ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትና የሥራ ዕድል ፈጠራ

የዓለም ሥራ ድርጅት (ILO) የሌበር ቤዝድ ፕራክቲሽነርስ አህጉራዊ ኮንፍረንስን ማካሄድ የጀመረው እ.ኤ.አ በ1990 በታንዛኒያ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኮንፍረንሱ በየሁለት ዓመቱ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ በተለያዩ ሀገራት ሲዘጋጅም ቆይቷል። የዘንድሮ 20ኛው ኮንፍረንስ ደግሞ ሰሞኑን በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ተካሂዷል።

ኮንፍረንሱ አህጉራዊ ኮንፈረንስ ሲሆን፣ በዋናነት በዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) እና ኮንፍረንሱን እንዲያዘጋጅ በተመረጠው ሀገር በቅንጅት ይዘጋጃል። ኢትዮጵያ 17ኛውን ኮንፍረንስም እ.ኤ.አ በ2017 አዘጋጅታለች።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የ‹‹ሌበር ቤዝድ ፕራክቲሽነርስ ኮንፈረንስ›› በዋናነት የሚያተኩረው ሀገራት በሚተገብሯቸው የተለያዩ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ፕሮግራሞች (ፕሮጀክቶች) የሰው ኃይልን በስፋት መጠቀም፣ ዘላቂና ጥራት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በሂደቱ የሠራተኞችን ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ደህንነት ማረጋገጥ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ማመላከት ነው።

የዘንድሮም ኮንፍረንስ ‹‹የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራሞች›› በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል። መሪ ሃሳቡ የዘላቂ ልማትን አስፈላጊነት የሚያንጸባርቅ እንዲሁም ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ፕሮግራሞች ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ብቻ ሳይሆን የአካባቢ ጥበቃን፣ የማህበረሰብ ደህንነትን፣ አካታችነትን እና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጡ የሚገባ መሆኑን አጉልቶ ያመላክታል።

ኮንፍረንሱ፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ የዓለም የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ ሰላምና ጸጥታ፣ የሀገራት የንግድ ፖሊሲዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ በሠራተኞች ደህንነት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚያሳድሩትን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽእኖዎች በመፈተሽ ስኬቶችን ይበልጥ ለማዳበር እና ለችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ ለማፍለቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

ይህም የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ ድህነት ቅነሳንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሃሳቦችን በማፍለቅ የጋራ አንድነት እና ቁርጠኝነት ለማምጣት ያስችላልም ተብሏል።

ኮንፍረንሱ የከተማና መሠረተ ልማት ሚንስቴር እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከዓለም ሥራ ድርጅት(ILO)ጋር በመተባበር ካዘጋጁት ከዚህ ኮንፈረንስ ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በሚገባ ማሳየትና ማስተዋወቅንም ያለመ ዓውደ ርዕይ ተካሂዷል።

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ መድረክ የኢትዮጵያን የልማት ሥራዎችና የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማስጎብኘትን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምክክር ሲደረግበት ቆይቶ ትናንት ተጠናቅቋል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገሮች ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የልማት ፕሮግራሞች ለሁሉን አቀፍ የልማት ዕቅዶች ትኩረት የሰጡ ናቸው። መንግሥት ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና ማህበራዊ አለመመጣጠን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የልማት መርሀግብሮችን እየተገበረ ይገኛል። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ማሻሻል አስችሏል።

የሀገሪቱ የልማት ግቦች ለሥራ ፈጠራ ትኩረት እንደሚሰጡ ጠቅሰው፤ ድህነትን መቀነስ፣ የሥራ ዕድል መፍጠርና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን አመላክተዋል።

እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያሉ መርሀግብርን በመተግበር እና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ ከባቢ መፍጠር እየተቻለ ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፤ ይህም ሁሉን አቀፍ እና የሥራ ተደራሽነትን ማረጋገጥን ያጠቃለለ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም ውጤቶች እየተገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ሁሉ የመንግሥት እና የሕዝቡን ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አስታውቀዋል።

አሁንም ቀጣይነት ያለው እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣትና የሥራ እድል የበለጠ ለመፍጠር መሥራት እንደሚያስፈልግ አመላክተው፤ የሥራ ፈጠራንና የአካባቢ ደህንነትን ያጣጣመ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በማስመዝገብ የአፍሪካውያንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ ያሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመፍታት ስልቶችን በመለየት እና በመሟገት የጋራ ርምጃ ለመውሰድ የሁሉንም ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ኮንፈረንሱ የዘርፉን ተግዳሮቶች በመፍታት የተሻለ መንገድ ለመቅረጽ እንዲሁም ለማፍለቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚመክር ጠቁመው፤ አፍሪካን ከድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ከሥራ አጥነት የጸዳች ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ትብብርና የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚንስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት የፈጠራ ፖሊሲዎችን ማበረታታት፣ ሰፊ የሥራ ዕድልን መፍጠር እና አካባቢን መጠበቅ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያም ለአካባቢ ጥበቃ፣ ምቹ ለሆነ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ቅድሚያ ሰጥታ እየሠራች ነው። በኮንስትራክሽንና መሠረተ ልማት በኩልም ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው።

መንግሥት በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ እና ጠንካራ ማህበረሰቦችን ለመገንባት ቁርጠኛ ነው ያሉት ሚንስትሯ፤ ለሥነ-ምህዳር ተስማሚ ለሆነ ዘላቂ ልማት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ።

በቅርብ ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዚህ ዋና ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል። በመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮግራም፣ በገጠር መንገድ ትስስር ፕሮግራም፣ በቤቶች ልማት ፕሮግራም እና የኮሪዶር ልማት መርሃ ግብር በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ማህበራዊ ትብብርን እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን በማጎልበት ሁሉም ዜጋ በሀገሪቱ ዕድገት ውስጥ የራሱ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ እየተቻለ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ሚንስትሯ እንዳሉት፤ በተለይ በመሠረተ ልማት በ65 የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪዶር ልማት እየተካሄደ ነው። ይህም የሥራ ዕድል የፈጠራና የሥራ ባህልን ያሻሻለ ነው። በከተሞች እየተካሄደ ያለው የኮሪዶር ልማት ከተሞችን ከማስዋብ ባሻገር ፋይዳ አለው። ዜጎች በነፃነት በአካባቢያቸው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ትውልድ እንዲቀረፅ እያደረገ ነው። የቆሻሻ መጣያ የነበሩ ስፍራዎች ገፅታቸው ተቀይሮ የመዝናኛ ማዕከል እንዲሆኑ ተደርገውበታል።

ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን በተለይም በመሠረተ ልማት ዘርፍ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት የሚያሻሽል ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮግራሞችን በማካሄድ ፈር ቀዳጀ መሆኑን አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ዓለም በውስብስብ ፈተናዎች ላይ በመሆኗ በአሁኑ ወቅት ለሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታ እንደሌለም አመላክተዋል። ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ልዩነት፣ ጂኦ ፖለቲካዊ ግጭት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህም ፈተናዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገሮች ለሚስተዋሉ የሥራ አጥነት ችግሮችና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ሆነዋል። ለዚህም ፈጠራና ተግባራዊ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በቅርበት እንደምትሠራ ጠቅሰው፤ መንግሥት ለሥራ ፈጠራ፣ ለዘላቂ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራና የሥራ ስምሪት ለአካታችና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ማህበራዊ ፍትህ መሠረት መሆናቸውን ይገነዘባል ያሉት ሚንስትሯ፤ ኮንፈረንሱም ኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ከምትገኝባቸው የኮሪዶር ልማትና የሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ስኬቶች ተሳታፊዎች ልምድ የሚቀስሙበት እንዲሆን መደረጉን አመላክተዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ የሚስተዋሉትን ሥራ አጥነት፣ ድህነት እና የእኩልነት መጓደል ችግሮችን ለመፍታት አዳዲስ ፖሊሲዎች፣ ስልቶች እና ፕሮግራሞች እንዲዘጋጁ ዕድል እንደሚፈጥር ያመላክታሉ። የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ሥራ አጥነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዜጎች መፈናቀልና የዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን መጋፈጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ለአካባቢ ጥበቃ እና ሚዛን ቅድሚያ የሚሰጡ ዘላቂ አሠራሮችን መከተል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ከኮንፈረንሱ ጎን ለጎን በተካሄደ ውይይት ላይ የፕላንና ልማት ሚንስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ኢንሼቲቮች የኢኮኖሚ ዕድገትን ከማሳለጥ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ናቸው።

በኢትዮጵያ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት በመዘርጋትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ጉልህ ሚና በማጤን መንግሥት ዘርፉን በማበረታታት ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን አመላክተዋል።

ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ በአመዛኙ በግብርና ላይ የተመሠረተ የሥራ እድል ፈጠራ እንደነበር ሚንስትሯ አስታውሰው፤ የብዝሃ ኢኮኖሚ አሠራርን በመከተል ከግብርና ባሻገር በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚ የሥራ እድል ፈጠራውን የሚያሳልጡ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይን ቁልፍ አጀንዳ አድርጋለች ያሉት ሚንስትሯ፣ ይህም በሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴው ላይ አበረታች ውጤቶች እንዲገኙ እያደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል። የኮሪዶር ልማትን ጨምሮ በግንባታው መስክ የተገኘው ውጤት በዚህ በኩል ተጠቃሽ መሆኑን ይገልጻሉ። በሀገሪቱ ወደ ሥራ የገቡት ቀድሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚባሉት የአሁኖቹ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩበትን ሁኔታም ጠቅሰው አስረድተዋል።

የሥራና ክህሎት ሚንስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በሴፍቲኔት መርሃ ግብር በገጠርና በከተማ የሥራ እድል ፈጠራ ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው። ክህሎት መር ፖሊሲ አሠራርን በመተግበርም የተቋማት ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የሠለጠነ የሰው ኃይል ወደ ሥራ እንዲገባ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ፍሬያማ መሆናቸውም አስታውቀዋል።

በተለይም በዲጂታል መስክ ስታርታፖችን በመደገፍ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ በተዘረጋው የማበረታቻ ሥርዓት በርካታ ስታርታፖች ምህዳሩን እየተቀላቀሉ ነው ያሉት ሚንስትር ዴኤታው፣ በክህሎት ልማት ዘርፍ ቀጣናዊ ትብብሮችን በማጠናከር ለጋራ ብልፅግና ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉም ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት እና የተመድ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተወካይ ኩምቡላ ንዳባ፤ ሀገራት የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ በማተኮር የሥራ ዕድል ፈጠራን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አፍሪካ ከፍተኛ የወጣቶች ሥራ አጥነት ተግዳሮት እንዳለባት ተናግረው፤ ይህን ተግዳሮት የመፍታቱ ሥራ የሥራ ዕድል ማሳደግንና ኢኮኖሚያዊ አማራጮችን መመልከትን ይጠይቃል ሲሉ ተናግረዋል።

የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማሳደግ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በማተኮር በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል ያሉት ኩምቡላ ንዳባ፤ በአሠሪዎችም ሆነ በሠራተኞች መካከል መልካም ግንኙነት መፍጠር እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ጤናማ የሥራ ካባቢን ለመፍጠር ዘላቂነት ያላቸው አካሄዶችን መከተል ይገባል። የጉባዔው ተሳታፊዎች ችግሩን ለመፍታት የመፍትሔ ሃሳቦችን ማፍለቅ ይኖርባቸዋል። ኮንፈረንሱ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንድታሳይ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You