አዲስ አበባ ጽዱና ውብ ከተማ እየሆነች ነው። ከቆሻሻ ገንዳው ተርፎ ተዝረክርኮ የሚታይ ቆሻሻ የለም። ጉንፋን አስም ራስ ምታት የሚቀሰቅስ የሚገለማ ሽታ እየጠፋ ነው። የደረቅ ቆሻሻ አወጋገዳችን እየተሻሻለ ይገኛል። ከየቤቱ የሚወጣ ቆሻሻ ከስር ከስር ስለሚነሳ ለመታጠን ለመቃጠል የሚጠብቅ ቆሻሻ የለም። በዘመቻ ቆሻሻ ማቃጠል ትዝታ እየሆነ ነው። ምን አለፋችሁ ሕዳር ሲታጠን ራሱ ዓመቱን ሙሉ እየታጠነ ነው።
የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ጽዱና አረንጓዴ ስለአደረጋት እንደበፊት ቆሻሻ የትም ለመጣል እንዳይመች አድርጎታል። የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በተካሄደባቸው ሰፈሮችና መንገዶች ለኅዳር ሲታጠን የሚሆን ቆሻሻ የለም። ሁለተኛው የኮሪደር ልማት ሲጠናቀቅ፤ ፕሮጀክቱ በክልሎች ሲሰፋ፤ ወደ ገጠሩ የሀገራችን ክፍል ሲሸጋገር ደግሞ ኅዳር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታጠነ ማለት ነው። ኅዳር ሲታጠንም ትዝታና ታሪክ ሆነ ማለት አይደል። ስለ ኮሪደር ልማቱ ትንሽ ልበልና ትዝታችን ወደ ሆነው ኅዳር ሲታጠን እመለሳለሁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እንደ ኮዬ አደባባይ፣ ጎሮ እና ሰሚት ባሉ “የከተማዋ መግቢያ” እና “ማስፋፊያ ላይ በሚገኙ” አካባቢዎች እየተከናወነ ይገኛል። 43 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ፤ ከሸገር ከተማ የኮሪደር ልማት ጋር “በማስተሳሰር” እንዲከናወን ታቅዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የኮሪደር ልማት” ሲል የጠራውን ዋና ዋና መንገዶችን የማስዋብ፣ የእግረኛ መንገድን የማስፋት፣ መዝናኛ ቦታዎችን የመገንባት እንዲሁም የመንገድ ዳር መብራት እና ቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመሮችን በዘመናዊ መንገድ የመዘርጋት ሥራ የፊታችን የካቲት ወር ዓመት ይሆነዋል።
የከተማዋን ታዋቂ እና ነባር አካባቢዎችን የሸፈነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት፤ አምስት መስመሮችን የያዘ ነው። በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ሲኤምሲ ይገኙበታል።
የከተማ አስተዳደሩ፤ በድምሩ 48 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍነው ለመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት፤ 33 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም መግለጻቸውም ይታወሳል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግምገማ እየተደረገበት የተካሄደው ይህ የኮሪደር ልማት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነችን ጨምሮ ከፍተኛ የከተማዋ ኃላፊዎች ግንባታ የሚከናወንባቸውን መስመሮች ተከፋፍለው ሥራውን መርተውታል።
ከኮሪደር ልማቱ መስመሮች ውስጥ ቀድሞ የተመረቀው በከንቲባዋ ክትትል ስር የነበረው ከአራት ኪሎ ፒያሳ የሚደርሰው መንገድ ሲሆን፣ ከመገናኛ ሲኤምሲ የተዘረጋውን ልማት ጨምሮ ሌሎቹ መስመሮች በተለያዩ ጊዜያት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት 32 የውሃ ፏፏቴዎች እንዲሁም 70 የሕዝብ መናፈሻ ስፍራዎች እና የፈጣን ምግብ አገልግሎት መሸጫ ቦታዎች ተገንብተዋል።
በምዕራፍ ሁለት የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ የተደረገው ይህ ጥናት በከተማዋ የፕላን እና ልማት ቢሮ የተዘጋጀ ነው። በአጠቃላይ 43 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው የምዕራፍ ሁለት የኮሪደር ልማት፤ ቦሌ፣ ለሚ ኩራ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞችን እንደሚያካትት የጥናት ሰነዱ ያሳያል።
ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በአምስት መስመሮች ላይ የሚከናወን ነው። ከእነዚህ መስመሮች ውስጥ ከፍተኛ ዝርመት ያለው “ከአንበሳ ጋራዥ – መብራት ኃይል – ጎሮ – ኮዬ አደባባይ” የሚደርሰው መንገድ ነው። ይህ መስመር 14.8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።
“ከቦሌ ካርጎ – ቡልቡላ – ኮዬ አደባባይ” የሚደርሰው ሁለተኛው ረጅም መስመር ደግሞ 12.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ውስጥ የተካተተው ሌላኛው መስመር “ከቦሌ ድልድይ” ተነስቶ “በቦሌ ሆምስ – በአየር መንገድ ቪአይፒ መግቢያ” አድርጎ መዳረሻው “ጎሮ” አካባቢ ነው።“ከጎሮ አደባባይ” የሚነሳው አራተኛው መስመር አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚኖረው በጥናት ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
ይህ መስመር “ከጎሮ አደባባይ – በሰባ ሁለት አካባቢ – ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ አካባቢ – ፍየል ቤት – ሲ ኤም ሲ አደባባይ” አካባቢዎችን ይሸፍናል።“ከፍየል ቤት – ፊጋ – ሰሃሊተ ምህረት አደባባይ – ጃክሮስ” የሚደርሰው አምስተኛው መስመር ደግሞ 5.9 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው።
በከተማዋ የአስተዳደር ወሰን ማብቂያ አካባቢ የሚገኙ አካባቢዎችን ያካተተው ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ፤ “በትግበራ ላይ ከሚገኙ የሸገር [ከተማ] የልማት ኮሪደሮች ጋር በማስተሳሰር የሚከናወን” እንደሆነ የጥናት ሰነዱ ያመለክታል። ወደ ኅዳር ሲታጠን ሲመለስ፤
«በኢትዮጵያ የኅዳር በሽታ የሚታወቀው የአንደኛውን የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ተከትሎ የተከሰተውና በመላው ዓለም ለ200 ሚሊዮን ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ‘እስፓኒሽ ፍሉ ‘ ነው:: ወረርሽኙ በ24 ሳምንታት የቀሰፈው ሕይወት፤ ኤች አይ ቪ ኤድስ በ24 ዓመታት ከቀሰፈው በአያሌው ይበልጣል:: ወረርሽኙ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ብዙ ሰው የጨረሰው በኅዳር ወር ስለነበር ‘የኅዳር በሽታ’ እየተባለ ይጠራ ነበር:: ወረርሽኙ ወደ ወለጋ በመዛመቱ የንፋስ በሽታ ‘ዱኩባ ቂሌንሳ’ የሚል ስም ወቶለት ነበር::
ይህ መቅሰፍት በሀገራችን በ1911 ዓ.ም ወርዶ ብዙ ሰው ጨርሷል:: ወረርሽኙ በጉንፋን በሳል ይጀምርና ትኩሳት፣ ማስለቀስ፣ ነስር፣ ተቅማጥና ተውከት ከማስከተሉ ባሻገር አእምሮም ያስት ነበር:: ከዚያም በሦስት በአራት ቀን ይገድላል:: የቤተሰቡ አባላት በሙሉ አልጋ ላይ ይውሉ ስለነበር አስታማሚ ስለሚጠፋ በርሀብና በውሃ ጥም ብዙ ሰው ይጎዳ ነበር:: ከአራት ቀን ያለፈ ሕመምተኛ ግን ይድናል:: አፍላው በሽታ ከኅዳር 7 እስከ 20፣ 1911 ዓ.ም ነበር:: በየቀኑም ሁለት ሦስት መቶ ከዚህ በላይም ይሞት ነበር:: በአንድ መቃብር ሁለት ሦስት ሬሳ እስከ መቅበር ተደረሰ::
በዚያ ሰሞን መቃብር የሚቆፍርና ሬሳ ተሸክሞ ወደቀብር የሚወስድ ሰው ማግኘት ችግር ነበር:: ባል የሚስቱን፤ አባት የልጁን ሬሳ እየተሸከመ ቀበረ:: መቃብር ይቆፍርና ቤቱ ሄዶ ሬሳ ይዞ ሲመለስ ሌላው ቀብሮበት ያገኘዋል:: ቤተሰብ በሙሉ የታመመባቸው በየቤታቸው እየሞቱ አውሬ በላቸው:: በበሽታው ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪና ልዕልት ወ/ሮ መነን በጠና ታመው ነበር፤ ንግስት ዘውዲቱም አልጠናባቸውም እንጅ ታመው ነበር:: ከመኳንንት ከንቲባ ወሰኔ ዘአማኒኤል፤ ከካህናትም ሐዲስ አስተማሪው አለቃ ተገኘ ሞቱ:: አለቃ የመምህር ወ/ጊዮርጊስ ደቀ መዝሙር ነበሩ::
በዚያ ወራት በአዲስ አበባ የነበረው ጭንቀት በስፍራው ተገኝቼ ተመልክቼዋለሁ:: የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ በሰፈራቸው በጉለሌ ክፍል በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውሃ ሲያድሉ ሰነበቱ:: በእግዚአብሔር ቸርነት ከበሽታው አምልጠን ነበርና እኔንና ጎጃሜ ኃይለ ማርያምን ውሃ በገንቦ እያሸከሙ እሳቸው ቁራሽ እንጀራ ይዘው ይሄዱና ከቤቱ ደጃፍ ሲደርሱ እኛን ውጪ አስቀርተው ውሃውንና ቁራሹን ይዘው ይገቡ ነበር:: እኛን ማስቀረታቸው በሽታ እንዳይዘን ስላሰቡልን ነው::
በሌላ ስፍራም የዚህን ዓይነት ትሩፋት የሰሩ መንፈሳውያን ሰዎች ነበሩ:: ለምሳሌ ሙሴ ሴደርኩይስት የተባሉ ስዊድናዊ ሚስዮናዊ አስተማሪ በየሰፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውሃ መድኃኒት በመስጠት ትሩፋት መስራታቸውን ሰምቻለሁ:: እኒህ ሽማግሌ ከጥቂት ቀናት በኋላ በዚሁ በሽታ ታመሙና ሞተው ጉለሌ ተቀብረዋል::
የኅዳር በሽታ (ግሪፕ) በአዲስ አበባ ብቻ አልተወሰነም:: ወደ ባላገር ተላልፎ ብዙ ሰው ፈጅቷል:: ሆኖም በባላገር የአዲስ አበባን ያህል አልጠነከረም ይባላል:: በዚህ በሽታ በመላ ኢትዮጵያ የሞተው የሕዝብ ቁጥር እስከ 40 ሺህ ድረስ መገመቱንም አስታውሳለሁ:: በተለይ ኅዳር 12፣ የሚካኤል ዕለት ብዙ ሰው ሞተ:: ስለሆነም ወረርሽኙ እስከዛሬ በየዓመቱ የኅዳር ሚካኤል ዕለት በየሰፈሩ ቆሻሻ ሰብስቦ በማቃጠል ‘ኅዳር ሲታጠን ‘ በሚል ይዘከራል:: …» በማለት ‘ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ‘ ደራሲ መርስኤ ኀዘን ወ/ቂርቆስ ይነግሩናል::
በነገራችን ላይ እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴ እና ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ያለስስት የመሰከሩለትን ይህን ድንቅ መፅሐፍ ካላነበባችሁት እንድታነቡት እና ከመፅሐፍት መደርደሪያችሁ እንድትጨምሩት በታላቅ ትህትና እጋብዛለሁ::
ሻሎም !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም