በአገር ደረጃ ሰላም ሰፍኖ ማየት የብዙዎች ፍላጎት ቢሆንም ጥቂት የማይባል አካል ግን ሰላምን ለማደፍርስ በብርቱ ሲጥር ይስተዋላል፡፡ ኢትዮጵያ አንዱን ችግር ታግዬ ጣልኩ ስትል ሌላ ተግዳሮት ደግሞ ከፊቷ ድቅን እያለ የልማት ሩጫዋን ለማስቀረት እግሯን ለመያዝ ይፈጨረጨራል፡፡ ይሁንና ታግላ እየጣለችና ድል እየተጎናጸፈች ዛሬ ላይ መድረስ ችላለች፡፡ እንዲያም ሆኖ በሙሉ አቅሟ ፊቷን ወደሰላም እንዳትመልስ የሚደረጉ ሴራዎች አሁንም እንዳሉ ይታወቃል፤ ያንንም ቢሆን በተለመደው ብርታቷና በዜጎቿ ጥረት ለማለፍ የተቻላትን ሁሉ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ከዚህም አንዱ እምቢኝ! ብለው የያዙትን ዓላማ ከሰላማዊ ትግል ይልቅ ወደትጥቅ ትግል ወስደው ወደበረሃ ገብተው የሰነበቱ የተለያዩ ታጣቂ ኃይላት ጋር የተለያዩ ድርድሮችን በማካሄድ የሰላም እጇን መዘርጋት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ ከዓመታት በፊት ወደበረሃ ወርዶ ዓላማዬን በኃይል በመታገል አሳካለሁ ሲል ከነበረ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል፡፡ አዲስ ዘመንም ከዚህ ግንባር ሊቀመንበር ከሆኑት ከአቶ ጋትሉዋክ ቡም ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አቶ ጋትሉዋክ አንደኛ ዲግሪያቸውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች በኃላፊነት የሰሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በክልሉ ከተማ ልማት ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ በተመሳሳይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝምን ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊነት መርተዋል፡፡ እንዲሁም የጥቃቅንና አነስተኛ እና በክልሉ ትምህርት ቢሮም በኃላፊነት ደረጃ አገልግለዋል፡፡
የክልሉ መምህራን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአስተዳደር ዲን ሆነም ሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ የኃላፊነት ስራ በኋላ ከአመራር እርከን ወርደው በባለሙያ ደረጃ ተመድበው እየሰሩ የነበሩና ከዚያም ነፍጥ አንግበው ለመታገል ወደበረሃ የወረዱ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅትም መንግሥት የሰጠውን ዕድል ተጠቅመው በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡ ከእኚህ ከወቅታዊ እንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ሰላምን የሚገልጹት እንዴት ነው? ፋይዳውስ ምንድን ነው ከሚለው ጥያቄ ቃለ ምልልሳችንን እንጀምር?
አቶ ጋትሉዋክ፡- እኔ ሰላምን የምተረጉመው ማንኛውም ዜጋ በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደቤቱ መመለስ ሲችል ነው:: ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት እኩል መብት ሲኖረው እና ይህ መብት ደግሞ በአግባቡ ሲጠበቅለት ነው :: ጉዳዮቻችን በሕግ እና በሕግ ብቻ ሲታዩ ማለት ነው :: አንዱ የበላይ ሌላው ደግሞ የበታች የሚሆን ከሆነ ግን ሰላም ያለ የሚመስለው ለጊዜው እንጂ ዘለቄታ አይኖረውም::
የትኛውም ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው ሰላም እንዳይኖር የሚያደርጉ ምክንያቶች አሉ:: ከእነዚህ መካከል ዋንኞቹ ናቸው ብዬ ከምጠቅሳቸው አንዱ የምለው የሰው ልጅ እኩልነት ሳይረጋገጥ ሲቀር ነው:: ሌላው ደግሞ መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት ሳይሟላ ሲቀር ነው:: ከዚህ ጎን ለጎን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጠር ከሆነም ሰላም ምኞት ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል::
ሰላም የማይኖር ከሆነ አገር የምታጣው ብዙ ነገር አለ:: በተለይም የአገር ኢኮኖሚ ከማደግ ይልቅ ማሽቆልቆል ይጀምራል፤ ከዚህ በተጨማሪ አምራች የሆኑ ዜጎችን አገር ለማጣት ትገደዳለች:: ይህ ሲሆን ቀደም ሲልም የነበራት ገጽታም የምታጣ ትሆናለች:: ይህ እንዳይሆን ደግሞ መንግሥት ለሰላም መስፈን ሲል እያከናወናቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች መልካም የሚባል ነው:: ይህ አካሄዱም የሚያስደንቀው እና የሚያስመሰግነውም ጭምር ነው:: ይህን መልካም ስራ በቀጣይም እንዳይደፈርስ በማድረግ አጠናክሮ የሚያስቀጥል ከሆነ የያዘውን ግብ ከዳር ያደርሳል የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑ ሰላማዊ ትግሉን ለመቀላቀል ጥሪ ተቀብላችሁ መጥታችኋል፤ እርስዎ ይመሩት የነበረው ድርጅት ዋና ዓላማው ምን ነበር?
አቶ ጋትሉዋክ፡– የድርጅታችን ዋና ዓላማ የነበረው የበለጸገ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው:: በተለይም የራሱን መብት በራሱ መወሰን የሚችል ማኅበረሰብ ለመፍጠር ነበር የትጥቅ ትግል ውስጥ የገባነው:: በተለይም የጋምቤላ ሕዝብን ከጭቆና እና ከረሃብ ጎዳና ማስወጣት ዋናው ዓላማ ነው:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ እኩልነትን ለማረጋገጥም ሲባል ነበር ወደበረሃ ለመውረድ የተንደረደርነው::
ወደ በረሃ ከመሄዳችን በፊት በዚያው በጋምቤላ ውስጥ ሆነን ለመታገል ሞክረን ነበር:: ይሁንና እንዳስበነው ሊሆንልን አልቻለም:: በዚህ የተነሳ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ እና አስገዳጅም ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ምርጫችን ወደ በረሃ በመውረድ መታገል ነበር::
በዚህ ውስጥ እያለን በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ጥሪ ተደረገልን:: በተደረገልን ጥሪ መሰረትም መልሰን እንደድርጅት መነጋገር እና መወያየት ጀምርን:: ከተወያየንም በኋላ ለሰላም ያለንን ቁርጠኛነት ለማሳየት ተዘጋጀን::
የሰላም ቁርጠኝነታችን ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ ይህንን የሰላም ፈላጊነታችንን እናረጋግጥላቸው በሚል ወስነን ወደ ሰላማዊ ትግል ፊታችንን ለማዞር ተስማማን:: ለዚህም ነው የበረሃ ትግልን ወደጎን በማድረግ ሰላማዊ የሆነ ትግል ለመታገል የመጣነው::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንደጠቀሱት የድርጅቱ ዓላማ የበለጸገ ማኅበረሰብ መፍጠር እና በተለይም የጋምቤላን ሕዝብ ከጭቆና ጎዳና ማስወጣት ነው፤ በዚህ ዓላማ ለምን ያህል ጊዜ ታገላችሁ? ያገኛችሁትስ ውጤት ምን ነበር?
አቶ ጋትሉዋክ፡– የውስጥ ትግል በመተው ወደበረሃ ወርደን የቆየነው ለሁለት ዓመት ያህል ነው:: በነበርንበት የትጥቅ ትግል ውስጥ ሆነን ማንኛውም በትጥቅ ትግል ውስጥ ያለ ድርጅት ሊያጋጥመው የሚችለው ችግር ገጥሞናል ከዚህም ውስጥ ወደ በረሃ አብረውን የወረዱ የምንወዳቸው የትግል አጋሮቻችንን በሞት አጥተናል::
በሞት ያጣናቸው ጓዶቻችን ከጎናችን ባለመኖራቸው የሚያስቆጭ ነው:: በትጥቅ ትግል ወቅት የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም ጓዶቻችን አሉ:: ከዚህም በተጨማሪ የደረሰበን ብዙ እንግልትም አለ::
በእርግጥ የጓዶቻችንን ከአጠገባችን ማጣት ቁጭታችንን ከፍ ያደረገው ነው:: ይሁንና የሕዝብ ጥያቄ ያለመሳሪያ ድምጽ መመለስ የሚቻል ከሆነ ስለምን መስዋዕትነት እንከፍላለን ወደሚለው አመለካከት መምጣት ችለናል:: ይህ ደግሞ መሆን አለበት ብለን የምናምንበት አመለካከት ነውና ወደዚህ ጉዳይ መምጣት ችለናል:: ምክንያቱም የያዝነው የሕዝብ ጥያቄ መሰረታዊ እና ሕገ መንግሥታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ናቸው:: እነዚህ ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች እስከሆኑ ድረስ መመለስም ያለባቸው በሰላማዊ መንገድ ብቻነው ብለን እናምናለን::
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ሕገ መንግሥታዊ ናቸው ያሏቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ነበሩ?
