
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በመጀመሪያ አከላለሉ ወረዳ አራት በአሁኑ ወረዳ 12 ነዋሪ የሆኑና የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ላለፉት አምስት ዓመታት ከሥራ አጥነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት የተሸጋገሩበት ቦታ መንግሥት ለአልሚዎች በሊዝ ጨረታ ስለሸጠው ቅሬታቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምርመራ ዘገባ ቡድን አቤት ብለዋል።
የሥራ እድል የተፈጠረላቸው እነዚህ አምስት ወጣቶች፣ በተገኘላቸው የሥራ እድል “ጀሀን ገላን የመኪና እጥበትና አረንጓዴ ልማት” የሚል ማኅበር ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት መሥርተው ራሳቸውን በቤተሰብ ላይ ሸክም ከመሆን ባለፈ ለአካባቢው ወጣቶች ምሳሌ በመሆን በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ናቸው። የዝግጅት ክፍላችንም ሕዝብ ይፈርድ ዘንድ የወጣቶችን ቅሬታና የሚመለከተውን አካል ምላሽ አካቶ እንደሚከተለው ሰንዶታል።
የወጣቶቹ አቤቱታ
የዛሬ አምስት ዓመት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍል ከተማ በወረዳ አራት ወደ 31 ቦታዎች ተመርጠው ወጣቶች እንዲደራጁ ተደረገ። በወቅቱ ከተለያየ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ የተመረቁ አምስት ወጣቶች ደግሞ ወንዝ ዳር የሆነና በወቅቱ ጽዱ ያልነበረን ቦታ ራሳቸው በመምረጥ ቆሻሻውን አጽድተው ለመጠቀም በተመቻቸው የሥራ እድል ለመሥራት ቆርጠው ቦታውን ጠየቁ፤ በየጊዜው የሚታደስ ውል በማሰርም እንዲፈቀድ ተደረገላቸው። ይህ ቦታ ቀድሞ ወረዳ አራት ይገኝ የነበረ ሲሆን፣ ከስምንት ወር በፊት ግን ወደ ወረዳ 12 የተካለለ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ወጣቶቹ፣ ቦታውን ይረከቡት እንጂ በሥፍራው የሞተ ፈረስና ውሻ እንዲሁም የፈርስና ቆዳ መጣያ ከመሆኑ የተነሳ ለማጽዳት ብዙ ተቸገሩ። ብዙ ዋጋ ከፍለውም አጸዱ። በዓል በመጣ ቁጥር ቆሻሻ እንዳይጣልም ውጭ ከማደር ጀምሮ ቆሻሻ አለመጣልን ባሕል ለማድረግ ተጉ። ቦታው ላይ በገንዘብ የማይተመን ጉልበታቸውን ያፈሰሱ ሲሆን፣ ይህን ሲያደርጉ ግን ቦታውን ከመፍቀድ ባሻገር ለአምስት ዓመት በሙሉ ከመንግሥት ያገኙት ድጋፍ አልነበረም። በራሳቸው ተነሳሽነት ችግኞችን በመትከል አካባቢውን ወደ አረንጓዴነት ቀየሩ።
በግቢያቸውም ቡና፣ ሙዝ፣ ዘይቱና እና ሌላም የፍራፍሬ ዓይነት ተከሉ። ቦታው በተሻለ ሁኔታ በመጽዳቱም የአካባቢው ሰው ደስተኛ ከመሆኑም ባሻገር ለራሱ ማንበቢያ፤ የልጆቹ ደግሞ መዋያም አድርጎ መጠቀም ጀመረ። እነርሱም ከመኪና እጥበት በሚያገኙት ገቢ እየተዳደሩ መምጣታቸውንና በአሁኑ ጊዜ ለአምስት ሰዎችም የሥራ እድል መፍጠራቸውን ለምርመራ ቡድኑ አስረድተዋል።
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እየሠሩ ባሉበት ወቅት፤ ምንም ዓይነት ግንዛቤው ሳይኖራቸው ቦታው የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በወጣው አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ለጨረታ መቅረቡን ሰሙ። ይህንንም የተረዱት ጨረታውን መወዳደር የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቦታውን ለማየት በመጡ ጊዜ እንደሆነ ያብራራሉ። ቦታው በመሃሉ ወንዝ ያለው ስለሆነ አረንጓዴ ተብሎ የተከለለ ነው። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ለሕንፃ መሥሪያ በሚል ለጨረታ ስለመውጣቱ ይገልጻሉ።
ወጣቶቹ፣ በወረዳው በበጎ ፈቃደኝነት ይሳተፋሉ፤ ቤተሰብ ለሌላቸው ሰዎች በሚደረገው ድጋፍ ግንባር ቀደም ተሳታፊዎችና አስተባባሪዎች ናቸው። ጸጥታ ላይ በቋሚነት ይሠራሉ፤ ምሽት ላይ ጥበቃ ይወጣሉ። የማኅበረሰብ ፖሊስ ላይ አበርክቷቸው ከፍተኛ ነው። የሀገር መከላከያ አስገዳጅ ወደሆነው ጦርነት በገባበት ጊዜ ቁሳቁስ በማሰባሰብ በበጎ ፈቃድ ተንቀሳቅሰዋል። አካባቢውን አረንጓዴ ለማድረግም ብዙ ብር ተበድረዋል።
መንገድ ላይ የጸጥታን ጉዳይ ለመከታተል ፖሊስ ለተከላቸው ካሜራዎችና ለኮሙኒቲ ፖሊስ ስልክ በቋሚነት ካርድ የሚሞሉት እነርሱ ናቸው። በዓል በመጣ ቁጥር ለአራት ያህል ቤተሰብ ድጋፍ ያደርጋሉ።
ቦታው ተላልፎ ሊሰጥ መሆኑን ሲሰሙ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበትና የአረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊውን ስለጉዳዩ እንደጠየቁ የሚገልጹት ወጣቶቹ፣ እንደዚያ ዓይነት ቦታ ስለመኖሩ፣ እነርሱ ስለማልማታቸውና በጨረታም ስለመውጣቱ እንደማያውቁ ኃላፊው መግለጻቸውን ለምርመራ ቡድኑ አስረድተዋል። ነገር ግን ኃላፊው፣ ባለሙያ ልከው ቦታውን እንዲያዩ ካስደረጉ በኋላ የሰጧቸው “ስላለማችሁት እግዚአብሔር ይስጥልኝ” የሚል አጭር መልስ እንደሆነ ወጣቶቹ ገልጸዋል። ወጣቶቹ ይህ ዓይነቱ ምላሽ ሕልምን የሚገድል ዓይነት ምላሽ ሆኖብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ያስረዳሉ።
ያለፉትን አምስት ዓመታት ሌላ ቦታ ሮጠንበት ቢሆን በብዙ አትራፊዎች እንሆን ነበር። ዛሬ ግን አምስት ዓመት ከእድሜያችን ላይ የተወሰደ ሆኖብናል። በዚህ ቦታ ገንዘባችንንና ጉልበታችንንም ጭምር ያፈሰስነው በቀጣይ እንጠቀማለን በሚል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የሚመለከታቸውን አካላት በጠየቁ ጊዜም “ቁጥራችሁ አነስተኛ በመሆኑ በእናንተ ላይ ሰው እንጨምራለን” መባላቸውን ጠቅሰው፤ “አምስት ዓመት ሙሉ ለፍተን እንዴት ይህ ይሆናል?” ሲሉም ለጠየቋቸው ምላሽ እንደሰጡ አስረድተዋል።
በአካባቢው የልጆች መጫወቻም ሆነ ማንበቢያ ቦታ እንደሌለ ገልጸው፤ በአካባቢው ነዋሪዎችም የተወደዱት ለዚህ መሆኑን ጠቁመዋል። ሥራችን ከምናጣ መንግሥት ድጋፍ ቢያደርግልን መልካም ነው ሲሉም አቤቱታቸውን አሰምተዋል።
ወጣቶቹ፣ የወደፊት እቅዳቸውም ለልጆች የሚሆን መዝናኛ መሥራት ሲሆን፣ ከፍተኛ አመራሩ፤ የእነርሱን ሃሳብ የሚደግፍ እንጂ እድላቸውን የሚያመክን ምላሽ እንደማይኖረው ተማምነዋል። ብሩህ የሆነው የነገ ተስፋቸውን እንደማያመክኑም ተስፋ ሰንቀዋል። ይሁንና አሁን የተጋረጠብን ፈተና ከእድሜያችን ላይ አምስት ዓመት የተቀነሰብን ያህል ተሰምቶናል ሲሉ ጠቅሰው፤ እጣ ፈንታችን ምንድን ነው? ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ወጣቶቹ፣ አካባቢውን ጽዱ በማድረግ፣ በአካባቢ ጸጥታ ላይ ከፖሊስ ጋር በመተባበር፣ ማዕድ በማጋራት፣ በብዙ መስክ ተባባሪ በመሆን ላደረጉት እንቅስቃሴ የወረዳ 4 የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት፣ የወረዳ 4 የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ፣ የወረዳ 4 ሰላምና ጸጥታ አስተዳደርና ሌሎች ጽሕፈት ቤቶችም የምስጋና እና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋቸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ምስክርነትና የ“አይነሱብን” ጥሪ
ወጣቶቹ፣ 300 የሚጠጉ ነዋሪዎችን ፊርማ ሰብስበዋል። ፊርማቸውን ካኖሩላቸው መካከል አስተያየታቸውን ለምርመራ ቡድኑ የሰጡ በርካታ ሲሆኑ፣ እነዚህም አቶ አብደላ አቡበከር፣ ወይዘሮ ማርታ ታዬ፣ አቶ ኪሩቤል መለሰ፣ ወይዘሮ ሳሙኤላ ወልደሥላሴ፣ አቶ ሶሎሞን ደምመላሽ፣ አቶ ማቲያስ ሐጎስ፣ አቶ ኪዳነ ግርማ እና አቶ አይናለም ሸንተማ ይገኙበታል።
ነዋሪዎቹ ምስክርነታቸውን በሰጡበት ጊዜ እንደተናገሩት፤ ቦታው አምሮ ከመታየቱ በፊት የሰፈሩ ቆሻሻ ሁሉ መጣያ ነበር። ወጣቶቹ ግን ሳይጠየፉ አጽድተው የልጆቻችን መዋያ አድርገውልናል። ቅዳሜና እሑድ ልጆቻችን መጽሐፍ ያነባሉ። ለአምስት ዓመታት በዚህ ቦታ ለፍተዋል፤ የተከሉትን አትክልት ሳይቀምሱ ተነሱ ተባሉ። ታዲያ ልፋታቸው የማይታየው ለምንድነው? እኛን የአካባቢውን ሰዎች የጠቀሙንን ያህል ራሳቸውን ገና መጥቀም ያልጀመሩ ናቸው።
የአካባቢውን ቆሻሻ ማጽዳታቸው ብቻ ሳይሆን ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን ሌቦችንም ጭምር አደብ በማስገዛት ሚናቸው የላቀ ነው ይላሉ። በጸጥታው በኩል ያለው በጎ ተግባራቸው ለሌሎችም አርዓያ የሚሆን ነው። ወጣቶቹ ገንዘብ ላይ ብቻ ያተኮሩ ሳይሆኑ፤ አካባቢውን በማልማት ጭምር የተጠመዱ ናቸው። ሰፋ ያለ መሬት ቢያገኙ ከዚህ የበለጠ አካባቢውን አረንጓዴ የማድረግ ተነሳሽነት ያላቸው ናቸው ይላሉ።
በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ሥራና ክህሎት ምላሽ
በጀሀን የመኪና እጥበትና አረንጓዴ ልማት ማህበር ስም የተደራጁ ወጣቶች በሥራ አጥነት ስለመደራጀታቸውና ሕጋዊ ስለመሆናቸው የወረዳ 4 አስተዳደር ሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ጠይቀን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል።
በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ሥራና ክህሎት የአንድ ማዕከል ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ፍቅሬ ከበደ በጀሀን አረንጓዴ ልማትና መኪና እጥበት ማህበር ስም የተደራጁ ወጣቶች በሕጋዊ ማህበር የተደራጁ መሆናቸው ይገልጻሉ። ከዚህ በፊት ወረዳ 12 እና ወረዳ 04 አንድ ወረዳ የነበሩ ሲሆን በሪፎርሙ ለሕዝብ ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ሲባል ወደ ሁለት ወረዳ መከፈሉን ይናገራሉ።
አስተባባሪው እንደሚሉት፤ ቀጣና አራት የሚባለው ሰፈር ለብቻው ተለይቶ በወረዳ 04 ስር የነበረ ሲሆን፣ 2016 ዓ.ም ኅዳር አንድ አካባቢ ወደ ወረዳ 12 እንዲካለሉ ተደርጓል። ስለዚህ ማህበሩ በሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት በኢንተፕራይዝ ማደራጀት መመሪያ የተደራጀ ሕጋዊ ማህበር ነው። በ2016 የመጀመሪያ የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ 119/2014 የአደረጃጀት መመሪያ መሠረት በወጣ መመሪያ አንድ ሥራ ፈላጊ በሥራ አጥነት ሲደራጅ የሚሟላውን መስፈርት አሟልተው የተደራጁ ሕጋዊ ማህበር ናቸው።
የሚደራጁ ወጣቶች የሚያቀርቡት መረጃ ሥራ አጥ መሆንና አለመሆናቸውን በማስተቸት፤ የቀጣና ደጋፊ አመራር ሶስት ሰዎች አረጋግጠው ወደ ወረዳ በመላ ተተችቶ ከጸደቀ በኋላ ነው። ይህ ከሆነ በኋላ ሥራ አጥነት መታወቂያ አውጥቶ በመጀመሪያ ጥሪት ማፍሪያ በአገልግሎት ዘርፍ ይሠማራሉ። ይህ የሚሆን ንግድ ፈቃድ ማውጣት ስለማይገደዱ የመንግሥት መሬት ልማትና አስተዳደር፤ ሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት በጋራ በመሆን ቃለ ጉባኤ ይዘው እንደ አስፈላጊነቱ መሬቱን መንግሥት በሚፈልግበት ጊዜ የሚለቀቅ ሆኖ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የሚፈጠሩበት ቦታ በጊዜያዊነት መሬት ባንክ የገባ መሬት እንደሚሰጣቸው አቶ ፍቅሬ ያስረዳሉ።
ወጣቶቹ ሲደራጁ እንዲሁ ሳይሆን የንግድ ስያሜ በመስጠት ስለሚደራጁ በጀሀን ገላን መኪና እጥበትና አረንጓዴ ልማት ማህበር ስም የጥሪት ማፍሪያ ተሰጥቷቸው እየሠሩ ነው። ሲደራጁ የግል ኢንተርፕራይዝ እናደራጃለን፤ ሁለትና ከዚያ በላይ በሽርክና፤ በአክሲዮንና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአራት ዓይነት መንገድ ይደራጃሉ። ስለዚህ እነዚህ ወጣቶች የጥሪት ማፍሪያ ስለሆነ በዚያ ስም ተደራጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል።
ወጣቶች እየሠሩበት ያለው ቦታ በፊት በዚኔት የዘይት ፋብሪካ የሚለቀቅ ፍሻስ የሚጨመርበት ወንዝና የቆሻሻ መጣያ ነበር። ይህን በማጽዳት እንዲለማ አድርገውታል። ቦታው ሳይለማና ከለማ በኋላ ምን እንደሚመስል መረጃ ማየት ይቻላል። ስለዚህ በወጣቶቹ ጥረት በከፍተኛ ደረጃ የተለወጠ ሥፍራ ነው። ከ2016 ዓ.ም ኅዳር 1 ጀምሮ ወደ ወረዳ 12 እስከተጠቃለሉበት ድረስ ሕጋዊና ተጠሪነታቸው ለወረዳው ሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ሆኖ ሲሠሩ መቆየታቸውን አስተባባሪው አስረድተዋል።
የወረዳ 12 የሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ፋይላቸው እንዳልተላከለት ገልጾ፤ ይህ እስካልሆነ ድረስ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አልቻልንም ብለዋልና ፋይል አልመጣም መባሉ ከምን የመነጨ ነው? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ፍቅሬ፤ የወረዳ 12 የሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት የሆነው አቶ መስፍን የወረዳ 04 ንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነበሩና በደንብ የሚያውቁት ጉዳይ ነው። እንደ ፋይል የምናነሳ ከሆነ ግን ፋይሉን የመውሰድ ሥራ የወረዳው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ያልተወሰደ ፋይል ብዙ ነው። ፋይል ለግለሰቦች ስለማይሰጥ ታሽጎ ቃለ ጉባኤ ተይዞ በደብዳቤ ርክክብ ይፈጻማል። ፋይል ስጡን ብሎ መጠየቅ የነበረበት ራሱ ወረዳ 12 ነው። በክፍለ ከተማ ደረጃ ፋይል ውሰዱ ብለን ጠይቀናል፤ እስካሁን ግን አልተወሰደም። ንግድ ፈቃድ ያላቸው እና ግብር የሚገብሩ አካላት ፋይላቸው እስካሁን አለመወሰዱን ገልጸዋል።
በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ምላሽ
በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ በለጠ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ጽሕፈት ቤት ይሠሩ በነበሩበት ወቅት በጀሀ ገላን የመኪና እጥበትና የአረንጓዴ ልማት በሚል የተደራጁ ወጣቶች ወደ እርሳቸው ቢሮ መጥተው እንደነበር በመጥቀስ፤ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የሚያደራጀው የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት ስለሆነ በወቅቱ ወደዚያ ሂዱ ብለናቸዋል። ከዚያም ምን እንደወሰዱ እውቅናው ባይኖረኝም የሥራ እድል የፈጠሩበት አካባቢ አሁን ወደነበረበት ደረጃ አድርሰውታል።
ከፍተኛ ቆሻሻ የሚጣልበት የነበረ ሥፍራ ሲሆን፣ ወጣቶቹ ተደራጅተው ቆሻሻውን በማጽዳት ከመኪና እጥበት ባሻገር አረንጓዴ በማድረግ የአካባቢው ማኅበረሰብ ጭምር የሚዝናናበት ቦታ አድርገውታል። አሁን ላይ የሚሠሩበት አካባቢ ወደ ወረዳ 12 የተካለለ ቢሆንም፤ ወጣቶቹ ግን በቦታው እየሠሩ ነው። እንደ ግለሰብ ቦታው ድረስ በመሄድ ጎብኝቼዋለሁ በርቱ ብያለሁ። ነገር ግን የአካባቢ ጥበቃና ከተማ ውበት ቦታውን ለአረንጓዴ ልማት መስጠትና አለመስጠቱን የማውቀው ነገር የለም ሲሉ አብራርተዋል።
አቶ ከበደ የሥራ ዕድል ፈጠራ ወጣቶችን በጊዜያዊነት እንዲደራጁ በተወሰነው ቦታ ላይ በኢ-መደበኛነት ሥራ ፈላጊዎች ይደራጃሉ። ካቢኔው በሚያውቀው መንገድ በጊዜያዊነት ለሁለት ዓመትም ይሁን ለአንድ ዓመት ወጣቶች ይደራጃሉ። ስለዚህ ካቢኔው ቦታው በማንኛውም ጊዜ ሲፈለግ ቦታውን ይለቃሉ። ለጊዜው ቆሻሻ እየተጣለበት ክፍት ሆኖ ከሚቀመጥ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሰፊ ስለሆነ በጊዜያዊነት ይጠቀሙ የሚል ሃሳብ ስለነበር ተደራጅተው እየሠሩበት ይገኛሉ። መሬቱን የመውሰድ ሥልጣን ያለው የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ስለሆነ ሲፈለግ መሬቱን ለሕጋዊ አካል ሲያስተላልፍና ሕጋዊ ሰነድ ይዘው ሲመጡ የማስለቀቅ ሥራ እንሠራለን። የአረንጓዴ ልማት ሥራ ላይ እየሠሩ እንዴት ይለቃሉ ለሚለው ግን ግንዛቤው እንደሌላቸው አስረድተዋል።
ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ እድል ሲፈጠርላቸው ለተወሰነ ዓመት መሆኑን ያብራሩት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ ይህ ሲሆን የተወሰነ ጥሪት ከያዙ በኋላ ወደሚቀጥለው ደረጃ እንደሚሸጋገሩ መመሪያው ይገልጻል። አረንጓዴ ልማት ግን ውበት ነውና የመሸጋገር ሁኔታቸው ጊዜ ደርሷል፤ አልደረሰም የሚለውን መመሪያውና ፖሊሲው የሚመልሰው ነው። ስለዚህ መንግሥት የተለያዩ ሥራ አጥ ወጣቶቸን እያደራጀ የሥራ እድል እየፈጠረ እያሸጋገረ ነውም ብለዋል።
ወጣቶቹ፣ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ቦታ የወንዝ ዳርቻ ነው። የወንዝ ዳርቻ ደግሞ ለአረንጓዴ ልማት ሥራ ይሆናል የሚል የግል አስተያየት እንዳላቸው የገለጹት አቶ ከበደ፤ ነገር ግን ቦታው ከዚህ ለተሻለ ልማት መንግሥት ከፈለገው ወጣቶቹ ተሸጋግረው የማይሠሩበት ምክንያት የለም። ለሌላ ልማት እንዲውል ከተፈቀደ በከተማ አስተዳደር ደረጃ ቦታው ተጠንቶ ለልማት የማዋል ሥልጣን አለው። ወረዳ ግን ይህን ቀይሩ፤ አድርጉ አታደርጉ የማለት ሥልጣን የለውም ብለዋል።
በፊት ቦታው ላይ ትንሽ ዛፎች ስለነበሩ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ወጣቶች የሚሰበሰቡበት አካባቢ ነበር። ስለዚህ ሥራ ከጀመሩ ወዲህ ከአዋኪ ነገሮች ጽዱ እንዲሆንና የአካባቢው ሰላም እንዲጠበቅ ሆኗል። አካባቢውንም ከቆሻሻ አጽድተውታል። ወረዳ 04 በነበሩበት ጊዜ ለወረዳው መልካም አስተዳደር መስፈን የመረጃ ምንጮቻችን በመሆን በሰላምና ጸጥታ አብረውን ይሠሩ ነበር። ስለዚህ ጠቅለል ሲል በልማትና በጸጥታው ዘርፍ ጥሩ እየሠሩ የነበሩ ወጣቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ከሚያገኙት ገቢ ቀንሰው እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ ለሚደረግ የድጋፍ ጥሪ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አቶ ከበደ ገልጸዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምላሽ
የምርመራ ቡድኑ፣ በሥራ ፈጠራ የተደራጁ ወጣቶች ላለፉት ዓመታት በሥራ ዕድል ፈጠራ በተሰጣቸው ቦታ ላይ ቋሚ ንብረት ለማፍራት የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ለፍሬ በደረሱበት ወቅት ምንም ጥሪት ሳያፈሩ መሬቱ በሌላ ልማት ለጨረታ መውጣቱ ዛሬን ሳይሆን ነገን እንጠቀማለን ብለው የለፉበትን ከንቱ ማስቀረት አይሆንም ወይ? የመሬት አጠቃቀሙ ምን ይላል ስንል ጉዳዩ የሚመለከተውን አነጋግረናል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በመሬት ልማትና አስተዳደር የመሬት ባንክና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ስዩም ደስታ እንደሚሉት፤ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ መሆኑ ይታወቃል። ከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው የሊዝ ጨረታዎችን ያወጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለ5ኛ ዙር ጨረታ ወጥቶ ከቅርብ ቀን በፊት ተጠናቋል። ጨረታው በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ የወጣ ነው። ለጨረታ ሲወጣ የሚጫረተውን አካል ቦታው ድረስ ባለሙያ ሄዶ ያስጎበኛል። ቅሬታ የተነሳበት ቦታም ሁለት ብሎክ ላይ ጨረታ በኮድ ቁጥር 241 እና በኮድ ቁጥር 242 ወጥቷል። የቦታ ስፋታቸው አንድ ሺህ 225 ካሬ ሜትር እና አንድ ሺ 309 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ቦታዎች ጨረታ ወጥተው ሰው ጎብኝቷቸዋል። ይሁንና እስካሁን ድረስ የጨረታ ቦታው አሸናፊ ይኑረው አይኑረው የማውቀው ነገር የለም።
የከተማው የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ግን እየገለጸ ስለሆነ አሸናፊውን ሊያውቀው ይችላል። ስለዚህ አሸናፊ ከመጣ ቦታውን እናስረክባለን። ጨረታ የወጣበት ቦታ መሬት ባንክ የገባ የመንግሥት መሬት ነው። ስለዚህ መሬት ባንክ የገባ መሬት ደግሞ መንግሥት ለተሻለ ልማት ያውላል። ቅሬታ አቅራቢዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አልነበራቸውም። የነበራቸው ጊዚያዊ የመጠቀሚያ ፈቃድ ነው። ለጊዚያዊ መጠቀሚያ የተሰጠው ቦታ ለተሻለ ልማት ሲፈለግ እንደሚነሱ ውል ገብተዋል።
ጊዚያዊ የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ወጣቶች በተሰጣቸው ቦታ ላይ ቋሚ ንብረት ለረጅም ጊዜ ለመጠቀም ያስችለናል ብለው እንዳያለሙ መሬቱ ላይ ለምን ቁጥጥር አልተደረገም? ወጣቶቹ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲያለሙ ቆይተው ፍሬ አፍርቶ የልፋታቸውን ውጤት ለመቅመስ ሲዘጋጁ የሊዝ ጨረታ ሲወጣባቸው ከፍተኛ ቅሬታና መደናገር ፈጥሮባቸዋልና ለምን እንዲህ ሆነ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ፣ አቶ ስዩም ሲመልሱ እንዳስረዱት፤ ጨረታ የሚወጣው በፕላን መሠረት ነው። የቦታው ፕላን የሚያሳየው ቅይጥ የመሬት አጠቃቀም ነው። ይህ ማለት መኖሪያና ንግድ ነው። ስለዚህ ቦታው ቅይጥ ከሆነ የአካባቢው ፕላን በሚፈቅደው አሠራር መሠረት ቦታውን አልሚው ያለመዋል ማለት ነው።
አረንጓዴ ቦታዎች የታወቁ ናቸው። ፕላንና ካርታ አላቸው። ስለዚህ ቦታው ለአረንጓዴ የተተከለ ቢሆን ኖሮ መንግሥትም አይነካውም ጨረታም አይወጣበትም ነበር። ዛፍ በየቦታው ሊተከል ይችላል፤ ይሁንና ፕላኑ ግን ለአረንጓዴ የተከለለ ቦታ አይደለም። የአረንጓዴ ቦታዎችን የሚወስነው የአዲስ አበባ ፕላን ኮሚሽን ቢሮ ነው። ሲወሰን የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ካርታ ይወስዳል። በአረንጓዴ የተከለለ ቦታ ከሆነ ካርታ ስለሚወጣበት ማንም እንደማይነካው አስረድተዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ሁልጊዜም የሚሠራ ሥራ ነው ያሉት አቶ ስዩም፤ በፊት ሥራ ያልነበራቸው ሰዎች ሥራ እድል ተፈጥሮላቸው ቦታው ላይ ሥራ እየሠሩ ነበር። ስለዚህ ቦታው ለተሻለ ልማት ስለዋለ ነገ ወደ ሥራ አጥነት ይሄዳሉ ማለት አይደለም። በሌላ ቦታ የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል። ስለዚህ ዛሬ ቦታው ለጨረታ ስለወጣ ነገ ወጣቶችን ዜጋ አይደላችሁም፤ የሥራ ዕድል ፈጠራው እዚህ ላይ ተቋርጧል የሚል ሃሳብ የለም። የሥራ ዕድል ፈጠራ የቆመ ነገር አይደለም። ሥራ ያልነበራቸውን ወደ ሥራ እያመጣ ያለ ተቋም ሥራ የነበረውን ሰው አፈናቅሎ ወደ ሥራአጥነት አይመልስም። ስለዚህ ይሠሩበት ወደ ነበረው ሥራ መመለሳቸው እንደማይቀር ቡድን መሪው ገልጸዋል።
የሰነድ ማስረጃ
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበትና እና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል። ምላሹም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቁጥር-Tረ1/2/9931 በቀን መጋቢት 22/2017 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ መሠረት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበትና እና አረንጓዴ ልማት ጽ/ቤት ምላሹን በደብዳቤ ቁጥር አቃ/ቃ/የከተ/ው/እ/ለ/ጽ/ቤት,3312 በቀን 08/08/ 2017 ዓ. ም ሰጥቷል።
እንደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽ/ቤት ምንም ዓይነት ውል ያልሰጠ መሆኑን አሳውቋል። ነገር ግን ደብዳቤውን መነሻ በማድረግ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፕላንና ልማት ጽ/ቤት በሰጠነው ኮርድኔት መሠረት ቦታው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመዋቅራዊ ፕላን የመሬት አጠቃቀም መረጃ መሠረት በአነስተኛ ጥግግት ቅይጥ መኖሪያ ምድብ ውስጥ የሚገኝ ነው። በዚህም የመሬት አጠቃቀም ምድብ ውስጥ ለመኖሪያ የሚሆን ግንባታዎች፣ ከ2000 ካ.ሜ በታች የሆኑ የማምረቻ ማከማቻ ተቋማትን ጨምሮ አረንጓዴ ቦታዎችን የሚፈቅድ መሆኑን ከፕላን አንጻር መረጃ ያገኘ መሆኑን በሚያስረዳ ደብዳቤ ገልጸዋል።
የጋዜጠኞች ትዝብት
የምርመራ ዘገባ ቡድኑ፣ የወጣቶችን ቅሬታ ባጤነበት ጊዜ የተረዳው የሥራ እድል ፈጥረው እየሠሩበት ያለው ሥፍራ በጊዚያዊነት ሆኖ ውሉ ግን የሚታደስ ነው። ይሁንና ወረዳውም ሆነ ክፍለ ከተማው ዘላቂ የሚሆን አትክልትና ፍራፍሬ ተክለው ሲያለሙ በዝምታ አልፎ አሁን ላይ የድካማቸውን ፍሬ ሳያገኙ ቦታው በሊዝ መሸጡ በወጣቶቹም ሆነ በአካባቢው ማኅበረሰብ ቅሬታን አጭሯል። በተጨማሪም በሚመለከታቸው የወረዳውና የክፍለ ከተማው አመራሮች ክትትልና ድጋፍ አለመደረጉና ቦታው ለልማት እንደሚፈለግ ለወጣቶች ግንዛቤ አለመሰጠቱ ለወጣቶቹ ቅሬታው አንዱ ምንጭ ሆኗል።
ለአካባቢው ነዋሪ፣ ለማለፍ እንኳን የሚከብድ ቦታን ስላጸዱትና በጥረታቸው ስላለሙት፣ ለልጆቻቸው እንደ መዝናኛ እያገለገለ ነው፤ በመሆኑም ለልማት መፈለጉ ከፍተኛ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተገንዝቧል። የወጣቶቹን ለበጎ ተግባር ተሳታፊ መሆናቸውንም ተረድቷል።
በምርመራ ቡድን ሪፖርተሮች
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም