እግር ኳስ በዘመናችን ቂሪላ የማንከባለል ጉዳይ ብቻ አይደለም። ተወዳጁ ስፖርት ከመዝናኛም በላይ ሆኖ ትልቅ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖውም እየፈረጠመ የመጣ ትልቅ ዘርፍ ነው። በነዳጅ ሃብቷ የከበረችው የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገር ሳዑዲ ዓረቢያ በእግር ኳስ ስሟ የሚጠራ ሀገር አልነበረችም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሳዑዲ ስፖርቱን ከፈጠሩትና ትልቅ ደረጃ ካደረሱት በላይ የእግር ኳስ ሀገር ካልሆንኩ እያለች ይመስላል።
ሳዑዲ እግር ኳስ ላይ የሙጢኝ ያለችው ሌላው ስላደረገው ሳይሆን ፈርጀ ብዙ ጥቅሙን በቅጡ ተረድታ ትርፍና ኪሳራውንም አጢና ነው። በዚህም ካለፉት ቅርብ ዓመታት ጀምሮ የዓለም ኮከቡን ክርስቲያኖ ሮናልዶን ጨምሮ ኔይማር ጁኒየር፣ ሳዲዮ ማኔ፣ ቤንዜማ ወዘተ የዓለም ኮከቦችን በሊጓ ሰብስባ ትልቅ የእግር ኳስ አብዮት አፈንድታለች።
ይህ አብዮት ደግሞ በሊጎቿ ከዋክብት በመሰብሰብ ብቻ የተገደበ አይደለም። የመካከለኛው ምሥራቅ የፈረጠመ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተፅዕኖዋም በእግር ኳሱ እንዲደገም ሙሉ ትኩረቷን ወደ ስፖርቱ እንዳዞረች ምልክት ተደርጎ ተቆጥሯል።
ሳዑዲ ታላቁን የእግር ኳስ መድረክ የዓለም ዋንጫን በ2034 ለማስተናገድ ለፊፋ ጥያቄ ካቀረበች ሰነባብታለች። ፊፋም ዕድሉን እንደሚሰጣት ጥያቄውን ካቀረበችበት ወቅት ጀምሮ ፍንጮች መታየታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የገልፏ ሀገር ግን በዚህም አላበቃችም የሴቶችን የዓለም ዋንጫ በ2035 የማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት ሸሽጋ አታውቅም፡፡
ሴቶች እስከ ቅርብ ዓመት ድረስ እንኳን ኳስ ሊጫወቱ ስቴድየም ተገኝተው መመልከት የማይችሉባት ሳዑዲ ዓረቢያ የሴቶችን ዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ማለሟ ብዙዎችን ሊያስገርም ይችላል፡፡ ሳዑዲ ሴቶች እግር ኳስን እንዲጫወቱ ከፈቀደች በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት እንኳን አላለፉም፣ የሴቶች ብሔራዊ ቡድኗ የተመሠረተው በ2022 ቢሆንም የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የቴክኒክ ዳይሬክተራ ሞኒካ ስታብ ግን በሳዑዲ መጪው ዘመን ለሴቶች እግር ኳስ ብሩህ ነው ይላሉ።
የ2026 የኤሽያ የሴቶች ዋንጫን እንደምታዘጋጅ ቀደም ብላ ያረጋገጠችው ሳዑዲ በእግር ኳስ ላይ እንዲህ የዘመተችው ካለምክንያት አይደለም። ሀገሪቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘወትር የጎደፈ ስም እንዳላት ተቀናቃኞቸ ደጋግመው ይናገራሉ፡፡
ከተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የምትወስደው ጠንከር ያለ ርምጃም በምዕራባውያን አይወደድላትም። የሞት ፍርድ የሚፈፀምባት ሀገር መሆኗም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ገፅታዋን አጉድፎታል። በዚህም እንደ ሀገር ጥሩ ገፅታ አላት ለማለት ይቸግራል፡፡
ትንሿ አገር ኳታር ከሁለት ዓመት በፊት ዕጣ ፋንታዋ ተመሳሳይ ነበር። የ2022 ዓለም ዋንጫን በማስተናገዷ ግን ኳታር በዓለም ዘንድ የነበራት ገፅታ በእግር ኳስ ተፅዕኖ ምን ያህል እንደተቀየረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ሳዑዲ ጎረቤቷ ከእግር ኳስ በገንዘብ የማይተመን ጥቅም እንዳገኘች አስተውላለች። በእግር ኳስ ላይ የተያያዘችውን አብዮት ጠበቅ አድርጋ መያዝ የጀመረችውም ከ2022 ዓለም ዋንጫው ወዲህ ነው። ለዚህም የተዘረዘሩትን ርምጃዎች አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መውሰዷ ግልፅ ማስረጃ ነው።
አልጋ ወራሹ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን ሳዑዲን መምራት ከጀመሩ ወዲህ ከዚህ ቀደም እንኳን ሊተገበሩ ሊታሰቡ የማይችሉ በርካታ ለውጦችን መሬት እያወረዱ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል ሴቶች ስቴድየም ገብተው ጨዋታ መመልከት እንዲችሉ እንዲሁም እንዲጫወቱ ከመፍቀድ አንስቶ መኪና እንዲያሽከረክሩ መደረጉ ዋነኞቹ ናቸው። አልጋወራሹ ልዑል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለዘመናት ቀጥ አድርጎ የያዘው የነዳጅ ሀብት እንደሚያልቅ ተረድተው ቱሪዝምን የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ለማድረግ ዘለግ ያለ እቅድ ነድፈው እየሠሩ ይገኛሉ። ቱሪዝም ደግሞ የጎደፈ ገፅታ ባላት ሀገር የታሰበውን ያህል ውጤት ላያመጣ ይችላልና ሳዑዲ ይህን መለወጥ ግድ ይላታል። ለዚህም እግር ኳስን ሁነኛው መንገድ እንደሆነ ተረድታ ረጅሙን ጉዞ ጀምራዋለች።
ሳዑዲ አሁንም ከሰብዓዊ መብት አያያዝና ከሞት ፍርድ ተፈፃሚነት ጋር በተያያዘ ብዙ ጥርስ ያስነከሰባት ጉዳይ እያለ እግር ኳስን ተጠቅማ የጎደፈ ስሟን ለማፅዳት የምታደርገው እንቅስቃሴ ከጅምሩ መብጠልጠሉ ግን አልቀረም። ይህንንም ትልልቅ ሚዲያዎችና ፀሐፊዎች ዘወትር ከመተቸት አልቦዘኑም። ሳዑዲ ግን “ውሾቹም ይጮሃሉ ግመሎቹም መጓዛቸውን ይቀጥላሉ” ያለች ይመስላል። ይህንንም አዳዲስ ዘመናዊ ግዙፍ ስቴድየሞችን በመገንባት እያሳየች ትገኛለች፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም