አዲስ አበባ፡-ሕዝቡ ወንድማማችነቱን በማጎልበት የጽንፈኛና አሸባሪ ኃይሎችን እኩይ ዓላማ ሊያከሽፍ ይገባል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገለጹ፡፡
አቶ ኃይሉ አዱኛ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ ወንድማማችነቱን በማጎልበት የጽንፈኛና አሸባሪ ኃይሎችን እኩይ ዓላማ ሊያከሽፍ ይገባል፡፡
መንግሥት ሁሉንም የፀጥታ አካላት አሰማርቶ የሕግ የበላይነትን በማስከበር የሕዝቡን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት ይሠራል፡፡
የክልሉ መንግሥት በጽንፈኛ ኃይሎች የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ አጥብቆ እንደሚያወግዝና ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን በትኩረት እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ኃይሉ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስከበር የሕዝቡን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ጽንፈኛው ፋኖ አሰቃቂ ድርጊት መፈጸሙን ጠቅሰው፣ ጽንፈኞች ድርጊታቸው ተመሳሳይና ግባቸውም በኦሮሞና አማራ ሕዝብ መካከል ግጭት መፍጠር፣ ጥላቻን መንዛትና አንድነት እንዳይኖር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጽንፈኞች ግባቸው አንድ ሲሆን የሚለያዩት በሚናገሩት ቋንቋ ብቻ መሆኑን በመግለጽ፣ ሽብርተኛው ሸኔም አሰቃቂ ግድያዎችን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲፈጽም መክረሙን ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞ ሕዝብ ልማቱን እንዳይሠራ በማደናቀፍ፣ ንብረቱን በመዝረፍ፣ አሰቃቂ ግድያዎችን ሲፈጽም መኖሩን ጠቅሰው፣ ሸኔም ሆነ ራሱን ፋኖ ነኝ ብሎ የሚጠራው ጸንፈኛ በሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለውን ወንጀል መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት በአሸባሪው ሸኔም ሆነ ጽንፈኛው ፋኖ የሚፈጽሙትን አሰቃቂ ድርጊት አጥብቆ ይኮንናል ያሉት ኃላፊው፣ መንግሥት በአሸባሪው ቡድን ሸኔና በጽንፈኛው ፋኖ ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በክልሉ በሚንቀሳቀሰው አሸባሪው ሸኔና በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሰውም ጽንፈኛው ፋኖ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የጽንፈኛ ኃይሎች እየተወሰደባቸው ያለውን እርምጃ መቋቋም ሲያቅታቸው ሕዝቡን ለማነሳሳት አሰቃቂ ድርጊቶችን በንፁሐን ላይ እየወሰዱ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ጽንፈኞች በድርጊታቸው ሕዝቡ ተጠልፎ ወደ ብሔር ግጭት እንዲገባ፣ ሀገር እንዳትረጋጋና ሠላሟ እንዳይጠበቅ ማድረግ መሆኑን በመግለጽ፣ የክልሉ ሕዝብ የሽብርተኛና ጽንፈኛ ቡድኖችን እኩይ ተግባር በመገንዘብ አንድነቱን፣ ወንድማማችነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ግጭት እንዲቆም ሠላማዊ ሰልፎችን በመውጣት ጥያቄውን በማቅረቡ መንግሥትም የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ እየሠራበት እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የክልሉ መንግሥት ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ሠላምን ለማስፈን እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
የሽብርተኛው ሸኔ አባላት ሕዝብ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሠላም እየተመለሱ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ መንግሥት የሕዝቡን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሠላም አማራጮች የተመለሱትን ተቀብሎ ሥልጠና በመስጠት የሚያቋቁማቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚንቀሳቀሱ የሸኔ ታጣቂዎች የተከፈተውን የሠላም በር ተጠቅመው ወደ ሠላማዊ መንገድ እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም