የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ስትራቴጂክ ጠቀሜታ

የዓለም ንግድ ድርጅት(WTO) አባል ለመሆን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ደጅ በመጥናት ላይ ለምትገኝ ሀገር፤ ለዛውም እነ አሜሪካና አውሮፓ የገበያ ከለላ በመስጠት፣ ከፍተኛ ታሪፍ በመጣል፣ በተለይ ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ከቻይና ጋር የንግድ ጦርነት ለመቀስቀስ እየተዘጋጁ ባለበት፣ የWTO ቀጣይ ህልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በዚህ ወሳኝ ሰዓት ጎረቤታዊ፣ ቀጣናዊና አኅጉራዊ የንግድ ትስስሮችን ማጠናከር ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ነው። የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለዛሬ መጣጥፌ መነሻዬ ያደረግሁት ከዚህ አንጻር ነው። ሰሞነኛው 15ኛው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና በሙሉ አቅሙ ወደ ትግበራ መግባቱ ሳይዘነጋ።

የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሀገራቸው በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የሚጣለውን ቀረጥና ሌሎች ከቀረጥ ውጭ ያሉ ተግዳሮቶችን በሂደት በመቀነስ የአፍሪካ የእርስ በርስ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ የተቋቋመ የንግድ ቀጣና ነው። ከ15 በመቶ በታች የሆነውን የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2040 ከ15 እስከ 25 በመቶ እንደሚያሳድገው የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) መረጃ ያሳያል።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ካጸደቁ ቀዳሚ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ በመሆኗ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። አሁን ላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በመሳተፍ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችላት ብሔራዊ የንግድ ቀጣና መተግበሪያ ስትራቴጂ አዘጋጅታለች። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና መመስረት በአኅጉሪቱ የምጣኔ ሀብታዊ ትስስርን ለማጠናከርና ሰፊ የገበያ እድሎችን መሠረት ለማጽናት የማዕዘን ድንጋይ ነው።

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በአህጉሪቱ አባል ሀገራት መካከል የምጣኔ ሀብታዊ ትስስርን ለማጠናከርና ሰፊ የገበያ እድሎችን ለመፍጠር እንደሚያስችል፤ ቀጣናው ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የሚልቀውን የአፍሪካ ሕዝብ እና ከ3 ነጥበ 4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሆነውን አጠቃላይ አኅጉራዊ ገቢ ያቀናጀ ግዙፍ የገበያ እድል የመፍጠር ዓላማ አለው። ይህ አፍሪካን በዓለም ላይ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብት ከገነቡ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍና ጠንካራ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችላት መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለመሆኑ ነፃ የንግድ ቀጣና ምንድነው፤ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውስ የሚለውን ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው እሴት የሚጨምሩ የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች፣ የማምረት ሥራዎች እንዲሁም ንግድ የሚከናወንባቸው ከባቢ ናቸው የሚል ትርጓሜ ሲሰጣቸው ይሰማል። ከዚህ በሻገር ነፃ የንግድ ቀጣና ማለት ምንም ዓይነት የንግድ እንቅፋት የሌለበት ሥፍራ ወይም ታሪፍና ታክስ ያነሰበት አካባቢ ተብሎ እንደሚጠራም በጉዳዩ ላይ የተሰነዱ የተለያዩ ጽሑፎች ያስገነዝባሉ።

ኢንቨስተሮች በነፃ የንግድ ቀጣናዎች መክፈል ያለባቸው ታሪፍና ታክስ ስለሚቀንስ ኢንቨስት ለማድረግ ብዙ ካፒታል የሚያገኙበት፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያግዝ፣ የቢሮክራሲ ሂደቶች የሚቀንስ አማራጭ ስለመሆኑም በተለያየ ጊዜ ሲነገር ይደመጣል።

ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩትም፣ በነፃ የንግድ ቀጣናዎች የሚገቡ ነጋዴዎች የተለያዩ የታክስ ነክ እንዲሁም ከታክስ ጋር ያልተያያዙ ማበረታቻዎች የሚያገኙ ሲሆን፣ ነፃ ቀጣናዎቹ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል ለሀገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ፣ ለግሽበት መቀነስ የሚኖራቸው ወሳኝ ሚና፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያላቸው አበርክቶ፣ በአጠቃላይ የሚፈጥሩትን በጎ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ምክንያት በማድረግ ሀገሮች ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን ያቋቁማሉ፣ ያስፋፋሉ።

የጎረቤት ሀገሮች ነፃ የንግድ ቀጣናዎች ለንግድ መቀላጠፍ ያበረከቱት በጎ ተፅዕኖ ሲኖረው፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር፣ ሰፊ መሬት ያላት ኢትዮጵያ ግን ይህንን ሥርዓት እስከ ዛሬ ባለማቋቋሟ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች። ኢትዮጵያ አበክራ ነፃ የንግድ ቀጣና አቋቁማ ቢሆን ኖሮ ትልቅ ገበያ በመመሥረት ከጎረቤት ሀገሮችም ሆነ ከመላ ዓለም ጋር በሚኖራት የንግድ ግንኙነት ላይ የወሳኝት ሚና ይኖራት ነበር። ይህ ባለመሆኑ ግን ማግኘት የሚገባትን እንድታጣና በንግድ ግንኙነቶች ላይ የወሳኝነት ሚና እንዳይኖራት አድርጓል። በታቃራኒው መሆን የነበረበትና ትክክለኛው አካሄድ በሀገር ውስጥ በርከት ያሉ የንግድ ቀጣናዎችን በማቋቋም ዓለም አቀፍ ነጋዴዎች በእነዚህ የነፃ ንግድ ቀጣናዎች በመግባት በኢትዮጵያ ያለውን ትልቅ ገበያ ለመያዝ ውድድር ማድረግ ነበረባቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በሎጂስቲክስ ዘርፉ ያሉ ጥንካሬዎችና ድክመቶችን፣ እንዲሁም ውጫዊ ተግዳሮቶችና ዕድሎችን በመለየት ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፖሊሲዎች የመነጨ ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ ጉዳይ ሲሆን፣ ሰነዱም ስድስት ዓበይት ስትራቴጂዎች፣ 22 ንዑሳን ስትራቴጂዎችና 98 ኢኒሼቲቮችን አካቶ በአሥር ዓመታት ውስጥ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ አፈፃፀም በዚህ ወቅት ካለበት 122ኛ ደረጃ በማሻሻል ወደ 40ኛ ደረጃ ከፍ ማድረግን ያለመ ስለመሆኑም ይገልጻል።

በብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂና በአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ውስጥ ከተጠቀሱት ኢኒሼቲቮች አንዱ ‹‹ነፃ የንግድ ቀጣና ማቋቋም›› እንደሆነ ይታወቃል። ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት የተጣለው ግብ በሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ውስጥ ከተካተተ ጀምሮ በተለይም ባለፉት ዓመታት ሰፊ ጥናት ሲከናወን መቆየቱ የሚገለጽ ሲሆን፣ የተደረገው ጥናት አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ በብሔራዊ የሎጂስቲክስ ካውንስል ልዩ የኢኮኖሚክ ቀጣናዎችን ማቋቋም እንደ አንድ የፖሊሲ ፕሮግራም፣ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ደግሞ እንደ ፓይለት ፕሮጀክት ተይዞ ሲሠራ ቆይቷል።

የፕሮጀክቱ መሳካት ሀገሪቱን የሎጂስቲክስ ሥርዓት በመሻሻል የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ቅልጥፍናን የሚያመጣ፣ ለኢንዱስትሪና ከተሞች ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል መፈጠር፣ ለኑሮ ውድነት መቀነስና ለሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል። ይህ ነፃ የንግድ ቀጣና የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥተውት የሚሠራበት መሆኑን ፣ ከዚያም ውስጥ ኢንዱስትሪ ፍሪ ዞን፣ ኤክስፖርት ፕሮሰሲንግ ዞን የሚሉት ይጠቀሳሉ። በዓለም ላይ 5,400 የሚደርሱ ነፃ የንግድ ቀጣናዎች እንዳሉ ፣ ለአብነትም በቻይና የሼንዜንና ሃይናን ኤክስፖርት ፕሮሰሲንግ ዞኖች የቻይና ሕግ የማይሠራባቸው ዞኖች ተብለው እንደሚወሰዱ ሲነገር ይሰማል።

የነፃ ንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ መፈጠር በትልቅ ዜናነቱ የሚያነሱት በርካቶች ሲሆኑ፣ ይህም የሚያመጣቸውን የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ከግምት በመውሰድ ነው።ነፃ የንግድ ቀጣና በዋነኛነት በሦስት መሠረታዊ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት ጉዳይ ነው። የመጀመሪያው የአምራች ዘርፉን የተመለከተ ሲሆን፣ ይህም ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያመርት ወይም ከተመረተ በኋላ ኤክስፖርት የሚያደርገውን ነው። ሁለተኛው የአስመጪና ላኪ ድርጅቶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ይሄ ደግሞ ጥሬ ዕቃና አላቂ ዕቃ አስመጪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ዕቃዎችን በማምጣት በቀጣናው ውስጥ የሚያከማቹበት፣ የሚያቀናብሩበት እንዲሁም መልሰው ወደ ውጭ ሀገሮች የመላክ ሥራዎች የሚያከናወኑበት ነው። እንዲሁም ሂደቱን ለማሳለጥ ቀልጣፋ የሆነ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚሰጥበትም ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣናው የሚሰጠውን አገልግሎቶች የሚያቀላጥፉ የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ የደረቅ ጭነትና የምክር አገልግሎቶች በቅንጅት የሚሰጥበት ነው።

በነፃ ቀጣናው የሀገሪቱ የጉምሩክ ሥርዓትና አጠቃላይ ሕጎች ልማቱን ለማሳለጥ በሚያስችል ሁኔታ ላልተው የሚተገበሩበት መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን፣ በዚህ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ የሚገቡ አምራቾች ከነፃ የንግድ ቀጣናው ሳይወጡ የምርት ግብዓቶችን የሚያገኙበት ከመሆኑ ባሻገር፣ ከነፃ የንግድ ቀጣና ውጭ የሚያመርቱ ኩባንያዎች በግብዓትነት የሚጠቀሟቸውን ያላለቁ ምርቶች ከውጭ ሲያስገቡ እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው ቀረጥና ታክስ በነፃ ንግድ ቀጣና ውስጥ ተግባራዊ የማይደረግ በመሆኑ የምርት ወጪ የሚቀነስ ነው። ይህም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና እንዲገቡ ትልቅ ብርታት የሚሰጥ እንደሚሆን ይታሰባል።

ነፃ የንግድ ቀጣና መቋቋም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ከዚያው ጎን ለጎንም የውጭ ምንዛሬ፣ የኤክስፖርት ዕድገት፣ የኤክስፖርት ምርት ስብጥር ከማሳደግ በሻገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ የሚጫወተው ሚና በትልቁ የሚነሳ መሆኑ ይብራራል። የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድም የራሱን ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል የሚባለው የነፃ ንግድ ቀጣና እንቅስቃሴ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና የሠራተኞች ክህሎትን ለማሳደግ የሚጫወተው ሚና ግዙፍ ነው። በተጨማሪም የነፃ ንግድ ቀጣናው የሚመሠረትበት አካባቢን ወይም ቀጣናን በማልማትና በማሳደግ ረገድ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑም ይገለጻል።

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር እንደመሆኗ መጠን የገቢ ዕቃዎችን በዋናነት የምታስገባው የጂቡቲ ወደብን በመጠቀም መሆኑ ይታወቃል። በተመሳሳይ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ ዕቃዎችም ይህንኑ የጂቡቲ ወደብ በመጠቀም ወደ መዳረሻ ገበያዎች ይጓጓዛሉ። ድሬዳዋ ደግሞ ከጅቡቲ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ከመሆኗ ባሻገር ወደ ጂቡቲ ወደብ የሚያደርሱ ለጭነት ተሽከርካሪዎች ምቹ የሆነ መንገድና የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት መስመር የሚያልፍባት በመሆኗ ለሎጂስቲክስ አገልግሎት ምቹ አድርጓታል። ከጂቡቲ ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናው የሚገቡት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕቃዎች የሚከትሙት በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል (ኢስተርን ዞን) በተለይም በድሬዳዋ ደግሞ 50 ከመቶ የሚሆኑት የሚራገፍበት መሆኑ ድሬዳዋን አስመርጧታል።

ድሬዳዋ በተዘረጉ የባቡርና መንገድ መሠረተ ልማቶች፣ ኢንዱስትሪ ፓርክና የደረቅ ወደብ አማካይነት ነፃ የንግድ ቀጣናውን ዕውን ለማድረግ አመቺ መሆኗ ሌላው የሚነሳ ጉዳይ ነው። በድሬዳዋ የተቋቋመው ነፃ የንግድ ቀጣና ለመጋዘንነትና ለኤክስፖርት ማቀነባበሪያነት የሚያገለግሉ ሼዶች ዝግጁ መሆናቸው፣ በቀጣናው ውስጥ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና የኢንዱስትሪ ፓርኩ ከድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ጋር የሚያገናኘው መንገድ መጠናቀቅ ለንግድ ቀጣናው መሳለጥ አስፈላጊ የሆኑ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ መጋቢ መንገዶች፣ የውኃ አቅርቦትና ተያያዥ አገልግሎቶች የተሟሉ መሆናቸው ድሬዳዋን ተመራጭ አድርጓታል።

በድሬዳዋ በተመሠረተው ነፃ የንግድ ቀጣና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ጋር የተሳሰረ ሲሆን፣ የተለያዩ አልሚዎች ገብተው በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በኢምፖርትና ኤክስፖርት የሥራ መስኮች እየተሰማሩ ይገኛል። የነፃ ቀጣናው የዝግጅት ሥራዎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና አካላት በኩል ሲከናወን ቆይቷል።በነፃ ቀጣናው የሚተገበሩ የሕግ ማሕቀፎችን ጨምሮ ምስረታውን ለመጀመር የሚያስችል የመሠረተ ልማት ዝግጅት በኮርፖሬሽኑ በኩል ተጠናቆ አገልግሎት መጀመር የሚቻልበት ደረጃ ላይ ከደረሰ ሰነባበተ።

በዓለም ላይ ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን (ነፃ የንግድ ቀጣናዎች) ሲኖሩ፤ በተለያዩ የአደጉ በሚባሉ ሀገሮች ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና የተጫወተው የንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ በተሟላ ሁኔታ ሥራ መጀመሩ፤ የወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ፣ የዕውቀት ሽግግርን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል።

ይህ የነፃ ንግድ ቀጣና አሠራር በአፍሪካ ውስጥ በጂቡቲ፣ በሶማሌላንድ፣ ኬንያ ውስጥ ውጤታማነቱ በተሞክሮነት የተወሰደ ሲሆን፤ ከዚያም አልፎ ከሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች ውስጥ የቱርክ ሀገር ተሞክሮ ተቀምሯል። በጥናት የሚመለስ ቢሆንም የተለያዩ ዝርዝር መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ ከመገኛ ቦታቸው፣ ለገበያ ካላቸው ቅርበት አንፃር ሞጆ፣ አዳማ፣ ሰመራ ዓይነቶቹ አካባቢዎች በቀጣይ ለነፃ የንግድ ቀጣና ዞንነት ታሳቢ ከተደረጉት ውስጥ እንደሚገኙበት ይነገራል። ለዚህ መጣጥፌ ኢዜአን፣ ፋናን፣ሪፖርተርንና ሌሎች ምንጮችን ተጠቅሜያለሁ። ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You