የዓለም ጤና ድርጅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትሮ ማድረግ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ሊታደግ እንደሚችል ያስገነዝባል። በኢትዮጵያም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች 51 በመቶ እንደተሻገሩ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ 21 ከመቶ የሚሆኑት ተጠቂዎች ወጣቶች ሲሆኑ፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ለሞት ይዳረጋሉ። ይህንን ችግር ለመፍታትም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ማህበረሰቡ የሚሳተፍበትን የስፖርት ለሁሉም መርሃ ግብር ላይ አተኩሮ በመስራት ላይ ይገኛል።
በዚህ ወቅት በስፖርቱ ዘርፍ በተለየ ሁኔታ ትኩረት የተሰጠው ለስፖርት ለሁሉም ልማት መሆኑን በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ በቀለ ያስረዳሉ። ለዚህም ምክንያት የሆነው ህብረተሰቡን በስፖርቱ በማሳተፍ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማውና ተጠቃሚ እንዲሆን ነው። ነገር ግን በዚህ እንቅስቃሴ ተተኪ በመሆን በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሀገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን ማፍራትም ሌላኛው ዓላማው ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ የሚያጠነጥነውም ህብረተሰቡን በስፖርት ተሳታፊ ማድረግ በሚለው ሃሳብ ላይ በመሆኑ ይህንኑ ሊደግፍ ይችላል።
የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት በአዲሱ የስፖርት ሪፎርም ከዚህ ቀደም ያልተሰራበት በሚል ለይቶ ተቀምጧል። በዚህም መሰረትም በዚህ ዓመት በእንቅስቃሴው ተሳታፊ ለማድረግ የታቀደው 480ሺ የሚሆን የማህበረሰብ አካል በሚኖርበት አካባቢ፣ 280ሺ የሚሆነው ደግሞ በሚሰራበት አካባቢ ተሳታፊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ሲሆን፤ 24 ሚሊዮን የሚሆኑትንም በስፖርት ለሁሉም እንቅስቃሴው ለማካተት እየተሰራ ነው። በዚህም ከአጠቃላይ ህብረተሰብ 20 ከመቶ ለመሸፈን ታስቦ ከ19 በመቶ በላይ የሚሆነው መሳካቱን ቡድን መሪው ያስረዳሉ።
ከዚህ ቀደም በተካሄደ የስፖርት ለሁሉም ብሄራዊ የአንድ ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብርም፤ በሁሉም ክልል 5ነጥብ4 ሚሊዮን ህዝብ ተሳታፊ መሆኑ ተረጋግጧል። ሁሉም ጋር የነበረው እንቅስቃሴ ተመሳሳይ ባይሆንም እንደ አዲስ አበባ እና ደቡብ ክልሎች ባሉት የተሻለ ሁኔታ ነበር። ችግሩ በተለይ ጎልቶ በሚታይበት አዲስ አበባ ያለው ተሞክሮ አመርቂ የሚባል ሲሆን፤ ህብረተሰቡ ግንዛቤው ስላለው የመርሃ ግብሩን መካሄድ ሳይጠብቅ አካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም ታይቷል። በድሬዳዋ፣ ሃረሪ እና የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች ያለው እንቅስቃሴም አበረታች የሚባል ነው።
ነገር ግን በትምህርት ቤቶች ውስጥ ንቅናቄውን በሚፈለገው ልክ ማስኬድ አልተቻለም። በተለይ ባንዲራ መውጫና መውረጃ ላይ በየቀኑ ከ20-30 ደቂቃ ወስደው እንዲሰሩ ለማድረግ ቢሞከርም እንደታቀደው አልሄደም። በአንጻራዊነት በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ያለው የተሻለ ቢሆንም፤ እንደአጠቃላይ ሲታይ ስኬታማ ሊሆን አልቻለም። ለዚህም እንዲረዳ ሁለት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተዘጋጅተዋል፤ ይሁንና አሁንም ለውጥ እየታየበት አይደለም።
ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የአንድ ሰዓት ስፖርት ለሁሉም መርሃ ግብርም ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል። ይህም ህብረተሰቡ በዕለት ተዕለት ህይወቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለአንድ ሰዓት ማድረግ ልምድ እንዲሆነው ያስችላል። ሰራተኞችን በሚመለከትም 28 የሚሆኑ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችን ያካተተ የስፖርት ውድድር በተያዘው ወር አጋማሽ ማካሄድ ተችሏል።
ውድድሩ የራሱ ህግና ደንብ ተዘጋጅቶለት በ7 የስፖርት ዓይነቶች ነበር የተካሄደው። በቀጣይም አንደኛው ሀገር አቀፍ የሰራተኞች ስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫልን በአማራ ክልል ደሴ ከተማ ላይ ለማካሄድ ታቅዷል። በዚህም ህብረተሰቡን በውድድርም ሆነ በመዝናኛ መልክ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆን ጤናውን መጠበቅ ይችላል ተብሎ ታስቧል። በሂደትም ንቁ፣ ጠንካራና አሸናፊ ማህበረሰብን መፍጠር የሚለውን ግብ መምታት ይቻላል የሚል እም ነት አለ።
መንግስት ለዚህ እንቅስቃሴ ትልቅ ትኩረት እንደመስጠቱ ከፍተኛ በጀትም ተመድቦለታል። ከዚህ ባሻገር ስመጥር አትሌቶችንና ስፖርተኞችን በዚህ የልማት ስራ በማሳተፍም ማህበረሰቡን ለማነቃነቅም ይሰራል። ይህ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ስራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም