የዛሬው ፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ግንፍሌ ሺ ሰማኒያ ተብሎ ወደሚጠራው ሰፈር ይስደናል:: ዝግጅት ክፍሉም በወይዘሮ ትዕግስት ጥበቡ እና በአራዳ ክፍለ ከተማ እንዲሁም በአራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ 7 አመራሮች መካከል የተፈጠረን ውዝግብ ይዳስሳል::
ቅሬታዋ አቅራቢዋ፣ «በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ እና በዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 የሚገኙ አመራሮች በፈጸሙት የመልካም አስተዳደር ችግር ለዓመታት መንግስት ሲያስተዳደረው የነበረን የቀበሌ ቤት ከህግ እና ከመመሪያ ውጪ በሆነ አግባብ ወደ ግል ይዞታነት እንዲዞር ተደርጓል:: በመልካም አስተዳደር ችግር ሀገሪቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ያልተገባ ጫና የኢትዮጵያ ህዝብ አይቶ ይፍረድ» ስትል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት ብላለች::
የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኛቸውን ማስረጃዎች በጥልቀት በመመርምር የሚከተለውን ዘገባ ሰርቷል:: መልካም ንባብ::
አቤቱታ አቅራቢዋ
እንደ ቅሬታ አቅራቢዋ ወይዘሮ ትዕግስት ጥበቡ ገለጻ፤ አሁን ላይ ውዝግብ የተነሳበት ቤት 1944 ዓ.ም በአያቷ ፊታውራሪ ገብረሚካኤል ወልደተንሳይ የተሰራ እና በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 በቤት ቁጥር 037 ተመዝግቦ የሚገኝ ነው::
ውዝግብ ያስነሳው ቤት በደግር ዘመነ መንግስት በአዋጅ 47/67 መሰረት በመንግስት ትርፍ ቤት ነው በሚል መወረሱን ወይዘሮ ትዕግስት ታስረዳለች፤ በወቅቱ ከቤቶች አስተዳደር ጋር ተያይዞ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ፊታውራሪ ገብረሚኤል ከነበረባቸው ችግር በመነሳት የተወረሰውን ቤት በኪራይ መልኩ ተመልሶ ተሰጥቷቸው እንደነበር ትገልጻለች::
ቤቱ በኪራይ መልኩ በምን አግባብ ለፊታውራሪ ገብረሚካኤል እንደተመለሰ የምትጠይቀው ወይዘሮ ትዕግሰት፤ በትርፍ ቤትነት የተወረሰውን ቤት፤ ፊታውራሪ ገብረሚካኤል በባንክ ብድር እንደሰሩትና ምንም እንኳን ቤቱ ለቤተሰባቸው አስፈላጊ ቢሆንም ከባንክ የተበደሩትን ብር ለመክፈል እንዲያግዛቸው በማሰብ ቤቱን ማከራየታቸውን ትናገራለች:: ከባንክ የተበደሩት ብድር ክፍለው በጨረሱ ጊዜም የተከራየውን ቤት ለቤተሰብ ግልጋሎት በመፈለጉ አዋጅ 47/67 ከመታወጁ አንድ አመት ቀደም ብሎ ተካራዮች እንዲወጡ አድግርገው እንደነበር ታመለክታለች ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በ1967 ዓ.ም ቤቱ በአዋጅ 47/67 እንደሚወረስ ለፊታውራሪ ገብረሚካኤል ይነገራቸዋል:: ይህን ተከትሎ ፊታውራሪ ገብረሚካኤልም ይወረሳል የተባለው ቤት ትርፍ ቤት እንዳልሆነና ቤተሰባቸው እየኖሩበት እንደሚገኝ ለመንግስት ያስረዳሉ:: ይሁን እንጂ መንግስት የፊታውራሪ ገብረሚካኤልን አቤቱታ ባለመቀበል ከባንክ ብድር ገብተው የሰሩት ቤት በትርፍ ቤትነት በቁጠር ወረሰ ::
