አዲስ አበባ፡- የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ወደ ተሐድሶ ሥልጠና ማዕከላት የማስገባት ሥራ ተጀምሯል። ወደ ተሐድሶ ሥልጠና ማዕከላት የሚገቡ የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል።
በዚሁ መሠረትም የመጀመሪያ ዙር የመቀሌ የተሐድሶ ሥልጠና ማዕከል የሚገቡ የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የነፍስ ወከፍ እና የቡድን የጦር መሣሪያ ትጥቃቸውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አስረክበዋል።
የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት ተከትሎ የቀድሞ ታጣቂዎች ከአንድ ዓመት በፊት የከባድና መካከለኛ የጦር መሣሪያ ትጥቃቸውን የአሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ታዛቢዎች በተገኙበት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ማስረከባቸው ይታወሳል።
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይም የብሔራዊ ተሐድሶ ምክትል ኮሚሽነርና የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ፣ የመከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ መኮንኖች፣ የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽነሮች፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮች፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎች ተባባሪ አካላት ተገኝተዋል።
የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች በየሥልጠና ማዕከላቱ የሚኖራቸውን ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው መደበኛ ሕይወታቸውን የሚመሩበት የገንዘብና የቁሳቁስ መቋቋሚያ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፤ በትግራይ ክልል መቀሌ፣ እዳጋ ሐሙስ እና ዓድዋ በተዘጋጁ ሦስት ማዕከላት በሚቀጥሉት አራት ወራት 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በዘላቂነት የማቋቋምና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ እንደሚከናወን ማሳወቃቸው ይታወሳል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም