የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን በሚገኘው የቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች ዩኒየን እና በኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ መካከል የተፈጠረ ውዝግብ ያስመለክተናል::
የቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ለበርካታ ዓመታት ከአርሶ አደሩ ቡና እና ቅመማ ቅመሞችን በመሰብሰብ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ሲያርብ ቆይቷል:: በነበረውም ቆይታ አርሶ አደሮችን እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በማገናኘት የድልድይነት ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል:: ከሽያጭ የሚያገኘውን ገንዘብ ምንም አይነት የግብር ክፍያ ሳይቆርጥ ለአርሶ አደሮች ሲያከፋፍልም ነበር:: ነገር ግን የጅማ የገቢዎች ቅርንጫፍ ዩኒየኑ በራሱ ገበያ አፈላልጎ እንደሸጠ በማድረግ ከህግ ውጪ ግብር እንድንከፍል ጠይቆናል::
ከመጠየቅም ባለፈ የዩኒየኑን እና የሥራ አስኪያጁን የባንክ ሂሳብ ዘግቶ ዩኒየኑ ምንም አይነት ስራ መስራት እንዳይችል ሆኗል:: በዚህም ዩኒየኑ ለከፍተኛ ኪሳራ ከመጋለጡም ባለፈ ለመፍረስ ተቃርቧል:: በገቢዎች ላይ የተጸመብንን በደል የኢትዮጵያ ህዝብ አይቶ ይፍረደን” ሲሉ የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ ጌታሁን ተክሌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን አቤት ብለዋል::
የመልካም አስተዳደር እና የምርመራ ቡድኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን መረጃዎች በሚከተለው መልኩ አጠናክሮታል::
ከአቤቱታ አቅራቢው አንደበት
እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ፤ የቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች ዩኒየን ከ2ሺ በላይ አባላትን በውስጡ የያዘ በ14 መሰረታዊ ማህበራት በ1997 ዓ.ም የተመሰረተ ነው። መነሻ ካፒታሉም ሁለት መቶ 10 ሺህ ብር ነበር:: ከአቶ ጌታሁን ተክሌ በፊት ዩኒየኑ አራት ሥራ አስኪያጆች የመሩት ሲሆን፤ አቶ ጌታሁን አምስተኛ ሥራ አስኪያጅ ናቸው:: እርሳቸው ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከመምጣታቸው በፊት ዩኒየኑ ያን ያህል ትርፋማ እንዳልነበር በማስረጃዎች አስደግፈው ይናገራሉ::
በ2003 ዓ.ም ላይ ዩኒየኑ በጣም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቆ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ጌታሁን፤ በወቅቱ መንግሥት ባደረገው ከፍተኛ ድጋፍ ከመዘጋት መዳኑን ይገልጻሉ:: በ2003 ዓ.ም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከፍተኛ የሆነ የማህበራት ንቅናቄ መደረጉን ተከትሎ በ2004 ዓ.ም የቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው መቀጠራቸውን ያስረዳሉ::
እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ፤ የይርጋ ጨፌ፣ የኦሮሚያ እና የሲዳማ ቡና አምራች ገበሬዎች የህብረት ስራ ዩኒየኖች በሀገር አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ዩኒየኖች ናቸው::የቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች ዩኒየንም በእነዚህ ዩኒየኖች ልክ በሀገር አቀፍ ደረጃ ታዋቂ መሆኑን አመላክተዋል::
እንደሀገር ከሚገኙ ትልልቅ ዩኒየኖች መካከል የኦሮሚያ ዩኒየን በቀዳሚነት እንደሚቀመጥ የሚናገሩት አቶ ጌታሁን፤ ሲዳማ በሁለተኝነት እንደሚከተል፤ የይርጋጨፌ እና ቤንች ማጂ እየተቀያየሩ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን እንደሚይዙ ይናገራሉ:: በተጨማሪም በሀገሪቱ ከሚገኙ አጠቃላይ 496 የቡና ነጋዴዎች ውስጥ 29ኛ እንደነበር ጠቁመዋል::
ከላይ የተጠቀሱት ጨምሮ በሀገራችን የሚገኙ የበርካታ የህብረት ስራ ዩኒየኖች ቦርድ ሰብሳቢ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ጌታሁን፤ በገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ አካውንቱ ተዘግቶ ከስራ እንቅስቃሴ ውጭ ከመሆኑ በፊት የቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን እንደሀገር በከፍተኛ የስራ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደነበር ያስረዳሉ::
ህብረት ስራ ዩኒየኑ ከስራ ውጪ የተደረገው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ግጭት በተፈጠረበት ወቅት ስለነበር ሁሉም አመራር ትኩረቱ በተፈጠረው ችግር ላይ ነበር:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦር ሜዳ ላይ መሄዳቸውን እየተመለከትን እኛ ስለዩንየኑ ብንጮህ ትክክል አይሆንም:: ሀገር በከፍተኛ ችግር ውስጥ እያለች ለህብረት ስራ ንግድ ተብሎ ሌላ ችግር መፍጠር ተገቢ አይደለም:: ምክንያቱም ንግድ የሚነገደው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው ፤ ንግድ በህይወት የሚኖሩ ሰዎች ለመኖር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንጂ ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት የሚደረግ አይደለም:: የሰው ልጅ የሚሰራው የተሻለ ኑሮ ለመኖር በማሰብ ነው:: የንግድ ውድድሩም በዚያው ልክ ነው:: ሀገር በጦርነት ውስጥ ሆና የመንግሥት መዋቅር ለማህበራት አይደለም መደገፍ ችግራቸውን ለማየት እና ለመስማት የሚፈለግ አልነበረም::
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2013ዓ.ም በገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ወደ ቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች ዩኒየን ቢሮ ያቀናል:: በዚህ ወቅት ዩኒየኑ ለሀገር እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቆ የቫት ተጠቃሚ ቢሆኑ ደግሞ ሀገርን የበለጠ በመጥቀም እንደሚችል ለዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ ይገልጻል:: ሥራ እስኪያጁም እንደዜጋ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ይስማማሉ::
የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ በመንግሥት ሥራ በአመራርነት አገልግለው ስለነበር የቫት ተጠቃሚ ለመሆን መጀመሪያ ኦዲት መደረግ እንዳለባቸው ይረዳሉ:: የገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ህብረት ስራ ዩኒየኑን ኦዲት ለማድረግ ጥያቄ አቀረበ:: ዩኒየኑም የገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ ጥያቄን በቅንነት ተቀብሎ ኦዲት እንዲደረግ ፈቀደ::
ነገር ግን የጅማ ቅርንጫፍ ዩኒየኑ በ2000ዓ.ም አካባቢ የቫት ደረሰኝ አሳትሞ ነበር በሚል ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ 41 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ እንዳለበት በምርመራ የኦዲት ግኝት ማግኘቱን አሳወቀ:: በግኝቱ መሰረት የተገኘውን 41 ሚሊዮን ብር ህብረት ስራ ዩኒየኑ እንዲከፍል ጠየቀ:: ሥራ አስኪያጁም እንዴት? የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ይገልጻሉ:: ይሁን እንጂ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ገንዘቡን ካልከፈላችሁ በሚል የዩኒየኑን እና ሥራ አስኪያጁን የባንክ አካውንት ዘጋ::
ይህን ተከትሎ ሥራ አስኪያጁ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የደረሰ ጥያቄ አቀረበ:: በተለይም የገንዘብ ሚኒስቴር ኦዲት የተደረገው ልክ አለመሆኑን ገልጾ፤ ቅጣቱና ወለድ እንዲነሳ ወሰነ። ይሁን እንጂ ፍሬ ግብሩን ግን የማንሳት ስልጣን የሚኒስቴሮች ምክር ቤት መሆኑን ተነገራቸው:: በዚህ ውሳኔ ለመጠቀም ጉዳዩን በፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሶስተኛ ዙር ደብዳቤ በኢሜል መጻፋቸውን ያስረዳሉ:: በተለያዩ ቢሮዎች ባደረግናቸው ማመልከቻዎች አሁን ላይ ዩኒየኑ 18 ሚሊዮን እንዲከፍል ተወስኖበታል::
ዩኒየኑ ለውጭ ገበያ በሚያቀርበው ቡና በዓመት ከ10 ሚሊዮን በላይ ዶላር ለሀገሪቱ ያስገኝ ነበር:: አሁን ላይ ህብረት ስራ ዩኒየኑ ግብር አልከፈለም በሚል አካውንቱ በመዘጋቱ ከአርሶ አደር አልፎ ለሀገሪቱ የሚያስገኘው ዶላር ሙሉ በሙሉ ቆሟል:: ይህንንም የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ካደረገው ኦዲት ማየት ይቻላል:: በዩኒየኑ ላይ በሚደረገው ነገር እንደ ግለሰብ በጣም አዝናለሁ የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የእርሳቸው ትልቁ ሃሳብ በኮፕሬቲቭ ዘርፍ ደሃው ገበሬ አድጎ ማየትን እንደነበር ይገልጻሉ::
የገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አገኘሁት ባለው የምርመራ ኦዲት የስምንት ዓመት የቫት ግብር ክፈሉ ባላቸው ጊዜ የቤንች ማጂ የጫካ ቡና የገበሬዎች ዩኒየን ተቃውሞ አነሱ:: የተቃውሞው መነሻም ዩኒየኑ የቫት ደረሰኝ ሳያሳትም እንዴት የቫት ግብር ይሰበስባል? የሚል ነበር:: አቤቱታ አቅራቢው ቀደም ባለው ጊዜ ገቢዎች ቢሮ መስራታቸውን አውስተው፤ የገቢ ደረሰኝ የሌለው ነጋዴ ካለ የገቢ ደረሰኝ አውጥቶ እንዲሰራ እንደሚደረግ ያስረዳሉ::
በህጉ መሰረት ዩኒየኖች ገቢ መሰብሰብ የሚችሉት የህብረት ስራ ኤጄንሲ በሚያሳትመው ደረሰኝ ነው:: ይህ ስልጣን ለህብረት ስራ ኤጀንሲው የተሰጠ ነው:: በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ዩኒኖች ገቢ የሚሰበሰበው የህብረት ስራ ኤጄንሲ በሚያሳትመው ደረሰኝ ብቻ ነው:: ገቢዎች ደግሞ የህብረት ስራ ኤጀንሲ በሚያሳትመው ደረሰኝ የምትሰበስቡ ከሆነ የሀገር ገቢ ይቀራል የሚል ቅሬታ አነሳ::
ይህ እውነት ነው:: አዋጅ ላይ ቢኖርም እንደ ባለሙያ በግሌ ኮፕሬቲቭ በኤጀንሲ የተደገፈ ሆኖ እንዲኖር አልፍልግም:: የተፈለገው ቫት እና ቅድመ ግብር እንድንሰበስብ ነው:: ምክንያቱም ዩኒኖች ከግብር ነጻ ናቸው:: እሱን መሰብሰብ ነበረብን እንጂ ግብር የምንከፍል ሰዎች አልነበርንም:: ምክንያቱም እኛ የገበሬዎች “ኤጀንት” ነን:: ነገር ግን ገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት “በህገወጥ ደረሰኝ ግብር ሰብስበህ ጥቅም ላይ አውለሀል የሚል ነው::” “ይህ ትክክል አይደለም” ሲሉ ይገልጻሉ::
ዩኒየኑ እንደ ኤጀንት ከአርሶ አደሩ ቡና ሰብስቦ ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ በኢትዮጰያ ምርት ገበያ በኩል እንዲሸጥ ያደርጋል እንጂ በራሱ ገበያ አፈላልጎ ለገበያ አያቀርብም:: በመሆኑም ቡናው ከተሸጠ በኋላ ዩኒየኑ ከተሸጠው ቡና የኮሚሽኑን ብቻ ወስዶ ለአርሶ አደሮች ገንዘቡን ያከፋፍላል::
ዩኒየኑ 15 በመቶ የሚሆነውን ከአርሶ አደሮች የተሰበሰበን ቡና በሀገር ውስጥ ይሸጣል:: ነገር ግን ከዚህም ምንም ገንዘብ ተቀናሽ ሳይደረግ ለአርሶ አደሮቹ ገንብ ይከፈላል:: እኛም ያደረግነው ከቡና ሽያጭ ከሚገኘው ገንዘብ ምንም ሳንቆርጥ ለቡና አምራች አርሶ አደሮች ገንዘብ እንከፍላልን ያሉት አቶ ጌታሁን፤ ይህን ደግሞ ገቢዎችም እንደሚያውቁ አመላክተዋል::
ገንዘቡ ለአርሶ አደሮች መሰጠቱን የሚያውቀው ገቢዎች “ገንዘቡን ከአርሶ አደሮች መልሳችሁ ሰብስቡ” ሲል ለዩኒየኑ አሳወቀ:: ዩኒየኑም ለ21 ሺ አባል አርሶ አደር ያከፋፈሉትን ገንዘብ መልሶ መሰብሰብ እንደማይችል ገልጾ፤ ከዚህ በፊት ከተከናወነ ሽያጭ አሁን ላይ ከአርሶ አደሩ ግብር መጠየቅ በአካባቢው የሰላም ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አሳወቀ:: የዞኑ አስተዳዳሪም ይህን እንደሚረዱ አስገነዘበ:: ነገር ግን ሰሚ አልተገኘም:: በመሆኑም የዞኑ አስተዳዳሪም ጭምር ስለጉዳዩ ከገቢ እና ጉምሩክ እስከ ገንዘብ ሚኒስቴር ድረስ ሄደው አቤት ማለታቸውን ይናገራሉ::
የገንዘብ ሚኒስቴር ቡናው የተሸጠው በሀገር ውስጥ ገበያ ወይም በውጭ መሆኑን አረጋግጣችሁ ግብሩን ቀሪ አድርጉ ብሎ ደብዳቤ ለገቢዎች ሚኒስቴር ጻፈ:: ነገር ግን የጅማ ገቢዎች ቅርንጫፍ እኛ የውጭ ገበያ የተሸጠው ላይ ሳይሆን በሀገር ውስጥ በሹጡት ቡና ላይ ነው ግብር የጠየቅነው የሚል ምላሽ ሰጠ:: ዩኒየኑ ሲሸጥ የነበረው ሀገር ውስጥና ውጭም ነበር:: ሀገር ውስጥ አልሸጥንም አላልንም የሚሉት አቶ ጌታሁን፤ ነገር ግን ቡናው ሲሸጥ ከገበሬዎች ላይ ለግብር ተቀናሽ አለማድረጋቸውን መግለጻቸውን ይናገራሉ::
ከዩኒየኑ ጋር ተያይዞ የነበረውን እውነታ ያውቁ የነበሩት የዞኑ አስተዳዳሪ የዩኒየኑ አባል የሆኑት አርሶ አደሮችን ከዚህ ቀደም በተደረገው የቡና ሽያጭ ከወሰዳችሁት ገንዘብ የተወሰነውን መልሳችሁ መክፍል አለባችሁ የሚል ትእዛዝ ለማስተላለፍ ሞከሩ:: ነገር ግን ዩኒየኑ ከ21 ሺህ በላይ ገበሬ ላይ እንዴት አድርጎ ነው ገንዘብ መሰብሰብ የሚችለው? የሚለውን መፍትሔ ማስቀመጥ አልተቻለም:: በመሆኑም እስካሁን የተጠየቅነውን ገንዘብ መክፈል አልቻልንም:: በገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት “ዩኒየናችሁን የምትፈልጉ ከሆነ 18 ሚሊዮኑን ብር ክፍሉ” እያለ ነው::
በፌዴራል ህብረት ስራ ኮሚሽን ጭምር ችግሩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ማሳወቃቸውን የሚናገሩት አቶ ጌታሁን፤ ነገር ግን እስካሁን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መልስ ስላልተገኘ እስከሁን ድረስ የህብረት ስራ ዩኒየኑ እና የሥራ አስኪያጁ የባንክ ሂሳብ መዘጋቱን ጠቁመዋል::
ጥሩ የሚሰራ ዩኒየን ስለነበር የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነጻ መኪና አስገብቶ ነበር:: በዩኒየኑ ስር የሚተዳደሩ 21 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ ማሽነሪዎች ወደሀገር የገቡት ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ነው::ከጅምሩ ጀምሮ ዩኒየኑ መንግሥትን የበደለው ነገር የለም:: በዩኒየኑ ውስጥ ታቅፈው ያሉ አርሶ አደሮች ህይወታቸውን ለውጠዋል:: ቡና ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ለሀገራችን ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ችሏል:: በዚህም ዩኒየኑ “በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ” ተሸላሚ መሆን የቻለ ነው::
በገቢዎች ሚኒስቴርም እንደ ዩኒየን አመራር ብዙ ተቃውሞ የለኝም:: ነገር ግን ዩኒየኑ ስራ እንዳይሰራ በመደረጉ የበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኢኮኖሚ የጎዳ ከመሆኑም ባሻገር የስራ ተነሳሽነትንም እያዳከመ ነው:: አሁንም የጅማ ቅርንጫፍ የባንክ ሂሳባቸውን ዘግቶ በመያዙ መጋዝን ላይ ያለውን ቡና መሸጥ አለመቻላቸውን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩም እየመጣ ገንዘባችንን ስጡን እያለ እየጠየቀ መሆኑን ጠቁመዋል::
በዚህም የዞኑ አስተዳደር ጭምር የጅማ ቅርንጫፍ ገቢዎችን እስከማነጋገር መድረሱን ይገልጻሉ:: ነገር ግን የተሰጠው ምላሽ የተጠየቀውን ግብር 25 በመቶ ከፍሎ ክስ መመስረት እንደሚችል እና ክስ እስከሚመሰረት ድረስ የባንክ ቼክ ወይም ንብረት በማስያዝ ስራ ይቀጥል የሚል ምላሻ ነው::
ዩኒየኑ መጋዘን ላይ የ29 ሚሊዮን ብር አለው:: ነገር ግን ቡና ለመሸጥ ሲታሰብ ሥራ የአስኪያጅ ሆነ የዩኒየኑ አካውንት ዝግ ነው:: በቡና ጉዳይ ገበያ የመጣው ሁሉ ተጠያቂ እሆናለሁ በሚል ፈርቶ ይሸሻል:: አሁን ላይ ክፈሉ የተባለውን 18 ሚሊዮን ብር የዩኒየኑን ተሽከርካሪዎች እና የቡና ኢንዱስትሪዎች በባንክ እንደ ዋስትና በማስያዝ ለመክፈል እየተሞከረ ነው::
ዩኒየኑ ጥፋት ባልሰራበት አካውንቱ ታግዶ ለኪሰራ እና ለብተና እየተዳረገ ነው:: ቡና ሸጦ በስሩ ለሚገኙ 21 ሺህ አርሶ አደሮች አከፋፈለ ተከፋፈለ እንጂ ለሌላ ዓላማ አልዋለም:: ብሩን እንሰብስብ ቢባል እንኳን 21 ሺህ አርሶ አደር ላይ እየዞሩ ይህን ያህል ብር አምጣ ማለት ከባድ ነው::
እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም ግብር ለመሰብሰብ በመፈለግ ለደብብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ደብዳቤ ጽፈዋል:: ነገር ግን ለደቡብ ብሔር ብሔረረሰቦችና ህዝቦች ክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ መሰብሰብ አትችሉም ብሎ በአዋጅ ጠቅሶ እንዳስቆማቸው እና በዚያ መሰረት ግብር ሳይሰበስቡ መቅረታቸውን ያስረዳሉ::
አሁን ላይ ዩኒየኑ ብቻ ሳይሆን ብድር አቅራቢ የነበሩ ባንኮች ጭምር እየተጎዱ ነው:: የባንክ ወለድ ብቻ 50 ሚሊዮን ብር ደርሷል:: ሶስት ዓመት ሙሉ ቡና መሰብሰብ አልተቻለም:: 21 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች ስራ አቁመዋል:: ከ280 ሰራተኞች መካከል አሁን ላይ የቀሩት 31 የሚሆኑት ናቸው:: እነዚህም ቢሆን ደመወዝ ተከፋይ አይደሉም::
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች
ሰነድ አንድ፡- ለሚመለከተው ሁሉ በሚል በደብዳቤ ቁጥር ግሕቢ/አ14/1/538/07 በቀን 16/03/07 በተጻፈ ደብዳቤ እንደተመላከተው፤ የቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን በፌዴራል ኅብረት ሥራ በአዋጅ ቁጥር 147/1991 እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦቸና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በወጣው የኅብረት ሥራ ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 111/1999 መሠረት ተቋቁሞ የምዝገባ ህጋዊ ሰውነት የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተሰጥቶት ሲሰራ ቆይቷል::
ይሁንና ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በግዥ፣ በሽያጭና በጨረታ ላይ ለመሳተፍ ውድድር በሚያካሂድበት ወቅት አለአግባብ የንግድ ፈቃድ የቫት ተመዝጋቢ ስለመሆኑ ማስረጃ እንዲያቀርቡና ቲ.ኦ.ተ እንዲከፍሉ እየተገደዱ መሆኑን ገልጾ፤ በቁጥር 1167/ሕ-6ደ/2007 በቀን 2/03/2007 በተፃፈ ማመልከቻ ተጨማሪ የንግድ ፈቃድ ሳያስፈልግና ተ.ኦ.ተ እንዳይቆረጥባቸው የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የግብይትና ኅብረት ሥራ ቢሮ ጠይቀዋል::
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የግብይትና ኅብረት ሥራ ቢሮ ለተጠየቀው ጥያቄ ለሚመለከተው ሁሉ በሚል በቁጥር ግሕቢ/አ14/1/538/07 በቀን 16/03/07 በተጻፈ ደብዳቤ እንደተመላከተው ፤የቤንች ማጂ የጫካ ቡና አምራች ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን በፌዴራል ኅብረት ሥራ በአዋጅ ቁጥር 147/1991 እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦቸና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በወጣው የኅብረት ሥራ ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 111/1999 መሠረት ተቋቁሞ የምዝገባ ህጋዊ ሰውነት የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተሰጥቶት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሷል::
በዚሁ መሠረት የኅብረት ሥራ ዩኒየኑ በአዋጅ ቁጥር 111/1999 አንቀጽ 14 ንኡስ አንቀጽ 7 ላይ በህጋዊ መንገድ የተመዘገበ ማንኛውም ኅብረት ሥራ ማህበር ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ተጨማሪ የንግድ ፈቃድ ሳያስፈልገው በማንኛውም የንግድ ሥራ ተግባራት ላይ መሰማራት እንደሚችል አመልክቷል:: በተጨማሪም በአዋጅ ቁጥር 147/1991 አንቀጽ 41 ንኡስ አንቀጽ አንድ በተራ ፊደል “ረ” ላይ በመንግሥት የሚከናወኑ የአገልግሎት የኮንስትራክሽን የማምረት የግብይት እና ሌሎችም ጨረታዎችን የመንግሥት መሥሪያ ቤት ለኅብረት ሥራ ማህበራት በሚያሟሉት ደረጃ ቅድሚያ ሊሰጥ ይችላል በሚል ልዩ መብት ተሰጥቶታል።
እንዲሁም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግሥት የታክስ አስተዳደር ባለስልጣን ታህሳስ 2000 ዓ.ም ከተካፋይ ሂሳብ ላይ ግብር ቀንሶ ገቢ የማድረግ ሥርዓት የአፈጻጸም መመሪያ የተሻሻለው አንቀጽ 2.4.6 ላይ ከተካፋይ ሂሳቦች ላይ ግብር ተቀናሽ የማይደረግባቸው የገቢ ዓይነቶች አካላትና ግብይቶች በሚለው አንቀጽ ሥር በገጽ 16 በተራ ቁጥር ስምንት መንግሥታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ የግል ድርጅቶች ማለትም ብዙኃን ማህበራት፣ የኅብረት ሥራ ማህበራት ወዘተ ከፍትህ ሚ/ር እና ከሚመለከተው አካል የምዝገባ ምስክር ወረቀት ሲያቀርቡ ላከናወኑት የዕቃ፣ የንብረት ሽያጭ ለሰጡት አገልግሎት ክፍያ ሲፈጸምላቸው ከተካፋይ ሂሳብ ተቀናሽ አይደረግባቸውም በሚል መደንገጉን ተመላክቷል::
ሰነድ ሁለት፡- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የገንዘብ ሚኒስቴር በቁጥር ታ/ክ/ቀ/5/413 በቀን 8/9/2014 ለገቢዎች ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ እንደተመላከተው፤ የቤንቺ ማጂ የጫካ ቡና አምራች ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ከአባላቱ ተሰብስቦ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ወደ ውጭ በተላከ ቡና ላይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ያልተሰበሰበ የተጨማሪ እሴት ታክስ ፍሬ ግብር፣ ወለድና ቅጣቱን ጨምሮ ብር 25 ሚሊዮን 790ሺህ 450 ነጥብ ዘጠኝ እንዲሁም ቅደመ ግብር፣ ፍሬ ግብር፣ ወለድና ቅጣት ጨምሮ በድምሩ ብር 5 ሚሊዮን 963 ሺህ 199 ነጥብ 19 እንዲከፍል ተጠይቋል::
በዚሁ የታክስ ጫና ምክንያት የባንክ ሂሳቡ በመታገዱ ምክንያት ሥራ ለማቆም ተገዷል:: በመሆኑም ህብረት ስራ ዩኒየኑ ለሀገር የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት የተቋረጠ በመሆኑ፣ በግለሰብ አባላት ዘንድ ከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ የፈጠረ መሆኑን በመግለፅ ጉዳዩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ታይቶ እልባት እንዲሰጠው የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር አጠ34/1610 በተፃፈ ደብዳቤ መጠየቁን ግልጾ በዚህም መሠረት፡-
አንደኛ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 280/2002 አንቀጽ 7(2) መሠረት የቡና ወጪ ንግድ ግብይት በዜሮ በመቶ (Zero rated transaction) የማስከፈያ ልክ የሚስተናገድ በመሆነ የቡና ምርቱ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ወደ ውጪ የተላከ መሆኑ ተረጋግጦ የታክስ ክፍያ ቀሪ እንዲደረግ፤ እንዲሁም ዩኒየኑ በተፈጠረ የሕግ ብዥታ ምክንያት የቅድመ ግብሩን ክፍያ ሊሰበስብ ያልቻለ መሆኑን ማረጋገጥ የተቻለ በመሆኑ ለገንዘብ ሚኒስቴር በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 648/2001 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 19(3) እንዲሁም በፌዴራል ታክስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 407/2009 አንቀጽ 7 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እንዲከፍል የተጠየቀው የግብር ዕዳ (ወለዱና ቅጣቱን ጨምሮ በምህረት ቀሪ እንዲደረግ፤ የተወሰነ መሆኑን እየገለፅን በዚሁ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ እናሳስባለን የሚል ነው::
ውድ አንባቢያን በቀጣይ ከገቢዎች ሚኒስቴር የሚሰጠውን መልስ፤ አዋጅ እና መመሪያዎች ምን ይላሉ የሚለውን ይዘን የምናቀርብ ይሆናል::
በመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም