ስያሜውን ያገኘው በሁለት ምክንያት ነው። የመጀመሪያው እና ዋናው የተገደሉት ሰዎች 60 መሆናቸው ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ዘመኑ በ1960ዎቹ መሆኑ ነው። ይህ ክስተት በጥቅሉ በተለምዶ የ60ዎቹ ግድያ እየተባለ ይጠራል። የተገደሉት ሰዎች ሲቆጠሩ 59 ናቸው የሚሉ የታሪክ ፀሐፊዎችም አሉ፤ ሆኖም ግን ቁጥሩን በማጠጋጋት ይመስላል ‹‹60ዎቹ›› እየተባለ የሚጠራው።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 50 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን በዚህ ሳምንት ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም በደርግ መንግሥት የተፈጸመውን የ60ዎቹን ግድያ እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው በዚህ ሳምንት የተከሰቱ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የታሪክ ክስተቶችን እናስታውስ።
ከ91 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም ጋዜጠኛ፣ የታሪክ ፀሐፊ እና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ተወለደ።
ከ61 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 13 ቀን 1956 ዓ.ም (ኖቬምበር 22 ቀን 1963) 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ጆን ፊዝጄራልድ ኬኔዲ (ጆን ኤፍ ኬኔዲ) ተገደሉ። ጆን ኤፍ ኬኔዲ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩ ሲሆን በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለው ቤተ መጻሕፍት በስማቸው (ኬኔዲ ላይብረሪ) ይጠራል።
ከ19 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 13 ቀን 1998 ዓ.ም አንጌላ ሜርክል የጀርመን የመጀመሪያዋ ሴት መራሂተ መንግሥት ሆነው ተሾሙ። ሜርክል ለ16 ዓመታት ያህል የጀርመን መራሂተ መንግሥት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው ከ16 ዓመታት በኋላ ከታኅሳስ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለኦላፍ ሾልዝ ለቀዋል።
ከ138 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 14 ቀን 1879 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ተቆረቆረች። እቴጌ ጣይቱ ፍል ውሃ ፊል ፊል ወደሚልበት መስክ ወርደው ሳሉ፤ ከዚህ በፊት አይተዋት የማያውቋት አንዲት ልዩ አበባ አይተው ስለማረከቻቸው ቦታውን ‹‹አዲስ አበባ›› ብለው በመሰየማቸው የአዲስ አበባ ከተማ መነሻ መሆኑ በታሪክ ይነገራል።
ከ28 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 14 ቀን 1989 ዓ.ም 175 መንገደኞችን አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET961 የመንገደኞች አውሮፕላን፣ በሦስት ኢትዮጵያውያን ጠላፊዎች ተጠልፎ በኮሞሮስ ደሴት ላይ ተከሰከሰ፤ በአደጋው ጠላፊዎቹን ጨምሮ 125 ሰዎች ሞቱ፡፡
ከ50 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 15 ቀን 1967 ዓ.ም 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ እንዳለው የሚነገርለት የ‹‹ድንቅነሽ›› (ሉሲ) ቅሪተ አካል በኢትዮጵያ፣ አፋር ውስጥ ሐዳራይቶ በሚባል ቦታ ተገኘ። ቅሪተ አካሉን (አፅሙን) ያገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ካርል ዮሃንሰን የተባሉ አሜሪካዊ የቅሪተ አካል ጥናት ባለሙያ ናቸው። ቶም ግሬይ የተባለና በወቅቱ የድህረ ምረቃ ተማሪ የነበረ የቅሪተ አካል ጥናት ባለሙያም የፕሮፌሰር ዶናልድ ዮሃንሰን ረዳት ሆኖ ይሰራ ነበር።
ከ8 እና 4 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 16 ቀን እንደሚዋደዱ የሚነገርላቸው ጓደኞችና ወዳጅ የነበሩት፤ ሁለቱ የዓለማችን ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ ኩባዊው አብዮተኛ ፊደል ካስትሮ እና አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ማራዶና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩበት ነው። ፊደል ካስትሮ ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ፤ ከአራት ዓመት በኋላ ህዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ አርጀንቲናዊው ዲዮጎ አርማንዶ ማራዶና ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
አሁን በዕለቱ በዝርዝር ወደምናየው የ60ዎቹ ግድያ ታሪክ እንሂድ፡፡
ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት በመጣል አዲስ አብዮት የፈጠረው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ሙስና እና ሌብነትን አጥብቆ በመፀየፍ፣ ከምንም በላይ ደግሞ በቆራጥ አገር ወዳድነቱ ሥርዓቱን የታገሉት ጠላቶቹ ሳይቀር ይመሰክሩለታል። ‹‹ባለአባት›› በሚል ኋላቀር አስተሳሰብ የጌታ እና ሎሌ ሥርዓት የነበረበትን ገርስሶ መሬትን ለአራሽ ገበሬ በመሥጠቱ በድሃው ማሕበረሰብ ሲመሰገን ኖሯል።
በእነዚህ ሁሉ ጥሩ ሥራዎቹ ውስጥ ግን ስሙ በመጥፎ እንዲነሳ ያደረጉት ጥቁር ታሪኮች አሉት። ከእነዚህ የደርግ ታሪኮች አንዱ እና ዋነኛው የ60ዎቹ ጀኔራሎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያ ነው። ‹‹አብዮት ልጆቿን በላች›› እየተባለም ይገለጻል።
ክስተቶቹን ለማስታወስ፤ የፍሰሐ ያዜን ‹‹የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ ቅጽ 2›› መጽሐፍ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ (የተለያየ ዓመት ዕትም) እና የሌተናል ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› መጽሐፍ ምንጮቻችን አድርገናል።
ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የደርግ ሊቀ መንበር ሆነው ከተሾሙ ጊዜ ጀምሮ በደርጉ አባላት መካከል መስማማት አልነበረም። ይባስ ብሎ ወደለየለት ስድድብና አተካራ ውስጥ ገቡ። ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያምም ስለ ጀኔራል አማን ጉዳይ ለመወያየት የደርጉን አባላት ሰበሰቡ። ከዚሁ ጎን ለጎንም ከአንደኛው ብርጌድ ስድስተኛ ክፍለ ጦር የተውጣጡ ወታደሮች ጀኔራል አማንን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ ቢታዘዙም ‹‹እንዴት አማንን በሚያህል ጀግና ላይ አፈሙዝ እናነጣጥራለን? … አናደርገውም!›› ብለው እምቢታቸውን ገለፁ።
በዚህ ምላሽ ክፉኛ የደነገጠው ደርግ፤ ጦሩ አፈሙዙን ወደ ደርግ ሊያዞር እንደሚችል ስጋት ቢገባውም የመጣው ይምጣ በማለት በቅርብ የተገኙ የደርግ ጥበቃ ኮማንዶዎችን ከጥቂት የቡድኑ አባላት ጋር በማጣመር በሻለቃ ዳንኤል አስፋው መሪነት ወደ ጀኔራል አማን መኖሪያ ቤት ላከ። ጀኔራል አማን እጅ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከነ ሻለቃ ዳንኤል ጋር ተኩስ ገጠሙና የተወሰኑትን ገድለው በመጨረሻ ግን ተገደሉ፡፡
ከደርግ አባላት ጋር ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩት ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም የጀኔራሉን መገደል ሲሰሙ፤ አጀንዳውን በቁጥጥር ስር ወዳሉት የንጉሰ ነገሥቱ ባለስልጣናት ጉዳይ አዞሩት። (እርሳቸው ግን በደርግ አባላት ተገድጄ ነው አጀንዳውን ያነሳሁት ብለዋል)
‹‹አማን አንድ ወታደር ነው፤ የእርሱ ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ አይደለም፤ ይልቅ የነዚያን ደም መጣጮች ጉዳይ ዳር ሳናደርስ ከዚህ አዳራሽ አንወጣም›› ያሉት ንዑስ የደርግ አባላት፤ ደርግ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ባለስልጣናት ስማቸው እየተጠራ ‹‹በለው … ይገደል … ይሙት …›› በሚል የወታደሮች ፍርድ የስብሰባው አዳራሽ ድብልቅልቁ ወጣ፡፡
ብዙዎችን አስገርሞና አሳዝኖ የነበረው ‹‹በለው … ይገደል … ይሙት …›› ሲሉ የነበሩት ንዑስ የደርግ አባላት ብዙዎቹን ታሳሪዎች በስምም በመልክም የማያውቋቸው መሆኑ ነው። በእርግጥ ብዙዎቹ ታሳሪዎች በሙስና የነቀዙ ግለሰቦች እንደነበሩ የታሪክ ፀሐፍት ያስረዳሉ። ነገር ግን ለኢትዮጵያ ሀገራቸው የደከሙ እንደነ አክሊሉ ሀብተወልድ ያሉ ብርቅዬ ሰዎችም ከታሳሪዎቹ መካከል ነበሩ። በሙስና የነቀዙት ግለሰቦች ክስም ቢሆን ጉዳያቸውን ለመመርመር በተቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን በኩል መጣራት ይገባው ነበር የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
እንግዲህ በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝና አስደንጋጭ ውሳኔ 52 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለስልጣናትና 8 የደርግ አባላት (ባለስልጣናት) ሞት ተፈረደባቸውና ተገደሉ።
በነገራችን ላይ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ስለ ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም በሚያትተው ርዕስ፤ ጥፋቱን ወደ ጀኔራሉ ወስደውታል። እርሳቸው የሚሉት፤ ጀኔራሉ ኤርትራን ለማስገንጠል ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለሁ ነው። በአንድ ስብሰባ ላይም ኤርትራን ለማስገንጠል እንደሚሰሩ በግልጽ የተናገሩት ነው ብለው የጀኔራል አማን ሚካኤል አምዶን ንግግር በመጽሐፋቸው ላይ በጥቅስ ውስጥ አድርገው አስፍረዋል።
ያም ሆነ ይህ አብዮት ልጆቿን ትበላለች የሚለው እውን ሆና የጦር ልምድ፣ የዲፕሎማሲ ልምድ እና የፖለቲካ ልምድ ያላቸውን ሁሉ የአብዮቱ ሰይፍ አረፈባቸው።
እነዚህ 60 የጦር መኮንኖች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተገደሉት በተለያየ ምክንያት ነው። ኃይላቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ተጠቅመዋል በሚል ውንጀላ የተገደሉ ባለስልጣናት፤ ጸሃፌ ትዕዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድን ጨምሮ 17 ናቸው። ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ ተጠቅመዋል በሚል ውንጀላ ደግሞ 34 ባለሥልጣናትና የጦር መኮንኖች ተገድለዋል፤ አብዛኞቹ የጦር መኮንኖች ናቸው።
‹‹የእርስ በእርስ ጦርነት ለመቀስቀስ በተሸረበ ደባ እና ታላቁን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግታት በተደረገ አሻጥር›› በሚል 5 የተገደሉ ሲሆን ሦስቱ ካፒቴን ናቸው። ‹‹ለመስሪያ ቤት የተገባን ቃል ኪዳን ባለመጠበቅ እና በጦር ኃይሉ ውስጥ ክፍፍል ለመፍጠር ሙከራ ማድረግ›› በሚል ውንጀላ ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶምን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።
ጸሐፌ ትዕዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ በደርግ ታጣቂዎች ከመገደላቸው ቀደም ብለው በዕለቱ (ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም) እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹እኛን በመግደል ኢትዮጵያን ከድህነቷ የምታወጧት ከሆነ፣ ድርጊታችሁን እንደ ታላቅ በረከት በፀጋ እንቀበላለን›› ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ ከድህነት ወጣች ወይ? የሚለውን ለታሪክ ፍርድ እንተወው!
ባለሥልጣናቱ የተከሰሱበት ጉዳይ ሳይነገራቸው ክስ ሳይመሠረትባቸው ለወራት በእስር ቆይተዋል። ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ግን የደርግ አባላት እና ንዑስ ደርግ በመባል የሚታወቁ በታላቁ ቤተ መንግሥት ተሰበሰቡ። በስብሰባው የደርጉ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ጀነራል አማን አንዶም ግን አልተገኙም።
በባለሥልጣናቱ ላይ አንዳችም ክስ ሳይመሠረትባቸው ደርግ ራሱ ከሳሽ ራሱ ፈራጅ ሆኖ ሥልጣኑን ተጠቅሞ በዚሁ ቀን በስብሰባ የግድያ ውሳኔ አሳለፈባቸው። በ60ዎቹም የቀድሞ ባለሥልጣናት ላይ የግድያ እርምጃው የተወሰደው ከርቸሌ ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት ግቢ ውስጥ ሲሆን፣ አስከሬናቸውም እዚያው እንዲቀበር ተደርጎ ዘመድም እንዳይጠይቅ ተከልክሏል።
በዚህ እርምጃ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ አገረ ገዢዎች የካቢኔ ሚኒስትሮችና የጦር ጄኔራሎች ያለፍርድ ውሳኔ ነው የተገደሉት። ‹‹ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› ሲል የነበረው ደርግ በትረ ሥልጣኑን እንደጨበጠ ‹‹በደም ተጨመላለቀ›› የሚል ወቀሳ ሲሰነዘርበት ኖረ።
ግድያውን አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። የሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች በሚል ገነት አየለ በጻፉት መጽሐፍ ላይ የግድያ እርምጃውን ለመውሰድ አስቀድሞ የተያዘ አጀንዳ እንዳልነበር ኮሎኔል መንግሥቱ ገልጸዋል። ‹‹ማንም አመነም አላመነም እኔ የምናገረው እውነቱን ነው፤ በበኩሌ የተወሰደውን እርምጃ አልደገፍኩትም፤ ሌሎችም የደርግ አባላት በስልሳዎቹ ግድያ ሊጠየቁ አይገባም፤ ምክንያቱም በተቆጡ በተናደዱ የንኡስ ደርግ አባላት ድምጽ ተውጠን በዚያ ውስጥ ተዘፍቀን የተላለፈ ውሳኔ በመሆኑ። እኛ የተነሳንለትና ቆመንለት የነበረው ዓላማ ይሄ አልነበረም። ያንን የመሰለ ውሳኔ ለመወሰን አላሰብንም ነበር።›› ብለዋል። የዚያን እለት ብቸኛው አጀንዳ የጀነራል አማን ጉዳይ እንደነበረም ጠቅሰው፣ ስለ ኃይለስላሴ መንግሥት ባለሥልጣኖች የሚል ነገር ጨርሶ አልነበረም ተብሏል። ችግሩ ኮሎኔል መንግሥቱ በዚያ ጉዳይ ላይ ‹‹አድርገነዋል›› ይላሉ ወይ የሚለውን የማመን አለማመን ጉዳይ ነው።
በደርግ ዘመን ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍስሃ ደስታ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚል መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ጉባዔውን በሊቀመንበርነት መምራት ብቻ ሳይሆን አጀንዳውን አዘጋጅተው አቅርበዋል ሲሉ ጽፈዋል። ኮሎኔል መንግሥቱ ኅዳር 13 ቀን 1967 ዓ.ም የእስርና የአብዮታዊ እርምጃ ደብዳቤ ጽፈዋል። በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ስምና ፊርማ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ‹‹በቀድሞ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የተላለፈውን ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ ተግባራዊ ስለማድረግ ይመለከታል›› በሚል የተጻፈ ነው።
በዚሁ ደብዳቤ ለ54 ሰዎች መቀበሪያ ጉድጓድ እርምጃው በሚወሰድበት ቦታ በዶዘር እንዲቆፈር ታዝዟል፤ እርምጃው የሚወሰድባቸው ባለሥልጣናት ዝርዝርም ተለይቷል። ኮሎኔል መንግሥቱ እንዳሉት ሳይሆን በእስረኞቹ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ነው ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ስብሰባ የተካሄደው።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ በመጀመር የካቢኔ ሚኒስትሮች፣ ጠቅላይ ገዥዎች፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረቦች፣ የንጉሡ ባለሥልጣናት ስማቸው ሲጠራ ተሰብሳቢዎቹ በወሬ ወይም በአሉባልታ የሰሙትን እየተናገሩ ድምጽ መስጠቱ ቀጠለ። ሃምሳ ዘጠነኛው ተራ ሲደርስ በቃ የሚል ስለተሰማ ሰብሳቢው ለዛሬ እዚህ ላይ እናበቃለን፤ የቀሩ ካለ ሌላ ጊዜ ይታያል በማለት የድምጽ መስጠት ሂደት ቆመ ሲሉ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።
ያም ሆነ ይህ ሁሉም ያመኑት ነገር ቢኖር 60ዎቹ መገደላቸውን ነው። የተገደሉት ሰዎች ደግሞ በየዘርፉ ልምድ እና እውቀት የነበራቸው ናቸው። እንዲህ አይነት ታሪኮችን ስናስታውስ ዋና ቁም ነገሩ ከስህተቶች ለመማር ነው፤ አኩሪ የሆኑ የአባቶቻችንን ጀግንነትና ጥበብ ደግሞ እንድናስቀጥላቸው ነው። እንደ ዓድዋ፣ ጉራዕ፣ ጉንደት፣ ካራማራ የመሳሰሉ የድል ታሪኮቻችንን በኩራት ስንናገራቸው እንደ ሰገሌ ጦርነት እና የ60ዎቹ አይነት የእርስበርስ ግድያዎችን ደግሞ ከስህተቶቻችን እንድንማርባቸው ነው። ምክንያቱም የ60ዎቹ ግድያ የደርግን ታሪክ ጥላሸት ቀብቶታል።
በአኩሪ ታሪኮቻችን እንኩራ፤ ከስህቶቻችን እንማር!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም