ኢትዮጵያ ቱሪዝም ለሀገር የሚያበረክተውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ለመለካት እንዲቻል የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት (Tourism Satellite Account) ሥርዓት በቅርቡ ዘርግታ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ በዚህም ቱሪዝም ለአጠቃላይ የምርት እድገት 2 ነጥብ 7 በመቶ፣ ለሥራ ፈጠራ 3 ነጥብ 88 በመቶ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት (ለካፒታል ክምችት) 5 ነጥብ 2 በመቶ ቀጥተኛ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ከቱሪዝም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ከሚገለጹ ንዑስ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ምርት (ቱሪዝምን የሚወክሉ እና የኢትዮጵያን መስህቦች የሚያስተዋውቁ ቁሳቁስ እና ልዩ ልዩ ምርቶችን) እድገት አንዱ ነው። የቱሪዝም ምርት በከፍተኛ ሁኔታ የግል ድርጅቶችን፣ ማህበራትንና ግለሰብ ነጋዴዎችን በማሳተፍ አካታች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥም የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ። ንዑስ ዘርፉ በቀጥታ ከሥራ እድል ፈጠራና የኢኮኖሚ አቅምን ከማሳደግ ባሻገር የኢትዮጵያን መዳረሻዎች (ባሕላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ ሀብቶች) ለማስተዋወቅ እንደሚረዳም ይነገራል።
በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሆኑ የእጅ ሥራ ውጤቶችን፣ ባሕላዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ ቁሳቁሶች፣ ታሪካዊ ሁነቶችን የሚወክሉ እና ሌሎች መስህቦችን የሚያንፀባርቁ የቱሪዝም ምርቶች ገበያ ላይ እንዳሉ ይገለፃል። ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ካላት እምቅ አቅም አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ምርቶቹ በቱሪስቶች እጅ አይደርሱም። ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙም ቢሆን አመርቂ አለመሆኑ ይነገራል።
መንግሥት ይህንን ክፍተት መሙላት እንዲያስችል የግሉን ዘርፍ የሚያበረታቱ የድጋፍ ማሕቀፎችን በተለያየ መልኩ ያደርጋል። ማህበራትን በማደራጀት፣ ብድርና ሥልጠናዎችን በማመቻቸት የኢትዮጵያን መስህቦች የሚወክሉ አልባሳት፣ ቁሳቁስ እና ሌሎች የስጦታና ባሕላዊ መገልገያዎችን የሚያቀርቡ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ እየሠራ ነው። ከመንግሥት ድጋፍ ባሻገር በመስኩ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች እንዲሁም ወጣቶች አበረታች ጅምር እያሳዩ ነው። የዝግጅት ክፍላችን ይህንን በተመለከተ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ቃኝቷል።
ኢብራሂም ሳፊ ይባላል። የባሌ ጎባ ነዋሪ ነው። የሚኖርበት አካባቢ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ በዓለም አቀፍ ቅርስ የተመዘገበ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኝበት ነው። በቱሪዝም መስህብነት ከሚጠቀሱ የኢትዮጵያ ተመራጭ መዳረሻዎች ውስጥም አንዱ ነው።
ኢብራሂም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ አካባቢውም የሚያስተዋውቁ፤ ለጎብኚዎች የትውስታ ስንቅነት የሚያገለግሉ የጥበብ ሥራዎችን በሽያጭ ያቀርባል። የቱሪዝም ምርቶችን እና የጥበብ ውጤቶች በአካባቢው ከሚያቀርቡ ጥቂት ተመራጭ መደብሮች መካከልም የዛሬው እንግዳችን የቱሪዝም ምርት ውጤቶችን የያዘው የባሌ አርት ጋለሪ አንዱ ነው።
