የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ አገልግሎት ምርጥ አየር መንገድ በመባል ተሸለመ

አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ አገልግሎት የዓመቱ ምርጥ አየር መንገድ በመሆን ለስምንተኛ ጊዜ ተሸልሟል።

በግብፅ ካይሮ በተካሄደው 56ኛው የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር አጠቃላይ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ አገልግሎት የዓመቱ ምርጥ አየር መንገድ በመባል ሽልማቱን ማሸነፉ ተገልጿል። አየር መንገዱ ሽልማቱን ሲያሸንፍ የአሁኑ ለ8ኛ ጊዜ መሆኑ ተነግሯል።

የአየር መንገዱ የተሰጠው እውቅና ለአገልግሎቱ፣ ለትርፋማነቱ፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለው ትብብር፣ በአሕጉሪቱ በካርጎ አገልግሎት እድገት እና አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያገናኝ ላቅ ያለ የሥራ አፈጻጸም በማስመዝገቡ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፥ ሽልማቱ የአየር መንገዱ ቁርጠኝነት እና ጽናት ማረጋገጫ ነው።

በተጨማሪም ሽልማቱ የአፍሪካን ትስስር ለማሳደግና የኢኮኖሚ እድገትን ለማቀጣጠል ያለንን የማይናወጥ ተልዕኮ የሚያሳይ ነው ሲሉ አንስተው፤ ለዚህም ለተጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

በአሠራር ብቃቱ እና ስኬታማነቱ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደንበኞች ምቹ የሆነ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትና የጉዞ ልምድን ማበርከቱን ቀጥሏል ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኔትወርክን በማስፋት፣ በዘመናዊ አውሮፕላኖች ላይ ኢንቨስት በማድረግ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የደንበኞች አገልግሎት በመስጠት አሕጉሩን ለማገልገል ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱን ጠቁመዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You