ታላቁ ገጣሚ መንግሥቱ ለማ ተማሪዎቻቸው ፊት ይቆሙና “ዜናን ዜናነህ አነበበው…” ማለትን ያዘወትሩ ነበር። ምክንያቱም ዜናነህ ከነስሙ ለዜና የተፈጠረ ሰው ነበርና። “ዜናነህ” ብለው ስም ያወጡለት ወላጆቹም ነብይነት ቢቃጣቸው ነው። እርሱ ግን የኖረው ስሙን ነው። ዜናነህ ዜና አንባቢ ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም። ደራሲም ሆኖ መጻሕፍትን ጽፏል። ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅምና ደራሲነትና ጋዜጠኝነቱ ተጋግዘው ወደ ሀያሲነትም አድርሰውታል።
ከኋላኛው የ1960ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ከሀገር እስከወጣበት 1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ በበርካታ የሬዲዮና ቴሌቪዥን አድማጭና ተመልካች ውስጥ ትውስታን ቀብሯል። በወቅቱ ልጅ የነበረ የልጅነት እጣኑን፣ ወጣት የነበረም የወጣትነት ከርቤውን አሁን ላይ ሆኖ በትዝታ እንዲምግ አድርጎታል። ምን ከሀገር ወጥቶ ቢከርምም ብዙዎች “ከአዕምሯችን የማይወጣና የማይፋቅ ዜና አንባቢ ነው” ሲሉ ይገልጹታል። በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ “…ከሰዓቱ ዜና ጋር ዜናነህ መኮንን ነኝ” የሚላት የመግቢያ ሰላምታው ልብን ትፈነቅላለች።
ዜናነህ በዓይነ ምስል ድቅን የሚለው በዜና አቀራረቡ ብቻም ሳይሆን ራሱም የሚቀርብበት መንገድ የተለየ ነበር። ሁሌም በአለባበሱ ቄንጠኛና ሽቅርቅር ብሎ የሚታይ ዘናጭ ነበር። የሰላምታ እጅ አሰቃቀሉ መገለጫው ነው። ዜናውን ሲያነብ ያለውን የድምጹን ውበት ያደመጡ በትክክል ለዜና አንባቢነት የተፈጠረ ሰው ነው ይሉታል።
በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን መንደር ውስጥ ትልቅ ስም የነበረው አንጋፋ ጋዜጠኛ ነበር። በዚያ ብቻ ሳይሆን በጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ውስጥም የዜናነህ ድምጽ በልዩ አቀራረቡ የሚታወቅ ነበር። የመካከለኛውን ምስራቅ የፖለቲካ ድርና ማግ እንደ ጥጥ ፈትል እያሾረ አፍ ያስከፍት ነበር።
ዜናነህ ከምንጩ ሲቀዳ የትውልድ ቀዬው ወደ ሰሜን ጎንደሯ የአዘዞ ከተማ ይወስደናል። ዝናባማው ክረምት በመውጣት፣ ብሩህ ፀሐያማው በጋ በመምጣት ሲተላለፉ፣ ያኮረፈ ሰማይ ለመሳቅ ሲል በወርሃ መስከረም 1945ዓ.ም ነበር ውልደቱ። ነገር ግን በተወለደባት አዘዞ ከተማ ውስጥ በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት በላይ የልጅነት ሕይወት አልነበረውም።
ገና ትንሽ ልጅ ሆኖ ለአቅመ ፊደል ቆጠራ ሲቀራረብ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ ቢመጣም፤ አሁንም በውል የሚያስታውሰውን ልጅነቱን ከዚህ ለመጀመር አልቻለም ነበር። ምክንያቱም በድጋሚ ፊታቸውን ወደ ጅማ በማዞራቸው ነው። ባይሆን የሕይወት አጀማመሩ ከጅማ ሊሆን ይችላል። ከአሁኑ የመምህራን ማሠልጠኛ፣ ከቀድሞው ፃዲቁ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደል ቆጠራ ያዘ። ነገር ግን ገና ከልጅነቱ ከአንድ ቦታ እርጋ ባይለው ዞሮ ሦስት ማዕዘን ገጨ። ተመልሶ ወደ ጎንደር ሄደ።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ከዚያው ጀመረ። ጀመረ እንጂ አልጨረሰም። ከአንድ ቦታ ጀማምሮ መጨረሻው ሌላ ስለሆነ አሁንም ያልደረሰበትን አዲስ ሀገር ፍለጋ ያዘ። የድሬዳዋን የባቡር ሀዲድ ተከትሎ ድሬ ገባ። ከዚህ በኋላም የሚታወቀው መልሶ አዲስ አበባ መግባቱን ነው። ዜናነህ ከልጅነቱ አንስቶ ብዙ ፍላጎትና ብዙ ህልም ያለው ይመስላል።
በግማሽ ሕይወቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ቀጥሎ፣ በግማሽ ጎኑ ደግሞ ሙዚቃን ፍለጋ ወደ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ነበር የሄደው። ሁለቱንም መሳ ለመሳ ሲያሯሩጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ቀድሞ አለቀና ከነሙዚቃው ይዞት ሄደ።
የጋዜጠኝነትን ሕይወት ገፍቶ እንዲገባበት በበርካታ ጉዳዮች መበርቻና አርአያ የሆነው አሳምነው ገብረወልድ ስለመሆኑ ራሱ የሚያወሳው የታሪክ ክፋዩ ነው። ይሁንና አስቀድሞ ፖለቲካ እንደ ውሃ የሚጠማው፣ አፍቃሪ ፖለቲካ ነበር። ይህ ማንነቱ የመጣው እንዲሁ ከመውደድ ብቻ ሳይሆን የተማረውም ፖለቲካ ስለነበረ ነው። ላመነበት ሽንጡን ገትሮ እስከ ጥግ ድረስ መሟገት ባህሪው እንደነበር የቅርቦቹ ይናገሩለታል። ሲከራከርም ጉዳዩ ከሮ እስኪበጠስ አሊያም እስኪረታ ጥርሱን ነክሶ የሚታገልም ነበር። ምናልባትም ከአንደኛው የፖለቲካ አጥር መንጠላጠያ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ዘሎ ለመግባት ዓይኑን የማያሽ ዓይነት ነበር። ነገር ግን በመንገድ ሳለ የመለሰው ይሄው የአሳምነው የጋዜጠኝነት መልክና ተምሳሌት ነበር።
አስቀድሞ እምብዛም ባያስተውለውም የጋዜጠኝነት ፍላጎት ውስጡ እንዳለ መረዳት ጀመረ። ገና እታች ትምህርት ቤት ሳለ ጀምሮ አብዝቶ ሬዲዮ የሚያደምጥ ከመሆኑም በትምህርት ቤቱ የሚኒ ሚዲያ ክበብ ውስጥ፤ የአሁኑኑ ማይካራፎን የያኔውን ሜጋፎን ይጨብጥ ነበር። ይህችንም እያስታወሰ ጋዜጠኛ የመሆኑ ነገር ከውስጡ ተባባሰ። በዚህች የውስጥ እሳት ላይ ቤንዚን የሆነለትን ሌላ አጋጣሚ ደግሞ አገኘ።
በየጊዜው ባገኘው ሁሉ ግጥሞችን ሲሞነጫጭር ነበርና ግጥሞቹ አንድ ጊዜ ላይ ግን በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ የመውጣቱን ዕድል አገኙ። “በቃ እችላለሁ!” ማለት ነው ሲል በራሱ ርግጠኛ ሆነ። ተወዳጁን ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ለመሥራት ራሱን ፍለጋ ቆርጦ ወጣ።
ዜናነህ ከዜና ጋር የመገናኘት ጉጉቱ ባየለበት ጊዜ ወዳጆቹ ጥሩ መካሪዎች ነበሩ። የመግቢያ መንገዱን ሲፈልጉና ሲመክሩትም ጭምር መስመሩ እንዲታየው አድርገውታል። ከስኬት መልስም ደጋግሞ በየአጋጣሚው የሚያነሳው እነርሱኑ ነው። ፊቱን ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አዙሮም ከዚያው ማፈላለጉን ተያያዘው። በ1968ዓ.ም ሲቋምጠው የነበረውን አግኝቶ ድምጹም በሬዲዮ ለመሰማት በቃ።
በሪፖርተርነት ከተቀጠረ በኋላ ገና በመጀመሪያው አንድ መሰናዶ የማቅረብ አጋጣሚ መልካም ሆነለት። ወቅቱ ፖለቲካው የተጧጧፈበትም ነበርና “የአብዮት መድረክ” የተሰኘው መሰናዶው ከሚወደው ፖለቲካ ጋር አቆራኘው። የኢህአፓና የሜኢሶንን ፖለቲካዊ አኩኩሉን በማስቃኘት አንድ ብሎ የጀመረው ዝግጅቱ ከፍ ብሎ ተደመጠለት። የፖለቲካው ትኩሳት አዝማሚያው አስፈሪ ቢሆንም ሙያውን ለማሳደግና ተወዳጅነቱን ለመጨመር ግን እምብዛም ጊዜ አልፈጀበትም ነበር።
እዚህም እዚያም እያነፈነፈ የወቅቱን ወሳኝ ወሳኝ መረጃዎች በማቀበሉ ተካነበት። ጭብጥና ፖለቲካዊ ዳራው የማይመቻቸው እንኳን እሱን ለማድመጥ ይወዱ ነበር። ከአቀራረቡ ጀምሮ የተዋጣለት ስለነበረ ሳይወዱ በግድ ጆሮ የሚይዝ ነበር።
በዚያ ቀይ ሽብር በዚህ ነጭ ሽብር ዥንጉርጉር ጥላ በዘረጉ ሰሞን ላይ ዜናነህ ከነበረበት የሬዲዮ ሞገድ ወደ ቴሌቪዥን ሳተላይት ተሸጋገረ። ከሬዲዮ ጣቢያ ተወስዶ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ “ዜናን ከየአቅጣጫው” የተሰኘ ዝግጅት አቅራቢ ሆነ።
ጠለቅ ጠብሰቅ ያለውን የጋዜጠኝነት ክህሎቱን ያገኘውም በዚህ ወቅት ነበር። ለበርካታ ዓመታት የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያው የዜና ምሰሶ ሆኖ የሰነበተው ዜናነህ በብዙኃኑ ዓይንና ልብ ውስጥ ምስሉን፣ ማራኪ ድምጹን ደግሞ በጆሮ አስቀርቶታል። ታዲያ በወቅቱ አንድ ፈተና የነበረው ነገር ዓመት በዓል በደረሰ ቁጥር ሁሉ አፍ የለመደውን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን ቃል በቃል ማለቱ ነበር።
ጊዜው የሶሻሊዝም እንደመሆኑ በሬዲዮ ሞገድም ሆነ በቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ ሆነው “እንኳን አደረሳችሁ” ማለት ክልክል ነው። “…አደረሳችሁ” ሲባል በተዘዋዋሪ አንድ ያደረሰ ኃይል ስለመኖሩ የሚገልጽ ቃል ነውና በሶሻሊዝም ሥርዓት ደግሞ ይህ እግዜር አለ ብሎ እንደመስበክ ስለሚቆጠር ነው። እናም በ”…አደረሳችሁ” ምትክ “…ደረሳችሁ” ነበር አማርኛው። ታዲያ ዜናነህም ሳት እያለውም ሆነ አውቆ አንዳንዴ “እንኳን አደረሳችሁ” ማለቱ አይቀርም ነበር።
የነበረው ሥርዓት ለስህተት መሽሎኪያ ያነበረው በመሆኑ ቀላል ነገር ቢመስልም በተለይ ለዜና አንባቢዎች የነበረው ፈተና ከበድ ያለ ነበር። ቃላት እንኳን በዋዛ አይታለፉም። አንድ ጊዜ ላይ “ጄኔራል” ማለት የነበረበትን አንዱን ሰውዬ “ኮሎኔል” ብሎ በማንበቡ ከላይ በግልምጫ አሹቅ አድርገውታል። ዜናነህ ከኃላፊው ፈቃድ አፈንግጦ የመሰለውን የማይል ቢሆንም አንዳንድ በቆሪጥ እይታ ከዓይን ስር መጣሉ እንደ አብዛኛውም ሁሉ የነበረበት ነው። “ይህ የኢትዮጵያ ድምጽ ነው!” የርሱ መለያ የሆነች መግቢያው ነበረች። ይህቺን ዓረፍተ ነገር ከአፉ አውጥቶ እንዲተፋት የተመከረባቸው አጋጣሚዎችም ጥቂት አልነበሩም።
ከዜናው ወጣ ብለው ባሉ በሌሎች ዝግጅቶችም ሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚናገርበት ወቅት ሃሳቡን በልበሙሉነት አፍረጥርጦ የሚናገር የነበረ በመሆኑ ያልተቀሰረበት ጣትና ያልተወረወረበት ዛቻና ማስፈራሪያ የለም። በዚህ ብዙ ዋጋ እንደከፈለበት የሚያውቁ ይናገሩታል።
ታዲያ በዛቻና ማስፈራሪያ መርዝ የጠነከረው ቀስት ውርወራ ቀጣይ መዳረሻውን እስር ቤት አድርጎታል። “ዜናነህ ምን አጥፍቶ ታሰረ?” ቢባል ምላሹን አሳሪውም የሚያውቀው አይመስልም። በርግጥ ዜናነህ የፖለቲካ ፍቅር የነበረው ቢሆንም የኢህአፓ አባል አልነበረም። ሰግን ነህ ተብሎ ታሰረ። በመጀመሪያ የፍርድ ሸንጎው ላይ ሲቀርብ የተነበበለት ክስ አፍቃሪ ኢህአፓ ነህ የሚል ነበር። በኋላ ላይ ምንም ተጨባጭ ማስረጃም ሆነ መረጃ ሊያገኙበት ባልመቻላቸው ደግሞ ሌላ አመጡበት።
“የልዑል ራስ መኮንን ልጅ ነው” የሚል ነበር። በማይመስል የአሉባልታ ቅራሪ እያጠመቁ ያላንከራተቱት እስር ቤት አልነበረም። ከማዕከላዊ እስከ ዓለም በቃኝ እስር ቤት ድረስ ገባ ወጣ ሲያደርጉት ድፍን 2 ዓመታት ሞሉ። ከዚያ ግን ምንም ዓይነት ወንጀል የሌለበት መሆኑ ሲረጋገጥ ተፈታ። ለሁለት ዓመቱ እስርም የሞራል ካሳ ይሆነው ዘንድ አንድ ዓመት መርቀው ለ3 ዓመታት በነፃ እንዲኖር ከብስራተ ወንጌል ውስጥ የመኖሪያ ቤት ሰጡት።
ዜናነህ መኮንን ሁሌም በልበሙሉነት በራሱ መንገድ ራሱን ብቻ የሚከተል ሰው ነበር። እርሱ ራሱን ቢከተልም በክፉ ተመልክተው ከኋላው እሱን የሚከተሉት ግን አልጠፉም ነበር። ጥቃቅን ከሚባሉ ነገሮች ውስጥ እንኳን ባለጋራዎቹ እንደ እህል ነቀዝ ብቅ እያሉ ይታዩት ነበር። በብዙ ጉዳዮች ብዙዎችን በመታዘቡ “ቅናት” የምትለዋ ቃል በርሱ ዘንድ አስቀያሚው ነበረች።
ከወዳጆቹ ጋር ሲያወራ ብቻ ሳይሆን ከአንድም ሁለት ጊዜ ከሚዲያ ላይ ሲናገር “ቅናት የሚባለው ነገር የእውነት ደምና አጥንት እንዳለው የተረዳሁት ያኔ ነበር” በማለት በትንሹ እንኳን በአዋዋልና በኑሮ ምርጫው የሚበሽቁ እንደነበሩ ይናገራል። ታዲያ አንዳንዴ “ጠላትህ ቢበዛ ደስ ይበልህ” ማለት እንደዚህ ነው።
ያስመረረው ክፋታቸው ወስዶ መጽሐፍ ላይ ጣለው። እየተከተሉ ፍዳውን ካበሉት ራሱን ነፃ ለማውጣት ሲያውጠነጥን “ነፃነት” የሚል የሃሳብ ማግ ከምናቡ ተሳሰረና በብዕር አውርዶ መጽሐፍ አደረገው። ዜናነህ መኮንን የመጀመሪያው የሆነውን መጽሐፉንም ጽፎ አስነበበ። “ከጣሪያው ስር” ሁለተኛውም የልቦለድ መጽሐፉ ነው። “በረከተ ራዕይ” ሠላሳ ያህል ግጥሞችን የያዘ የሲዲ ሥራው ነው።
ዜናነህ በዜናም በመጽሐፍም ሳይቆም ደግሞ ቲያትርም ጽፏል። ቅናት የሚሉት የሕይወት ጋሬጣው እየመጣ ፊቱ ድቅን ቢል “የመንገድ ላይ ወግ” ሲል ምን ያህል ወደኋላ ጎትቶ እየፈጠፈጠን እንዳለ በቲያትሩ ያሳየናል።
ሥራዎቹን ጠቅለል ባለ መልኩ ከቃኘናቸው ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ መዳረሻቸው ከፖለቲካ እስከ ሃይማኖት ነው። አጥብቆ ፍትህና ነፃነትን ይጠይቅባቸዋል። የተዛቡትን ማህበረሰባዊ ስንክሳሮቻችንን ለማቅናትም ሲታገልባቸው እናገኘዋለን። “ስለምንድነው ሥራዎችህን ሁሉ በእንጉርጉሮ መሳይ ዜማ የምትቃኛቸው?” በማለት ብዙዎችም ይጠይቁታል።
“የኔ ሥራዎች ከማህበረሰቡ ጓዳ የተቀዱ ናቸው። ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል ከሚል ማህበረሰብ ወጥቼ ከዚህ ሌላ ምን ልጽፍ እችላለሁ” ሲል ይመልሳል። የብዕር ቀለሙ የማህበረሰቡ የኑሮ ጠብታ ነውና በርግጥም ኑሮው እንጉርጉሮ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ሲኖር ከዚህ የተለየ ከወዴትም ሊያመጣው አይችልም። በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከ18 ዓመታት በላይ ሲሠራ ሥራና ሕይወት የነገረችውም ይሄው ነው።
የመጨረሻው የደርግ ሥርዓት፤ ለዜናነህ መኮንንም የመጨረሻው የሀገር ውስጥ መሰንበቻው ነበር። ዘመነ ደርግ አክትሞ ዘመነ ኢህአዴግ ሲገባ፣ ዜናነህም ወደ ሀገረ እስራኤል ተሰደደ። ሲሄድ ብቻውን አልነበረም። አስቀድሞ ከእስር እንደተፈታ ትዳር መስርቶ የወለዳቸውን 2 ጨቅላ ልጆቹን ይዞ ነበር። ባለቤቱ ግን በፍቺ ተለይታው ነበር። ከሀገር ከወጣ እልፍ ክረምትና በጋ ተፈራርቀው፣ ሠላሳ ጊዜ መስከረም ጠብታለች።
ባህር ማዶ ከተሻገረ 30 ዓመታት ተቆጥረዋል። ከጎንደር አዲስ አበባ የጀመረው ኑሮው ኢየሩሳሌም ላይ ቀጠለ። በዚያ ብቻ የተገታ ግን አልነበረም። አብዛኛውን ዓመታት ያሳለፈው በእስራኤል ቢሆንም በልጅነት ጅምሩ ላይ የነበረውን ዓይነት እሽክርክሪት መድገሙ አልቀረም። ከእስራኤል ጀርመን፣ ከጀርመን ኖርዌይ፣ ከኖርዌይ እስራኤል ዞሮ በሦስት ማዕዘን ተገናኘ። በእነዚህ ሁሉ ሀገራት ተምሯል። ሠርቷል።
በእስራኤል ውስጥ የሠራው ግን የሚበልጥ ነበር። በዚያ ሆኖ የራሱን የግል ሬዲዮ ጣቢያ አቋቁሟል። ከወደ ኢየሩሳሌም ሆኖ ለረዥም ዓመታት ዶቺቬሌን ሲያስኮመኩም ቆይቷል። ወጣቶችን እያሰለጠነ ለቁም ነገር ማብቃት አንደኛው የሕይወት ክፍሉ ነበር። በተለያዩ ጊዜያትም አጫጭር ፊልሞችን ዳይሬክት በማድረግ ይታወቃል።
“አንተ ከሀገርህ ልትወጣ ትችላለህ። ሀገር ግን ካንተ ውስጥ አትወጣም! እናም ኢትዮጵያ ሀገሬ ሳልገባ አምላክ አይግደለኝ!” በማለት ብዙ ጊዜ የምኞት ጸሎቱን ያደርስ ነበር። ሀገሩ የመግባት ተስፋውን ከውስጡ ቋጥሮ ከዚያ መሄድ መሄድ፣ ከወዲህ መምጣት መምጣት አሰኘውና ስለመንገዱ ማሰብ ማሰላሰል ጀመረ። ወደ አንድ ሆስፒታል ጎራ ብሎም ምርመራ ሲያደርግ ግን የመርዶ ያህል የሚያስደነግጠውን ዜና ነገሩት።
“ሁለቱም ኩላሊቶችህ ከጥቅም ውጭ ሆነዋል” አሉት። ገና ከአምስት ወራት በፊት ከሞተችው እናቱ ሀዘን በቅጡ ሳያገግም ሌላ ሀዘን ልቡን ወጋው። ከዚያን በኋላ በሳምንት ለሦስት ቀናት የኩላሊት እጥበት እያደረገ ኑሮውን በመግፋት ቀጠለ። ከአምስት ዓመታት በፊት በእስራኤል ኢትዮ ቴሌቪዥን (IETV) ቀርቦም የገጠመውንና የሆነውን ሁሉ በተሰበረ ልብ ገልጾ ነበር። ከህክምናው ጀምሮ ኑሮው ምስቅልቅል ማለቱንም አንስቶት ነበር።
ሀገሩ የመግባት ተስፋውም ተሟጦ መና ቀረ። ለ “ጋዜጠኛ ጡረታ አይወጣም” የሚላት ንግግር ደግሞ ነበረችው። ለዚያም ይሆናል አልጋ ላይ ሆኖ እንኳን ጋዜጠኝነቱን አላቆመም ነበር። ጋዜጠኛውን ግን የረታው ህመም ሳይሆን ሞት ነበር። ዓመታትን ከህመሙ ጋር ሲሰቃይ ቆይቶ ከሰሞኑ ኅዳር 1 ቀን 2017ዓ.ም አረፈ። በ72 ዓመቱ ነብሱን የሞት አሞራ ነጠቀው።
ከሀገሩ እንደወጣ፣ ሀገሩን እንደተጠማ ሳይመለስ በዚያው አሸለበ። በሕይወት የናፈቃት ሀገሩ በድኑም ሳያርፍባት ቀረ። ዜናነህ ካለመኖር ወደ መኖር፣ ከመኖር ወደ አለመኖር… ሕይወት የሦስት ማዕዘን ጀንበር ናት።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም