“ኖሃው አለኝ”

ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል። ይህ የሕይወት እውነታ ነው፤ በጥቂቶች የሕይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የሕይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ለተቸገሩት ያዝናሉ፤ ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ፤ በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሔ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው ዓምዳችን ሕይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።

በእንባ ዘለላዎች የተቋጨ የሃዘን ሸማ ከተከናነቡት ጋር አብሮ ማቅ የሚለብስ፤ ኑሯቸው ደርጅቶች ከሚስቁት ጋርም አብሮ የሚፈነድቅ የሰው ልጅ ሕላዌ የሚገደው የሕይወት ማጣፈጫ የምድር ጨው ሞያ ነው ጋዜጠኝነት። በመሆኑም ሰሞንኛ ጽሁፌን ለማሳካት እንደተርብ ወዲያ ወዲህ ስኳትን ወዳጄ ቢኒያም አለማየሁ ቀትሩን በጀበና ጥላ ለማሳለፍ እግራችንን እናጥፍ ዘንድ ሃሳብ አቀረበ። ግብዣውን ተቀብለን የመዳፍ ያህል ስፋት ባላት ቤት ዘልቀን፤ ሊታዘዘን ወገቡን ይዞ ከፊታችን የተሰየመው ወጣት አቦል ጀባ እንዲለን ነገርኩት።

ወጣቱ ከቤቱ ደጃፍ ተቀምጦ ማዶ ማዶ እያየ አገጩን በእጁ ጭኖ ሃሳብ ያንቀራጭ ነበር። “እመት አይሞላልሽ ወጡ ቆረጠብሽ አለች አያቴ ሙሉ ጎጃም ቢተው” ብሎ ተረተና “ያንተ ነገር! ልጠይቀው ባላልክ እንጂ? ለምን ይሆን መተከዙ? አለኝ እየሳቀ ወዳጄ ቢኒያም። ምን ታደርገዋለህ ባልንጀሬ? ካለቀሱት ጋር እንዳለቅስ ከሳቁት ጋር እንድስቅ በልጅነቴ የተጣባኝን ሞያ ለብሻለሁ፤ ደግሞም እወደዋለሁ፤ በዚያ ላይ ደመ ቀዝቃዛ አይደለሁም። ዋናው ቁምነገር ግን “ጋዜጠኛ ስትሆን የግድ ደራሲ ትሆናለህ” እንዲል በዓሉ ግርማ ከወረቀት ማሳ የብዕር ሞፈር እየሳብኩ የፊደል አዝመራ መውቃት እሻለሁ። እያንዳንዷን የሕይወት ገጽ መበርበር እጣ ፋንታዬ ሆኗል አልኩት በሾምኩት ጀበና በኩል ብዕሬንና አንደበቴን እንደውሽማ ወጥ እንዲያጣፍጥልኝ የጋሼ ስብሃትንና የበዓሉን የስነጽሁፍ ውቃቢ ተለማመንኩት፤ ሽቅብ የሚምዘገዘገውን የእጣን ጪስ ተከትዬ።

የፈረስ ጭራ የመሰለ ቡና ቀድቶ ፍንጃሉን ሲያቀብለኝ ካፍንጫዬ የደረሰው መአዛ ቀድሞ አምሮቴን ቆረጠውና ሞያህ ሚስት ለምኔ ያሰኛልሳ? አልኩት ወግ ለመጀመር ያህል። “ሳይቀምስ የሚፈርደው ሳያይ የሚሸሸው በዛ እንጂ ካልክስ አዎ!” አለ የቋጠረውን ፊቱን በስሡ እየፈታ።

“ወንድ ያፈላውን ቡናስ አልጠጣም” የሚል ደንበኛ አልገጠመህም እንዴ? አልኩት በማስከተል። “ያስጨነቀኝስ እሱ አይደል? የምሸሻትን ሴት የግዴን እንድቀርባት እየተጫነኝ ነው” ብሎ ዝም ሊል ሲል ወተወትኩትና ሴቶችን የሚሸሽበትን ምክንያት ከስሩ ፈልፍሎ አወጋኝ።

በአስራዎቹ መጨረሻ እድሜ ላይ ሳለ ትምህርት ቤት የሚያውቃት ልጅ በፍቅር ሸርባው ሕይወቱ መደነቃቀፍ ገጠመው። ብጻት ባለጸጋ ቤተሰቦች ያሏት መሆኗን፣ እሱ ደግሞ እጅ ከሚያጥራቸው ወላጆች መገኘቱን እያሰበ ልቡ ውስጥ የሚንቀለቀለውን የፍቅር እሳት በስጋት ተመልክቶት ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሆነበት። አንድ ቀን ሶደሬ እንዲያዝናናት ሃሳብ ባቀረበችለት ጊዜ ገንዘብ የሚጠይቀው ሁነኛ ዘመድ ስላልነበረው “አንቺን ከማጣ ራሴን ልጣ” ብሎ የቀን ሥራ ሲያፈላልግ የድንጋይ ሸከማ አገኘና “ስለፍቅር በድንጋይ የተወገሩስ አሉ አይደል? እንኳን የኔ ድንጋይ ሸከማ ይቅርና?” በማለት የጉልበት ሥራውን ተያያዘው። በቀን የሚያገኛትን ሰላሳ ብር አጠራቅሞ መሻቷን ፈጸመላትና ማስታወሻ እንዲሆን ፎቶ ከመነሳት ባሻገር ያንገት ሃብል ገዛላት፤ ይሁን እንጂ ጦስ ጎተተባቸው። በአንደኛው የትምህርት ቀን ማለዳ አክስቷ የቋጠሩላትን ምሳ ሊያስገቡ ቦርሳዋን ሲከፍቱ አንገት ላንገት ተቃቅፈው አበባ እየሰጣት የሚያሳይ ፎቶ ተመለከቱና እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው ክፍለሀገር ለሚገኙ እናቷ ያዩትን ነገር አጣፍጠው ተረኩላቸው። ከዚህ በኋላ “የት ወጣሽ? የት ገባሽ?” የሚለው ቁጥጥር ብጻትን ቀየዳትና ከፍቅሩ ጋር እንደልብ መገናኘቱ ቀረ። ከሁሉም በላይ ሁኔታውን ያከፋው እናቷ እመጣ ብለው የፈጠሩት አምባጓሮ ነው።

ፍቅረኛውን አይኗን ሳያያት በመዋሉ ስሜቱ ደፍርሶ በጊዜ የተኛው ፍቅሩ የለሊቱ አካፋይ ሰዓት ላይ የደሳሳ ጎጆው በር በሃይለኛ እርግጫ የኋሊት ሲንጋለል ድንጋጤው መሬት ተከፍታ ብትውጠው በወደደ ነበር፤ ነገር ግን አልሆነም። መለዮ የለበሱ ሁለት ሰዎች አንጠልጥለው ካቆሙት መኪና ሲጨምሩት ብጻትን አያትና ምን እንደተፈጠረ ቢጠይቃት መልስ ሳትሰጠው መንገድ ተጀመረ። በጉዟቸው ቃል አልተለዋወጡም። ንግግር የነሱት ጮላፊዎቹ ከአንድ ሆቴል በር ሲያወርዱት የግዱን ከብጻት ጋር እየተገፋ ወደውስጥ ዘለቀ። እንደመርፌ በሚወጋ አስተያየት የተቀበሉት እናቷ “የኛ ደፋሪ” አሉት አለባበሱን አይተው በመጠየፍ እንትፍ እያሉበት። ከምላስ የሳሳች ነጠላ ጫማና አርባ አራት ቦታ የተደረተ ሸሚዝና ሱሪ ነበር የለበሰው። ግራ ተጋብቶ ባንክሮት ሲያስተውላቸው “ለነገሩ አንተ ምን ታደርግ፤ የገዛ ልጄ ናት ያዋረደችኝ” አሉ በድጋሚ በንቀት እየተመለከቱት። “ስለምን መድፈር ስለምን መዋረድ ነው የሚያወሩት እናታችን?” አለ የሰው ሁሉ አይን እሱ ላይ እንደሆነ ሲታዘብ ሽምቅቅ ብሎ። “ያም ሆነ ይህ ትታይና የምናገኘውን ውጤት ይዘን እንፋረዳለን” አሉና ሲጠቅሷቸው እነዚያው መለዮ ለባሽ ሁለት ሰዎች ብጻትን እያጣደፉ ይዘዋት ወደሆስፒታል ከነፉ።

ከግማሽ ሰአት ቆይታ በኋላ ተመልሰው የታሸገ ፖስታ አቀበሏቸውና ሲከፍቱት ከነክብረ ንጽህናዋ መሆኗን እንዳነበቡ ወረቀቱን እያጠፉ “ለዛሬ ተርፈሃል፤ ለተንግዲሁ ግን አቅምህ ጋር ነው መስተካከል” አሉት በረዥሙ እየተነፈሱ። “ቢያውቁት ኖሮ እንኳንስ ላልተፈጠረ ወንጀል ቢሆን እንኳን አጥንት የሌለው ምላስ አጥንት ይሰብራል፤ ለማንኛውም ሽበትዎትን አያቅሉት” ብሏቸው ሊወጣ ሲል “በህግ አምላክ እንዳትወጣ” አሉት ንግግሩ በርብሯቸው። ወላጆቹ ሃብት ባያቆዩትም በመልካም እሴቶች የተቃኘ ሞራል አውርሰውታልና ርምጃውን ገቶ “እርስዎ የናቁት ሕግ ለኔ መሥራቱ ከርስዎ እንደምሻል ማሳያ ነውና በክብር እቆማለሁ” አላቸው የጎሪጥ እየተመለከታቸው። “አንድ ጊዜ ከመናገር ሶስት ጊዜ ማሰብ” የሚለውን ብሂል ዘንግተው በተናገሩት ነገር በተራቸው አፍረው አንገታቸውን ሲደፉ ፍቅሩ ሃሳቡን ቀጠለ። “ንግግርዎ የቱንም ያህል ለጆሮ ቢጎረብጥም ሰው ሳልሆን ሰው መፍጠር እንደሌለብኝ አስተምሮኛልና ብሎም አይቀጥልም እንጂ ቢቀጥል እንኳን የምወልደው ልጄ እንደርስዎ አይነት አያት እንዲኖረው አልሻምና ከንግዲህ አጠገቧ አልደርስም” ብሎ ሃሳባቸውን ሳይጠብቅ ተቻኩሎ ወጣ።

ቆፈኑ ቆዳውን ሰርስሮ ካንጀቱ ሲገባ ስምንት ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚኳትኑ እናቱ ስቃያቸው በሃሳቡ ተሰነቀረና የሱ “ፍቅር ፍቅር” ማለት ሕሊናውን አሳድፎት ከልቦናው አለቀሰ። ከአልበርታን ስታይን እናት ሃሳብ ተውሰው ስኬታማ ሳይሆን ዋጋ ያለው ሰው ለመሆን እንዲጥር የመከሩት እናቱ እሱን ለማሳደግ እንደ እማሆይ ትሬዛ ያልተቀበሉት ውርደት የለም። አንድ ባለጸጋ ቢነኩት የሚቆሽሽና የጨረቃን ውበት የሚያስንቅ መኪና እያሽከረከረ መጥቶ ካጠገባቸው ሲቆም እማሆይ ትሬዛ በከፈተው መስኮት እጃቸውን ሰደው “ለተራቡ ልጆች ዳቦ የምገዛበት ያለህን ፍራንክ ስጠኝ” በማለት ይማጸኑታል፤ ሰውዬው ግን በዘረጉት እጃቸው መዳፍ ላይ ምራቅ ተፋባቸው። እማሆይ ትሬዛ ሳይቆጡ በፍጹም ትህትና “ግድ የለም ይሄ የኔ ድርሻ ነው፤ የልጆች ዳቦ መግዣስ?” አሉት አይናቸው እንባ እያቀረረ። ፍቅሩ የጸጸት ጅራፍ እየለበለበው ወደ ቤቱ ሲያዘግም ያሳለፈው የሕይወት ውጣ ውረድ ከስር መሰረቱ እሱነቱን አስነበበው።

1981 ዓ.ም በወርሃ መጋቢት ከአባቱ አቶ ጸጋዬ ገብረእግዚአብሄርና ከእናቱ ከወይዘሮ ክብነሽ አባይ ለቤቱ ስድስተኛ ልጅ የሆነው ፍቅሩ ጸጋዬ በተለምዶ አጠራሩ በሸገር ማህጸን አውቶቢስ ተራ አብዶ በረንዳ ሰፈር ተወለደ። እድሜው ቀለም ለመውጋት ደርሶ ዳግማዊ ብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቢያስገቡትም ወላጆቹ የመክፈል አቅም አንሷቸው ከሁለተኛ ክፍል በላይ መዝለቅ አልቻለም፤ ይሁን እንጂ ባካባቢው ማኅበረሰብ ጥረት ከቀበሌ የድህነት ማስረጃውን በማስወጣት የካቲት 23 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውሮ ፊደል መቁጠሩን እንዲቀጥል አስቻሉት። የቤቱን ምሰሶ አባቱን በሞት ሲነጠቁ እናቱ ጫንቃ ላይ የወደቀውን ኃላፊነት ለማገዝ ሲል በአስራ ሶስት ዓመቱ የቀኑን ትምህርት ወደማታ ለውጦ በወር አርባ ብር እየተከፈለው ደረቅ እንጀራ ማከፋፈሉን ተያያዘው፤ አቻ ጓደኞቹ ግን “መላጣ፣ የስላሴ ጦጣ። እንደአህያ ሸክሙ በዝቶበት ጸጉሩን መለጠው” እያሉ ሲያሾፉበት ጊዜ እንጀራ ማከፋፈሉን ትቶ ወደድንጋይ ሸከማ ሥራውን ቀየረው። ይህን ጊዜ ነበር የብጻት ፍቅር አሳሩን አብልቶ ቁም ስቅሉን ያሳየው።

ስምንተኛ ክፍልን በጥሩ የሚኒስትሪ ውጤት ተሻግሮ ዘጠኝና አስርን ለመማር እግሩ ድላችን ትምህርት ቤትን የረገጠው ፍቅሩ በመሃል ትምህርቱን እያቋረጠ ከአንድም አምስት ጊዜ በሕገወጥ መንገድ ከሀገር ውጪ ለመሰደድ ሞክሮ ነበር። በድንበር ጠባቂዎች እየተያዘ ተመለሰ እንጂ። ነገሩን ሲያከፋው የማትሪክ ውጤትም አልመጣለትም። በእናቱ ተግሳጽ የነጠፈው ተስፋው ነፍስ ዘርቶ ፒያሳ ይገኝ በነበረው ስካፌር ማሰልጠኛ የምግብ ዝግጅት ተማረና ቤቴል ሆስፒታል ለመቀጠር በቃ። እትፍ ሳይቆይ አየር መንገድ በጽዳት ሥራ ተቀላቀለ። በሥራው ላይ እንዳለ መንጃ ፍቃድ ቢሰለጥንም መኪና የሚሰጠው ጠፋና ዳግም በሴቶች የጸጉር ሥራ ሰለጠነ፤ በዚህም ጠብ የሚል ነገር አጣ። ቤት ውስጥ ሽንቁሩ በዛና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ሲል በትውልድ መንደሩ በተከፈተው መነሃሪያ ፋርማሲ ሂሳብ ያዥነትን ከጽዳት ጋር ደርቦ መሥራት ጀመረ። የኑሮ ትግሉ እያየለ ሲመጣ ጣውላ ቤት፣ አናጺነት፣ መስተንግዶ፤ ብቻ ምን አለፋችሁ ያልሞከረው ሥራ የለም።

አሁን ደግሞ ይኸው “ኖሃው አለኝ” በሚለው የቡና ሥራ ኑሮን ለማሸነፍ እየጣረ ነው። በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ መልካም ትብብር አንድ ወንድምና ሁለት እህቶቹ ጋር ለአራት ተደራጅተው የጀመሩት የቡና ሥራ እንደጠበቀው ባይሆንም ያን ጊዜ የቀን ሥራ በሚሠራበት ወቅት እናቱን ከኪራይ ቤት አውጥቶ ለኮንዶሚኒዬም ማብቃቱ ዛሬ ላለበት የሥራ ሞራል ብርታት እንደሆነው በኩራት ይናገራል እንግዳዬ ፍቅሩ ጸጋዬ።

የቡና ሥራውን ገና እንደጀመረ ከደም የወፈረ እንባ የሚያስነቡ ክስተቶች ነበሩበት። አንድ ወንድ ይመጣና ቡና እንዲቀዳለት ያዘዋል። ጀበናውን ጥዶ እሳት ሲያርገበግብ ያይና አልፎ ሃጁ ደንበኛ “ልጂቷ የለችም እንዴ?” ማለት። ፍቅሩ የፈጠረበትን ፍርሃት ለመሸሸግ እየታገለ “እንደጣደችው ባንክ ቤት ደርሼ ልምጣ ብላ ሄዳ ነው” አለ ሲሸሽ የነበረው ጥያቄ አይኑን አፍጥጦ እየሞገተው። “ወንድ ያፈላውንማ አልጠጣም” ብሎ ትቶት ሲሄድ ፍቅሩ አምርሮ አነባ። “ወትሮስ አንተ እንደቀስት የተወደሩ የደረት ላይ ብርቱካን ጡቶች፣ እንደበሬ ሻኛ የሚገላበጥ ዳሌ የለህ? አትፍረድባቸው አይን መያዣ ቢያጡብህ ነው መሸሻቸው” አለ ጓደኛው ከድር የሱፍ የኮረኮሩት ያህል እየሳቀ። “የመጣ ሁሉ እንደሱ እያለ ነው ሞራሌን ሰብሮት የሚሄደው” አለ ፍቅሩም በመልሱ ሀዘን ፊቱን እያኮማተረው። እና ምን አሰብክ? አልኩት አሁናዊ እቅዱን ለማወቅ እየጓጓሁ። “የጀመርኩትን የቡና ሥራ አስፍቼ ምግብም ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነኝ” ብሎ የሰየመልንን ገበታ ተሻምተን ብንቀምሰው ጣት የሚያስቆረጥም ማለፊያ ምግብ ነው። ለስንብት ሳኮበኩብ ወዳጁ አብነት ደረሰና ስለፍቅሩ የሥራ ሞራል ሃሳብ እንዲሰጠኝ በጠየኩት ጊዜ ምስክርነቱን እንዲህ ሲል አካፈለኝ። “ምንም እንኳን ጥናት ቢያስፈልገውም በኔ እሳቤ የንግድ ሥርዐታችን ጾታዊ ፈቃድ ይታይበታልና ፍቅሩን በጅጉ ቢፈትነውም እሱ ግን ተስፋ ሳይቆርጥ እየታተረ ለዚህ መብቃቱ ከራሱ አልፎ ለኛም የሞራል ስንቅ ሆኖናል” አለ የቀረበለትን ቡና እየላፈ።

እያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ ጾታን አይጠይቅምና በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ ያለልዩነት እንትጋ መልዕክቴ ነው።

ሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You