ይህን ተከትሎ ፊታውራሪ ገብረሚካኤል ምንም እንኳን ሳያምኑበት ቤቱ በትርፍ ቤትነት ቢወሰድባቸውም የቤተሰባቸው ቁጥር ብዙ ስለሆነ የተወረሰው ቤት በኪራይ እንዲሰጣቸው መንግስትን በደብዳቤ ይጠይቃሉ:: መንግስትም ፊታውራሪ ገብረሚካኤል ያለባቸውን ችግር ከግምት በማስገባት የተወረሰባቸውን ቤት በ60 ብር እንዲከራዩት ፈቀደላቸው ::
ፊታውራሪ ገብረሚካኤል እና ቤተሰባቸው ለአንድ ዓመት ያህል በቤቱ በኪራይ ኖረውበታል የምትለው አቤታ አቅራቢዋ፤ ይሁንና ከአንድ ዓመት የኪራይ ቆይታ በኋላ በ1968 ዓ.ም ቤቱ ግራዝማች በቀለ ሙላት ለተባሉ ግለሰብ ተላልፎ መሰጠቱን ትገልጻለች :: ፊታውራሪ ገብረሚካኤል እና ቤተሰባቸው በኪራይ ከተሰጡት ቤት የወጡበት ምክንያት በታጣቂዎች ተገደው እንደሆነም ትናገራለች::
ቤቱ ለግራዝማች በቀለ በምን መልኩ ተላልፎ እንደተሰጠ የሚያሳዩ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በዋቢነት አቅርባለች :: ግራዝማች በቀለ እና ቤተሰባቸው አሁን ላይ ውዝግብ በተነሳበት ቤት ውስጥ ከ50 ዓመት በላይ ኖረውበታል የምትለው አቤቱታ አቅራቢዋ፤ ሲኖሩበት ግን ከመንግስት ጋር ምንም አይነት ውል አልነበራቸውም ትላለች፤ ለተከራዩት ቤት ኪራይ እንደማይከፍሉም ጠቅሳ፤ ይህም የታወቀው የጋራዝማች በቀለ ቤተሰቦች ቤቱን ለመሸጥ ካርታ ለማውጣት በሂደት ላይ በነበሩበት ወቅት መሆኑን ታስረዳለች::
እንደ ወይዘሮ ትዕግስት አባባል፤ ውዝግብ የተነሳበት ቤት በአዋጅ 47/67 ሲወረስ ፊታውራሪ ገብረሚካኤል ምንም አይነት የካሳ አበል አልተቀበሉበትም:: በአንድ ወቅት እንደ ሀገር አበል ያልተበላባቸው ቤቶች ለባለቤታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ስለነበር አሁን ውዝግብ የተነሳበትን ቤት እና ሌሎች ከፊታውራሪ ገብረሚካኤል ተወርሰው የነበሩ ቤቶቹን ለማስመለስ ወይዘሮ ትዕግስት እና ቤተሰቦቿ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር፤ ነገር ግን በመንግስት ተጀምሮ የነበረው አበል ያልተበላባቸውን ቤቶች የማስመለስ ሂደት ምክንያቱን በውል በማታውቀው ሁኔታ መቆሙን ሰማች::
በ2013 ዓ.ም የግራዝማች በቀለ ቤተሰቦች በቤቱ ላይ ካርታ ለማውጣት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው የሚል መረጃ እንደሰማች የምትናገረው አቤቱታ አቅራቢዋ፤ የሰማቸውን መረጃ ለማረጋጋጥ ወደ ወረዳ ሰባት ማቅናቷንና ወረዳ ያገኘችው መረጃም የሰማችው መረጃ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑን ታስረዳለች ::
ይህን ተከትሎ «እንዴት መንግስት የወረሰው እና መንግስት የሚያስተዳደረው ቤት ላይ ካርታ ይወጣበታል? ቤቱ ወደ ግል ከዞረ ደግሞ እኛ የፊታውራሪ ገብረሚካኤል ቤተሰቦች አበል ያልበላንበት መሆኑ እየታወቀ ለእኛ መመለስ ሲገባው እንዴት ለተከራዮች ተላልፎ ይሰጣል?» በማለት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው በአራዳ ክፍለ ከተማ ለወረዳ ሰባት ለሚገኙ የመንግስት አመራር አቤት ማለቷን ትገልጻለች::
