ጉብኝቱ የሀገራቱን ወዳጅነት ወደ ላቀ ስትራቴጂክ አጋርነት የለወጠ ነው

የኢትዮ- ፈረንሳይ ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ዛሬም ቢሆን የሀገራቱን ብሔራዊ ጥቅሞች መሠረት ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ የቀጠለ ነው። ሀገራቱ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈም በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያም ለጋራ ተጠቃሚነት ተባብረው የመሥራት ሰፊ ታሪክ ያላቸው ናቸው።

ይህ የሀገራቱ ግንኙነት ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ሀገራቱ ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትብብር ባለፈም፤ በወታደራዊ ዘርፎችም አዲስ የትብብር ምዕራፍ ከፍተው እየሠሩ ነው። ቀጣይ ግንኙነታቸውን ወደላቀ ስትራቴጂክ አጋርነት በማሻገርም በትኩረት እየተንቀሳቀሱ ይገኛል፡፡

የአሁኑን ሳይጨምር ባለፉት ስድስት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለት ጊዜያት በፈረንሳይ ኦፊሻል የሥራ ጉብኝቶችን አድርገዋል። ጉብኝቶቹ በሀገራቱ መካከል የነበረውን ወዳጅነት በሁለንተናዊ መልኩ ማጠናከር ያስቻሉ፤ የትብብር ስምምነቶች እንዲፈረሙም አስቻይ ሁኔታዎችን የፈጠሩ ናቸው።

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን 2011 ዓ.ም በማድረግ በርካታ የትብብር ስምምነቶችን ፈርመዋል። ከስምምነቶቹም መካከል የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት እና የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት ተጠቃሽ ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዳግም በመመለስ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሀገራቸው ያላትን ድጋፍ አረጋግጠዋል። ለሪፎርሙ ስኬት የሚያስፈልገውን ዓለም አቀፍ ድጋፍ በማፈላለግ ሂደት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተው ተመልሰዋል። በወቅቱም በፈረንሳይ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የታደሰውን የብሔራዊ ቤተመንግሥት ሙዚየም መርቀው ከፍተዋል ።

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ የፈረንሳይን ሕዝብ እና መንግሥት በመወከል ሆነ በግላቸው ለሀገራችን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ፤ የሁለቱ ሀገራት የቀደመ ግንኙነት ወደ አዲስ ሁለንተናዊ የትብብር ምዕራፍ አሳድጎታል። ከሁሉም በላይ የፈረንሳይ ሕዝብ እና መንግሥት ለኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት ያላቸውን አጋርነትም በተጨባጭ አሳይቷል።

ከእዚህም ባለፈ የፈረንሳይ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰላማዊ የባሕር በር ጥያቄ ከመቀበል ጀምሮ፤ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግሥት እየሄደበት ያለውን መንገድ በመደገፍ ረገድ የሚጠቀስ ነው። በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር በሚደረገው አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥረት ውስጥም የፈረንሳይ መንግሥት ስትራቴጂክ አጋርነት ከፍ ያለ ነው።

የፈረንሳይ መንግሥት ለአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የሰላም እና የልማት ጥያቄ ዋነኛ አጋር መሆኑ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሥልጣን ዘመን በተጨባጭ እየታየ ነው። ይህ የፕሬዚዳንቱ ከፍ ያለ የትብብር እና የወዳጅነት መነሳሳት ከኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ከፍያለ እውቅና ተችሮታል።

በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ዓለም አቀፍ የሽብር ስጋት፤ በተለይም አሁን ላይ በቀይ ባሕር የንግድ ቀጣና እያጋጠመ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት የፈረንሳይ መንግሥት የሕዝባችንን የባሕር በር ጥያቄ ከቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ዳር አስተሳስሮ በማየት እየሄደበት ያለው መንገድ ለኢትዮጵያውያን ያለውን አጋርነት በተጨባጭ ከማሳየት ባለፈ ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም ያለውን ቀና አመለካከት የሚያሳይ ነው።

በአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐይ የፈረንሳይ ጉብኝት፤ በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማሳደግ የተደረሰባቸው ስምምነቶች፣ በተለይም ሀገራችን ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመረችው ጥረት ትልቅ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ፤ ለእዚህም የፈረንሳይን አጋርነት የሚያሳይ ነው።

ሀገራችን የውጪ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሀገራዊ ጸጋዎችን በተሻለ መልኩ አልምቶ ለዜጎች የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የጀመረችው ጥረት ይህንን ለማሳካት እያደረገቻቸው ያሉ የፖሊሲ እና የሕግ ክለሳዎች የፈረንሳይ ባለሀብቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስቻይ ሁኔታዎችን የፈጠሩ፣ እድሎችን ወደ ተጨባጭ ልማድ መለወጥ የሚያስችሉ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም “ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ግንኙነታችንን እና ትብብራችንን በሚያጠናክሩ ሰፋ ያለ መጠነ ርዕይ ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መወያየት ምንጊዜም አስደሳች ነው። ለተደረገልን ደማቅ አቀባበል እና በታኅሣሥ ወር በአዲስ አበባ ከነበረን ውይይት ቀጥለን ስላካሄድነው ፍሬያማ ውይይት ምስጋናዬን እገልጣለሁ። ትብብራችን በብዙ ጠቃሚ ዘርፎች የቀጠለ ሲሆን፤ የንግድ ትስስሮቻችንን የበለጠ ማሳደግ ከቅድሚያ የትኩረት ማዕከሎቻችን አንዱ ነው።” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ያጋሩት መልዕክትም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ከእዚህም በላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለልኡክ ቡድናቸው በፓሪስ የተደረገላቸው ደማቅ የወዳጅነት አቀባበል፤የፈረንሳይ ሕዝብ እና መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ያላቸውን ከፍ ያለ ከበሬታ ያንጸባረቀ የቀደመው የወዳጅነት የታሪክ ምዕራፍ ወደ ላቀ ስትራቴጂክ አጋርነት መለወጡን ያመላከተ ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You