባትም በመስኮት ብቻ ነው:: ተፈጥሮን እያወቋት አይደለም ማለት ነው:: ትምህርት ደግሞ በክፍል ውስጥ ንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮን በማስተዋል ጭምር ነው:: ስለዚህ ከልክ ያለፈ ቅንጦት ከተፈጥሮ እያራቃቸው ነው ማለት ነው::
አንድ ሰው ተመራማሪ ለመሆን የግድ መጎሳቆል የለበትም:: የግድ በዝናብና ፀሐይ መመታት የለበትም:: የግድ አቧራና ጭቃ ውስጥ መግባት ላይኖርበት ይችላል:: የግድ የድሃ ሰዎችን አኗኗር ማየት ላይጠበቅበት ይችላል::
ዳሩ ግን ከእነዚህ ሁሉ የራቀ ዜጋ አገሩን ያውቃል ማለት ይቻላል? እነዚህን ነገሮች ለማወቅ የግድ የድሃ ልጅ መሆንን አይጠይቅም:: በአገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪና ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ተፈጥሮን እና ማህበራዊ ሕይወትን ያስተዋሉ ናቸው:: የምርምር እና የሀሳብ ግብዓት ያገኙትም በእነዚያ ነገሮች ውስጥ ስለተሳተፉ ነው:: ስለዚህ ከልክ ያለፈ ቅንጦት ተማሪዎች ነገ አገር ተረካቢ ሲሆኑ ለብዙ ነገር እንግዳ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል:: ይህ ደግሞ በስፋት የሚታየው የሀብታም ልጆች ባሉበት የግል ትምህርት ቤቶች ነውና ትምህርት ቤቶች ብዙ ነገሮችን ማሳየት አለባቸው::
አሁንም ልድገመውና የግል ትምህርት ቤቶችን ጉዳይ ያደረኩት ከክፍያ መጋነን ጋር ተያይዞ እንጂ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጋ ተመራማሪ መፍጠር የሚያስችል ብዙ አሠራር አለ ማለቴ አይደለም:: እንዲያውም ይባስ ብሎ መጻፍና ማንበብ የማይችል የ4ኛ ክፍል ተማሪ የሚገኘው የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ነው:: ተማሪም ሆነ መምህር እስከ ሳምንት ድረስ ከክፍል የሚቀሩበት ግዴለሽነት ያለው የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ነው::
በአጠቃላይ የግል ትምህርት ቤቶችን የተጋነነ ክፍያም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ ግዴለሽነት መቆጣጠር የሚችለው መንግሥት ነው:: ጥራትን እና ሥነ ምግባርን መቆጣጠር የሚችሉት የመንግሥት የትምህርት ተቋማት ናቸው:: ስለዚህ የትምህርት ነገር እንደ ቀላል የሚታይ መሆን የለበትም::
የግል ትምህርት ቤቶች ባይኖሩ ኖሮ መንግሥት ይህን ሁሉ ዜጋ በዚህ ልክ የትምህርት ተደራሽ ማድረግ ያስቸግረው ነበር:: ስለዚህ የግል ትምህርት ቤቶች ሚና ቀላል አይደለም:: ፈጣን እና ዘመኑን የሚመጥን ዜጋ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ደግሞ ከምንም በላይ የሚመሰገን ነው:: ዳሩ ግን የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን፣ ባህልና ታሪኮችን እንዳያውቁ ማድረግ ደግሞ ስህተት ነው:: የአገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ወግ ማወቅ ዓለምአቀፉን ለማወቅ እንቅፋት አይሆንም:: እንዲያውም ሙሉ ዓለምአቀፍ ያደርጋል::
በነገራችን ላይ ስለግል ትምህርት ቤቶች ከሁለት ወላጆች የሰማሁት ምስክርነት አለ:: እንዲያውም አንደኛዋ ወላጅ ሦስት የተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች ታውቃለች:: በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች የሥነ ምግባር ግድፈት እንደሚታየው ሁሉ በብዙ የግል ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ጥንቃቄ ነው ያለው:: ከመምህር እስከ ተማሪ ሕግና ደንብ የማክበርን ልምምድ እያደረጉ ነው የሚሄዱት::
በአጠቃላይ የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ሳይሆን የዕውቀት መፎካከሪያ ይሁኑ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2015