በኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ የቀረበው ክስና የተሰጠው ምላሽ

የተለያዩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አትሌቶች በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በአመራሮቹ ላይ ከቀናት በፊት በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ መመስረታቸው ይታወሳል። ፌዴሬሽኖቹንና አትሌቶቹን ወክለው ክሱን ያቀረቡት ጠበቆች ከትናንት በስቲያ በኃይሌ ግራንድ ሆቴል በቀረበው ክስ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይህንን ተከትሎም ኦሊምፒክ ኮሚቴ መግለጫ አውጥቷል።

ጠበቆቹ በሰጡት መግለጫ ከሳሾቹ የኢትዮጵያ ቴኒስ እና ቦክስ ፌዴሬሽኖች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ መሆናቸውና እነሱን ወክለው ችሎት ላይ እንደሚቆሙ አስረድተዋል።

የኢትየጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደ ተቋም፣ በግል ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ ዋናና ምክትል ጸሐፊዎቹ አቶ ዳዊት አስፋውና አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንዲሁም አቃቤ ነዋይ ዶ/ር ኤደን አሸናፊ መከሰሳቸውን የገለጹት ጠበቆቹ፣ አራት ፌዴሬሽኖች ክሱን ለመቀላቀል ጠይቀው ጉዳዩን እያዩ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል። ”አራት ፌዴሬሽኖች የዚህ ክስ አካል ለመሆን ጠይቀውናል እያጠናነው ነው፣ ከማን ጋር ነው የምንጋጨው ብለው የሰጉም አሉ፣ ማንም በህግ አንጻር እኩል ነው ብለን ነው የምናምነው፣ የምንጋጨውም ግለሰብ የለም፣ መንግሥት ጣልቃ ይገባል ብለንም አንሰጋም” ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኦዲት አልተደረገም የሚለውን ጉዳይ አፅንኦት የሰጡት ጠበቆች፣ ተቋሙ ወደ 1 ቢሊዮን ብር በካሽና በአይነት ያለው ሂሳብ ኦዲት እንዲደረግ መጠየቃቸውን ጠቅሰው፤ ወደ 48 ሚሊዮን ብር ለአኖካ ስብሰባ ተብሎ መንግሥት ክፍያ መፈፀሙን፣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ክፍያ ፈጽመው ኦዲት እንዳልተደረገ፣ ከ400 ሺህ ዶላር በላይ የሆኑ ትጥቆች በየዓመቱ ከአዲዲስ ኩባንያ ቢላክም የት እንደገባ እንደማይታወቅ ገልፀዋል።

“ኦሊምፒክ በተካሄደ ቁጥር ወደ 600 ሺህ ዶላር የሚገመት የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ይደረጋል፤ ለመላው አፍሪካ ወደ 500 ሺህ ዶላር ድጋፍ ተደርጓል፤ ለኦሊምፒክ ውድድር ተሳትፎ 30 ሺህ ዶላር ለስልጠና ተብሎ ደግሞ ከ15-20 ሺህ ዶላር በየዓመቱ ይመጣል፤ 198 ሺህ ዶላር ወጣቶችን ለማትጋት ተብሎ ይሰጣል፤ እስካሁን ግን ምንም ኦዲት አልተደረገም፤ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም የሚጠበቅበት ኃላፊነቱን አልተወጣም። በዚህም አዝነናል። ዋናው ጥያቄያችን ከላይ የገለጽናቸው ገቢዎች የት ገቡ ወይም ለምን ወጪ ተደረጉ የሚለው ምላሽ ያስፈልገዋል፣ ችሎቱን የጠየቅነውም ይህንን ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ጠበቆቹ አቶ አያሌው ቢታኒ ፣ አቶ ኃይሉ ሞላና አቶ ጳውሎስ ተሰማ ለመደበኛ ችሎት አቀረብን ባሉት የክስ ማብራሪያ፣ “ግንቦት 5 እና ሰኔ 14/2016 የተደረጉት የኮሚቴው ህገወጥ ጉባኤና ውሳኔዎቹ ይሰረዙ፤ ተገቢ በሆነ አግባብ አጠቃላይ ወጪ ላይ ኦዲት ይደረግ፤ በፓሪስ ኦሊምፒክ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደተካሄደ የሚያሳይ ነገር ስላለ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በፈረንሳይ ኤምባሲ በኩል እነማን ሄዱ እነማን ተመለሱ የሚለው እንዲጣራ ጠይቀናል፤ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በ64 ሚሊዮን ብር ወጪ የውሃ ማምረቻ ፋብሪካ ለማሰራት ማሽኖችን ከውጪ አስገብቷል። የገቡት ማሽኖች እውነት ለፋብሪካው ስራ የሚጠቅሙ ናቸው የሚለው ይጣራል” ሲሉም አጠቃላይ የክሱን ጭብጥ አስረድተዋል።

ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው መንግሥታዊ ተቋም ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ዳኝነት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ያቀረብነው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘቱ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንደ ወሰዱትም ጠበቆቹ አብራርተዋል። በዚህም ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ችሎቱ ፊት ቀርቦ ምላሽ እንደሚሰጥና ለደረሰው ጉዳትም ወጪን እንደሚሸፍን ገልፀዋል።

‹‹በግልና በኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ላይ የተወሰነው የ11 የባንክ ሂሳብ ቁጥር እገዳ ጊዜያዊ ነው። እገዳው እስከ ችሎቱ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የጸና ነው” በማለትም ሂደቱን ገልጸዋል።

“ግለሰባዊ አጀንዳ የለንም፤ ይሰቀል ይገደል የምንለው ሰውም የለም፤ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር የገጠምነው ክርክር ዋናው ዓላማ ስፖርቱን ለመታደግ ብቻ ያደረግነው መሆኑ ታሳቢ እንዲደረግ እንጠይቃለን” ሲልም ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ተናግሯል።

የጠበቆቹን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሰጠው ባለ 6 አቋም የምላሽ መግለጫ “ከሳሾች በውሸት ቃለመሀላ ፍርድ ቤቱን ያሳሳቱ በመሆናቸው ራሳቸው በህግ የሚጠየቁበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም” ብሏል። ከዚህ ቀደም በኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ የስፖርት ትጥቆችን መርካቶ ድረስ ሄደው በመቸብቸብ በፈፀሙት ህገ ወጥ ተግባር በኮሚቴው የታገዱ አካላት ስልጣን በሌለው መደበኛ ፍርድ ቤት ከሳሽ ሆነው መቅረባቸውም እጅግ አሳፋሪ ነው” ሲል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ገልጿል።

በተጨማሪም ጠበቆቹ ‹‹በውሸት ቃለመሀላ ያገኙትን እግድ ልክ ተከራክረው እንዳሸነፉ መግለጫ መስጠታቸው የቱን ያህል በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት እንደማይሰሩ በግልፅ የሚያሳይ ነው። ሀገርን ለማስቀጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል” ሲል ኮሚቴው አስጠንቅቋል።

የስፖርት ነክ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማይታዩ እና መደበኛ ፍርድ ቤት ስልጣን እንደሌላቸው እየታወቀ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ጥያቄ ማንሳት ሲገባ የውሸት ቃለመሀላ በማቅረብ እና ተረኛ ችሎቱን በማሳሳት እግድ ያወጡበት መንገድ ከሳሽ ነን የሚሉት ግለሰቦች ተከራክረው ማሸነፍ የሚችሉበት የእውነተኛ የህግ መሰረት የሌላቸው መሆኑን ያሳያል ሲልም ኮሚቴው በመግለጫው ጠቁሟል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You