አቶ ጋትሉዋክ፡- ሕገ መንግሥታዊ መሰረት ያላቸው ጥያቄዎች ናቸው ካልናቸው መካከል አንዱ የእኩልነት ጥያቄ ነው:: ለምሳሌ በጋምቤላ ከልል ውስጥ የሚገኙ ነባር ብሔረሰቦች በእኩል እየተዳኙ እና መሰረታዊ አገልግሎት ብሎም የፖለቲካ እኩል ተጠቃሚ ናቸው ማለት አንችልም ነበር:: በዚህ የእኩል ተጠቃሚነት ላይ ችግር አለ:: ለምሳሌ ከስልጣን ብሎም ከሀብት ክፍፍል ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችል ነው:: ይህ ብቻ ሳይሆን ሌላም ችግር አለ::
እውነቱን ለመናገር በብልጽግና ጊዜ እንደ አገር የተጀመሩ በጣም በርካታ ጠንካራ ስራዎች አሉ:: እነዚህ ጠንካራ የምንላቸው ስራዎች ልክ እንደሌላው ክልል ሁሉ በጋምቤላ ክልል ውስጥ መታየት መቻል አለባቸው ባይ ነን:: ለምሳሌ እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት እየተከተልን ያለው ስርዓት የኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን ስርዓት ነው:: ይህን የኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን ስርዓት እስከተከተልን ድረስ በጋምቤላም ክልል መሆን ያለበት በዚሁ መሰረት ነው የሚል እምነት አለኝ::
ስለዚህ የመጀመሪያው ክልሉም መመራት ያለበት በብዙኃን ነው ባይ ነኝ:: ሁለተኛው ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለውም የብሔር ውክልና እስከሆነ ድረስ ያንኑ ማድረግ ተገቢ ነው:: ምክንያቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስሌቱ በሬሽዮ የሚሰራ ሲሆን፣ ለምሳሌ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ እንዲሁም ከሶማሌ እና ከሌሎችም እንደሆነው ሁሉ ጋምቤላ ላይም ተግባራዊ መደረግ አለበት እንላለን::
ጋምቤላ ክልል ላይ ለምሳሌ የኑዌር ብሔረሰብ በሕዝብ ብዛት ስሌት ሲታይ ከጋምቤላ ክልል 47 በመቶ ያህል ነው:: በተመሳሳይ ስሌት ሲታይ የአኙዋክ ብሔረሰብ ደግሞ 21 በመቶ ነው:: ማጃንግ ደግሞ አራት በመቶ ሲሆን፣ ኮሞ እና ኦፖ 08 በመቶ ነው:: ሌሎች የተቀሩት ደግሞ ከመሃል ኢትዮጵያ የመጡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሆኑ ኢትዮጵያውያን ብሔር እና ብሔረሰቦች ናቸው:: ስለዚህ ይህን መሰረት በማድረግ በክልሉ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ይሁን የውክልና አሰጣጥ ይስተካከል የሚል አቋም ነው ያለን::
ምክንያቱም ከማዕከላዊ መንግሥት አሰራር የምንለይበት ምንም ዓይነት ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም:: እየተዳደርን ያለነው በአንድ መንግሥት ነው:: ከዚህ ውጪ መሔድ እንደሌለብንም ስለምናምን ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ ይደረግ ነው እያልን ያለው::
ካለፈው ምርጫ ጋር በተያያዘም ቅሬታ ነበረን፤ በምርጫው እኔም እንደ አንድ ግለሰብ ተወዳድሬያለሁ:: በወቅቱ እኔ ስወዳደር የነበረው የጋምቤላ ነጻነት ግንባርን ወክዬ ሳይሆን በሌላ ድርጅት ውክልና ነበር::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የሰላም ትግሉን እንድትቀላቀሉ ጥሪ ደርሷችሁ አምናችሁበት ከመጣችሁ በኋላ የተስማማችሁበት ጉዳይ ይኖር ይሆን?
አቶ ጋትሉዋክ፡- አዎ! የተስማማንባቸው ጉዳዮች አሉ:: ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ቀደም ሲል የነበርንበት ይታወቃል፤ ስናካሄድ የነበረውም የትጥቅ ትግል እንጂ የሰላም ትግል አልነበረም:: ስለዚህም የደረሰንን ጥሪ ተቀብለን በሰላም ለመታገል ስምምነታችንን በፊርማችን አረጋግጠናል:: በአሁኑ ወቅት ቀደም ሲል በጋምቤላ ነጻነት ግንባር ስም ላለፉት ጊዜያት ሲታገል የነበረ ኃይል ከዚህ በኋላ በኃይል ታጥቆ የሚታገል አይሆንም::
ሰላምን የምንፈለግ በመሆናችን የሰላም ትግሉን በይፋ ተቀላቅለናል ማለት ነው:: ይህ በራሱ ራሱን የቻለ ዋና ስምምነት ነው ባይ ነኝ:: በሌላ በኩል ደግሞ የታጠቁ አባላቶቻችን የትጥቅ መሣሪያቸውን መፍታት ብቻ ሳይሆን ወደ ስልጠናም እንዲገቡ ተደርጓል:: ከዚህ በተጨማሪ በእስር ቤት የነበሩ የእኛ አባላት ከእስር እንዲፈቱም ላቀረብነው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡን ተስማምተናል:: በዚህ ጉዳይም ሕገ መንግሥቱን መሰረት ያደረገ ፊርማ ተፈራርመናል:: በተለይ ደግሞ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥም ነው ተስማምተን የተፈራረምነው::
አዲስ ዘመን፡- በማረሚያ የሚገኙ አባላቶቻችሁ ምን ያህል ናቸው? ምን ያህሉ ታራሚስ ነው እንዲፈታ ከስምምነት የደረሳችሁት?
አቶ ጋትሉዋክ፡- እንዲፈቱልን ከስምምነት ላይ የደረስነው 15 አባላት ናቸው:: ከዚህ በፊት በፌዴራል ደረጃ የታሰሩ አባላት ነበሩ:: ነገር ግን እነርሱ ተፈትተዋል::
አዲስ ዘመን፡- የትጥቅ ትግሉን በመተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሔድ ወስናችኋልና ከክልሉ መንግሥት ጋር በምን ዓይነት ሁኔታ ለመጓዝ ነው ያቀዳችሁት?
አቶ ጋትሉዋክ፡- የሰላም መንገድ ለመከተል እስከመጣን ድረስ ከክልሉ መንግሥት ጋር ለመስራት ያሰብነው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ነው:: በተለይም በምንጋራቸው ጉዳዮች ላይ መስራት የሚጠበቅብን በጋራ እና በአንድነት ነው ብዬ አስባለሁ:: ምክንያቱም ከሰላም ብዙ ማትረፍ ይቻላል በሚል መንፈስ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሔድ እስከተስማማን ድረስ የክልሉ የሰላም ጉዳይ ይመለከተናል:: ክልሉ ሰላም ሆነ ማለት የሁላችንም ሰላም ተጠበቀ እንደማለት ነው:: ክልሉ ሰላም ሆነ ማለት ልማቱም እድገቱም ይመጣል:: ለዚህ ደግሞ በአብሮነት መስራቱ ተገቢ ይመስለኛል::
ሌላው ቀርቶ የሚነሱ የእኩልነትም ሆኑ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ቢኖሩ በጋራ በመስራት የተሻለ እድገት በማስመዝገብ መመለስ የሚቻል ሲሆን ይህም ስራ የጋራ ስራ ይሆናል የሚል አተያይ አለኝ:: ምክንያቱም የእኛ ፍላጎት ከክልሉ ጋር በኅብረት መስራት ነው:: ይህ ግን በቀጣይ በጋራ የምናየው ጉዳይ ይሆናል ብዬ አስባለሁ እንጂ አሁን ላይ ሆኜ እርግጠኛ መሆን እና መገመት አልችልም::
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዴ በጋምቤላ ክልል በኩል ኢትዮጵያ የምትዋሰንበት ድንበር አካባቢ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ፤ በዚህ ጉዳይ ያልዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ጋትሉዋክ፡- በእርግጥ ይህ ራሱ የጋራ ስራ ነው እንጂ የክልሉ መንግሥት ስራ ብቻ አይደለም የሚል እምነት አለኝ:: ደግሞም የፌዴራል መንግሥትም ስራ ነው:: በተለይ ደግሞ በጋምቤላ ክልል በኩል ከደቡብ ሱዳን ጋር የምንጋራው ድንበር ስላለ አንዳንድ ችግሮች ሲከሰቱ ይስተዋሉ ነበር:: በእርግጥ ችግሩ ወደከፋ ደረጃ ከመዝለቁ በፊት መንግሥት ከክልሉ ጋር በመሆን መፍትሔ ያለውን እያስቀመጠና እየሰራ እዚህ መድረስ ተችሏል::
እንደሚታወቀው ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል የሚገቡ የሙርሌ ጎሳዎች አሉ:: ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ የሚያመላልስ ቡድንም አለ:: ይህ በተለይ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን መከላከል በዋናነት የፌዴራል መንግሥት ስራ ነው:: ከዚህ ጎን ለጎን የክልሉ መንግሥት ብሎም እኛም አጋር ሆነን የአገራችንን እንዲሁም የክልላችንን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለብን እረዳለሁ:: በዚህ አጋጣሚ እንዲያውም እኛ በጋራ ለመስራት ቆርጠን ተነስተናል፤ ይህ የሚሆነው ግን የክልሉ መንግሥት ዕድል ሲሰጠን ነው::
አዲስ ዘመን፡- እናንተ የትጥቅ ትግሉን ትታችሁ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መጥታችኋል፤ ከዚህ በኋላ ክልሉም አገርም ሰላም እንዲሆን ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ጋትሉዋክ፡– ከዚህ በኋላ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ መሰረታዊ የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ነው:: እንደ እኔ እምነት መሰረታዊ የሆኑ የመብት ጥያቄዎች ወይም የአንድ ማኅበረሰብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የሌላውን ማኅበረሰብ የማይጎዳ እስከሆነ ድረስ ለጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ያን ያህል የሚከብድ ነው ብዬ አላስብም:: እናም መሰረታዊ የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ብሎም ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች መፍትሔ ማግኘት አለባቸው::
እነዚህ ጥያቄዎች በማይመለሱበት ሁኔታ ብዙ ሰላም አለ ማለት አያስደፍርም:: ጥያቄዎች በሰለማዊ መንገድ ባልተመለሱበት ቦታ ሰላም መጣ ቢባል የተቀበረ ፈንጂ ይሆናል እንጂ ትክክለኛ ሰላም ነው ለማለት ያስቸግራል::
ስለዚህ መሆን ያለበት ነገር ቢኖር መሰረታዊ የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን፣ ይህም ማለት የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም ማለት ነው:: ይህ ሲሆን በአገር ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል::
ለምሳሌ የእኛን ድርጅት መውሰድ ትችያለሽ፤ እኛ በተደረገልን የሰላም ጥሪ አገር ውስጥ ገብተናል:: ይሁንና አንግበን የነበሩ ጥያቄዎች ገና አልተመለሱም:: ቢሆንም የእኛ አመለካከት በመጀመሪያ ለሰላም ቅድሚያ እንስጥ የሚል ነው:: ምክንያቱም ሰላም ከሁሉ መቅደም ያለበት ጉዳይ ነው:: ሰላም በሌለበት የማንንም መብት ለማክበር ያስቸግራል:: ጥያቄ ለማስመለስም ሆነ በጋራ ለመልማት የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው:: የሕዝብ ጥያቄን መመለስም የሚቻለው ሰላም ሲረጋገጥ ነው:: ይህ ሰላም የሚመጣው ደግሞ በአንድ አካል ብቻ በሚደረግ ጥረት ሳይሆን በጋራ ነው:: እኛም ይህን በመገንዘብ የሰላሙ አካል ለመሆን ፈቅደን ነው ወደ አገራችን የገባነው::
አዲስ ዘመን፡- የተረጋጋች አገርን ከመመስረት አኳያ የእናንተ ድርሻ ምን ይሆናል?
አቶ ጋትሉዋክ፡- የእኛ ድርሻ የሚሆነው የተመኘነው ሰላም ሙሉ በሙሉ እንዲረጋገጥ ከመንግሥት ጎን በመሆን በጋራ መስራት ነው:: እንደ አንድ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ብሎም ለሰላም እንደሚተጋ ድርጅት የበኩላችንን ለሰላም መደረግ ያለበትን ስራ ሁሉ እንሰራለን ብዬ አምናለሁ:: በሌላ በኩል እንደ ዜጋ ሲታይ ለሰላም የተቻለኝን ሁሉ ለማበርከት ግዴታ እንዳለብኝ ይሰማኛል:: ስለዚህም በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለብን:: ለዚህ ነው ስለሰላም ሲባል ከመንግሥት ጎን በመሆን እንሰራለን የሚል አቋም የያዝነው::
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት እንደ አገር የያዛቸው ትልልቅ አጀንዳዎች አሉት፤ ከዚህ አኳያ ለተፈጻሚነታቸው የእናንተ ሚና ምንድን ነው?
አቶ ጋትሉዋክ፡- የእኛ አስተዋጽኦ የሚሆነው በመንግሥት የተያዙ ትልልቅ አጀንዳዎች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው አቅማችን በፈቀደው ሁሉ በጋራ መስራት ነው:: ልማቱ ለአገራችን የሚደረግ ስራ እስከሆነ ድረስ እኛም የዚሁ ተጠቃሚዎች ነንና የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁዎች ነን::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን መረጃ ከልብ ላመሰግንዎ እወዳለሁ::
አቶ ጋትሉዋክ፡- እኔም ዕድሉ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 23/2015