ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦታዋ ማራቶን ለድል ይጠበቃሉ

የኦታዋ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ነገ በካናዳ መዲና ሲካሄድ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ይሳተፋሉ። የአሸናፊነት ግምቱ የተሰጠውም ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነው።

ለ51ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኦታዋ ማራቶን ነገ ከሰዓት 8:00 ላይ ሲጀመር አስራ አንድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ተፎካካሪ ናቸው። የውድድሩ አዘጋጆች ከሦስት ቀን በፊት ባወጡት የተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር መሠረት እንደ የግል ምርጥ ሰዓታቸው በቅደም ተከተል የአሸናፊነቱ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

በእዚህም በ2022 ዙሪክ ማራቶን ደ ባርሴሎና ስታሸንፍ 2፡23፡11 ያስመዘገበችው አትሌት መሠረት ገብሬ ኦታዋ ላይ ፈጣን ሰዓት ያላት ቀዳሚዋ አትሌት በመሆን የአሸናፊነት ግምቱን ወስዳለች። ቦንቱ በቀለ ፈጣን ሰዓት ያላት ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ነች። 2፡23፡39 በዙሪክ ማራቶን ደ ሴቪያ 2020 ላይ ያስመዘገበችው የራሷ ምርጥ ሰዓት ነው።

በ2023 ሂውስተን ማራቶን 2፡25፡35 መሮጥ የቻለችው ሙልዬ ደቀቦ፣ በሮም 2025 ማራቶን 2፡28፡22 ያስመዘገበችው ሳሌም ፈንቴና ሊዝበን ማራቶን 2023 ላይ 2፡29፡20 ሰዓት የሮጠችው ፋንቱ ሹጊ ነገ ኦታዋ ላይ የሚፎካከሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

በወንዶች መካከል በሚካሄደው ፉክክር የ2021 የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ ኬንያዊው አትሌት አልበርት ኮሪር ዳግም ወደ ኦታዋ ማራቶን መመለሱ ታውቋል። 2019 ላይ ይህን የኦታዋ ማራቶን ያሸነፈው ኮሪር በ2023 የኒውዮርክ ማራቶን የኦሊምፒክ ባለድሉን ታምራት ቶላ ተከትሎ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ያስመዘገው 2:06:57 ሰዓት የግሉ ፈጣን ሰዓት ሲሆን፤ ይህም በነገው የኦታዋ ማራቶን ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል። በርቀቱ የግል ፈጣን ሰዓታቸው መሠረት በአንድ ማይክሮ ሰከንድ የዘገየ ፈጣን ሰዓት ያለው ኢትዮጵያዊው አትሌት በላይ ጥላሁንም ከኬንያዊው እኩል የአሸናፊነት ግምት አግኝቷል። በላይ በእዚሁ የፈረንጆች ዓመት 2025 ዙሪክ ማራቶን ደ ሴቪያ ያስመዘገበው 2፡06፡58 የግል ፈጣን ሰዓቱ ነው።

ሁለቱ ተቀራራቢ ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች እርስ በርስ ከሚያደርጉት ፉክክር በተጨማሪ ከሌሎች ብርቱ ተፎካካሪዎች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ የውድድሩ ክብረወሰን እንዲሰበር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። የኦታዋ ማራቶን ክብረወሰን 2022 ላይ በኢትዮጵያዊው አትሌት አንዷለም ሽፈራው የተመዘገበ ሲሆን፤ ሰዓቱም 2:06:04 ነው።

በ2022 ዙሪክ ማራቶን ደ ሴቪያ 2፡07፡15 ያስመዘገበው አብዲ አሊ ገልቹ ሌላኛው ጠንካራ ተፎካካሪ ኢትዮጵያዊ አትሌት ነው። ደረጄ አዱኛ – 2፡08፡54 ዙሪክ ማራቶን ደ ሴቪያ 2025፣ አዳሙ ጌታሁን – 2፡11፡24 ቴል አቪቭ ማራቶን 2023፣ ደመቀ ተስፋዬ – 2፡11፡48 ቲ.ሲ.ኤስ አምስተርዳም ማራቶን 2024፣ ፀጋዬ በቀለ – 2፡12፡57 ቪዬና ሲቲ ማራቶን 2011 በመሮጥ ያስመዘገቡት ሰዓት በነገው የኦታዋ ማራቶን ከጠንካራ ተፎካካሪዎች መካከል እንዲጠቀሱ አድርጓል።

የአምናውን የኦታዋ ማራቶን ኢትዮጵያውያን በሁለቱም ፆታ ቀዳሚ ሆነው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። ሌንጮ ተስፋዬ 2:12:41 በሆነ ሰዓት የወንዶቹን ውድድር ሲያሸንፍ፣ በሴቶች ማረጓ ኃየሎም በ2:32:20 ቀዳሚ ሆና ማጠናቀቋ አይዘነጋም። በዘንድሮው ውድድር ግን ሁለቱም የአምና ባለድሎች አይሳተፉም።

በእዚህ ውድድር ላይ ከኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች በተጨማሪ የካናዳና አሜሪካ አትሌቶችም ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You