ፑቲን ሩሲያ በውጊያው አዲስ ሚሳኤል መሞከሯን እንደምትቀጥል ጠቆሙ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ሀገራቸው አዳዲስ ሚሳኤል መሞከር እንደምትቀጥል ተናግረዋል። ፑቲን ዩክሬንን ለማጥቃት ‘አዲስ ሚሳኤል’ መጠቀማቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠው የዩክሬን አጋሮች የሆኑትን ምዕራባውያንን በጽኑ አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ የመካከለኛ ርቀት ሚሳይል ባስወነጨፈች ማግስት ፑቲን ባሰሙት ንግግር ሩሲያ ኦሬሽንክ የተባለውን አዲስ ሚሳኤል ያስወነጨፈችው ዩክሬን የአሜሪካ ባለስቲክ ሚሳይልን እና የእንግሊዝን ክሩዝ ሚሳይል ወደ ሩሲያ በማስወንጨፏ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። ፕሬዚዳንት ፑቲን አክለውም፤ ሩሲያ በጦርነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ያዋለችው ኦሬሽንክ ሚሳኤል ስኬታማ ነው ያሉ ሲሆን ሁኔታውን እና የደህንነት ስጋቱን እየታየ ሙከራዎቹ ይቀጥላሉ ሲሉ ተደምጠዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ሩሲያ እነዚህ አይነት መሳሪያዎች ክምችት አላት። መሳሪያዎቻቸው የሩሲያን ተቋማት እንዲመቱ በሚፈቅዱት ሀገራት ወታደራዊ ተቋማትን ለመምታት እያጤነች ነው። አሜሪካ እና ብሪታኒያ ዩክሬን የረጅም ርቀት መሳሪያዎቻቸውን ተጠቅማ ሩሲያን እንድታጠቃ መፍቀዳቸውን ተከትሎ ጦርነቱ ወደ ዓለም አቀፍ ግጭት እየተሸጋገረ መምጣቱን አብራርተዋል።

የአሜሪካና የብሪታኒያ ሚሳዔሎቻቸው ሩሲያን ለማጥቃት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተከትሎ ሞስኮ አዲስ የመካከለኛ ርቀት ሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል በዩክሬን ወታደራዊ ተቋም ላይ በመተኮስ የአጸፈ ምላሽ ሰጥታለችም ነው ያሉት። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ኬቭ አዳዲስ አደጋዎችን መከለል እና ይህን መሳሪያ ለማክሸፍ የሚያስችል የአየር ሲስተም እያለማች መሆኑን ገልጸዋል። ኬቭ አዳዲስ አደጋዎችን ለመከለል ከምዕራባውያን አጋሮቿ ጋር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ፤ አዲሱን የሩሲያ ሚሳኤል ተኩስ ግጭት አባባሽ መሆኑን ገልጸው፤ መከላከያ ሚኒስትራቸው እሳቸውን ወክለው ከምዕራባውያን አጋሮች በአየር መከላከያ ስርአት ዙሪያ እየተወያዩ መሆኑን ጠቁመዋል። ሩሲያ ይህን ብትልም የአሜሪካ ባለስልጣናት ግን ሩሲያ የተጠቀመችው ሚሳይል ለሙከራ ብቻ ነው፤ ያላት ክምችትም የተወሰነ ነው።

ኢንተርሚዲየት ሚሳይል ከ3000-3500 ኪሎ ሜትር ርቀት መምዘግዘግ የሚችል ሲሆን የትኛውንም የአውሮፓ ወይም የአሜሪካ ቦታ መምታት ይችላሉ ተብሏል። በተጨማሪም የደህንነት ባለሙያዎች እንደሚሉት ኦሬሽንክ ሚሳኤል በአንድ ጊዜ ብዙ ቦታዎችን መምታት እና በርካታ ተተኳሾችን መያዝ የሚችል መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፤ ከአህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ጋር የመመሳሰል ባህሪም እንዳለው አል ዓይን ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You