ቤቱ ከሶስት አካላት በአንዱ መሆን አለበት የምትለው ወይዘሮ ትዕግስት፤ አንደኛ ቤቱን መንግስት በልዩ ሁኔታ ልዩ የሚያስተዳደረው መሆን ነበረበት፤ ሁለተኛ የቀበሌ ቤት ሆኖ የሚከራይ ቤቶች አስተዳደር የሚመራ እና በሶስተኛነት ቤቱ በማካካሻነት የተሰጠ ከሆነ ደግሞ ቤቱን በማካካሻነት ለተሰጠው አካል ካርታ ሊሰራለት አንደሚገባም ታስረዳለች::
ነገር ግን ጉዳዩን ለማማከር ወደ ወረዳ ሰባት ባቀናችበት ወቅት ጉዳዩ የሚመለከታቸው በወረዳው የሚገኙ ሹመኞች እና ባለሙያዎች ስለቤቱ በጭራሽ እንደማያውቁት እና በማን እየተዳደረ እንደሚገኝ መረጃው እንደሌላቸው የገለጹላት መሆኑን ታመለከረታለች:: ይህን ተከልትሎ አቤቱታ አቅራቢዋም በአዋጅ 47/67 መንግስት ቤቱ የተወረሰበትን፣ መንግስትም በወቅቱ መልሶ ለቤሰቦቿ በኪራይ ሰጥቶ እንደነበር የሚያሳዩ እና ለእነግራዝማች በቀለ እንዴት ተሰጣቸው የሚለውን የያዙ የሰነድ ማስረጃዎችን ለወረዳ አመራሮች ታቀርባለች::
ይህን ተከትሎ የወረዳ አስተዳደሪው ‹‹ያቀረብሽው የሰነድ ማስረጃ የቤቱን ትክክለኛ ምንነት አይገልጽም›› የሚል ምላሽ እንደሰጣት የምትናገረው ወይዘሮ ትዕግስት፤ ይህን ተከትሎ ስለቤቱ ምንነት ሊያስረዱ ይችላሉ የምታላቸውን ሰነዶች በሙሉ ለወረዳ አስተዳደሩ ታቀርባለች:: ይሁንና የሰነድ ማስረጃዎችን የተመለከተው የወረዳ አስተዳደር ቤቱን በወረዳው እንደማይታወቅ በድጋሜ ገልጾ፤ ጉዳዩ በወረዳው ማለቅ ሲገባው ጉዳዩ በፍርድ ቤት ቢታይ አዋጭ እንደሆነ አቅጣጫ እንደሰጣት እና ወደፍርድ ቤት በመሄድ በህግ ማሳየት እንዳለባት እንደአማከራት ታስረዳለች ::
ጉዳዩ በራሱ መጨረስ ሲገባው ወደ ፍርድ ቤት የገፋበት ዋና ምክንያት ከበላይ አካል በሚደረግበት ጫና መሆኑን እንደነገራትም ትግልጻለች :: ይህን ተከትሎ ጉዳዩን ለማሳወቅ ወደ ክፍለ ከተማ መምጣቷን ጠቅሳ፤ ነገር ግን ለበርካታ ጊዜ ወደ ክፍለ ከተማ ብትመላለስም እኛ በስልክ ደውለን እንጠራሻለን በማለት ምላሽ ከመስጠት ውጭ ሊጠሯት አለመቻላቸውን ታስረዳለች:: በክፍለ ከተማ አመራሮች ተስፋ የቆረጠችው አቤቱታ አቅራቢዋ፤ በ2013 ዓ.ም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዷን ጠቁማለች::
ከፍርድ ቤቱም እግድ በማውጣት በቤቱ ላይ ካርታ ለማውጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ማስቆሟን ታስረዳለች። ይሁንና በወቅቱ ልጅ በመውለዷ ጉዳዩን የሚመለከትላት ሰው በማጣቷ እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ስጋት ስለነበር ጉዳዩ በተንጠልጠል ላይ እያለ ወደ ፍርድ ቤት ሳትሄድ መቅረቷን ትናገራለች ::
ይህን ተከትሎ ፍርድ ቤት ምን እንደወሰነ የማታውቀው አቤቱታ አቅራቢዋ፤ ከአራስ ቤቷ ስትመለስ በ2014 ዓ.ም ጉዳዩ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማጣራት እንቅስቃሴ ትጀምራለች :: ጉዳዩ የሚመከታቸውን የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮችን ማናገሯን የምትጠቅሰው ወይዘሮዋ፤ በቤቱ ካርታ እንደወጣበት እና ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ መሸጡ እንደተነገራት ታስረዳለች ::
ይህን ተከትሎ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ለምን ቤቱ ይሻጣል? ብላ ብትጠይቅም ምላሽ የሚሰጣት ሰው እንዳጣች ትናገራለች :: እስካሁንም ድረስ ስለቤቱ ጉዳይ ወረዳ እና ክፍለ ከተማ ጉዳዩ የሚመከታቸውን አካላት እየጠየቀች ብትገኝም አመራሮች እርስ በእርሳቸው እንደማይስማሙ እና አንድ አይነት መልስ እንደማይሰጧት ጠቁማለች ::
ውዝግ የተነሳበት ቤት በወፍ በረር
ቤቱ በ1944 ዓ.ም የተሰራ ሲሆን፣ በ200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው :: ሰባት ክፍሎችም አሉት :: ወለሉ የጣውላ ፤ ግድግዳው የጭቃ እና በውሃ ልክ የሰተራ ነው :: ቤቱ የራሱ የሆነ ኩሽና እና የንጽህና መጠበቂያ ቤት ያለው ሲሆን፣ የግቢውም አጥር በቆርቆሮ የታጠረ ነው :: ቤቱ በ1944 ዓ.ም ሲሰራ ስድስት ሺህ ብር ወጭ ተደርጎበታል:: በአጠቃላይ ቤቱ ይህ ጎደለው የማይባል ነው :: እስከዛሬ ድረስ ቤቱ ምንም አይነት እድሳት ሳይደረግለት ሰዎች እየኖሩበት ይገኛል::
ከሰነድ የተገኙ ማስረጃዎች
ሰነድ አንድ፡- ውዝግብ የተነሳበት ቤት መገኛ ቦታው በቀድሞ ስሙ በሸዋ ክፍለ ሀገር፣ አዲስ አባባ ከተማ፣ ምስራቅ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ መካከለኛ 09 ንዑስ ወረዳ 02 ቀበሌ አፈንጉስ ነሲቡ የሚገኝ ሲሆን፤ በካርታ ቁጥር 6361 የተመዘገበ እና የቦታው ስፋት 988 ካሬ ሜትር እንደነበር ፤ ቦታው የተገዛው እና ግንባታ የተካሄደውም በ1944 ዓ.ም ሲሆን፣ ቦታው የተገዛበት ሁለት ሺህ 500 ብር ነው :: በአዋጅ 47/67 ከተወረሰው ቤት በተጨማሪ 200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤት መኖሩ፤ የተወረሰው ቤትም ሰባት ክፍሎች ያለውና በቅጽ 003 የተመዘገበ መሆኑን የሚያሳይ ሰነድ አንደኛው ነው ::
ሰነድ ሁለት፡- አዋጁ ከታወጀ ከቀናት በኋላ ትርፍ ቤት የነበራቸው ፊታውራሪ ገብረሚካኤል የተወረሰባቸውን ቤት ትርፍ ቤት እንዳልሆነ አቤቱታ ያቀረቡበት እና አቤቱታቸው ውድቅ መደረጉን ፤ነገር ግን ከነበረባቸው ችግር አኳያ ቤቱን በወር 60 ብር እየከፈሉ እንደጠቀሙበት በህብረተሰባዊት ኢትየጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት የሥራና ቤት ሚኒስቴር የቤቶች አስተዳደር ድርጅት ጋር የኪራይ ውል የተዋዋሉበት እና ኪራይ የከፈሉበት ሰነድ ሁለተኛው ነው :: በዚህ ሰነድ ፊታውራሪ ገረሚካኤል ቤቱን ከሐምሌ 30 ቀን 1967 ዓ.ም ጀምሮ ኪራይ መክፈላቸው ተመላክቷል::
ሰነድ ሶስት፡- ግራዝማች በቀለ ሙላት የተባሉ ግለሰብ በ8/6/68 ዓ.ም የተጻፈ የአከራይ እና ተከራይ የውል ስምምነት እንደሚያመላክተው፤ በሸዋ ክፍለ ሀገር አዲስ አበባ ከተማ ምስራቅ ክፍለ ከተማ ወረዳ መካከለኛ 09 ንዑስ ወረዳ 02 ቀበሌ አፈንጉስ ነሲቡ ሰፈር (ቶኩማ ቀበሌ) የሚገኝን ቤት ከህብረተሰባዊት ኢትየጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት የሥራና ቤት ሚኒስቴር የቤቶች አስተዳደር ድርጅት በ60 ብር እንደተከራዩ ያመላክታል::
ሰነድ አራት፡- የአዲስ አባበ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት፤ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በኦሮሚያ ክልል መቱ ከተማ በግራዝማች በቀለ ተመዝግቦ የሚገኝ የነበረ እና መንግስት በአዋጅ 47/67 በማካካሻነት የወሰደው ቤት ስለመኖሩ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክላለዊ መንግስትን ጠይቆ ነበር :: የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትም ለአዲስ አባበ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ፤ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት እንዳሳወቀው በመቱ ከተማ በግራዝማች በቀለ ተመዝግቦ የሚገኝ የነበረ እና መንግስት በአዋጅ 47/67 በማካካሻነት የወሰደው ቤት ስለመኖሩ ቀን እና ቁጥር በተጠቀሰበት በደብዳቤ አሳውቋል:: ሰነድ አምስት፡- ግራዝማች በቀለ፣ በአዋጅ 47/67 በመቱ ከተማ የሚገኘውን ቤታቸውን ያስረከቡበት ቁጥር እና ቀን ያለው ቅጽ ለዝግጅት ክፍላችን ቀርቧል::
መመሪያው ምን ይላል? እንደወረደ!
ከመንግስት ቤቶች አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 5/2011 ተብሎ በተጠቀሰው መመሪያ ክፍል ስደስት ንዑስ ቁጥር ስድስት የቤት አበል እና ማካካሻ ምን መምስል እንዳለበት በግልጽ ተቀምጧል:: በዚህ መሰረት መመሪያው አንደወረደ ምን ይላል የሚለውን እንደሚከተለው አቅርበናል :: በዚህ ክፍል ቁጥር 30 ስለ አበል አከፋፈል በግልጽ ተመላክቷል:: በዚህ መሰረት፡-
1. በአዋጁ 47/67 አንቀጽ 20 እና 21 መሰረት መኖሪያ ቤታቸውን ወይም ድርጅታቸውን ወይም ሁለቱንም በትርፍነት ወደ መንግስት ይዞታ ተዘዋውሮባቸው ከቤት ኪራይ በስተቀር ሌላ ገቢ የሌላቸው እና ከብር 100 በታች ኪራይ የነበረውን ቤት አሰረክበው አበል ሲከፈልባቸው የነበሩ ቤቶችን መረጃ አደራጅቶ ይይዛል፣
2. ቢሮው ወይም ቢሮው የሚወክለው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ “1” መሠረት አበል የተፈቀደላቸውን ግለሰቦች ዝርዝር፣ የቤቱ ሁኔታና የአበል መጠን የሚገልጽ መረጃ በማዘጋጀት አበል እንዲከፈል ለፋይናንስ ቢሮ ያስተላልፋል፣
3. የቀበሌ ቤቶቹ በቢሮው አስተዳደር ወይም ባለቤትነት ስር ሆነው ነገር ግን የአበል ክፍያው በፌደራል የመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን እየተከፈላቸው ቆይቶ የአበል ክፍያ የተቋረጠባቸውን ግለሰቦች ጥያቄ ተቀብሎ በማጥራት እና ከፌዴራል የመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ይከፈላቸው የነበረውን ክፍያ እና ክፍያው የተቋረጠበትን ቀን በጽሁፍ ጠይቆ መረጃውን በማደራጀት ውሳኔ እንዲሰጥበት ለቢሮው ያቀርባል፣
4. ቢሮው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ “2” መሠረት አበል ሊከፈለው የሚገባው ቀደም ብሎ አዋጁ ሲታወጅ ጀምሮ አበል የሚቀበል መሆኑ በቅድሚያ መረጋገጥ ይኖርበታል፣
5. ትርፍ ቤት አስረክበው ቅድሚያ አበል ይቀበሉ የነበሩ ባልና ሚስት ከሁለቱ አንዱ በሞት ሲለዩ _ ለአካለ _ መጠን ያልደረሱ ልጆች በሚያቀርቡት የወራሽነት ማረጋገጫ መሠረት ቀድሞ ይከፈል ከነበረው አበል 50 በመቶ ወይም ግማሽ ይከፈላቸዋል፤ ሆኖም ተከራዩ እና የትዳር ጓደኛው ሁለቱም በሞት ቢለዩ ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች ብቻ ቀድሞ ሲከፈል የነበረው አበል ይከፈላቸዋል፣
6. አበል የሚከፈለው አበል የሚከፈልበት ቤት በቦታው እስካለና ከተከራየ ብቻ ሆኖ ቤቱ አርጅቶ ወይም በልማት ከፈረሰ ወይም አበል ተቀባዩ በተለያየ መንገድ የራሱን ገቢ ማግኘቱ ከተረጋገጠ አበል እንዲቋረጥ ይደረጋል፣
7. በዚህ አንቀጽ መሠረት የተከፈለው የአበል ክፍያ ለቤቱ ከሚከፈለው ካሳ ተቀናሽ ይሆናል:: ጠቅላላ ክፍያው ለቤቱ ከሚሰጠው ካሳ መብለጥ የለበትም፤ ስለ ካሳ ግምት፣ ውዝፍ ክፍያ ሌሎች ከአበል ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ጥያቄን ቢሮው መረጃዎችን በማሰባሰብ እና በማጥናት ለከተማው አስተዳደር ካቢኔ አቅርቦ ያስወስናል፤ ሲወሰንም ተግባራዊ ያደርጋል::
8. የአበል ክፍያ መጠኑ ከቤቱ ወርሐዊ ኪራይ ዋጋ መብለጥ የለበትም:: ሲል ያስቀምታል ::
ከዚህ በተጨማሪ በመመሪያ ቁጥር 5/2011 ክፍል ስድስት፣ ንዑስ ቁጥር 31 በአደራ የተያዙ ቤቶችን ለመመለስ መሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች በግልጽ ተቀምጧል ። በዚህ መሰረት፡-
1. በአደራ ያስረከበው ቤት በአዋጁ ያልተወረሰ መሆኑ በደብዳቤ/በሰነድ ተረጋግጦ ከሚመለከተው አካል ሲቀርብ፣
2. የቀድሞ የግል ቤቱን የመንግስት ቤቶችን ለማስተዳደር ስልጣን ለተሰጠው አካል በአደራ ማስረከቡን የሚገልጽ ቅጽ ወይም ሰነድ ተረጋግጦ ሲቀርብ፣
3. በማካካሻ የተሰጠው ቤት የመንግስት ቤቶችን ለማስተዳደር ስልጣን ከተሰጠው አካል መረከቡን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ሲቀርብ፣
4. በማካካሻ የተሰጠው ቤት በአሁኑ ወቅትም በእጁ የሚገኝና እየተገለገሉበት ያሉ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ቤቱን ከሚያስተዳድረው አካል ሲቀርብ፣
5. ከላይ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ አመልካቹ በቀድሞው ቤት ላይ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ ባለመብቶች ያለመኖራቸውን ወይም የይገባኛል ጥያቄ በተጻፈ ደብዳቤ የሚያነሱ ካሉም ቤቱ በጠያቂው ስም መመለሱ የይገባኛል ባይ መብትን የሚያሳጣ መሆኑ በጽሁፍ/በአቃቢ ህግ በሚዘጋጅ ቅጽ/መረጋገጥ አለበት:
ሌላው ከማካካሻ እና አበል ጋር ተያይዞ በመመሪያ ቁጥር 5/2011 ክፍል ስድስት ንዑስ ቁጥር 32 እንደተመላከተው፤ በማካካሻነት የተያዘ ቤትን ለመመለስ መሟላት ስለሚገባቸው መስፈርቶች በግልጽ ያትታል:: በዚህ መሰረት፡-
1. የለውጡ ቤት እንዲጸናለት ለሚጠይቅ አመልካች ቤቱ ከመሰጠቱ በፊት በቅድሚያ ከፍ ብሎ አንቀጽ 31 ንዑስ አንቀጽ ከ1 እስከ 5 የተዘረዘሩት መስፈርቶች መሟላት አለባቸው::
2. የቀድሞ ቤቱ በልማት ምክንያት ከፈረሰ ወይም ለህዝብ አገልግሎት የተላለፈ ከሆነ ይህንኑ የሚያስረዳ የማረጋገጫ ደብዳቤ ቤቱን ለማስተዳደር ስልጣን ከተሰጠው አካል እንዲሁም በማካካሻ የተሰጠውን ቤት የራሱ ይዞታ እንዲሆን የጠየቀበት የጽሁፍ ማስረጃ መቅረብ አለበት::
ሌላው በመመሪያ ቁጥር 5/2011 ክፍል ስድስት ንዑስ ቁጥር 33 የማካካሻ ቤት መስተንግዶን በተመለከተ ተጠቅሷል:: በዚህ መሰረት፡-
1. የማካካሻ ቤት አሰጣጥ የተከናወነው በከተማው ከአንድ መንደር ወደ ሌላ መንደር ከሆነ እና ነባር ቤታቸው ያልፈረሰ ወይም በመንግስት እጅ የሚገኝ ከሆነ አመልካቾች በመረጡት በአንድ ቤት ላይ የባለቤትነት መብት የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፤ ይህንንም ለማድረግ የአመልከቾች የመጀመሪያ ምርጫ ሊጠበቅላቸው ይገባል:: ይህም አማራጭ ከአዲስ አበባ ወደ ሌላ ከተሞች ወይም ክሌሎች ከተሞች ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ለተገኙ የማካካሻ ቤቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጻሚ ይሆናል::
2. ማካካሻው በከተማው ከአንድ መንደር ወደ ሌላ መንደር ሆኖ የአመልካቾች የቀድሞ ቤት የፈረሰ እና በመንግስት እጅ የማይገኝ ከሆነ የቀድሞ ቤት ይመለስልኝ በሚል የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የሌለ በመሆኑ በምትክነት ይዘውት በሚገኘው የመንግስት ቤት ላይ የባለቤትነት መብት ሊፈጠርላቸው ይገባል::
3. በማካካሻነት የተሰጡ ቤቶችም ሆነ የግለሰቦች የቀድሞ ቤቶች ፈርሰው ከሆነ እነዚሁ ቤቶች በሚፈርሱበት ጊዜ አስቀድሞ በመግስት የተሰጡ መፍትሄዎች እንደሚኖሩ ይታመናል፤ ሆኖም ግን ገና ያልተስተናገዱ ሆነው ከተገኙ በቀድሞ አሰራር መሰረት የሚስተናገዱ ይሆናል::
4. የአደራና ማካካሻ ቤት ይመለስልኝ ጥያቄ ለክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ቀርቦ መረጃው ከላይ በአንቀጽ 31 እና 32 መሰረት መሟላቱ ሲረጋገጥ ብቻ እና በወረዳ ደረጃ ተደራጅቶ ለክፍለ ከተማ ሲላክ የመጨረሻ ውሳኔ በክፍለ ከተማ ደረጃ አንደሚሰጥ ያስቀምጣል ::
በመጨረሻም ዝግጅት ክፍሉ ማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ያገባኛል የሚል አካል ካለ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ነው::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2015