የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አቅሞችን አስተባብሮ መጠቀም ያስፈልጋል

– ብሔራዊ የቡና ፕላትፎርም ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፡- የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ ጥራቱን ለማስጠበቅና የገበያ ዕድሎችን ለማፈላለግ ያለንን አቅም አስተባብሮ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገለጹ።

በቡና ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት በትብብር መሥራት የሚያስችል ብሔራዊ የቡና ፕላትፎርም ይፋ ተደርጓል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ቡና ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ባለድርሻዎች ውጤት ለማምጣት የሚያከናውኑት ሥራ በተበታተነ መልኩ የሚተገበር ነበር። በዚህም ምክንያት ማን ምን እንደሚሠራ የትኛው አካል በየትኛው ፕሮጀክት ላይ እንደሚሠራ ስለማይታወቅ የፕሮጀክቶች መደራረብና ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል።

የፕላትፎርሙ እውን መሆን በተበታተነ መልኩ የሚደረጉ ጥረቶችን የጋራ በማድረግ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ጥራትን ለመጠበቅና የገበያ ዕድሎችን ለማፈላለግ ያስችላል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ከደን ምንጣሮ ነፃ ምርት ሕግን ለማሟላትም ትልቅ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የ15 ዓመት የቡና ስትራቴጂ ቀርጻ በመተግበር ላይ መሆኗን አስታውሰው፤ በዚህም ከአምስት አልያም ከስድስት ዓመት በኋላ የቡና ወጪ ንግድ ገቢን 4 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል። ይህን ለማሳካት ደግሞ ያለንን አቅም አስተባብረን መጠቀም ይኖርብናል ብለዋል።

ፕላትፎርሙ ቡና ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላትን የሚያካትት መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይነትም ቡና ላይ ለመሥራት ፕሮጀክቶችን ይዘው የሚመጡ አካላት ሁሉ የፕላትፎርሙ አባል መሆን እንደሚችሉ ገልጸዋል ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው፤ ቡና ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ጥቅል ምርት አምስት በመቶ የሚያበረክትና ከወጪ ንግድ ገቢ 34 በመቶ የሚሸፍን ወሳኝ ምርት መሆኑን አመልክተዋል።

ዘርፉ ለአምስት ሚሊዮን አነስተኛ አርሶ አደሮች የኑሮ መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑት በአማካይ ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ቡናን የሚያለሙ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ብሔራዊ የቡና ፕላትፎርም መፈጠሩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የቡና ምርት ውጤታማነት ላይ የጋራ ራዕይ ለማስቀመጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ ያወጣው ሕግ የኢትዮጵያ ቡና ወጪ ንግድ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረትን ተነሳሽነት በምታከናውናቸው የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ የልማት ፕሮግራሞች ትደግፋለች። ይሁን እንጂ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ጊዜ የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል።

መንግሥት የቡና ዘርፉን ሪፎርም ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን አስታውሰው፤ የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟላት የሦስት ዓመት እቅድ ተነድፎ የተለያዩ ተግባራትም በመከናወን ላይ ናቸው። የተፈጠረው የትብብር ፕላትፎርም እነዚህን ሥራዎች ለመጋራትና ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመላክተዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You