‹‹የጋለሪያችን መገኛ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ነው›› የሚለው መስራችና ባለቤት የሆነው ኢብራሂም ሳፊ፤ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ጎብኚዎች ፓርኩን ጎብኝተው በሚወጡበት ወቅት በጋለሪው ውስጥ የመስህብ ስፍራውን የሚወክሉ የዱር እንስሳት ቅርፅ፣ የእጅ ሥራ ውጤቶች፣ ስዕልና ልዩ የጥበብ ውጤቶችን ያገኛሉ ይላል። ይህም ወደመጡበት አካባቢ በሚመለሱበት ወቅት ማስታወሻ ከመሆኑም ባሻገር ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በስጦታ ለማበርከት እንዲችሉ እድል የሚፈጥር መሆኑን ያስረዳል።
ከቁልፍ መያዣ እስከ ትላልቆቹ የዱር እንስሳት የአካል ቅርፅ ድረስ በመሥራት በጋለሪው ውስጥ እናቀርባለን የሚለው መሥራችና ባለቤቱ አቶ ኢብራሂም፤ የባሌ አርት ጋለሪ የአካባቢውን መስህብ የሚያስተዋውቁት እነዚህ የቱሪዝም ምርቶች የሚሰሩት መልሰው ጥቅም ላይ በሚውሉ (Recycle material) ቁሳቁሶች እንደሆነ ይገልፃል። በዋናነትም ግልጋሎት ሰጥተው የሚጣሉ ወረቀቶችና የፕላስቲክ ኮዳዎች በግብዓትነት እንደሚውሉ ይናገራል።
የቱሪዝም ምርቶቹ የኦሮሚያንና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ባሕል፣ የመስህብ ሀብት እና ማንነት የሚያንፀባርቁና በማስታወሻነት ለሚገዛቸው መልካም ትዝታን የሚያላብሱ መሆናቸውን ያነሳል። ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች እየተመረቱ የሚመጡ ቁሳቁስ የዚያን ሀገር ባሕል፣ እውቀትና ጥበብ የሚያንጸባርቁና የሚያስተዋውቁ ናቸው በማለትም ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በተመሳሳይ ስለ ኢትዮጵያ እንዲያውቁ መሰል ሀገር በቀል ምርቶችን (የጥበብ ውጤቶችን) ማቅረብ ሲቻል ሀገሪቱን በይበልጥ ለማስተዋወቅ እድል እንደሚከፍት ይናገራል።
የባሌ አርት ጋለሪ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉትን የባሕል አልባሳት ለቱሪስቶች በሚመች የሥነ ጥበብና ሌሎች አማራጮች ያስተዋውቃል የሚለው አቶ ኢብራሂም፤ ሁሉም ምርቶች የጎብኚዎችን ምርጫ በሚያሟላ መልኩ እንደሚዘጋጁ ይናገራል። ይህንን ስልት መከተላቸውም የኢኮኖሚ አቅም ከመፍጠር ባሻገር የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ እድል እንደፈጠረላቸው ይናገራል።
‹‹በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከሚታወቁ የቱሪዝም መስህቦች መካከል ቀይ ቀበሮ ቀዳሚዋ ነች። በዚህ ምክንያት በርካታ ቱሪስቶችም ለጉብኝት ይመጣሉ›› የሚለው የባሌ አርት ጋለሪ መስራች፤ ቀይ ቀበሮን ለማስተዋወቅ ሁሉም ጎብኚ በቀላል ዋጋ ገዝቶ መያዝ የሚችለውን የቁልፍ መያዣ ሰርተው ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ ይናገራል። አንደ ቱሪስት ፓርኩን ጎብኝቶ ወደ መጣበት ሀገር ሲመለስ ይህንን ቁልፍ መያዣ ቢገዛ በሚኖርበት አካባቢ ስለ ቀይ ቀበሮ፣ ስለ ባሌ ብሔራዊ ፓርክ እና ስለ ኢትዮጵያ የመስህብ ሥፍራዎች የማወቅ ጉጉት በወዳጅ ዘመዶቹ ላይ እንደሚፈጠር የሚያስረዳው አቶ ኢብራሂም በቀላል አማራጭ ሀገርን በዚህ መልኩ ለመላው ዓለም የማስተዋወቅ እድል የሚፈጥር አጋጣሚ መሆኑን ይገልፃል።
የባሌ አርት ጋለሪ 12 ሰዎችን ቀጥሮ ያሰራል። በጊዜያዊነት በርካታ ሥራ እድሎችን በአካባቢው ላይ በመፍጠር ይታወቃል። እንደ መስራቹና ባለቤቱ ገለፃ ከሆነ አሁን ላይ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና መስህቦችን የሚያስተዋውቁ ምርቶችን በስፋት ወደ ገበያው ለማስገባት በዓለም አቀፍ ደረጃም ለማስተዋወቅ ልዩ ልዩ ስልቶችን እየተከተሉ ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ ጋለሪው የሚያመርታቸውን ውጤቶች በአውደ ርዕዮች፣ በዲጂታል ሚዲያ (ማህበራዊ ድረ ገፆች) ያስተዋውቃል።
አቶ ኢብራሂም ጋለሪው የቱሪዝም ምርቶችን ከማቅረብ አንፃር በባሌ ዞን ብቻ ተገድቦ እንደማይቀር ይገልፃሉ። ይህ ግብ በአጭር ጊዜ እቅዳቸው ውስጥ የተሳካ መሆኑን በመግለጽም ራዕያቸው ግን ከዚያም የተሻገረ መሆኑን ያነሳሉ። በሂደትም የኦሮሚያን የኢትዮጵያን እንዲሁም የአህጉሪቱን (የአፍሪካን) የባሕል፣ የቅርስ፣ የታሪክ እና የልዩ ልዩ ሀገር በቀል እውቀቶችን የማስተዋወቅ ራዕይን መያዛቸውን ይናገራሉ።
ቦኩ ክራፍት ይባላል። በወጣት የሥራ ፈጣሪዎች ራዕይ የተመሰረተ ነው። የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች የሚያስተዋውቁ፣ የሥራ እድል የሚፈጥሩና የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ አማራጭ ከሚፈጥሩ ተቋማት መካከል ይመደባል። የቅርብ ጊዜ ምስረታ ታሪክ ቢኖረውም ለዓለም አቀፍና ሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የተለያዩ ባሕል፣ ወግና ታሪክና ጥበብን የሚያንፀባርቁ የቱሪዝም ምርቶችን ያቀርባል። የዝግጅት ክፍላችን በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ዳሰሳ ለማድረግ በፈለገበት ወቅት ምርቶቻቸውን በኦሮሚያ የቱሪዝም ሳምንት ላይ ሲያስተዋውቁ አግኝቷቸው አነጋግሯቸዋል።
ወጣት ፋንታሁን በላቸው ይባላል። የቦኩ ክራፍት መስራች አባልና ማናጀር ነው። ቦኩ ከተመሠረተ የአንድ ዓመት ከግማሽ እድሜ እንዳለው ይገልፃል። የማምረቻ ቦታው የሚገኘው በለገጣፎ አካባቢ መሆኑን በማንሳት የቆዳ ውጤቶቸን ከባሕላዊ ጥበቦች ጋር በማዋሃድ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ ያስረዳል። ድርጅታቸው የእቃ መያዣ ቦርሳዎችን፣ አጀንዳዎችን ለስጦታ የሚሆኑ ባሕልን የሚያንፀባርቁ ልዩ ልዩ ምርቶችን እንደሚሰራ ይናገራል።
‹‹ምርቶቻችን ቱሪዝምን የሚያበረታቱ ናቸው›› የሚለው ወጣት ፋንታሁን፤ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለጉብኝት፣ ለስብሰባ እና ለልዩ ልዩ ምክንያት የሚመጡ ዜጎች እነዚህን ምርቶች ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ያስረዳል። ከመገልገያ ቁስነታቸው ባሻገር ባሕልን፣ ሀገር በቀል እውቀትንና የኢትዮጵያን የመስህብ ሥፍራዎች በማስተዋወቅ ልዩ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ያነሳል። ተጠቃሚዎች ለጉዞ እቃ መያዣነት፣ ለስፖርት ትጥቅ፣ ለሌሎች እቃዎች መያዣነት እነዚህን ምርቶች እንደሚጠቀሟቸው የቦኩ ማናጀር ይናገራል።
የቆዳ ምርቶች በአብዛኛው ጊዜ ብቻቸውን እንደሚሰሩ የሚናገረው መስራችና ማናጀሩ ወጣት ፋንታሁን ባሕላዊ እሴትና እውቀቶች እንደማይካተትባቸው ያስረዳል። ቦኩ ክራፍት ይህንን ልምድ ለመቀየር በማሰብ መመስረቱን ይናገራል። በዚህም የኢትዮጵያን ባሕላዊ የእጅ ጥበብ ውጤቶች ባሕል፣ ታሪክ እና መስህብ በምርቶቻቸው እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ይገልፃል። በጥረታቸውም ተደራሽነታቸውን እያሰፉ መሆኑን የሚናገረው ማናጀሩ ቱሪዝም ላይ የሚሰሩ የግል ካምፓኒዎች፣ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከተዋቀሩ የመንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ጋር መቀናጀታቸውን ይናገራል። በቅርቡ በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ ምርቶቹን ለዓለም አቀፍና ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ሱቅ መክፈታቸው ይገልፃል።
ዓለም አቀፍ ገበያን ሰብሮ ለመግባት ጠንከር ያለና ተለዋዋጭ ስልት እንደሚያስፈልግ የሚገልጸው የቦኩ ክራፍት ማናጀር፤ በሀገር ውስጥ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ከመቀናጀት ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የቦኩ ክራፍት ምርቶችን ለማስተዋወቅ የሚያግዙ አውደ ርዕዮች ላይ አንደሚሳተፉ ይናገራል። ከእነዚህ አውደ ርዕዮች መካከል በየዓመቱ በኢትዮጵያ የሚዘጋጁ የቱሪዝም ሳምንቶች እንደሚገኙበት ይገልፃል። እንደ ኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ያሉ አውደ ርዕዮች የቦኩ ክራፍት የቱሪዝም ምርቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚረዱም ይገልፃል። በዚህ አውደ ርዕይ ላይ የሚሳተፉ የአፍሪካና የሌሎች ዓለም ክፍሎች ሀገራት የቱሪዝም ዘርፉ ካምፓኒዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ዓለም አቀፍ አድማሱ ለማስፋት እየሰራ እንደሆነ ይናገራል።
‹‹በቦኩ ክራፍት የሚሰሩ የቱሪዝም ምርቶችን በኢ ኮሜርስ አማራጭ ለማቅረብ እየሰራን ነው›› የሚለው ወጣት ፋንታሁን፤ በማህበራዊ ሚዲያ ቦኩ ክራፍት የሚያስተዋውቃቸውን ምርቶች በማዘዝ የሚጠቀሙ የሀገር ውስጥና የውጭ ተጠቃሚዎች እየበረከቱ መሆኑን ይገልፃል። በቅርቡ ምርቶቹን በተሻለ የቴክኖሎጂ አማራጭ የማስተዋወቅ እና በኢ ኮሜርስ ገበያው ላይ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ምርቶችን ለማድረስ እየሠሩ መሆኑን ያስረዳል። የዚህ ጥረት አካል የሆነውን ድረ ገፅ ገንብተው ማጠናቀቃቸውን የሚገልጸው ማናጀሩ፤ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉም ይናገራል። በዋናነት ትኩረታቸው ዓለም አቀፍ ቱሪስቱና ገበያው መሆኑን ተናግሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢኮሜርስ ገበያዎች (እንደ አማዞን ወዳሉ) ተደራሽ የመሆን እቅድ መያዛቸውን ይገልፃል።
እንደ ቦኩ ክራፍት ማናጀር ገለፃ መላው ኢትዮጵያ ያለውን የቱሪዝም መስህብ ሀብት ድርጅታቸው በሚሰራቸው የእጅ ጥበብ ውጤቶች ለመወከልና ለማስተዋወቅ ይሰራሉ። በተለይ ከውጭ ሀገር ዜጎች በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ባሕላዊ ምርቶች በቋሚነት የመጠቀም ልምድ እንዲኖራቸው ግንዛቤውን ለመፍጠር እንደሚሰሩም ያስረዳል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመሥራት ያሰቡትን እቅዳቸውን ማሳካታቸውን በመግለጽ በረጅም ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም ኢትዮጵያን በመወከል የሀገሪቱን ቱሪዝም የሚያነቃቁ፣ የሚያስተዋውቁና የቱሪስቱን ፍሰት ለመጨመር አጋዥ የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚሳተፉ ያስረዳል።
ሙሉ ለሙሉ በእጅ ብቻ የሚሰሩ የቱሪዝም ምርት ጥበቦችን ተደራሽ በማድረግ ተመራጭ የመሆን እቅድ እንዳላቸው ይገልጻል። ምርቶቹ ለቱሪስቶች በቀጥታ እንዲደርስም በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በሁሉም የመዳረሻ ሥፍራዎች ላይ ለመገኘት የሚያስችል አማራጭ ለመፍጠር ከፌዴራልና ከክልል ቢሮዎች ጋር እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቋል። ይህ ሂደትም በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ አመልክቷል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም