“አፋር ኋላቀር ነው እየተባለ የሚነገርበት ነጠላ ትርክት ዛሬ ላይመለስ ተቀብሯል” – አቶ መሐመድ አሊ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ

“አፋር ኋላቀር ነው እየተባለ የሚነገርበት ነጠላ ትርክት ዛሬ ላይመለስ ተቀብሯል”

– አቶ መሐመድ አሊ

የአፋር ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ

 

የአፋር ክልል በማዕድን ሀብትና በእንስሳት ሀብቱ የሚታወቅ ነው። ይህን ሀብት በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ደግሞ የክልሉ አመራርና ሕዝብ ድርሻ ነው። ክልሉ ባለው የተፈጥሮ ጸጋ እና ምቹ የሆነውን የመንግሥት አስተዳደር በማድረግ እንደ ሀገር በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ምን አከናወነ? ያለውን የመልማት ጸጋ በመጠቀም ለዜጎች ያመቻቸው የሥራ ዕድል ፈጠራ ምን ይመስላል? ቀደሞ በነበረው በኢህአዴግ መንግሥት እና በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱን እየመራ ባለው በብልፅግና መንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት የሚገልጸው እንዴት ነው? በሚሉና መሰል ጥያቄዎች ዙሪያ የዝግጅት ክፍላችን በተጠየቅ ዓምዱ ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት አቶ መሐመድ አሊ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ዘመን፡- በአፋር ክልል ከብልፅግና መንግሥት በፊትና በኋላ ያለው ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?

አቶ መሐመድ፡- አፋር ከብልፅግና መንግሥት በፊት እና አሁን በብልፅግና መንግሥት ያውን ስናጤን ከብልፅግና መንግሥት በፊት ያለው ምን እንደሚመስል በሁለት መልኩ ከፍሎ ማየት አስፈላጊ ነው። እንደሚታወቀው ከብልፅግና መንግሥት በፊት አፋር አጋር ከተባሉ ክልሎች አንዱ ነበር። የፖለቲካ ተሳትፎ የለውም። ሲተዳደር የነበረው በሞግዚት አስተዳደር ሲሆን፤ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ረገድ የነበረው ኢ-ፍትሐዊነት ነው፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ አይችሉም፤ አያውቁም፤ እየተባለ ሕዝቡ በሀገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠረ ነበር። ከእዚህም በተጨማሪ በርካታ ሰብአዊ በደል ሲደርስበት የነበረ ሕዝብ ነው። ምክንያቱም የሕግ የበላይነት የሚባል ነገር የለም። በወቅቱ ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች እንደሚታወቀው ግለሰቦች ጥቂቶች ናቸው። ሀገረ መንግሥት የተዳከመባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ለግል ጥቅም ሲባል በሙስና እና ብልሹ አሠራር የተዘፈቁ፣ በከፋፍለህ ግዛ ጽንሰ ሃሳብ ሀገርን ሲገዙ፣ ሲበድሉና ሲበዘብዙ የነበሩ ሰዎች ናቸው። በእዚህ ሥርዓት ውስጥ አፋር በብዙ ተጎድቷል።

ስለዚህ የነበረው ሥርዓት አፋርን ጨምሮ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሀረሪ ከፖለቲካ ውጪ ተደረጉ። እኛ ያልነውን ብቻ ተግብሩ! በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አይመለከታችሁም! ተብሎ ነበር። ሀገራችንን የብልፅግና መንግሥት መምራት ከጀመረ በኋላ ግን አፋር ዛሬ የፖለቲካ እኩል ተሳታፊነት ዕድል አግኝቷል። ይህም ወደ ማዕከል መጥቷል ማለት ነው። ስለዚህ ዛሬ ላይ አፋር ፍትሐዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ተረጋግጦለታል። የአፋር ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወንድሙ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ ተፈጥሮለታል። በመሆኑም ከመሰሎቹ ጋር ሆኖ አፋር ኢትዮጵያን እየመራ ነው ማለት ነው።

ሁለተኛ አፋር ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ ወጥቷል። እኔ ነኝ የማውቅልህ፤ እኔ ነኝ የማደርግልህ ከሚል አካሄድ ወጥቶ ዛሬ ላይ በነጻነት መንቀሳቀስ ጀምሯል። ራሱን በራሱ እያስተዳደረ የሚገኝ ሲሆን፤ በእውነተኛ ፌደራሊዝም ራሱን በራስ የማስተዳደር መብት የተጎናጸፈበት የለውጥ ጊዜ ላይ ነው።

አፋር አሁን ላይ ከማንም የሞግዚት አስተዳደርነትና ጣልቃ ገብነት ነጻ ወጥቶ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ችሏል። በሌላ በኩል ከብልፅግና መንግሥት በፊት ኢ- ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት ነበር። ከብልፅግና መንግሥት በፊት አፋር ላይ አንድ ፋብሪካ አልነበረም ነበር። ምንም ኢንዱስትሪ ፓርክ አልነበረም። ለይስሙላ ተንዳሆ የስኳር ፕሮጀክት ይባል ነበር። ነገር ግን ልክ እንደ ሌሎች ተቋማት የሀገር ሀብት የተበዘበዘበት ነው። የአፋር ሕዝብ ስለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሲነሳበት በጣም ያመዋል። ምክንያቱም በተንዳሆ ስም ብዙ የሀገር ሀብት ተመዝብሮበታል፡፡

ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው እንደፈለጉ የሚያደርጉበት እንጂ ለአፋር ሕዝብ የሚጠቅም አልነበረምና ነው። ዛሬ ግን በአፋር ክልል ኢንዱስትሪ ፓርክ አለ፤ በሰባት ዓመታት ውስጥ ከሦስት መቶ በላይ ፋብሪካዎች ተገንብተዋል። የጨው፣ የብሮሚን ማምረቻ ፋብሪካዎች በአፍዴራ አካባቢ ተገንብተዋል። ይህ ፋብሪካ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ነው። አፍዴራ ላይ ከ20 በላይ ፋብሪካዎች አሉ። ፋብሪካዎችን ወደ አፋር በማምጣት የአፋር ወጣት ጨው እንዲያመርት አድርጓል። ባለሀብቶች ፋብሪካ በመክፈት የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ አስችሏል። ለአካባቢው ማህበረሰብ ደግሞ እንደ ትምህርት ቤት ውሃ በመገንባት ማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል። የሥራ ባህል እንዲጠናከር አድርጓል። ይህም ሲባል ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር አስችሏል። ስለዚህ የውሃ፣ የጨው፣ የኬሚካል፣ የዳቦ ፋብሪካዎች በጥቅሉ ከሦስት መቶ በላይ ፋብሪካዎች በክልሉ ይገኛሉ።

የአፋር ክልል ከሚታወቅበት የተፈጥሮ ሀብት መካከል ማዕድን፣ ጨው፣ ወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮች ናቸው። ጨው ከብልፅግና መንግሥት በፊት ለማይገባቸው ሰዎች ተሰጥቶ ራሳቸው ሲጠቀሙ የአፋር ሕዝብ የዳር ተመልካች ነበር። በአሁኑ ሰዓት ግን በጥናት በመለየት የአፋር ሕዝብ በራሱ ሀብት መጠቀም አለበት በሚል የክልሉ መንግሥት በወሰነው ውሳኔ ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ወርቅ ከእዚህ በፊት በግለሰብ እጅ ነበር። ከወርቅ ምርት ሀገርም ሆነ የአፋር ሕዝብ ተጠቃሚ አልነበረም። አሁን ላይ ግን ወርቅና የከበሩ ድንጋዮችን የማዕድን ቢሮው፤ ሌሎችንም ሀብቶች እንዲከታተል የሚያስችል የማዕድን ኮርፖሬሽን የሚል ሌላ ቢሮ ጭምር ተቋቁሞ እየተከታተለ በተገቢው መንገድ ለክልልና ለሀገር ጥቅም እንዲሰጥ ተደርጓል። የአካባቢው ወጣቶች በርሃሌ፤ አፍዴራ ላይ ተደራጅተው የባለቤትነት ካርታ ጭምር ተሰጥቷቸው ለመንግሥት በትክክል ግብር እንዲገብሩ ተደርጓል።

በተጨማሪም በክልሉ ቱሪዝም ከእዚህ በፊት ልክ እንደሌሎች ሀብቶች በአግባቡ ማልማትና መጠቀም አልተቻለም ነበር። ከቱሪዝም ተጠቃሚ የነበሩት የማይገባቸው ሰዎች ናቸው። የክልል ቱሪዝም ቢሮ ሳያውቅና ሳይመዘገብ ሕግና ሥርዓት ባልጠበቀ መልክ ቱሩዝም ዘርፉ ይበዘበዝ ነበር። ከኢህአዴግ መንግሥት በኋላ ግን ጥናትን መሠረት ተደርጎ እየተሠራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚባሉት የትኞቹ አካባቢዎች ናቸው?

አቶ ማሐመድ፡- ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች የሚባሉት ዳሉል፣ ኤርታሌ፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ አፋምቦ፣ አፍዴራና የመሳሰሉ አካባቢዎች ናቸው። ከቱሪዝም ቢሮ ፈቃድ ይወስዳሉ፤ መክፈል ያለባቸውን ከፍለው ጎብኝተው ይመለሳሉ። ስለዚህ የቱሪስት ቁጥር ጨምሯል። የቱሪዝም ዘርፉ ልክ እንደ ሌሎች ዘርፎች በአግባቡና በትክክል ሁሉንም ያሳተፈና ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

አፋር 25 ወንዞች ያሉት ሲሆን፤ ዓመት ሙሉ የማያቋረጥ የአዋሸ ወንዝ አለው። በፊት አፋር ውስጥ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይቻልበት ነበር፤ በረሃ ነው፤ ከእዚህ የተነሳ ሰው የማይመጣበት ነው ተብሎ ነጠላ ትርክት ተተርኮበታል። የተኛ አንበሳ ተብሏል። ስለዚህ በነጠላ ትርክት ምክንያት እንዳንሠራና ያለንን ሀብት እንዳናውቅ አድርጎን ቆይቷል። ዛሬ ግን አፋር ሀብቱን በትክክል አውቋል። በመሆኑም የውሃ ሀብት ስላለ እንስሳት ከማርባት ጎን ለጎን በግብርና ሥራ ላይ እንዲሠማራ ተደርጓል። ከእዚህ በፊት በሁለት ዞን ነበር እርሻ ያለው፤ ዛሬ ላይ ግን በአምስቱም ዞኖች እርሻ ይታረሳል። ገበያ ላይ ዋጋ ያላቸው እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ፓፓያ፤፣ ማንጎ፣ ብርቱካን የመሳሰሉት አትክልትና ፍራፍሬዎች መመረት ጀምረዋል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ክልል ምን ያህል ሄክታር እየለማ ነው?

አቶ መሐመድ፡- ብዙ ሄክታር መሬት ነው እየለማ ያለው። ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በመጠን፣ በዓይነት እና በጥራት እየተመረተ ነው። ምክንቱም መሬቱ ድንግል መሬት ነው። በርከት ያለው ሕዝብ ከአርብቶ አደርነት ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት ከእዚያም ወደ አርሶ አደርነት እየተሸጋገረ ነው። አርብቶ አደሩ ጎን ለጎን እርሻ ሲጨምርበት ጥሩ ነው።

በሌላ በኩል ከኢህአዴግ ወዲህ አረንጓዴ አሻራ ለአፋር ክልል ወሳኝ ልማት ነው። ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነትና ለመሰል አገልግሎቶች የሚውለው የተለያዩ ዝርያ ያላቸው እጽዋት ዓይነቶች ተተክለዋል። ተክሎቹ ሎጊያ፣ ዱብቲ እና አሳይታ የተተከሉ ናቸው። አፋር ዛሬ ስለአረንጓዴ አሻራ፣ ስለአትክልትና ፍራፍሬ በደንብ ግንዛቤ ተፈጥሮለታል። አፋር ላይ በቆሎ አይበቅልም የተባለበት ቦታ ነበር፤ ግን አሁን ላይ እየበቀለ ነው። ስንዴና ጤፍ ጭምር ተዘርቶ እየተመረተ ነው፡፡

በሌማት ትሩፋትም አፋር አለው ከሚባለው ሀብቶች አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው። በእንስሳት ሀብት ክልሉ ይታወቃል። ግመል፣ የቀንድ ከብቶች፣ የፍየል እና የበግ ሀብት አለው። በተጨማሪም የዓሳ ሀብትም አለ። በዞን ሦስት ደጋ ሀቡር፣ ግርሌ እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ውሃ ስላለ ዓሳ ይመረታል። ሎጊያ አካባቢ የተንዳሆ ግድብ ጭምር በመኖሩ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ዓሳ ማምረት በመቻላቸው ምርቱን እስከ አዲስ አበባ በመላክ ለገበያ ያቀርባሉ።

ስለዚህ በሌማት ትሩፋት የእንስሳት ተዋጽኦዎች ቆዳን ጨምሮ ለገበያ እየቀረበ ነው። በአፋር ንብ በዘመናዊ ቀፎ ማነብ ተጀምሯል። የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ቢሮ ከሌሎች ክልሎች በተለይም ከሲዳማ ክልል ተሞክሮ በመውሰድ ዞን ሁለት ወይም ሰሜናዊ ዞን የሚባለው አካባቢ በፊት ከነበረው ባህላዊ ቀፎ ወደ ዘመናዊ ቀፎ በመሸጋር ማር እንዲመረት እየተደረገ ነው።

አፋር ሲባል አርብቶ አደር ሆኖ ሳለ ነገር ግን ወተት ያመጣ የነበረው ከሌላ ቦታ ነው። እንዳለው የእንስሳት ሀብት መጠን መጠቀም አልቻለም ነበር። ስለወተት ሲታሰብ አፋር ነው። ምክንያቱም አርብቶ አደር ነውና። ከብቶች፣ ግመሎች እና ፍየሎች በብዛት ያሉበት ክልል ነው። አሁን ላይ የግመል ወተት ለገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ወተት የሚያቀርቡበት ሸድና የገበያ ትስስር ተፈጥሯል። በሂደትም እሴት በመጨመር በማቀነባበር እንዲሸጥ ጥረት ይደረጋል።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በሰላሙ ረገድ ሲለካ ውጤቱ እንዴት ይገለጻል?

አቶ መሐመድ፡- ክልሉ በአሁኑ መንግሥት ያገኘው ትልቁ ነገር ሰላም ነው። በቀድሞ ጊዜ የተለያየ የሰላም ስጋት የነበረበት ክልል ነበር። አሁን ላይ አፋር የውስጡን ሰላም ማስጠበቅ ችሏል። አፋር በግጭቱ ጊዜም ከእዚያ በፊትም ሰላም ነው። የጎረቤቱን ሰላም ጭምር ማስጠበቅ ችሏል። ግጭቶች ይኖራሉ፤ ነገር ግን በሰላም መንገድ ይፈታሉ። የለውጡ አንዱ ትሩፋት ሰላም ነው። ግጭቶችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አይቻልም፤ ተነጋግሮ መቀነስ ግን ይቻላል። ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የነበረው ማህበራዊ ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረግ ነው። የነበረው ወንድማማችነትና ህብረ ብሔራዊነት እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ከእዚህ አንጻር በሰላም ላይ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ ናቸው።

አፋር የኢትዮጵያ ገቢ እና ወጪ ምርት የሚተላለፍበት መስመር ነው። ከጅቡቲ- ጋላፊ- መተሐራ ድረስ ያለው እንቅስቃሴ ሁሉ ፍጹም ሰላማዊ ነው። እንኳን ቀን ማታም ቢሆን የሚያልፉት በሰላም ነው።

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከመላው የኢትዮጵያ ክልሎች የመጡ ተማሪዎች በሰላም እየተማሩ ነው። በእምነታቸውና በማንነታቸው ተከብረው ባሕላቸውንና እምነታቸውን በነጻነነት የሚያራምዱበት ክልል ነው። በክልሉ ከ90 በመቶ በላይ ወጣት ነው። ስለሆነም ወጣቱን ያሳተፈ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ አመራሩ በአብዛኛው ወጣት ነው።

የብልፅግና ሥርዓት የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር አድርጓል። ወጣቱ ከወረዳ አስተዳዳሪ እስከ ቢሮ ኃላፊ መሆን ችሏል። ይህ በመሆኑ የሥርዓቱ ባለቤትነት እንዲሰማው አድርጓል።

አዲስ ዘመን፡- የከልሉ መንግሥት በሥራ ዕድል ፈጠራው ምን ያህል ሠርቷል?

አቶ መሐመድ፡- የክልሉ መንግሥት ቅድሚያ ከሚሰጠውና ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለው ጉዳይ ቢኖር የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው። ምክንያቱም አምራቹ ወጣት ኃይል ሥራ መሥራት አለበት። በሀገራቸውና በክልላቸው ተስፋ ሊኖራቸው ይገባል። በሥርዓቱ የፖለቲካ ተሳትፎ ተረጋግጦላቸዋል፤ በማህበር በመደራጀት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሠማርተዋል። በተጨማሪም በግብርና እና በእንስሳት እርባታና መሰል ሥራዎች እየተሳተፉ ነው። የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ በትኩረት እየሠራ ያለው ወጣቶች በአገልግሎት ዘርፍ፣ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች ሥራ መስኮች እንዲሰማሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ መሐመድ፡- በአፋር በመንግሥት አማካይነት መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል። ከተገነቡት መሠረተ ልማቶች የመንገድ መሠረተ ልማት ይገኝበታል። ከእዚህ በፊት መንገድ ያልነበራቸው አካባቢዎች መንገድ እንዲኖራቸው ተደርጓል። መንገድ ኖሯቸው የተበላሹ መንገዶችን ደግሞ በመጠገን ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል። ወረዳ ከወረዳ፣ ዞንን ከዞን የሚያገናኙ የጠጠር መንገዶች አሉ። በፊት ዞን ሁለት ወደ ሰሜናዊ ዞን ለመሄድ ከእዚህ ጭፍራ – አላማጣ፣ ከአላማጣ መሆኒ፣ ከመሆኒ ወደ መጋሌ ይገባል። ይህ በጣም አድካሚ ጉዞ ነበር። ዛሬ ግን በተሠራው የመንገድ መሠረተ ልማት ከሰመራ ተነስቶ ሰሜናዊ ዞን መድረስ ይቻላል።

ከሰመራ ተነስቶ ማዕከላዊ ዞን፣ ደቡባዊ ዞን፣ ፈንቲ ረሱ ዞን መድረስ ይቻላል። ምክንያቱም የመንገድ መሠረተ ልማቶች የተሠሩ ሥራዎች በሙሉ ውጤታማ ናቸው። የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነት ማደግ አንዱ ጥቅም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲጠናከር አድርጓል።

ጭፍራ ላይ ከወረባቦ፣ ከአላማጣ፣ ትግራይ ጨምሮ በአንድ ገበያ ላይ ተገናኝተው ብሔር ብሔረሰቦች ይገበያያሉ። አሳይታ ላይ ከአፋር የተለያዩ አካባቢዎች፣ ከአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ ክልል ጭምር ገበያ በጋራ የሚያካሂዱበት ነው። ይህ የሆነው በመንገድ መሠረተ ልማት አማካኝነት ነው። እናት በምጥ ስትያዝ ቶሎ ወደ ጤና ተቋም የምትደርስበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የመንገድ መሠረተ ልማት መዘርጋቱ የንግድ ትሰስር እንዲኖር አድርጓል።

ከአሁኑ መንግሥት በኋላ በርካታ ባለሀብቶች፣ ኢንቨስተሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የሚገቡባት ክልል ሆናለች። ሰመራ ልክ እንደስሟ አፋርን እንድትመስል እንደሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ያደገችና ልማት የተስፋፋባት ከተማ እንድትሆን የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራበት ነው።

አሁን ላይ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሃሳብ አመንጭነት በክልሉ የኮሪዶር ልማት እየተሠራ ነው። የመጀመሪያው የሰመራ ኮሪዶር ልማት 80 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፤ ጠቅለል ተብሎ ሲታይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቋል፤ ሁለተኛው ምዕራፍ እየተከናወነ ነው።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአየር መንገድ እስከ ቤት መንግሥት፤ ከሰመራ መግቢያ እስከ ዋናው አስፓልት ድረስ ተገንብቶ እየተጠናቀቀ ነው። በእዚህ ምዕራፍ የቴምር ዘንባባ ዛፎች ተተክለዋል። ይህ የኮሪዶር ልማት፤ መናፈሻዎች፣ የኳስ ሜዳዎች፣ ሙዚየሞች የተካተቱበት ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኮሪዶር ልማቱን በቀጣይ በክልሉ ሌሎች ከተሞች ለማከናውን እቀድ አለ?

አቶ መሐመድ፡- አዎ፤ በቀጣይ አዋሽ፣ አሳይታ፣ ዱብቲ፣ አብአላ ላይ ይጀመራል። አሁን እንደ ዋና ከተማ ሰመራ ላይ ይሁን እንጂ አፋር አሁን ሰመራን ጨምሮ ወደ ስምንት ከተማ አስተዳደሮች አሉት። ስለዚህ የኮሪዶር ልማቱ በእነዚህ የከተማ አስተዳደሮች ላይ የሚደርስ ይሆናል። የኮሪዶር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ከሌሎች ክልሎች ጋር የልምድ ልውውጥ እየተደረገ ነው። የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት በተገኙበት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተገንብቶ ተጠናቆ የሁለቱ ክልል ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ተመርቋል። በጥቅሉ በአሁኑ መንግሥት እውነተኛ ፌዴራሊዝም እውነተኛ ወንድማማችነት የታየበት ነው።

ፈተናዎች ይኖራሉ፤ ፈተና አልፏል፤ ጨርሰናል የሚባል ግን የለም። አፋር ላይ ስለብሔር፣ ስለጎጥ አይወራም። በቃ ሰው በሰውነቱ ብቻ ይከበራል። ሕዝቡ ወደ ልማቱ ዞሯል። ሕዝቡ በጋራ ልማትን በመሥራት በጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተጋ ነው። በጋራ በመሆን ሀገር በጋራ የመምራት ወንድማማችነትን ማጠናከር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመግባባት ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ሥርዓቱም የሚፈቅደው ያንን ነው። ኅብረ ብሔራዊነት፣ አቃፊነት፣ አሳታፊነት በመልካም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በክፉ ጊዜም በጋራ ሆኖ ማሳለፍንና መልካምን የጋራ አድርጎ ሀገርን በጋራ የመምራት፣ ወንድማማችነትንና አንድነትን ማጠናከር፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማጠናከር እንዲሁም በልማቱ ረገድ የመተጋገዝ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ይህ የብልፅግና ዋናው ጉዳይ ነው።

በአሁኑ ወቅት በእኛ ክልል ቅዳሜና እሑድ ሸቀጣሸቀጦችን ቀጥታ ከአምራቹ አካል በማምጣት ሕዝብ የሚያገኝበትን ሁኔታ አመቻችተናል። እንዲህ ሲባል በየአካባቢው የሚመረተውን ምርት በቀጥታ በማምጣት እንዲዳረስ ለማድረግ እየተሞከረ ነው ማለት ነው፤ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ደግሞ በስፋት እየሠራን እንገኛለን። ከሌሎች አንጻር ሲታይ እኛ ዘንድ ያን ያህል የኑሮ ውድነት የለም። እኛ ዘንድ የምርት ችግርም የለብንም። ሽንኩርት፣ ቲማቲምም ሆነ ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎች ጭምር በስፋት በመመረት ላይ ይገኛሉ።

ከእዚህ ቀደም አትክልትና ፍራፍሬ እንጠብቅ የነበረው ከጎረቤት ክልሎች ነበር። ዛሬ ግን ለጎረቤት ክልሎች ጭምር እያቀረብን እንገኛለን። ስለዚህ አትክልትና ፍራፍሬ ከጎረቤት ክልሎች ይጠበቅ የነበረው አፋር አሁን ለሌሎች ክልሎች ጭምር በማቅረብ ላይ ነው። ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እድል እየፈጠረ ነው፡፡

ሌላው የክቡር ፕሬዚዳንቱም የጠቅላይ ሚኒስትሩም ኢንሼቲቭ ነው። ክቡር ፕሬዚዳንት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ማለትም በክረምቱ ጊዜ የሚደረገው በበጎ ፈቃድ የሚሠራ ሥራ በተለይም ቤት ማደስ፣ ማዕድ ማጋራት እንደ ክልል መንግሥት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ነው። ቤት ማደሱም ሆነ ማዕድ ማጋራቱ ይህ እየሆነ ያለው በሁሉም ከተማ አስተዳደሮች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ነው። በተለይ ይህ ተግባር በኢፍጣር በረመዳን ጊዜ በስፋት የሚካሔድ ነው። በሕዝብ በዓላት ወቅትም እንዲሁ ነው።

አፋር በረሃ ነው እየተባለ ሲነገር ነበረ፤ አንድ ሰው ከየትኛውም ሀገሪቱ አቅጣጫ ወደ አፋር መሔዱን የሚናገረው ወደ በረሃ እየተጓዝኩ ነው በሚል ነው። አፋር ሁሉ ግን በረሃ አይደለም። አፋርን በረሃ ያስባለው ነገር ከእዚህ ቀደም ያለውን ሀብት እንዳያውቅ በመደረጉ ነው እንጂ አፋር ምድረ ገነት ነው። የነበረው ነጠላ ትርክት ወደ ክልሉ የሚመጡ ሰዎች ስለ አፋር እንዳያውቁ ተደርጓል። ከእዚህ የተነሳ አፋር ክልል ያለውን ሀብትና አቅም እንዳያውቅ አድርጎታል። አፋር ሙቀት አለ እንጂ በረሃ አይደለም። እኛ እየኖርን ነው። እኔን ከአዲስ አበባ ነዋሪ ጋር ብታስተያዩኝ ልዩነት የለኝም። ሙቀት ደግሞ አፋር ላይ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባም፣ መተሐራማ ሆነ አዳማና ባሕር ዳርም ሆነ ሌላው አካባቢ ይሞቃል።

ክልሉ ዛሬ የራሱን ሀብት የሚጠቀምበትን እድል አግኝቷል። በእዚያ እድል ተጠቅሞ በአሁኑ ወቅት ክልሉ እየለማ ነው። ስለዚህ እንደ ብልፅግና እንደ መንግሥትም በሀገራዊ አጀንዳ ሁሉ እኩል ተሳታፊ ከመሆናችንም በተጨማሪ ተጠቃሚነታችንም በእዚያው ልክ ሆኗል። አፋር እንደሚታወቀው ጨውን ብቻ ብንወስድ በእዚያ በጣም ሀብታም የሆነ ነው።

አፋርን የሚያቋርጠው አዋሽ ወንዝ ብቻውን እንኳ ራሱን የቻለ ሀብት ነው። አፈሩም ቢሆን ለም ነው። ማምረት የሚችል የሰው ኃይልም አለ። እኛ በአሁኑ ጊዜ የፋይናንስ ችግር የለብንም። ምክንያቱም የእንስሳት ሀብት፣ የማዕድን ሀበት፣ መሬት፣ ውሃ አለ። በእዚህ ላይ የተሟላ ሰላም ያለበት ክልል ነው። በሰላም ገብቶ በሰላም መውጣት የሚቻልበት ክልል እንደመሆኑ የሚያጨናንቅ ነገር የለም። በአፋር ጥቁር፣ ነጭ፣ ቀጭን፣ ወፍራም ብሎ ነገር የለም፤ ማንም በማንነቱ ተፈርጆ ባልሆነ ኮሮጆ ውስጥ አይገባም።

