“በሕይወት በሌለች እናታችን ስም የፍርድ ውሳኔ በማሰጠት ቤታችን ሊነጥቁን ነው” -አርቲስት ምናሉሽ ረታ

አመልካች ወይዘሮ ፋንታዬ ባዩ ወልደየስ ተጠሪዎች ከወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ እና ሻምበል ታረቀኝ ገ/ሕይወት እና ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ከተማ የቤት ቁጥር 198 ከሆነ ቤት ጋር ተያይዞ የተፈጠረን ውዝግብ ያስመለክተናል።

« እናታችን ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በ1988 ዓ.ም ሕጋዊ አካሄድን ተከልሎ የወይዘሮ ሣህለወርቅ ባዩ ሕጋዊ ወራሽ ከሆኑት ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ እና ሻምበል ታረቀኝ ገ/ሕይወት ከተባሉ ሰዎች የውርስ ቤት ገዝታ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1996 ዓ.ም ወይዘሮ ጤናዬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ይህን ተከትሎ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በ1988 ዓ.ም ገዝታው የነበረው ቤት ለአምስት ልጆቿ በውረስ ተላለፈ። ይሁን እንጂ በ2007 ዓ.ም የእኛ ነው ባይ ሰዎች መጡ። የእኛ ነው ባዮች እናታችን በሕይወት እንደሌለች እያወቁ እናታችንን በመክሰስ ፍርድ ቤት መቅረብ ባለመቻላቸው በሌሉበት አስፈርደናል በሚል የፍርድ ቤት ውሳኔ ያዙ። በውሳኔው መሰረትም በውርስ ያገኘውን ቤት እንወስዳለን አሉ። ይህን ተከትሎ የወይዘሮ ጤናዬ ወራሾች ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት ወስደን ብንከራከርም ቤቱን ለከሳሽ እንዲሰጥ የሚል ውሳኔ ተወሰነ ። ይህ ትክክል አይደለም ብለን ብንከራከርም ሰሚ አጥተናል። የተፈጸመብን በደል የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቶ ፍረደን›› ስትል አርቲስት ምናሉሽ ረታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደርና የምርመራ ቡድን አቤት ብላለች።

የኢትዮጵ ሕዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ እንዲችል የዝግጅት ክፍላችን በጉዳዩ ላይ ጥልቀት ያለው ምርመራ አድርጓል። ያገኘውን የምርመራ ውጤት በሁለት ክፍሎች ሸክፎታል። የመጀመሪያውን ክፍል እንዲህ አቅርቦታል። መልካም ንባብ ።

ከቅሬታ አቅራቢዋ አንደበት

በደል ተፈጽሞብናል ስትል ለዝግጅት ክፍላችን አቤት ያለችው አርቲስት ምናሉሽ ረታ ትባላላች። እንደ አርቲስት ምናሉሽ ገለጻ፤ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በ1988 ዓ.ም ሕጋዊ ወራሽ ከሆኑት ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ እና ሻምበል ታረቀኝ ገብረ ሕይወት ቡራዩ ከተማ ገፈርሳ ቀበሌ የቤት ቁጥር 198 ቤት የተመዘገበ 324 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቤት ገዝታ በሕይወት እስከተለየችበት እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ በስሟ በሕጋዊ መንገድ አስመዝግባ ስትገለገልበት ቆይታለች። ወይዘሮ ጤናዬ በ1996 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ ልጆቿ ማለትም አርቲስት ምናሉሽ ረታ፤ አቶ አሸናፊ ረታ፤ አቶ አለማየሁ ረታ፤ ወይዘሮ ሕይወት ረታና አቶ ኤርሚያስ ረታ በሕጋዊ መንገድ በፍርድ ቤት በማሳወጅ አሁን ውዝግብ የተነሳበትን ቤት ወረሱ። በእናታቸው ስም የንግድ ቤት በመክፈት መስራት ጀመሩ። ወራሾች በስራ መደራረብ ምክንያት የንግድ ስራቸውን ማከናወን ባለመቻላቸው ቤቱን በሕጋዊ ውል ለሌላ ነጋዴ በማከራየት ሲጠቀሙበት መቆየታቸውን ታስረዳለች።

ነገር ግን ሕጉን ተከትለን ወራሽነት አሳውጀን የተረከብውን ንብረት እነ ፋንታየ ባዩ የተባሉ ሰዎች በሕይወት የሌለች እናታቸውን በሕይወት እንዳለች በማስመሰል እና በፍርድ ቤት በመክሰስ እንዲሁም እናታቸው በሕይወት ኖረው ነገር ግን ፍርድ ቤት ለመቅረብ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ በማስመሰል የፍርድ ቤት ውሳኔ አስወሰኑ። ውሳኔውን መሰረት በማድረግ ቤቱን እንዲያስረክቧቸው የውሳኔ አፈጻጸም ማምጣታቸውን አቤቱታ አቅራቢዋ ታስረዳለች።

የአቤቱታ አቅራቢዋ ወላጅ እናት ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በህጋዊ መንገድ አሳውጃ እና ወርሳ ስትጠቀምበት ከነበረች ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ ግለሰብ በመግዛት ከቡራዩ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ጽህፈት ቤት ሕጋዊ ሰነድ ተሰጥቷቸዋል። የአፈር እና የቤት ግብር እየገበሩ ሲጠቀሙበት መኖራቸውን የሰነድ እና የሰው ምስክር እንዳላት ትግልጻለች።

እንደ አርቲስት ምናሉሽ ገለጻ፤ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በ1988 ዓ.ም የገዙትን ቤት በስማቸው ከአዞሩ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ አብነት ተብሎ ከሚጠራው ሰፈር የነበራቸውን ቤት በመሸጥ ቡራዩ ከተማ በገዙት ቦታ ላይ ቤት ወቅቱን በሚመጥን መልኩ በድንጋይና መሰል ቁሳቁሶች በማነጽ የሆቴል ንግድ ስራ እየሰሩበት እንደቆዩ ታስረዳለች።

ክሱ ከመቅረቡ በፊት ከሙዚቃ ስራ ጋር በተያያዘ ቡራዩ ከሚገኘው የእናቷ ቤት ወጥታ እንደነበር የገለጸችው አርቲስት ምናሉሽ፤ በቤቱ ወንድሞቿ፤ አንድ እህቷ እና እናታቸው ሲኖሩበትና የንግድ ስራ ሲሰሩበት እንደነበሩ ታስረዳለች።

‹‹ኑሮ ኑሮ ከሞት ዞሮ ዞሮ ከቤት›› ያለችው አርቲስት ምናሉሽ በ1996 ዓ.ም እናታቸው ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ትናገራለች። ከ1996 እስከ 2000 ዓ.ም ወንድሞቿ እየተቀያየሩ ቤቱን ያስተዳድሩት ጀመር። ይሁን እንጂ የንግድ ቤቱ በእናታቸው ስም ጤናዬ በዳሶ መታሰቢያ ተብሎ ይሰራ እንደበር ታስረዳለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2000 ዓ.ም እስካሁን በሕይወት በሌሉት በናታችሁ ስም ግብር ስትገብሩ ቆይታችኋል። ይህ አሰራር ትክክል ስላልሆነ ንግድ ፈቃዱን በስማችሁ አዙሩ የሚል አስገዳጅ ትዛዝ ከንግድ ቢሮ መጣ ። ይህን ተከትሎ የወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ወራሽ ልጆች በራሳቸው ስም ንግድ ፈቃድ ለማውጣት ተንቀሳቀሱ። በወቅቱ ንግድ ፈቃድ የሚሰጠውና ፈቃድ የሚያዞረው አምቦ ከተማ ስለነበር እናታቸው መሞታቸውን በማሳወጅ የንግድ ፈቃዱን ስም ቀየሩ። ይሁን እንጂ የአቤቱታ አቅራቢዋ ወንድሞች በቤቱ የነበራቸውን የንግድ ስራ አቋረጡ። 2006 ዓ.ም በቡራዩ ከተማ ፍርድ ቤት በሕጋዊ መንገድ የንግድ ቤቱን ሌላ ሰው አከራዩ። ከንግድ ቤቱ በጀርባ ያለውን ቤት ደግሞ አንድ ወንድማቸው ብቻ ለመኖሪያነት ይጠቀምብት እንደነበር ትናገራለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ 2007 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ ቤቱ የእኛ ነው ፤ ልቀቁ የሚሉ ሰዎች የፍርድ ቤት ውሳኔ ይዘው መጡ የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዋ ጉዳዩን ለማጣራት ሞክረው በወቅቱ በሕይወት በሌሉ እናታቸው ላይ ፍርድ ማረፉን እንደተመለከቱ ይናገራሉ።

አቤቱታ አቅራቢዋ እንደገለጸችው፤ የፍትህ ጉድለት መፈጠር የጀመረው ምንም አይነት መጥሪያ በሌለበት እና በሕይወት የሌለችውን እናታቸው በሕይወት እንዳለች አድርጎ በመክሰስ ከሳሾች ፍትህ ለማግኘት የሄዱበት ርቀትና ፍርድ ቤቶችም ብይን የሰጡበት አግባብ ነው።

“ፍርድ ቤት ተከሳሽ ባልቀረበቡት እና በሕይወት በሌሉ ተከሳሽ ላይ እንዴት ውሳኔ ሊሰጥ ቻለ?” ስትል አቤቱታ አቅራቢዋ ትጠይቃለች። በሕይወት በሌለ ሰው ላይ የተሰጠን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማሳረፉ ተገቢነው ብላ እንደማታምን ገልጻ፤ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት የሟችን ሕጋዊ ወራሾች ጠርቶ ማከራከር እንደነበረበት ትገልጻለች።

“መጥሪያ ሳይሰጥ ውርስ ሳይጣራ ሙት ይከሰሳል? ቤቱን የሸጠችው ሴትዮ ሕጋዊ ወራሽነቷን በምን አይነት መንገድ ነው ያስነሱት? ስትሸጥ ደግሞ ከባሏ ጋር ሆና ነው የሸጠችው። ባሏም ተከሳሽ ሆኖ ነው የቀረበው። በሏ ደግሞ ሞቷል። እሱም አልቀረበም። እንዴት ነው ሙት የሚከሰሰው? እኛ ተከሰን ወራሽነታችን ላይ ተከራክረናል ወይ? የወይዘሮ ጤናዬ ወራሾች አምስት ነን አንዳችን ቀርበን ነበር ወይ?” ስትል አቤቱታ አቅራቢዋ ትናጋራለች።

ዘግይተውም ቢሆን በሟች እናታቸው ላይ ብይን መሰጠቱትን ሰሙ ሕጋዊ ወራሽ ልጆች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱት። ፍርድ ቤትም በሟች ላይ ያስፈረዱትን ወይዘሮ ፋንታዬ ባየ እና ሕጋዊ ወራሾችን አከራከረ። በሟች ላይ ያስፈረዱትን እነ ወይዘሮ ፋንታየ ባዩን “ቤቱ የእናንተ ስለመሆኑ ፍርድ ቤት ወስኗል። ፍርድ ቤቱ የእናንተ ስለመሆኑ ለመወሰን የሄደባቸው ሂደቶችን የሚያሳዩ ሰነዶችን አቅርቡ?” ተብለው ተጠየቁ። ነገር ግን እነ ወይዘሮ ፋንታየ ባዩ “እኛ ሂደቱን የሚያሳይ ሰንድ የለንም። ያለን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ብቻ ነው” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን አርቲስት ምናሉሽ ትናገራለች። ይህን ተከትሎ አርቲስት ምናሉሽም ከሳሽ ወይዘሮ ፋንታየ ከፍርድ ቤቱ ውሳኔው ባሻገር ቤቱ የእነሱ ስለመሆኑ በፍርድ ቤት ጉዳዩ የታየበትን ሂደት እርቀት የሚያሳዩ ሰነዶች ማቅረብ ነበረባት። ነገር ግን የፍርድ ሂደቱን ባልቀረቡበት አግባብ እንዲከራከሩ ፍርድ ቤት መፍቀዱ በእራሱ ትክክል አለመሆኑን ታስረዳለች።

ከሳሽ ወይዘሮ ፋንታየ በውሳኔው መሰረት ቤቱን ሊረከቡ በመጡበት ወቅት አንድ ወንድማቸው ብቻውን በቤቱ ይኖር እንደነበር ያስታወሱት አቤቱታ አቅራቢዋ፤ የንግድ በቱን በፍርድ ቤት ያከራዩት የወይዘሮ ጤናዬ ሕጋዊ ወራሾች እያሉ ነጋዴው ወይዘሮ ፋንታየ የፍርድ ቤት ውሳኔ ይዘው ሲመጡ በመፍራት በሰፈር ውል ኪራይ መዋዋሉን እና ለኪራዩም ከገንዘብ ሰጥቶ እንደነበር ታስረዳለች። ይህን ተከትሎ የወይዘሮ ጤናየ ህጋዊ ወራሾች እነ ወይዘሮ ፋንታየን ከሰሱ። ፍርድ ቤቱም እነ ወይዘሮ ፋንታየን ኪራይ መቀበል እንደማይችሉ ውሳኔ አሳረፈ።

ቤቱ የእኛ ነው ባይ ሰዎች መምጣታቸውን ተከትሎ አርቲስት ምናሉሽ እና ቤተሰቦቿ ጠበቃ ቀጥረው ክርክር ጀመሩ። ጉዳዩ እስከ ሰበር ደረሰ። ጉዳዩ ሰበር ላይ እያለ ከሳሽ ወይዘሮ ፋንታየ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች ። ከሳሽ ስትሞት ቤተሰቦቿ እናታቸውን ወክለው ተከራከሩ። ሰበር ላይ ችሎቱ በጉዳዩ የሕግ ግድፈት አይቼበታለሁ አጣሩና ዝጉ አለ። ጉዳዩ በድጋሚ እንዲጣራ ተደረገ። በተደረገው ማጣራት ቤቱ የወይዘሮ ጤናዬ ወራሾች ስለመሆኑ ውሳኔ ተሰጠበት። ለውሳኔ ወይዘሮ ፋንታየ ቤተሰቦች እንዲቀርቡ ታዘዙ። እንዲቀርቡ በየሰፈራቸው መጥሪያ ተለጠፈ። የሚቀርብ ሲጠፋ ሁለት ጊዜ በጋዜጣ ታወጀ። ነገር ግን ችሎት የሚመጣ ጠፋ።

ውሳኔ አግኝቶ ፋይሉ ከተዘጋ በኋላ ቤቱ የነበረበት ቦታ በመንገድ ምክንያት ሲፈርስ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገዳማ የካሳ ክፍያ ለሕጋዊ ወራሾች ተከፋፍሎ ተሰጣቸው። ከካሳ ክፍያው በተጨማሪ ካርታ ያለው መሬት በስማቸው ተሰጡ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በክርክር ተረተው በጋዜጣ ጭምር ሲፈለጉ የነበሩ የወይዘሮ ፋንታየ ቤተሰቦች “መሬቱ የተሰጠን ለእኛ ነው። ገንዘቡ መሰጠት ያለበት ለእኛ ነው፡፡” የሚል ክስ ይዘው መጡ። ይህን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ስለጉዳዩ ሳያጣራ የክርክር መዝገብ ቁጥሩን እንዲቀይሩ አዘዘ። ቁጥሩ ከተቀየረ በኋላ ጉዳዩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሄደ። ይህን የወይዘሮ ጤናዬ ወራሾች ለምንድነው ቁጥሩን የሚቀየረው? ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀው እንደነበር ታስረዳለች ።

የፋይል ቁጥሩ ከተቀየረ በኋላ የፍርድ ሂደቱ በሙሉ መልኩን ቀየረ የምትለው አርቲስት ምናሉሽ ፤ ፍርድ ቤቱ በካሳ የወሰዳችሁትን ገንዘብ መልሱ፤ የወንድሞችሽ የወሰዱትን ገንዘብ የምታመጭው አንችው ነሽ የሚል ውሳኔ እንደተላለፈባት ታስረዳለች።

“570 ሺ ብር አካባቢ በእያንዳንዳችን የባንክ ሂሳብ ቁጥር የካሳ ብር ገብቷል። በእናቴ ድርሻ መጠየቅ ካለብኝም መጠየቅ የሚገባኝ የደረሰኝን ገንዘብ እንጂ የሁሉን ድርሻ ክፈይ መባሉ ፍትሐዊ አይደለም” ስትል መጠየቋን ነገር ግን ሰሚ አለማግኘቷን አቤቱታ አቅራቢዋ ታስረዳለች።

