ወጣቱ ኢትዮጵያዊ የፓራሊምፒክ ኮከብ አትሌት ይታያል ስለሺ በፓሪስ 2024 የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በዓይነስውራን ሙሉ በሙሉ(T 11) ምድብ በመካከለኛ ርቀት 1500 ሜትር አትሌቲክስ ውድድር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።
ትናንት ረፋድ በተካሄደውና ጠንካራ ፉክክር በታየበት ውድድር አትሌት ይታያል ከአሯሯጩ እሱባለው በቀለ ጋር በመሆን ከብራዚላውያን አትሌቶች ጋር ብርቱ ፉክክር አድርጎ 4:03:21 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። በወጣቱ የፓራሊምፒክ ኮከብ ይታያል ስለሺ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ከተማ የተወለደ ሲሆን እድሜው ገና 19 ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ታሪክ በእድሜ ትንሹ የዓለም ፓራ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳሊያ ባለቤትም ነው። ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ክለብ የተገኘው ይህ አትሌት ወደስፖርቱ የገባው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ዱባይ ላይ በተካሄደው የዓለም ፓራሻምፒዮና ሚኒማውን አማልቶ ሜይ 2024 ኮቤ ጃፓን ላይ በ1500 ሜትር ዓይነስውራን ሙሉ በሙሉ ምድብ 4:03:20 በመሮጥ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሏል። በዚህም ለፓሪስ የፓራሊምፒክ ውድድር የቀጥታ ተሳትፎ ዕድልን ማሳካት ችሏል።
በቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ ከሦስት ዓመት በፊት የርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረው ብራዚላዊ ጃክኩዊስ ሄልትሲን የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች አንዱ የነበረ ሲሆን፣ ፓሪስ ላይም በድንቅ ብቃት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።3፡55፡82 ውድድሩን ያጠናቀቀበት ሰዓት ሲሆን የርቀቱ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ሆኖም ተመዝግቧል፡፡
በጃፓን ኮቤ የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈው ሌላኛው ብራዚላዊ ኤግሪፒኖ ዶስ ሳንቶስ ጁሊዮ ሴዛር ትልቅ የአሸናፊነት ግምት ያገኘ አትሌት ቢሆንም መጨረሻ ላይ በወጣቱ ኢትዮጵያዊ ተቀድሞ በ4፡04፡03 ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያው አሸናፊ ሆኗል፡፡ ይህ ብራዚላዊ በዚሁ የፓሪስ ፓራሊምፒክ ከቀናት በፊት በ5000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ነበር።
እንደ ኦሊምፒክ ትኩረት እየተሰጠው በማይገኘው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ እስከ ትናንት ድረስ ሁለት የወርቅና አንድ የብር ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችላለች። ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በአትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ አማካኝነት ፓሪስ ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወቃል። ከትናንት በስቲያ ደግሞ በሴቶች 1500 ሜትር T11 ሙሉ በሙሉ ዓይነ ሥውራን አትሌት ያየሽ ጌቴ ከአሯሯጯ ክንዱ ሲሳይ ጋር በመሆን በራሷ የተያዘውን የዓለም ክብረ ወሠን በመስበር ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፋ ይታወሳል፡፡ በወንዶች T46 የእጅ ጉዳት የ1500 ውድድር ደግሞ አትሌት ገመቹ አመኑ 7ኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን የዲፕሎማ ባለቤት ሆኗል።
የፓራሊምፒክ ቡድኑ ድል በሚዲያም ይሁን በመንግሥት በኩል በሚገባው ልክ አልተወራለትም። ያም ሆኖ የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ቡድን ፓሪስ ላይ በአጠቃላይ በ4 ውድድሮች ላይ ተሳትፎ 2 ወርቅ፣ አንድ የብር ሜዳሊያ እና 1 ዲፕሎማ በማስመዝገብ ትልቅ ታሪክ በመሥራት ከዓለም 27ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ተሳትፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ውጤት የተመዘገበበትና ታሪክ የተሠራበት ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ በ4ቱ ውድድሮች ላይ 6 አትሌቶችን አሳትፋለች። ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ አሯሯጮች ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም