የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እና የዓለም እጅ ኳስ ፌዴሬሽን በትብብር የሚያዘጋጁት፣ የአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት በታች ወንዶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል። በውድድሩ ከ10 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ፣ 11 ብሔራዊ ቡድኖች እንደሚካፈሉም ተገልጿል፡፡
አሕጉራዊው ውድድር ‹‹IHF Africa continental trophy›› የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፣ ከነገ ጥቅምት 23 እስከ 27- 2017 ዓ.ም ይካሄዳል። በዚህ ሻምፒዮና ጠንካራ የአሕጉሪቱ ወጣትና ታዳጊ የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች ሲፋለሙ ኢትዮጵያ ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ዝግጅቱን ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
“ስፖርት ለአፍሪካ ሠላም” በሚል ሃሳብ የሚካሄደው ሲሆን፣ ይህ አሕጉር አቀፍ ውድድር ዓለም ላይ የሚታየውን የሠላም እጦት በስፖርታዊ ውድድሮች አማካኝነት ማርገብ እንዲቻልና ስፖርት ለሠላም መጎልበት ያለውን ሚና ለማጉላት ታስቦ እንደሚካሄድ ተጠቅሷል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውድድሩን በማዘጋጀት የሚገኙትን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅም እንደሆነም ተጠቁሟል። በሁለቱም የእድሜ እርከኖች ውድድሩን አንደኛ በመሆን የሚያጠናቅቁ ሁለት ብሔራዊ ቡድኖች አፍሪካን በመወከል በዓለም እጅ ኳስ ዋንጫ እንደሚወዳደሩ ተገልጿል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ታዳጊና ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት ሲሆን 6 ከ18 ዓመት በታችና 5 ከ20 ዓመት በታች በአጠቃላይ 11 ብሔራዊ ቡድኖች የሚፎካከሩ ይሆናል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ጊኒ፣ ካሜሩን፣ ዛምቢያ እና ናይጄሪያ በ18 ዓመት በታች ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ሲወዳደሩ፤ ሪዩኒየን፣ ዚምቧቡዌ፣ ሩዋንዳ፣ ጊኒ እና ኮንጎ በ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖቻቸው ይወዳደራሉ።
የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ከጀመረ ከሁለት ሳምንት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከፌዴሬሽኑ እና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሚደረግለት ድጋፍ ጥሩ ዝግጅት ማድረጉን አሠልጣኙ ገልጸዋል። ቡድኑ አስራ አራት ተጫዋቾች መርጦ ሆቴል በመሰባሰብ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን ሲያከናውን ቆይቷል። የሚደረጉት ቅድመ ዝግጅቶችና ከባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚደረገው ድጋፍ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም ውድድሩን፣ በገንዘብ የሚደግፉ ተቋማት አለመገኘታቸውን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት (ዶክተር)፣ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም የምሥራቅ አፍሪካ ዞን አምስት እጅ ኳስ ውድድርን በጥሩ ሁኔታ በማዘጋጀቷና ከ18 ዓመት በታች አሸናፊ በመሆና የአሁኑን ሻምፒዮና የማዘጋጀት ዕድል እንዳገኘች አስረድተዋል። ‹‹በሁሉም ስፖርቶች ውድድሮችን ወደ ሀገር በማምጣትና በደንብ በመሥራትና የኦሊምፒክ ስፖርተኞችን ማፍራት ይቻላል፡፡›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህም መሠረት ውድድሩ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ስፖርትን በማነቃቃት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ዓላማ አድርጎ በኢትዮጵያ እ ን ደ ሚ ካ ሄ ድ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከአስተናጋጅነት ባሻገር በውድድሩ ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀቷንም አክለዋል፡፡
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ዳንኤል ዳርጌ በበኩላቸው፣ ውድድሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ለስፖርቱ እድገት ጥልቅ እገዛ እንዳለው ጠቅሰው፣ መንግሥታዊ መዋቅሩና ሕዝባዊ አደረጃጀቱ አብሮ የሚሠራ ከሆነ ስፖርቱን ማሳደግ እንደሚቻል አስረድተዋል። ለዚህም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ጥናቶችን በማዘጋጀት፣ እቅዶችን በመንደፍና በመተግበር እየተሠራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
በእግር ኳስና እጅ ኳስ ስፖርት የታየው መነሳሳት፣ ጠንክሮ ከተሠራና በአፍሪካ ደረጃ ያለውን አመራር ማሳደግ ከተቻለ በሌሎች ስፖርቶችም ማምጣት ይቻላልም ብለዋል። ለስፖርቱ እድገት ትልቅ ሚና የሚጫወተው ሕዝባዊ አደረጃጀቱን ማጠናከር ግድ የሚል በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፣ ለክልሎች ትልቅ አቅም እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል። በጥር ወር የእጅ ኳስን ጨምሮ የሚካሄደው የፕሮጀክቶች ውድድር ክለቦች ታዳጊዎችን መመልመል የሚያችል ይሆናል። ብሔራዊ ቡድንና ክለቦችን ለማጠናከር ከታች ጀምሮ መሥራት ስለሚገባው፣ ከፌዴሬሽኑ ጋር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ አንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ነገ በሚጀመረው ውድድር በአጠቃላይ ከ180 በላይ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ሲሆን፣ አንድ ቡድን 17 ልዑክ እንደሚያካተት ታውቋል። ለአሠልጣኞች ሥልጠና የሚሰጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ከዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ሲመጡ፣ ውድድሩን የሚቆጣጠሩ ሁለት ባለሙያዎች እና ውድድሩን የሚመሩ አስር ዳኞችም የሚመጡ ይሆናል።
በዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም