የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤቱን በኢትዮጵያ ከፈተ

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ አንድነት ፓርክ ከትናንት በስቲያ በይፋ አስመርቆ ከፍቷል። በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ መከፈቱ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ጽሕፈት ቤቱ በኢትዮጵያ መከፈቱ የቦክስ ስፖርት እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ከማስቻሉም ባሻገር በሥራ እድል ፈጠራም ሚናው የጎላ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል። በሁሉም ስፖርቶች ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጽሕፈት ቤቱ በኢትዮጵያ መከፈቱ የቦክስ ስፖርትን እንደሚያነቃቃ ገልጸዋል፡፡ በስፖርት ዲፕሎማሲ ከተለያዩ የአህጉሪቱ ክፍሎች ለመጡ ሀገራት ግንኙነት ለመፍጠር ይረዳል፡፡ መንግሥት ለስፖርቱ ከመሠረተ ልማት ግንባታ ጀምሮ ቁርጠኛ በመሆኑ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ቀጣይ ሥራዎችን አቅዶ ለመሥራት ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እያሱ ወሰን በበኩላቸው፤ ጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ ላይ እንዲከፈት መንግሥትን ጨምሮ እገዛ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በእለቱ ምሽት ላይ በዓድዋ ሙዚየም የተካሄደውን የአፍሪካ ኢንተርናሽናል ቦክሲንግ አሶሲየሽን (IBA) ውድድርን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማዘጋጀት ለስፖርቱ እድገትና ተወዳጅነት እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

የስፖርት ቱሪዝምን ከማስፋት ከሀገር ገጽታ ግንባታ እና የውጪ ባለሀብቶችን ለመሳብ እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።፡ በተጨማሪም ስፖርተኞችን ተጠቃሚ ከማድረግና የውጪ ምንዛሬ ወደ ሀገር በማምጣት ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። በአፍሪካ ስም ደላሎችና ሌሎች አካላት እስከ አሁን እየተጠቀሙ እንደነበረና ያንን በማሸነፍ ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ እንዲካሄድ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም መሰል ትላልቅ ውድድሮችን ለማድረግ እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡

በምረቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ የኪነ-ጥበብ ሥነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የቦርድ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዓድዋ ሙዚየም ከ51 እስከ 96 ኪ.ግ ክብደት ባሉ የውድድር ዘርፎች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቦክስ ፍልሚያ አድርገዋል፡፡ በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ7 ሀገራት የተወጣጡ ቦክሰኞች ተሳትፈዋል። አንድ የሴቶችና ስድስት የወንዶች ፍልሚያ ፕሮፌሽናልና ሁለት ሴሚ ፕሮፌሽናል ግጥሚያዎችም ተከናውነዋል።

ኢትዮጵያን በ60 ኪሎ ግራም የወንዶች ፍልሚያ የወከለው አቡበከር ሰፋን ከ ጋናው ጆሴፍ ኮሜይ ጋር በ 6 ዙሮች ፍልሚያ ጥሩ ፍክክር አድርጎ ተሸንፏል፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ተመስገን ምትኩ በ75 ኪሎ ግራም ከሞሮኮው ቦክሰኛ ያሲን ኢሎራዝ ጋር የ3 ዙር ፍልሚያ አድርጎ ድል አልቀናውም።

በወንዶች 80 ኪሎ ግራም ከባድ ሚዛን ፍልሚያ ታንዛኒያዊው ዩሱፍ ቻንጋላዌ ከዲሞክራቲክ ኮንጎው ፒታ ካቤጂ በ8 ዙር ተፋልሞ አሸናፊ ሆኗል፡፡ 8 ዙሮችን በፈጀው የወንዶች 48 ኪሎ ግራም ቀላል ሚዛን ፍልሚያ ሩሲያዊው ኢድመንድ ኩሁዶዮን ሜክሲካዊውን ዳንኤል ቫላዴራዝ ገጥሞ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡ በወንዶች ተመሳሳይ 48 ኪሎ ግራም ቀላል ሚዛን ኡዝቤኪስታናዊው ኖዲርጆን ሚዝራክሜዶቭ ከካዛኪስታኑን ቴምራትስ ዝሁስፖቭ በ8 ዙር ያደረጉት ፍልሚያ በካዛኪስታናዊው ቡጢኛ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በወንዶች 80 ኪሎ ግራም ከባድ ሚዛን ፍልሚያ ታንዛኒያዊው ዩሱፍ ቻንጋላዌ የዲሞክራቲክ ኮንጎውን ፒታ ካቤጂ በ8 ዙር ተፋልሞ አሸንፎታል፡፡

በወንዶች 51 ኪሎ ግራም ቀላል የቀበቶ ፍልሚያ ዛምቢያዊው ፓትሪክ ችንዬምባ ጋናዊው አሎቲ ቲዮፊለስ በ4 ዙሮች ተፋልሞ የቀበቶ አሸናፊ መሆን ችሏል። በሴቶች መካከል በተካሄደው የ75 ኪሎ ግራም መካከለኛ ሚዛን ፍልሚያ ሞዛምቢካዊቷ ክራዲይ አዶሲንዳ ግራማኔ በናይጀሪያዊቷ ፓትሪሺያ ምፓታ በ 6 ዙር ፍልሚያ ተረትታለች።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You