የሰነድ ማስረጃዎች

ሰነድ አንድ፡- ይህ ሰነድ የወልመራ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያመላከት ነው። የወልመራ ፍርድ ቤት አመልካች ወይዘሮ ሕይወት ረታ፤ አቶ አሸናፊ ረታ፤ አቶ አለማየሁ ረታ፤ ወይዘሮ ምናሉሽ ረታ እና አቶ ኤርሚያስ ረታ እናታቸው ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በቀን 06/02/1996 ዓ.ም ማረፋቸውና በቀን 07/02/1996 ቀብራቸው መፈጸሙን በማስረጃ ተጠርቶ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ለወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት በማመልከቻ ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም አስፈላጊውን የሰውና ሌሎች ማስረጃዎችን ካጣራ በኋላ በዳኛ ታደሰ በየነ አማካኝነት አመልካቾች የወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ሕጋዊ ወራሽ መሆናቸው በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 842 (1) ጠቅሶ ውሳኔ አሳልፏል። ይህን ውሳኔ ተከትሎ ሕጋዊ ወራሾች በወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በሕጋዊ ሰነድ ተመዝግቦ የሚገኘውን ቤት ወርሰው ሲጠቀሙ ከ20 ዓመታት በላይ መሆኑን በሰነዱ ተመላክቷል።

ሰነድ ሁለት፡- ስለከተማ ቦታ አሰራርና አጠቃቀም በወጣው አዋጅ ቁጥር 292/78 አንቀጽ 9 መሰረት መጠኑ በግልጽ ተለይቶ ለወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በይዞታ እንዲጠቀሙበት መሰጠቱን በቁጥር ቡ/ል/28/88 መገለጹን እና ካርታ መሰጠታቸውን ሰነድ ያሳያል። በተጨማሪም የኦሮሚያ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ‹‹ የኪራይ መሬት የይዞታ የምስክር ወረቀት በሚል የወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ የዓምስቱ ልጆች ፎቶ ያለበት 324 ካሬ ሜትር ቦታ የተረከቡበት ሰነድ መኖሩ ያሳያል።

ሰነድ ሶስት፡- በቀን 02/ 03/1989 ዓ.ም የተጻፈ የድርጅት ቤት ሽያጭ ውል ስምምነት እንደሚያሳየው ውል ተቀባይ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ከውል ሰጭዎች ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለና ከሻምበል ታረቀኝ ገብረ ሕይወት በኦሮሚያ ክልል ወልመራ ወረዳ ልዩ ቀበሌ ገፈርሳ ቡራዩ ውስጥ የሚገኝ የቤት ቁጥር 198 የቦታ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ቢዩአር 28/88 በሆነው የተመዘገበ እና የቦታው ስፋት 324 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤትን በ35 ሺ ብር ለውል ተቀባይ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ መሸጡንና የቤቱን ሰነድ ለውል ተቀባይ ማስረከባቸውን ሰነዱ ያትታል።

በሰነዱ ላይ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ የሕግ ባለሙያዎች እና የውልና ማስረጃ ምዝገባ መምሪያ ቁጥር ደብሊውኤ/1989/77 በጽህፈት ቤቱ ቀርውበው መፈራረማቸውና የሕግ ባለሙያዎች መምሪያ የውልና ማስረጃ ምዝገባ ኃላፊ በቀን 24/6/1989 ዓ.ም ዲሳሳ ድሪብሳ በፊርማቸው ያረጋገጡበት ማስረጃ ያሳያል፡፡

ሰነድ አራት፡- ይህ ሰነድ ወይዘሮ ፋንታዬ የሀሰት ሰነድ ብለው ካቀረቡት የሰነድ ማስረጃ መካከል አንዱ ነው። ከሳሽ በጠበቃቸው አማካኝነት ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ጳውሎስ ምድብ ፍታብሔር ችሎት በቀን መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ እንደሚያስረዳው አመልካች ወይዘሮ ፋንታዬ ባዩ ወልደየስ ተጠሪዎች ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ፤ ሻምበል ታረቀኝ ገብረ ሕይወት እና ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ወራሽ አቶ አሸናፊ ረታ አቤቱታው በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9 መሠረት ተሻሽሎ የቀረበ እና የሶስተኛ ተጠሪ ወራሽ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ከኛ እና ከ2ኛ ተጠሪዎች ጋር ሻጭና ገዥ ሆነው በሕዳር 2 ቀን 1989 ዓ.ም ያደረጉት የቤት ሽያጭ ውል ፈርሶ ውሉ ቀሪ እንዲሆን አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

የአመልካች እህት የነበሩት ወይዘሮ ሣህለወርቅ ባዩ በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ አጠራር ወረዳ በ8 ቀበሌ 02 በአሁኑ አጠራር ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15/16 የቤት ቁጥር 068 ውስጥ ሲኖሩ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት መጋቢት 27 ቀን 1987 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ በመጠቆም የአመልካች የሟች እህቴ የወይዘሮ ሣህለወርቅ ባዩ ወራሽ መሆኔን በፍርድ ቤት አረጋግጨ የሟች እህቴን የውርስ ሀብት ለመያዝ ስሞክር ሟች አቶ ግዛቸው በቀለ እና አንደኛ ተጠሪ ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ ሚያዚያ 18 ቀን 1987 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ ለፍርድ ቤት አቅርበው ሟች ወይዘሮ ሣህለወርቅ ባዩ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ጥር 14 ቀን 1986 ዓ.ም በተፃፈ የስጦታ ውል ሰነድ አማካኝነት ንብረታቸውን ሰጥተውኛል የስጦታ ውሉ ፀድቆ ማስረጃ ይሰጠኝ በማለት የሐሰት ሰነድ ለፍርድ ቤቱ አቅርበው ባሰጡት ውሣኔ የሟች አውራሽ እህቴን ንብረት በመሉ ይዘው ሊያስረክበኝ ፈቃደኛ አልነበሩም የሚል አቤቱታ ቀርቧል፡፡

አቶ ግዛቸው በቀለ እና አንደኛ ተጠሪ ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ ለፍርድ ቤት አቅርበው ያፀደቁት የስጦታ ውል በሐሰት የተዘጋጀ ሰነድ እንጂ ሟች ወይዘሮ ሣህለወርቅ ባዩ የፈረሙበት የስጦታ ሰነድ አይደለም የሚል መቃወሚያ አመልካች ፍርድ ቤት አቅርቤ ክርክሩ ሲታይ ቆይቶ ሐምሌ 2 ቀን 2002 ዓ.ም በዋለው ችሎት የስጦታ ውል ተብሎ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ሰነድ ሟች ወይዘሮ ሣህለወርቅ ባዩ ያስፈረሙበት የሀሰት ሆነ በፎረንሲክ ምርመራ ስለተረጋገጠ ፍርድ ቤቱ ሰጥቶት የነበረው የስጦታ ሰነድ የማጽደቅ ውሣኔ ቀሪ አድርጓል። በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

አንደኛ ተጠሪ የሐሰት ሰነድ ለፍርድ ቤት አቅርበው በማፀደቅ በተሰጠው ውሣኔው አማካኝነት በቡራዮ ከተማ የሚገኘውን የቤት ቁጥር 198 የሆነውን ቤት በይዞታቸው ስር አድርገው ስለነበር ቤቱን እንዳይሸጡ እንዳይለውጡ በፍርድ ቤት እግድ ትእዛዝ ተሰጥቶበት ከክርክር ላይ እያለ አንደኛ እና ሁለተኛ ተጠሪዎች ምንም ሕጋዊ መብት ሣይኖራቸው ከላይ ቁጥሩ የተጠቀሰውን ቤት ለሦስተኛ ተጠሪ አውራሽ ለወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ለመሸጥ ተስማምተው ሕዳር 2 ቀን 1989 ዓ.ም በተፃፈ የሽያጭ ውል ሰነድ አማካኝነት ተዋውለው ለሶስተኛ ተጠሪ አውራሽ ለወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ማስተላለፋቸውን ከክፍለ ከተማው ማዘጋጃ ቤት ማወቅ እንደቻሉ አመልካች ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍትሐብሔር ችሎት እንደጠየቁ ያሳያል፡፡

1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የሽያጭ ውሉ የተዋዋለበት ንብረት ባለሀብት አለመሆናቸውን እያወቁ የሦስተኛ ተጠሪ አወውራሽ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ በንብረቱ ላይ መቃወሚያ ቀርቦ ጉዳዩ በፍርድ ቤት በክርክር ላይ መሆኑን እና ቤቱ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ የእግድ ትእዛዝ የተሰጠበት መሆኑን እያወቁ የግዥ ውል ተዋውለው ቤቱን ተረክበዋል። ይህም ውል ከሕግ ውጭ የተደረገ ውል ከመሆኑም በላይ የአመልካችን የወራሽነት መብት የሚጋፋና የንብረት ባለቤትነት መብት የሚያሳጣ ውል ስለሆነ ሊፈርስ ይገባዋል፡፡

ስለዚህ የሦስተኛ ተጠሪ አውራሽ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ከ1ኛ እና ከ2ኛ ተጠሪዎች ከሕግ አግባብ ውጭ በቡራዩ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የቤት ቁጥር 198 በሆነው ቤት ላይ ሕዳር 2 ቀን 1989 ዓ.ም የተዋዋሉት ውል እንዲፈርስ ሲሉ አመልካች ማቅረባቸው ያሳያል፡፡

በተመሳሳይ ቀን አመልካች ወይዘሮ ፋንታዬ ባዩ ወልደየስ በቀን መጋቢት 12 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጳውሎስ ምድብ ፍታብሔር ችሎት 1ኛ ተጠሪዎች ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ፤ ሻምበል ታረቀኝ ገብረ ሕይወት፤ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ወራሽ አቶ አሸናፊ ረታ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 223 መሠረት በቀረበ የማስረጃ ዝርዝር መግለጫ፣ አመልካች በ12/07/2005 ዓ.ም በተፃፈ አቤቱታ አሻሻልኩት ብለው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ በሐምሌ 12 ቀን 2003 ዓ.ም ጽፌ ባቀረብኩት የክስ አቤቱታ ያቀረብኩት የማስረጃ ዝርዝር መግለጫ አሁን ተሻሽሎ ላቀረበው ክስ ማስረጃዬ ስለሆነ ቀድሞ የቀረበው ማስረጃ ለተሻሻለውም ክስ በማስረጃነት እንዲመዘገብልኝ ብለው ማቅረባቸውን ያስረዳል፡፡

ሰነድ አምስት፡- ይህ ሰነድ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ የያዘ ነው። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቀን 20/05/2007 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 34211 በዳኛ አመሃ ታደሰ ከሳሽ ወይዘሮ ፋንታዬ ባዩ በጠበቃቸው አሰልፈው ገብረ መስቀል አንደኛ ወይዘሮ ተስፋነሽ በቀለ፤ ሁለተኛ ተከሳሽ ሻምበል ታረቀኝ ገብረህይወትና ሶስተኛ ተከሳሽ በሕይወት የሌሉት ወይዘሮ ጤና በዳሶ የቀረበ ክስ ላይ የሰጠው ፍርድ በቡራዩ ከተማ የቤት ቁጥር 198 የሆነው ቤት አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች መብት ሳይኖራቸው ለሶስተኛ ተከሳሽ በሽያጭ ማስተላለፋቸው ተከትሎ ውሉ እንዲፈርስ ዳኝነት መጠየቃቸው የሚገልጽ ሲሆን ውሳኔው ቤቱ ሙሉ ይዞታ ለከሳሽ ከሟች ሳህለወርቅ ባዩ በውርስ የተላፈ በመሆኑ ከሳሽ ሕጋዊ ባለመብት ናቸው። 3ኛ ተከሳሽ ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሰሶች ኅዳር 02/03/1989 ዓ.ም ያቋቋሙት ቡራዩ ከተማ አስተዳደር የቤት ቁጥር 198 ላይ ውል ፈርመዋል። ስለሆነም ውሉ በመፍረሱ ከሳሽ ሙሉ በሙሉ ይዞታው ከወይዘሮ ጤናዬ ይረከቡ የሚል ውሳኔ መወሰኑን ያመላክታል።

ሰነድ ስድስት ፡- የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀን ሰኔ 30/ 2009 ዓ.ም በቁጥር የሰ/መ/ቁ.13975 በዳኛ ጸጋይ አስማማው፤ ሙስጠፋ አህመድ፤ አብርሃ መሰለ፤ ጳውሎስ ኦርሺሶ እና ሰናይት አድነው በተሰየመ ችሎት እነ ወይዘሮ ምናሉሽ በወከሉት ጠበቃ ምትኩ አልማው አማካኝት ቀርበው ወይዘሮ ፋንታዬ ባዩ በሌሉበት፤ ሻምበል ታረቀኝ ገብረ ህይወት በሌሉበት የሟች ወይዘሮ ጤናዬ በዳሶ ወራሽ አቶ አሸናፊ ረታ በሰበር ችሎት ቀርበው ችሎቱ መዝገቡን መርምሮ የሰጠው ፍርድ እንደሚያስረዳው ቀድም ሲል በመ/ቁ.34/211 በቀን 20/05/2007 ዓም የተሰጠውን ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሀ/ቁ. 358 መሰረት በመቃወም ያቀረቡትን አቤቱታ የስር ፍርድ ቤቶች መቃወሚያው ውሳኔው ከተፈፀመ በኋላ የቀረበ ነው በማለት በብይን ውድቅ ማድረጋቸውን ያሳያል። በሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ሲሆን አመልካቾች ሐምሌ 23 ቀን 2008 ዓ.ም በፃፉት አቤቱታ በስር ፍርድ ቤቶች ብይን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡

የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ አመልካቾች በስር በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358 ላቀረቡት አቤቱታ ንብረቱ በአመልካቾች እጅ እያለና ፍርድ ሳይፈፀም እንደተፈፀመ ተደርጎ በአግባቡም ሳይጣራ በተፈፀመ ፍርድ መቃወሚያ ሊያቀርቡ አይችሉም ተብሎ አቤቱታቸው ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ለመመርመር ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡበት በታዘዘው መሰረት 2ኛ እና 4ኛ ተጠሪዎች መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈ የየራሳቸው መልስ ማቅረባቸውን ሰነዱ ያሳያል፡፡

1ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ መሆናቸው በመገለጹ ወራሾች እንዲቀርቡ በጋዜጣና በመኖሪያ አድራሻቸው ጥሪ ቢደረግም ያልቀረቡ ስለሆነ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል። አመልካቾች 2ኛ እና 4ኛ ተጠሪዎች የሰጡት መልስ ላይ የመልስ መልስ የአመልካቾች ጠበቃ አልሰጥበትም በማለታቸው የቀረበ የመልስ መልስ የለም። የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር ችሎቱ መርምሯል። በምርመራው መቃወሚያ የቀረበበት ፍርዱ ከተፈፀመ በኋላ የቀረበ ነው በማለት የስር ፍርድ ቤቶች የአመልካቾችን መቃወሚያ አቤቱታ ውድቅ ያደረጉት በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ችሎቱ ይዞ ውሳኔ አሳልፏል።

ውሳኔው በመጀመሪያ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 34211 ግንቦት 2008 ዓ.ም የተሰጥቶ በፌደራል ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 180089 ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም በትዕዛዝ ብይን በፍ/ብ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት መሻሩንና የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ለክርክር መነሻ የሆነው ቤት በውሳኔው መሰረት ወደ 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪ የተላለፈ መሆኑን አለመሆኑን በተጨባጭ ቤቱ በማን እጅ እንደሚገኝ በትክክል ውሳኔው የተፈጸመ መሆኑ አለመሆኑን አጣርቶ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጥበት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.341 መሰረት መዝገቡ መመለሱን ያስረዳል።

በመጨረሻም በክፍል ሁለት በሚኖረን ዝግጅት የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤን መልስ እና ከሰነዶች የምናገኛቸውን ማስረጃዎች ይዘን እንቀርባለን። እስከዚያው ቸር እንሰንብት።

መክሊት ወንድወሰን እና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You