
አንዳንዴ ቸገር እሚሉ ጉዳዮች ማጋጠማቸው አይቀሬ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ቸገር ከማለታቸውም በላይ ወሰብሰብ ማለታቸው የበለጠ አነጋጋሪ ያደርጋቸዋል። በተለይ ጉዳዩ ከሀገርና ሕዝብ ጋር ሲያያዝ ቋጠሮው እየጠበቀ፣ ውሉ እየጠፋ፣ መፍቻ ዘዴው ግራ እያጋባ ይሄድና ያልታሰበን፣ ምናልባትም ያልተጠበቀን ዋጋ ሲያስከፍል ሁሉ ይታያል። እያጋጠመን ያለውም ይሄው ነውና በእዚሁ ላይ ትንሽ ሃሳብ መለዋወጥ፤ “አሰባሳቢ” እና “ነጠላ” ትርክቶችን ለያይቶ ማየት፤ ጉዳትና ጥቅማቸውን መፈተሽ ያስፈልጋል።
በአንድ ሀገር የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ጉዳዮች የመወያያ ርእሰ ጉዳይ ሆነው ብቅ ማለታቸው የተለመደ ነው። በአሁኑ ሰዓትም ከ“ነጠላ ትርክት” ይልቅ “አሰባሳቢ ትርክት” የሚለው ተመራጭ ሆኖ በርዕሰ ጉዳይነት ብቅ ብሎ እያነጋገረ ይገኛል።
እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊም ሆነ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ሰዎች አተያይ ብሔራዊ ትርክት ስንል ኢትዮጵያ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ማለታችን ነው። ጥቃቅን ልዩነቶችን ትተን የጋራ በሆኑ ነገሮች ላይ ስንሰባሰብ የሚመጣ ጥላ ነው። ኢትዮጵያ የውጭ ወራሪዎችን ከመመከት አንጻር በምሥራቅ አፍሪካ ስትጫወት የነበረው ሚና ቀላል አይደለም።
በቀጥታና በጎረቤቶቿ አማካኝነት በውክልና የሚመጡባትን ሃይማኖታዊ እና ጎሳዊ ግጭቶችን የመፍጠር ሙከራዎችን ሁሉ ተቋቁማ የኖረች ታላቅ ሀገር ናት። ይሄ በራሱ ትልቅ ትርክት ነው። ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ነበረች፤ አሁንም ታላቅ ናት። ወደ ፊትም እጅግ ታላቅ ሀገር እናደርጋታለን የሚለው አመለካከት በራሱ የጋራ ትርክታችን ነው።
“አሰባሳቢ ትርክት”ን በሌላ ስሙ “ብሔራዊ ትርክት” በማለት የሚጠሩት ሰዎች አተያይ፣ ለምሳሌ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪው ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር አድርገውት በነበረ ቆይታ እንደ በየኑት ከሆነ ብሔራዊ ትርክት የአንድ ሀገር ሕዝብ በጋራ የሚኖረው እሴት፣ ግንዛቤ እና አስተሳሰብ ነው።
እንደ ዳንኤል ክብረት ብያኔ “ትርክት ሆን ተብሎም ይሁን በተለምዶ በዓላማ የሚዘጋጅ ንግርት” ሲሆን፤ “ብዙ ጊዜ ታሪክን፣ እምነትን፣ ባህልን እና አመለካከትን የሚይዝ ሲሆን፤ የሚነገርበት ምክንያትም አለው። የሚዘጋጀውም ለእዚያ ምክንያት ሲባል ነው። የሚካተቱት ከተዘጋጀበት ዓላማ ጋር የሚሄዱ ሃሳቦችና ታሪኮች ናቸው።
የትርክቶች በጎነትና እኩይነት በትርክት ቀራፂዎቹ እጅና ፍቃድ ወይም ቁጥጥር ስር ሊወድቅ” ይችላል። “ትርክቶች በበጎ ዓላማ ከተዘጋጁ በአንድ ሀገር ሕዝቦች መካከል መግባባትና አንድነት እንደሚፈጥሩ ሁሉ፣ በዕኩይ ዓላማ ከተዘጋጁ ደግሞ መቃቃር በመፍጠር የግጭት አዙሪት ውስጥ ያስገባሉ።” (የትርክት ዕዳና በረከት)
በዶ/ር ሙሉጌታ ምሁራዊ ግምገማ እያንዳንዱ ሥርዓት የራሱ ትርክት ያለው ሲሆን፤ የኢህአዴግ እና የደርግ ሥርዓቶችም የየራሳቸው ትርክቶች ነበሯቸው። በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ የነበረው ትርክት አሁን ላለንበት ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ደንቃራ ሆኗል።
ይህ የዶክተሩ አስተያየት በአሁኑ፣ ስለ አሰባሳቢ ትርክት አስፈላጊነት እየተሰበከ ባለበት ሰዓት በበርካታ መድረክ መሪዎችና አስተያየት ሰጪዎች እየተደገፈ ያለ ሲሆን፣ እንደ እነዚሁ ሰዎች አስተያየት ለውጥ መጣ እስከተባለበትና ኢህአዴግ በብልፅግና እስከተተካበት ዓመት ድረስ የነበሩ ነጣጣይና ጫፍ የረገጡ ትርክቶች በኢትዮጵያዊነት፣ አንድነትና አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ጥላቸውን አጥልተው፤ በጎሪጥ እንድንተያይ አድርገውን ነው ያለፉት። በመሆኑም ከእነዚህ አይነት ችግሮች ውስጥ በአስቸኳይ መንጭቀን መውጣት ይገባናል ባይ ናቸው።
የተለያዩ ሀገራት ልምድ እንደሚያመለክተው፤ አሰባሳቢም እንበለው ብሔራዊ ተረክ በግለሰቦች ወይም በአንድ በተወሰነ ቡድን ብቻ የሚቀነቀን ሳይሆን በጠንካራ ተቋማት ጭምር ተደግፎ የሚሠራበት ትልቅ ሀገራዊና ሕዝባዊ ተግባር ነው።
ምንም እንኳን በአግባቡ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ወደ ተግባር ገብቶ ውጤቱን ባናይም “ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን” የሚባለው ተቋም አሰባሳቢ ወይም ብሔራዊ ተረክን ለማቀንቀንና ለማስተጋባት፤ እንዲሁም በዜጎች አእምሮ ውስጥ ብሔራዊ ማንነትን ለማስረፅ ሁነኛ ተቋም ነው የሚሉ አሉ። ይህ እንግዲህ ወደ ፊት የምናየው ይሆናል። ወደ ገዥው ፓርቲ አተያይና አቋም እንምጣ።
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ኦፊሴላዊ ፌስቡክ ገፅ ላይ “ነጠላ ትርክቶችን በማረቅ አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ለሀገረ-መንግሥት ግንባታችን ታሪካዊ አሻራችንን እናሳርፍ!” በሚል ርዕስ ለንባብ እንደ በቃው ጽሑፍ ማብራሪያ ትርክት ምንዳም ዕዳም የሚሆነው እንደ አጠቃቀማችን ነው፡፡
በርካታ ሀገራት ትርክታቸውን ለመጪው ትውልድ አብሮነቱን በሚያጠናክር መልኩ በመግራታቸው ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታቸው የጎላ አበርክቶ አድርጎላቸዋል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የወል ያልሆኑ የማያሰባስቡ ነጠላ ትርክቶች ላይ ብቻ የተረባረቡ ሀገራት በረባ ባልረባው የሚያነታርክ ቁርሾ ለትውልድ አሸጋግረዋል፡፡
እንደ ፓርቲው የጽሑፍ ማብራሪያ ከሆነ “ከኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ምሥረታና ግንባታ ሂደት ሀገራችንን እየተፈታተኗት የነበሩና ያሉ ትርክቶች በሁለት ጽንፍ የሚገለጹ ሲሆኑ፤ እነሱም ፍፁማዊ አንድነትን ይዞ ብዝኃነትን ለመደፍጠጥ የሚደረግ የጠቅላይነት አስተሳሰብ እና የተጋመደውን የሕዝብ ማንነት ወደ ጎን በማለት አንድነትን ክዶ የኔ የሚሉትን ሕዝብ ከሌላው ወንድም ሕዝብ የመነጠል አባዜ ናቸው፡፡”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደሚሉት፤ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህ ዓይነቱ ችግር እንዳይከሰት “አሰባሳቢ ተረክን መፍጠር፣ መገንባት ያስፈልጋል።” በተለያዩ ጊዜያት አስተያየት ሰጪዎች ”ፅንፍና ፅንፍ የቆሙ ነጠላ ትርክቶች በምክንያታዊነት አስተሳሰብ ተገርተው ወደ መሀል እስካልመጡ ድረስ መሳሳቦች፣ መጠላለፎች እና መነታረኮች በተደመረ አቅም ሀገርንና የሕዝብን ሕይወት ለመለወጥ የሚደረግን ጥረት ከመጎተትና ከማባከን የተሻገረ እርባና ሊኖራቸው አይችልም፡፡
“እንደ ተባለው ብቻ ሳይሆን፤ ከላይ እንደ ተመለከትነው ገዥው ፓርቲም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከነጠላ ትርክት ይልቅ ምርጫቸው ያደረጉት አሰባሳቢ ወይም ብሔራዊ ትርክትን ነው። የእነዚህ ሁለት ወሳኝ አካላት ምርጫ “አሰባሳቢ ተረክን መፍጠር፤ መገንባት” የማስፈለጉ ጉዳይ ከሆነ የማይሳካበት ምንም አይነት ምክንያት የለምና ምርጫቸው ምርጫችን የሆን ሁሉ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም