
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አራት የቆዳ ፋብሪካዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየው “የቆዳ ልማት ዘላቂ ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት” ማጠቃለያ መርሐ ግብር ትናንት ተካሂዷል።
ማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አውሪሊያ ፓትሪዚያ እንዳስታወቁት፤ ዓለም አቀፉ የሌዘር ሥራ ቡድን ለአራት የኢትዮጵያ ቆዳ ፋብሪካዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል። ኤሊኮ አዋሽ እና ኤሊኮ አቢሲኒያ የቆዳ ፋብሪካዎች በወርቅ ደረጃ፤ ባቱ ቆዳ ፋብሪካ ደግሞ በብር ደረጃ የእውቅና የምስክር ወረቀት አግኝተዋል።
ኮልባ ታንሪ በቅርቡ የእውቅና ማረጋገጫ ኦዲቱን በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት የአቻ ግምገማ በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ያገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች ቁጥር አሁን ላይ ስድስት መድረሱን አስታውቀዋል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የቆዳ እሴት ሠንሠለት ውስጥ ያላትን ሚና ያጎላዋል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀቱ ዘርፉን ከዓለም አቀፍ የአካባቢ እና የጥራት ደረጃዎች ጋር ለማጣጣም እየተከናወነ ያለውን ጥረት አጉልቶ እንደሚያሳይ የገለጹት ሥራ አስኪያጅ፤ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ምስክር ወረቀት ያገኙት ቆዳ ፋብሪካዎች የአፍሪካን 60 በመቶውን የተረጋገጡ የቆዳ ፋብሪካዎች እንደሚወክሉ ጠቁመዋል።
አሥር የአፍሪካ ቆዳ ፋብሪካዎች በቆዳ ሥራ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት እንዳላቸው አመልክተው፤ የእውቅና ማረጋገጫው ከዓለም አቀፍ ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ በመሆኑ የገበያ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
የሞጆ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ እሸቱ ሹሜ በበኩላቸው፤ 60 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች በሞጆ ከተማ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። የቆዳ ኢንዱስትሪዎቹ ከጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ከማምረቻ ማሽን እና ጥራት ጋር የተገናኘ ክፍተቶች እንደነበረባቸው አስታውሰዋል።
ክፍተቱን ለመሙላት የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት “የቆዳ ልማት ለዘላቂ ሥራ ፈጠራ” በተሰኘ ፕሮጀክቱ አማካኝነት ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን የገለጹት አቶ እሸቱ፤ በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የቆዳ ኢንዱስትሪ ውስጥ ቁልፍ ተዋናይ በመሆን የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ማሳደግ እንደቻለች ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ 120 ሥራ አጥ ወጣቶች የቦታ፣ የማምረቻ መሣሪያ እና የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተው፤ በዚህም ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን አስታውቀዋል። ወጣቶቹ አሁን ላይ ከቆዳ ቦርሳ፣ ጫማ እና ሌሎች ምርቶችን እያመረቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከነዚህ ስኬቶች ጎን ለጎን ቆዳና የቆዳ ምርቶችን መመርመሪያ ላብራቶሪ በሞጆ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተገንብቶ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን የገለጹት አቶ እሸቱ፤ ላቦራቶሪው ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን የሚያሟሉ የቆዳ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጀገማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ጥራት እንዲጨምር ለቄራዎች ድርጅትና ለቆዳ ሰብሳቢ ነጋዴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በተናጠልና በመድረክ በመደበኛነት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውቀዋል።
በተለይም፣ የቆዳ አቅራቢዎችን ከፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ቆዳ ላይ ዕሴት ጨምሮ ያለቀላቸው የተለያዩ ጫማዎች፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ፣ ጓንት እና ሌሎች ምርቶችን በማዘጋጀት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል። በቀጣይም የቆዳና ሌጦ ጥራትን በማሻሻል ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን የተማሪዎች ቦርሳ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ መገባቱን አመልክተዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም