500 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ያስጠለለው የሱዳን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከወራት በኋላ የመጀመሪያው ሰብዓዊ እርዳታ መድረሱ ተገለጸ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጭነት መኪናዎች በሱዳን ለ18 ወራት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ቀያቸውን ለቅቀው የተጠለሉበት ዛምዛም ስደተኞች ካምፕ ሕዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም ደርሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም (ደብሊውኤፍፒ) በአቅራቢያው በምትገኘው የዳርፉር ከተማ ኤል ፋሸር በተካሄደው ከባድ ጦርነት እንዲሁም ዝናባማ ወቅት ተከትሎ “ለመሻገር ፈታኝ በሆኑ” መንገዶች የተነሳ የምግብ አቅርቦቱ ለወራት ተቋርጦ ቆይቷል ብሏል።
በሱዳን ጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል ባለው የሥልጣን ይገባኛል ሽኩቻ የተነሳ በዓለም ትልቁ የሰብዓዊ ቀውስ ተፈጥሯል። ይህ የሱዳን ጦርነት 10 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ሲያደርግ ማሕበረሰቡን ለረሃብ አጋልጧል። በዛምዛም የሚገኙ
ተፈናቃዮች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አል- ፋሸርን ከአገሪቱ መከላከያ ኃይል ለማስለቀቅ ያደረጉትን ከባድ ውጊያ ተከትሎ፣ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ተብሏል።
አል-ፋሸር በምዕራብ ዳርፉር ግዛት በአገሪቱ ወታደር ቁጥጥር ስር ያለች ብቸኛ ከተማ ነች። በነሐሴ ወር፣ ገለልተኛ የሆነ የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች ጦርነቱ ዛምዛምን ወደ ረሃብ እንደገፋ ተናግረው ነበር። በረሃብ የተጠቃን አካባቢ ለመመደብ የተቀመጡት መስፈርቶች ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆኑ አባወራዎች ለከፋ የምግብ እጦት የተጋለጡ መሆናቸውን፣ 30 በመቶ ሕጻናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዱ እና ከ10 ሺህ ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ሰዎች በየቀኑ በረሃብ ወይም በምግብ እጦት አልያም በበሽታ ይሞታሉ ይላል።
ወደ ዛምዛም የምግብ እርዳታ ጭነው የተንቀሳቀሱ መኪኖች የዓለም የምግብ ድርጅት “ለችግር በከፍተኛ
የተጋለጡ እና ከሌላው ተነጥለው ግጭት ያለባቸው አካባቢዎችን ” ለመድረስ የሚያደርገው ጥረት አካል ነው ሲል ገልጿል። በአጠቃላይ ከ700 በላይ የጭነት መኪኖች አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን ከአንድ ወር በላይ ለመመገብ
የሚያስችል በቂ እርዳታ ይዘው መላካቸውን መግለጫው አመልክቷል። የተወሰኑ የምግብ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት እያመሩ መሆኑም ታውቋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም