በሐረር የተከሰተው የውሃ እጥረት በኤሌክትሪክ አገልግሎት እና በክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መካከል ያስከተለው ውዝግብ

የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል የሚወስደን ሲሆን፣ በሐረሪ ክልል የውሀ ቢሮ እና በድሬደዋ ዲስትሪክት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መካከል የተፈጠረ ውዝግብ ያስመለክተናል።

የሐረሪ ክልል ውሀ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን ‹‹የድሬደዋ ሪጅን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስራት ያለበትን ባለመስራቱ የሐረር ሕዝብ በውሀ እጥረት እየተሰቃየ ነው። የድሬደዋ ዲስትሪክት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያደረሰ ያለውን በደል ተመልከቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን›› ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን አቤት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የግራ ቀኙን ሀሳብ አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድኑ ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኛቸውን ማስረጃዎች እንዲህ ሸክፎታል።

የሐረሪ ክልል ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ቅሬታ

ቅሬታ አቅራቢው አቶ ዲኒ ረመዳን ይባላሉ፤ የሐረሪ ክልል የውሀ ቢሮ ኃላፊ ናቸው። አቶ ዲኒ እንደገለጹት፤ ሐረር ከፍተኛ የሆነ የመጠጥ ውሀ ችግር ያለባት ከተማ ናት። ይህን ችግር ለመቅረፍ በረጅም፣ በመካከለኛ እና በአጭር ጊዜ የሚሰሩ ስራዎችን እያከናወኑ ነው።

ከተማዋ ውሀ የምታገኘው ከሁለት ቦታዎች ነው። አንደኛው ከሐረር ከተማ 72 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከድሬደዋ አካባቢ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከሐረር ከተማ ከ26 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ኤረር ተብላ ከምትጠራው የክልሉ ገጠራማ አካባቢ ነው።

እንደ ኃላፊው ከሆነ፤ የሐረር መልካምድራዊ አቀማመጥ ከፍተኛ ቦታ ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በከተማዋ አቅራቢያ የከርሰ ምድርም ሆነ የገጸ ምድር የውሀ አማራጮችን ማግኘት አልተቻለም። በመሆኑም የክልሉ መንግስት እና ውሀ ቢሮ የሐረር ከተማን እና የአካባቢዋ ሕዝብ ውሀ ለማጠጣት በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል።

ጥናቶችን መነሻ በማድረግ ከድሬደዋ እና ከኤረር ጉድጓዶችን በመቆፈር ወደ ከተማዋ ውሀ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል። ይሁን እንጂ አሁንም ከተማዋ ላይ በቂ የውሀ አቅርቦት የለም። ይህን ችግር ለመቅረፍ ሲባል የአጭር ጊዜ እቅድ እና ጥናት በማካሄድ ከድሬደዋ አካባቢ ከሐረር ከተማ ከ72 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ቦታ ጉድጓድ በመቆፈር የሐረርን ሕዝብ ውሀ ለማጠጣት ጥረት እየተደረገ ነው።

ውሀ የተገኘበት ቦታ በጣም ሩቅ በመሆኑ የተመረተውን ውሃ ወደ ሐረር መግፋቱ በራሱ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ጉልበት የሚፈልግ ነው። ከ72 ኪሎ ሜትር ላይ የሚመጣው ውሀ ከ1000 ሜትር ጥልቀት ካለው ጉድጓድ የተገኘ በመሆኑ ውሀውን ወደ ላይ ለመግፋት እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እና የኤሌክትሮ መካኒካል እቃዎች ማሟላት የጠየቀ ነው።

በዚህ ሁሉ ፈተናም ውስጥ ቢሆን ከአጭር ጊዜ እቅድ አንጻር ቢሮው ውሀ የማቅረብ ስራውን አላቆመም። ማድረግ ያለበትን ሁሉ እያደረገ ለሕዝቡ አገልግሎት እየሰጠ ነው። አሁን ላይ ያለው የውሀ ምርት በከተማዋ ካለው ከአጠቃላይ የሕዝቡ የውሀ ፍላጎት 50 በመቶ ነው። ይህም ቢሆን በቅርቡ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም የሆነ ነው። ከዚያ በፊት አጠቃላይ የነበረው የውሀ ምርት ከሕዝቡ ፍላጎት አንጻር 20 በመቶ ብቻ ነበር።

እንደ አቶ ዲኒ ገለጻ፤ በሀገራችን ካሉ ከተሞች አንጻር በዚህ ደረጃ የተወሳሰበ ኤሌክትሮ መካኒካል እቃዎች ያሏቸው የውሀ አግልግሎቶች የሉም። አንድ ሺህ ሜትር ወደላይ ውሀ ስትገፋ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በጣም ከፍተኛ ነው። ከድሬደዋ ወደ ሐረር የሚመጣው ውሀ በአራት ቅብብሎሽ የሚያልፍ ነው። ይህም በጣም ውድ ነው። የዚህ ሙሉ ወጭ የሚሸፈነው በክልሉ መንግስት ነው።

የውሀ አግልግሎቱ ወጭ በከፍተኛ ደረጃ የሚደጎመውም በክልሉ መንግስት ነው። አንድ ሜትር ኪውቢክ ውሀ ከድሬደዋ ለማምጣት 104 ብር አካባቢ ይፈጃል። የውሀ ቢሮው ደግሞ አንድ ሜትር ኪውቢኩን ለከተማዋ ነዋዎች የሚሸጠው 15 ብር ብቻ ነው። የተቀረውን የሚደጉመው የክልሉ መንግስት ነው። ይህም ሆኖ ወደ ከተማዋ በቂ ውሀ ባለመግባቱ ከፍተኛ የሆነ ጫና አለ።

አሁን ላይ የውሀ አግልግሎት እየሰጠን ያለነው ለከተማችን ብቻ ሳይሆን ከሐረር በድሬደዋ መስመር ለሚገኙ አራት ከተሞች ጭምር ነው የሚሉት፤ አቶ ዲኒ ሐረር ውሀ የምትጠጣው በኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን የደንጎ፣ የአዲሌ፣ የሐሮማያ እና የአወዳይን ከተሞችን ካጠጣች በኋላ ነው።

እዚህ አካባቢ ላይ የሚኖረው የሕዝብ ብዛት ደግሞ በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ ሳቢያ በአራቱ ከተሞች ያለው የውሀ ፍላጎቱ ይጨምራል። ይህም በየጊዜው ወደ ከተማዋ የሚገባውን ውሀ በእጅጉ እየቀነሰው መሆኑን ያስረዳሉ።

የከተሞቹን የውሀ ችግር ለማቃለል የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ይዘው እየሰሩ ቢሆንም፤ በአካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ስለሚያጋጥም ባሰቡት ልክ መስራት እንዳይችሉ እንቅፋት እንደተፈጠረባቸው ይገልጻሉ።

መብራት ከሌለ በፍጹም ውሀ አይኖርም። በከፍተኛ ኃይል አንድ ሺ ሜትር ወደ ላይ ተገፍቶ የወጣው ውሀ መብራት ሲጠፋ ወደኋላ ይመለሳል። ይህ ደግሞ በርካታ ጉዳቶችን ያስከትላል። ለአብነት ብንጠቅስ እንኳን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ እና የውሀ ብክነት ያመጣል።

መብራት ተቋርጦ ውሀ ወደኋላ ሲመለስ በከፍተኛ ገንዘብ የተገዙ የኤሌክትሮ መካኒካል ማሽነሪዎችን ለከፍተኛ ብልሽት ይዳርጋል። ይህም ችግሩን በ‹‹እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ያደርገዋል። በዚህ የተነሳም የመብራት መቆራረጡ በሚፈልገው ደረጃ ውሀ አምርተው ከተማቸውን ለማጠጣት እክል እንደፈጠረባቸው ያመለክታሉ።

ይህ ችግር ዛሬ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን ባለፉት ዓመታትም የነበረ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዲኒ፤ ለአብነት ያህል ባለፈው በ2015 ዓ.ም ብቻ ከጠቅላላ የዓመቱ ቀናት ውስጥ በ104 ቀናት ውስጥ መብራት አልነበረም። ይህም በዓመቱ ውስጥ 104 ቀናት ውሀ ማምረት እንዳይቻል አድርጓል። ከተማዋ ውስጥ ያለውን የውሀ ችግር በከፍተኛ ደረጃ አባብሶታል።

ይህንም ችግር ለመቅረፍ ከውሀ አገልግሎቱ ጋር ብቻ የተገናኘ የኤልክትሪክ ኃይል እንዲዘረጋለት ለማድረግ እና ክፍያ ለመክፈል እቅድ ተይዞ እሱን ወደ ትግበራ ገብቶ ነበር። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ድሬደዋ መብራት ኃይል አካባቢ ላይ ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች በመኖራቸው ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ መግባት አልቻሉም።

አሁንም ከፍተኛ የሆነ የኃይል መቆራረጥ እያጋጠመ ነው፤ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከድሬደዋ መብራት ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ደጋግመው ተነጋግረዋል። ንግግሩም ቢሆን ዛሬ ላይ የተጀመረ ሳይሆን ላለፉት በርካታ ዓመታት የተደረገ ነው። ነገር ግን አሁንም መፍትሔ ያላገኘ ችግር ሆኖ ቀጥሏል።

ገንዘብ ከፍለው ለውሀ አገልግሎቱ ብቻ የሚውል ሕዝብ ከሚጠቀምበት መስመር የተለየ የመብራት ኃይል መስመር እንዲዘረጋላቸው የክልሉ መንግስት በጀት መድቧል። ለማኅበረሰቡ ጥቅም ከሚሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመሮች ጋር የማይገናኝ መስመር እንዲሰጧቸው ያቀረቡት ጥያቄ አገልግሎት መሆኑን አስታውሰው፤ የተጠየቀው አገልግሎትም በነጻ እንዲሰጣቸው እንዳልጠየቁ አመላክተዋል።

ማንኛውም ፋብሪካ የሚከፍላቸውን ዋጋ ከፍለው አገልግሎት ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ብር ከፍለው አገልግሎት ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም አጥጋቢ ምላሽ አላገኙም። ይህን ችግር የክልሉ ውሀ ቢሮ ብቻ ሳይሆን ከላይ ያሉ አመራሮች ጭምር የሚያውቁት ነው የሚሉት የቢሮ ኃላፊው፤ አሁንም ከበላይ አመራሮች ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ ነው።

‹‹በአጠቃላይ ለዚህ ችግር ዋነኛ ችግር የሆነው የድሬደዋ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ነው፤ ከቁርጠኝነት ማነስ ውጭ ምንም ምክንያት የለውም›› ሲሉ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

የሐረሪ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ምላሽ

አቶ ፈሪድ አብዱልሰላም የሐረሪ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ናቸው። እንደ አቶ ፈሪድ ገለጻ፤ በሐረር ከተማ የውሀ ችግር እንዳለ ይታወቃል። ይህን ችግር ለመፍታት በውሀ ቢሮ በኩል በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፤ እየተሰሩም ነው።

በሐረር ከተማ የተፈጠረውን የውሀ ችግር መገንዘብ እንዲቻል በመጀመሪያ ደረጃ ሐረር ውሀ የምታገኘው ከየት ነው? የሚለውን መረዳት ያስፈልጋል። የሐረር ከተማ ውሀ የምታገኘው ከሁለት ቦታዎች ነው። አንደኛው በክልሉ ውስጥ ከሚገኝ የኤረር ከሚባል ቦታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኝ የውሀ ጉድጓድ ነው። ከነዚህ ጉድጓዶች ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ከድሬዳዋ የሚመጣው ነው።

ከእነዚህ ሁለት የውሀ መገኛዎች ለሐረር ከተማ ውሀ ለማምጣት ከተለያዩ ሶስት ሰብስቴሽኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ይቀርባል። በክልሉ ከሚገኘው ኤረር እየተባለ ከሚጠራው ቦታ ላይ ለሚገኘው የውሀ ጉድጓድ ከአንድ ሰብስቴሽን ብቻ የኤሌክትሪክ የሚቀርብ ሲሆን ይህም ከሐረር ክልል የሚነሳ ስለሆነ ያለምንም መቆራረጥ ለኅብረተሰቡ ውሀ ለማቅረብ አስችሎናል።

ይህ በመስመር ያን ያህል የጎላ ችግሮች የለበትም። ከዚህ በፊት አነስተኛ ችግሮች አጋጥመው የነበረ ቢሆንም በቀላሉ መፈታት ተችሏል። በተለይ ከቮልቴጅ ጋር ተያይዞ የነበረውን ችግር በቀላሉ መቅረፍ ተችሏል። አሁን ላይ ከፍተኛ ችግር የሚስተዋልበት ድሬዳዋ ከሚገኘው የውሀ ጉድጓድ ውሀ ወደ ሐረር ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ነው።

ከድሬደዋ ውሃ ለመሳብ ከሁለት የተለያዩ ሰብስቴሽኖች የኤሌክትሪክ ኃይል እንጠቀማለን። አንደኛው ከውሀ ጉድጓዱ ውሀውን ‹‹ፓምፕ›› ለማድረግ የሚያገለግል ሲሆን ሁለተኛው ከድሬዳዋ ወደ ሐረር ውሀ ገፍቶ ለማምጣት የሚያስችል ነው።

እነዚህን ሰብስቴሽኖችን የሚመግበው የስብስቴሽን ኃይል ሐሮማያ እና አዲሌ ይገኛል። በተለይም ከድሬዳዋ ወደ ሐረር ውሀ የሚገፉትን አራት ፓምፖችን የሚመግበው ሰብስቴሽን አዲሌ ላይ ያለው ሰብስቴሽን ነው። ይህ የኃይል መስመስር ልክ እንደ ሐረሩ ለውሀ አገልግሎቱ ብቻ የሚውል (dedicated) ነው።

ከዚህ በፊት ከሌሎች መስመሮች ጋር በተያያዘ ጊዜ የሚመጣ ችግር ነበር። ይህም መስመሩ ላይ ኃይል እንዲቆራረጥ መንስኤ ይሆን ነበር። አሁን ላይ ችግሩን ለማየት ከዋናው መስሪያ ቤት ባለሙያዎች መጥተው ተስተካክሏል። ነገር ግን መስመሩ ታወር ስለሆነ አልፎ አልፎ ስርቆትና ጉዳት የሚያስተናግድ በመሆኑ የኃይል መቆራረጥ ሁኔታ ይኖራል።

በተገቢው መንገድ መታየት ያለበት፤ ችግር የሚስተዋልበት ለድሬዳዋው የውሀ ጉድጓድ ኃይል የሚመግበው መስመር ነው። መስመሩ እንደሌሎቹ መስመሮች ለውሀ አገልግሎቶች ብቻ የሚውል እና ከሕዝብ አገልግሎት የተነጠለ አይደለም። መስመሩ ከኅብረተሰቡ ጋር በጋራ አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ስለዚህ ይህን መፍትሔ ለመስጠት የተወሰደው አማራጭ መስመሩን ለሁለት መክፈል የሚል ነው።

ከዚህ በፊት የተጠቀሱ ችግሮችን ለመፍታት የሐረር ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚና ባለሙያዎች፣ የድሬዳዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚና ባለሙያዎች፣ የውሀ ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ ሪጂን ኃላፊ ባሉበት ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማስቀመጥ ወደ ስራ ተገብቷል።

ስራ አስፈጻሚው እንደሚሉት፤ ድሬዳዋ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት በየዘርፉ የተከፋፈልናቸው የቤት ስራዎች ነበሩ። አንደኛው የውሀው መስመር ከኅብረተሰቡ መለየት አለበት የሚል ነው። መስመሩ ለውሀ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የገጠር ከተሞች አገልግሎት ስለሚሰጥ፤ ረጅም ኪሎ ሜትር ስለሚጓዝ የውሀው መስመር ላይ ጫና ያስከትላል። ቅድሚያ ይህ ችግር ሳይፈታ ሌሎቹ መስመሮች ቢሰሩ ትርጉም አይኖረውም።

ችግሩን ለመፍታት ግምት ወጥቶ ለሐረሪ ውሀ ቢሮ እንዲደርስና ቢሮው አስፈላጊውን ክፍያ ፈጽሞ የመስመር ዝርጋታው እንዲሰራ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነትወስዷል።

አሁን ባለኝ መረጃ የድሬደዋ ሪጂን ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመስመር ግምት አውጥቶ ለሐረሪ ክልል የውሃ ቢሮ ሰጥቶ ክፍያ እየተጠባበቀ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም መስመሩን የማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ ነው።

በአጠቃላይ ችግሩ አንድ ሳይሆን፤ ዘርፈ ብዙ መልስ የሚፈልጉ የተለያዩ ችግሮች የያዘ ችግሮቹን በአንድ ማእቀፍ አድርጎ መፈታት ይፈልጋል። ለዚህም ለሁሉም የስራ እቅድ ተከፋፍሏል። የሐረሪ ክልል፣ የድሬዳዋ ሪጅን የኤሌክትሪክ አገልግሎት፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ውሀ ቢሮ የሚወስዷቸው ስራዎች አሉ።

ችግሩ እስከመቼ ይፈታል? ተብሎ ለተነሳቸው ጥያቄ አቶ ፈሪድ በምላሻቸው፤ የተወሰኑት ችግሮች ተፈተዋል። አሁን ላይ በዋናነት የቀረው የድሬዳዋውን መስመር መስራት ነው። ለዚህም ክፍያውን የሚሸፍነው የክልሉ ውሀ ቢሮ ነው። ባለኝ መረጃ ግምት ቀርቦላቸዋል። ክፍያው እንደተከፈለ መስመሩን በመዘርጋት ችግሩ ይፈታል።

የመስመሩ ግመታ መቼ ነው የተከናወነው? ተብሎ ጥያቄ የተነሳላቸው ኃላፊው ግመታውን የሰራው ድሬዳዋ ሪጂን በመሆኑ የግመታ ቀኑን በእርግጠኝነት እንደማያስታውሱት፤ ነግር ግን ግመታ እንደተሰራለት እንደሚያውቁ አስታውቀዋል።

የድሬዳዋ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ምላሽ

የአዲስ ዘመን የምርመራና የመልካም አስተዳደር ቡድን ከሐረሪ ክልል ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን የቀረበለትን አቤቱታ መሰረት በማድረግ የሐረር የውሀ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ነው የሚል ቅሬታን በመያዝ የድሬዳዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ፍቅረማርያም አለማየሁ አነጋግሯል። ለሐረሪ ክልል የውሀ መቆራረጥ መንስኤ ምንድነው ብለው ያምናሉ? ስንልም ጥያቄ አንስተንላቸዋል።

ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ ከሐረር ውሀ ጋር ያለው ችግር ብዙ ነው። ሁሉንም ችግሩን በየዘርፉ ከፋፍሎ ማየት ያስፈልጋል። የራሳቸውም ችግር ይኖራል (የሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን)፤ ከውጭ የመጣ (External) ችግርም ይኖራል። በኤሌክትሪክ አገልግሎቱም በኩልም ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ።

መስመሩም ድንበር ተሻጋሪ መስመር ነው። የተለያዩ ቦታዎችን ነክቶ ነው እነሱ ጋር የሚደርሰው። አብዛኛውን ከዚህ በፊት በታወር የተሳበ መስመር ነው። የተወሰነው አካባቢ ደግሞ በእንጨት ምሶሶ የተተከለ ነው። የነበረውም ስኒ ተሰባሪ ስኒ ነበር። በዚህም ብዙ ግዜም ኃይል ይቆራረጥ ነበር። ይህን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል (EEP) ለረጅም ግዜ ጥገና ላይ ነበር።

ሌላው ችግር ደግሞ መስመሩ በሌቦች በተደጋጋሚ መዘረፍ አጋጥሞታል። የተዘረፈውን ደግሞ በጥገና ማስተካከል ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው መስመሩ የሚያልፈው አስቸጋሪ በሆኑ ተራራማ ቦታ ላይ ነው። በመሆኑም ወደ ቦታው ተሽከርካሪ መግባት አይችልም። ለጥገና በምንቀሳቀስበት ወቅት የጥገና እቃዎችን በሰው ጉልበት ለመውሰድ እንገደዳለን። ይህ ደግሞ በጣም አድካሚ እና ከፍተኛ ጊዜን የሚወስድ ነው። አንዳንድ ጊዜ የጥገና ስራዎችን ለመጨረስ ከሳምንት እስከ 10 ቀናት ሊወስድ ይችላል።

እንደዚህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ ከክልሉ መንግስት ጋር እንነጋራለን። በነገራችን ላይ ከሌቦች ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ችግር እነሱም ያውቃሉ። እረኞችም ሲኒ ሲሰብሩ የተወሰነ ግዜ ቴክኒካል ችግሩን ማግኘት ያስቸግራል። እነዚህን ችግሮች ለመለየት ከውሃ ቢሮ ኃላፊዎች እና ሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መፍትሔ ለማምጣት የተለያዩ ስራዎችን እንሰራለን።

ለችግሩ በዘላቂነት መፍትሄ የሚሆነው ለውሀ አገልግሎቱ ለብቻው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ለመዘርጋት የሚያስችሉ አማራጭ መንገድ ማሰብ ያስፈልጋል። በጊዜያዊ መፍትሔነት ደግሞ በራሳችን ወስደን የሚሰባበሩ ስኒዮችን በማይሰባበሩ ስኒዎች ቀይረናል። በተደጋጋሚ የሚወድቁትን ውስን የእንጨት ፖሎችንም ወደ ኮንክሪት ፖል ቀይረናቸዋል።

መስመሩ ድንበር ተሻጋሪ ነው። በመሆኑም የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት የሚቀንሱትን የተለያየ ፕሮቴክሽን ማቴሪያሎችን አሟልተናል። አሁን ባለው ሁኔታ በሲስተም ላይ ማየት እንደሚቻለው በርካታ ችግሮችን መቅረፍ ችለናል።

ዘላቂ መፍትሔውን ለመተግበር ግን ለክልል ውሀ ቢሮ ከአንድም ሁለት ጊዜ ደብዳቤ ጽፈናል። የዋጋ ግመታውን እንዲከፍሉ ጠይቀን አልከፈሉም። ለማስታወስም ሁለተኛ ደብዳቤ ጽፈን ነበር። እኛ ለሐረር ውሀ ልዩ ትኩረት ነው የምናደርገው። ምክንያቱም ተጠቃሚውም ብዙ ነው። ሐረር ብቻ አይደለም የሚጠቀመው፤ መሀል የሚገኙ ኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተጠቃሚ ናቸው።

የድሬደዋ ሪጅን በምልከታው እንደተገነዘበው አንዳንድ ጊዜ በሐረር የቧንቧ መስመሮች ይሰበራሉ:: በዚህም ሳቢያ ከ15 ቀን በላይ ውሀ እንዳላገኙ እናውቃለን። ይሄም በመብራት ምክንያት ሊባል ይችላል። 15 ቀን ሙሉ አልተሰራም። እነዚህን እና ሌሎችንም ምክንያቶች የሐረር ሕዝብ ውሀ እንደሚቸግር እናውቃለን።

ከዚህ ውስጥ የመብራት ችግር አንዱ ቢሆንም አሁን ግን ከዚህ በፊት እንደሚቆራረጠው አይቆራረጥም። በአዲሌ መስመር ላይ ‹‹የሴቲንግ›› ችግር ነበር። እሱንም በማጥናት ችግሩ ተፈቷል። ይሄንን ስል ሙሉ በሙሉ አይቆራረጥም እያልኩ አይደለም። ከሌላ አካባቢ ግን የተሻለ ነው።

ምሶሶዎችን ወደ ኮንክሪት ስንቀይር መቆራረጦች ነበሩ። አንዳንድ ስራዎችንም ለመጠገን ሲባል መቆራረጦች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እኛ ከውሀ ቢሮ ጋር ተቀራርቦ በመስራት ችግሮችን እየፈታን ነው። እንደመንግስት ተቋማት ችግሩን በመነጋገር መፍታትን ነው የምናስቀድመው።

የድሬዳዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠት ካለበት አገልግሎት ባለፈ ቴክኒካል ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚናገሩት ቢሮ ኃላፊው፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ ወጭ ማድረጋቸውን አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ስራዎች ሲኖሩ የሚኖረውን መቆራረጥ ለመቀነስ በጋራ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል አሰራር ለመፍጠር እየተሰራ ነው። በተቀናጀ ሁኔታ ፕሮግራም አድርገው ለመስራት ጥረት እያደረጉ ነው።

በሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የተጠየቀው ክፍያ ከተፈጸመ በናንተ በኩል መስመሩን ለመዘርጋት ፍቃደኞች ናችሁ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ፍቅረማርያም ፤‹‹የግመታ ክፍያውን ከፈጸሙ በእኛ በኩል የውሀ አገልግሎት መስመሩን ከሕዝብ መስመር ለይተን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን›› ሲሉ መልሰዋል። የመንግስት መስሪያ ቤት ሆኖ መገፋፋት ጥሩ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

በድሬዳዋ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል ግዜያዊ መፍትሔ ነው የሚሉትን ሁሉ አሟጠው መጠቀማቸውን ጠቁመው፤ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ግን የውሀ ቢሮ የተገመተውን ክፍያ መክፈል እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች

ሰነድ አንድ፡- የሐረሪ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ችግሩ እንዲቀረፍ በ2015 ዓ.ም በቀን 23/07/2016 በቁጥርሐ/ው/ፍ/01/36/33/284 ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ግመታ እንዲሰራላቸው የጠየቁበት ደብዳቤ ነው።

ሰነድ ሁለት፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቀን 08/10/16 ዓ.ም በቁጥር ድ66/17/130/016 በድጋሚ የዋጋ ግምትን ስለማሳወቅ በሚል ለሐረሪ ክልል ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ደብዳቤ ጽፏል። ይህም የሐረሪ ክልል ያገጠመውን ችግር ለመቅረፍ አንድ ርምጃ መሄዱን የሚያመላክት ሰነድ ነው።

ሰነድ ሶስት፡- የሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በቀን 18/01/2015 ዓ.ም በቁጥርሐ/ው/ፍ/01/36/ 25634 የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ጥናት ሪፖርት ይመለክታል በሚል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትለድሬዳዋ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥናት መደረጉን የሚያሳይ ሪፖርት ጽፈዋል።

የምርመራ ቡድኑ ትዝብት

የሐረሪ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን የሐረሪን ሕዝብ የውሃ ችግር ለመቅረፍ በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ እንደሚገኝ፤ ነገር ግን ከኤሌክትሪክ መቆራጥ ጋር ተያይዞ ችግር እንደገጠወመው ተመልከተናል።

ክልሉ የገጠመውን ችግር በፍጥነት ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ያሳዩት ቅንነት እና ተነሳሽነት ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሊማሩበት እና ሊወስዱት የሚገባ ተግባር ነው። ዋና ዳይሬክተሩ ችግሩ እንዲፈታ ያደረጉት ቅንነት የተሞላበትን ጥረት የምርመራ ቡድኑም ያደንቃል።

በመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You