ዛሬ አፋር ኋላቀር ነው እየተባለ የሚነገርበት ነጠላ ትርክት ላይመለስ ተቀብሯል። ምክንያቱም ማን ነው ኋላቀር? ማነውስ ቀዳሚው? እንደዚያ የሚባል ነገር የለም። የምንሰማራው እኩል ነው። እንደ ሀገር በሁሉም ነገር የምንሠማራው በእኩል ደረጃ ነው። ሁሉም ክልሎች የየራሳቸው ሀብት ሊኖራቸው ይችላል። አፋርና ኦሮሚያ አንድ ዓይነት ወይም እኩል ሀብት አይኖራቸውም። አፋርና ጋምቤላ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ሌሎችም ቢሆኑ እኩል ሀብት አይኖራቸውም።

አፋር ማዕድን፣ ጨው፣ የከበሩ ድንጋዮች አሉት፤ ክልሉ የቱሪስቶች መዳረሻም ጭምር ነው። ኤርታሌ የማያንቀላፋው ተራራ በቱሪስቶች ይጎበኛል። አሁን ባለንበት በእዚህች ዓለም ላይ በአፋር እንደሚገኘው ዓይነት የሚጮህና የማያንቀላፋ ተራራ ማየት ትልቅ ነገር ነው። አዲስ ፕላኔት የተባለለት ዳሎልም እንዲሁ ነው። አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ የአፋርም የኢትዮጵያም ሀብት ነው።

የነገው ሕልማችን የሆነው ቀይ ባሕርም ቢሆን ቅርባችን ከመሆኑም በተጨማሪ ሕልማችን ተሳክቶ እውን መሆኑ አይቀሬ እንደመሆኑ ወጪ ገቢ ምርታችን በአፋር በኩል የሚያልፍ ነው። ወደብ አልባ የነበረችው ሀገር ፈጥና የባሕር በር ባለቤት ትሆናለች። ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ሆኑ ሱልጣናችን የቀይ ባሕርን ጉዳይ ሲናገሩ፤ ከኤርትራም፣ ከጂቡቲም የሚመጣበት በአፋር ነው። የኢትዮጵያ ትልቁና ብሩህ ነገሯ ቀይ ባሕር ሲሆን፤ እሱ ሲታሰብ ደግሞ አፋር የሚጠቀስ መሆኑ አይቀርም። ይህ በንግግርና በትብብር የሚመጣ ነው። ንግግርን አለመቀበል ነገር ከታየ ግን አፋር በኢትዮጵያዊነቱ ከወንድሞቹ ጋር በመሆኑ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው። ሀገራት ስንትና ስንት ኪሎ ሜትር አቋርጠው ስለ አንድ ሀብት ይገባኛል ጥያቄ ያነሳሉ። ኢትዮጵያ ግን በቅርብ ርቀት ላይ ያለውን ቀይ ባሕር ብታነሳ ክፋቱ ምኑ ላይ ነው? ግብጽ ስንትና ስንት ኪሎ ሜትር ላይ ሆና ሕዳሴ ግድብ ትሻለች። ከሰመራ ኤሊዳር 200፤ ከኤሊዳር ቡሬ ደግሞ 70 ኪሎ ምትር ነው። 270 ኪሎ ሜትርና በሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ሲጤን ምንም ንጽጽር የሚያስፈልገው አይደለም። ግብጽ ግን ርቀት ሳያግዳት ስለሚገባን ነገር አሉታዊ እየተናገረች ትገኛለች። ሽንጧንም ገትራ ትከራከራለች፤ እኛ ግን ሕልማችን የሆነውን ቀይ ባሕር ለኢኮኖሚያችን እድገት እንዲውል የምናደርገውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እውን እናደርገዋለን።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡

አቶ መሐመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You