የከሸፈው ታላቅ የእግር ኳስ አብዮት!

በአንድ ወቅት በቻይና የተነሳው የእግር ኳስ አብዮት የዓለምን ትኩረት ስቦ ነበር። የሩቅ ምስራቋ አገር ቻይና ሱፐር ሊጓን የዓለም ከዋክብት ተጫዋቾች መገኛና የድንቅ የእግር ኳስ መናኸሪያ የመሆን ውጥን ይዛ ነበር የተነሳችው። አገሪቷ ይህን ውጥኗን እውን ለማድረግ ከስምንት መቶ ቢሊየን ዶላር በላይ ለስፖርቱ ኢንደስትሪ አፍስሳለች።

እግር ኳስን በእጅጉ እንደሚወዱ የሚነገርላቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ድጋፍ፤ ቻይና የዓለማችን ታላላቅ ከዋክብትን በገንዘብ በማማለል ሊጓን የማጠናከር ስራን “ሀ ” ብላ ጀመረች። የዓለማችን ስመጥር ከዋክብት በቻይና ክለቦች ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ወደ ሱፐር ሊጓ መትመም ጀመሩ። ከነዚህም መካከል ብራዚላዊው ኦስካር፣ አርጀንቲናዊው ካርሎስ ቴቬዝ እና ቤልጂዬማዊው አክስል ቪትዝል ይገኙበታል። የነዚህ ተጫዋቾች ሊጉን መቀላቀል ለሌሎች ታላላቅ ተጫዋቾች መምጣት ምክንያት ሲሆኑ ጊዜ አልወሰደም። በ2016 በቻይና የፈነዳው ይህ የእግር ኳስ አብዮት በአውሮፓ እግር ኳስ ላይም ትልቅ ስጋት እስከመደቀን ደርሶም ነበር።

ጣሊያናዊው የቀድሞው የቼልሲ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ በወቅቱ በሰጡት አስተያየት፤ “የቻይና ገበያ ለቼልሲ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ክለቦች በሙሉ አደጋ ነው ” እስከማለት ደርሰው ነበር። “ቻይና ሁሉንም የአውሮፓ ሊግ ወደ ቻይና ለማዘዋወር የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ያላት ትመስላለች ” ሲሉም ታሪካዊው የአርሰናል አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በወቅቱ ስጋታቸውን ገልፀው ነበር።

ጥቂት የማይባሉ ኮከቦች በቻይና ሱፐር ሊግ ወደ ሚገኙት ሲኤስኤል ቻንግቹን፣ ሄቤይ፣ ቤጂንግ ጉዋን፣ ጂያንግሱ ሰኒንግ ክለቦች መትመም ጀመሩ። ሱፐር ሊጉ በርካታ ገንዘብ ማውጣት ሲጀምር አገሪቱን ወደ እግር ኳስ ልዕለ ኃያልነት የመቀየር ፍላጎታቸው እውን መሆን የጀመረ መሰለ። የሱፐር ሊጉ እንቅስቃሴ ጠንካራ ወደ ሚባል ደረጃ መድረስ ቢችልም፤ የእግር ኳስ አብዮቱ የታሰበውን ግብ መምታት እንደማይችል ምልክቶች መታየት ጀመሩ። አንዳንድ ክለቦች በዕዳ ውስጥ የመዘፈቃቸው ዜና ይሰማ ጀመር።

እአአ በ2017 የቻይና ስፖርት ሚኒስቴር የሊጉን ወጪን በተመለከተ ጥያቄ ማንሳት ጀመረ። ወጪዎችን ለመግታት እና “ምክንያታዊ ያልሆነ ኢንቨስትመንት” ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ ጀመረ። ክለቦች “ገንዘብ ያባክናሉ” እና ለውጭ ተጫዋቾች “ከልክ በላይ ደመወዝ” ይከፍላሉ ሲል ወደ መክሰስ ተሻገረ። በዚህ ፈታኝ መንገድ ውስጥም ቢሆን በ2019 ሱፐር ሊጉ በጣም ትልቅ ደረጃ ላይ ደረሰ።

በብዙ የተጠበቀው የቻይና እግር ኳስ አብዮት አስር ዓመት ሳይሞላው ጉዞው በተቃራኒው አቅጣጫ ሆኖ ተስፋው መፈረካከስ ጀመረ። የቻይና ክለቦች ተጫዋቾችን ወደ ቻይና ሱፐር ሊግ ለመሳብ በሚል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ቢከፍሉም፤ ትርፋማ መሆን አልቻሉም። ቻይና የጀመረችው መንገድ የተሳሳተ መሆኑን የተረዳችው ግን ዘግይታ ነበር።

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ በገንዘብ ኃይል አገራቸውን ወደ እግር ኳስ ማዕከልነት የመቀየር ፍላጎታቸው የሚሳካ አለመሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። እግር ኳስን በገንዘብ አቅም ማላቅ እንችላለን ከሚለው ቅዥት የነቁት ብዙ ኪሳራ ከረደሰባቸው በኋላ ነበር። ፕሬዚዳንቱ አርፍደውም ቢሆን የእግር ኳስ ትዕይንቱ ልጓም እንዲበጅለት ቀጭን ትዛዝ ሰጡ። የቻይና እግር ኳስ ማህበርም ተከተላቸው። ክለቦቻቸው ዕዳ ውስጥ መዘፈቃቸውን ተከትሎ የቻይና እግር ኳስ ማኅበር በ2020 የደመወዝ ጣራ አስቀመጠ።

የባሕር ማዶ ተጫዋቾች በሳምንት የሚያገኙት ከፍተኛ ደመወዝ 52 ሺህ እንዲሆን ሲል ወሰነ። ይህም ቀደም ሲል ለከዋክብት ተጫዋቾች ከቀረቡት ኮንትራቶች እጅግ በጣም ያነሰ ነው።

ከ2021 በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ የፋይናንስ ችግሮች እየተባባሱ መጡ። በዚሁ ዓመት በሱፐር ሊጉ የሚጫወተው ጂያንግሱ ሱኒንግ ክለብ የዓለማችን ውዱ ተጫዋች የነበረውን የሪያል ማድሪዱ ጋሬዝ ቤልን ወደ ጂያንግሱ ሰኒንግ ለማዘዋወር አቀደ። የሦስት ዓመት ኮንትራት በመስጠት በሳምንት አንድ ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ነበር ዕቅዱ። ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን ጂያንግሱ ሱኒንግ በደረሰበት የፋይናንስ መቃወስ ሥራ አቆመ። የቡድኑን አውቶብስ ለመሸጥ ጨረታ እስከማውጣትም ደረሰ።

እንደ ጂያንግ ሱኒንግ ክለብ ሁሉ አብዛኛዎቹ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ደመወዝ ለመክፈል እጅ እስኪያጥራቸው የደረሰ የከፋ ችግር ውስጥ ተዘፈቁ። በዚህ ምክንያት በገንዘብ የማለሉት ውድ ተጫዋቾች አገሪቱን ጥለው መውጣት ጀመሩ። በብዙ የተጠበቀው የቻይና እግር ኳስ አብዮት አስር ዓመት ሳይሞላው ጉዞው በተቃራኒው አቅጣጫ ሆኖ ከሸፈ። የፕሬዚዳንት ዢ ቻይና ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የገዘፈ የሊግ ውድድር ባለቤት የመሆን ሕልም ዛሬ ቅዥት ሆኗል። የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረት የነበረው የቻይና ሱፐር ሊግም ዛሬ ላይ አስታዋሽ የለውም።

ቦጋለ አበበ

 አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You