
ከቅርብ ግዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች ይስተዋላሉ። እነዚህን ግጭቶች እልባት ሰጥቶ ሰላም ለማምጣት በርካታ ጥረቶችም እየተደረጉ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩትን አለመግባባቶች ለመፍታት ቀዳሚ ጥረት ከሚያደርጉት አካላት መካከል በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል። መንግሥት ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለውይይት የሚረዱ ንግግሮችን ለማድረግ ነፍጥን ምርጫቸው አድርገው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ቡድኖችን ለምክክር ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አድርጓል።
በሕዝብ ተመርጦ በሥልጣን ላይ የሚገኘው በብልፅግና ፓርቲ የተመሰረተው መንግሥት ‹‹ግጭትን ምርጫ ከማድረግ፣ ከመዋጋት እና የዜጎቸን መከራ ከማብዛት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መነጋገር ይሻላል›› በማለት ለዚያ የሚረዳ ምኅዳር በገለልተኛ ወገን እንዲደረግ ኮሚሽን እስከማቋቋም ደርሷል። የመንግሥት ዋናው ግብ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግም መሆኑን በተግባር ጭምር አሳይቷል።
መንግሥት ካሳያቸው ቁርጠኛ እርምጃዎች መካከል አንዱ የሆነው እና አስፈላጊ እርምጃ ተደርጎ በብዙሀን ሰላም ፈላጊ ወገኖች የሚወደሰው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋም ነው። ይህ ኮሚሽን በርከት ያሉ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ሲሆን ከተለያዩ ቡድኖች (የፖለቲካና የሀሳብ ልዩነት ካላቸው አካላት) አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ላይ ይገኛል። የዚህ አጀንዳን የማሰባሰብና በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲደረግ የማመቻቸት ግብ በሀገሪቱ ውስጥ ያለ ሁሉም ሰው ሀሳቡን የሚገልፅበት፣ የሚስማማበት እና የሚግባባበት ምህዳር ለመፍጠር ነው። የኮሚሽኑ ጥረት ከተሳካ በመላ ሀገሪቱ የተሟላ ሰላም ለማምጣት ይረዳል።
እዚህ ጋር አንድ ነገር ሊታወቅ ይገባል። የሰላም ግንባታ በመንግሥት ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም። ይልቁኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረትን ይጠይቃል። ሰላም ለማስፈን በሚደረጉ ሁለንተናዊ ጥረቶች ውስጥ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች መሳተፍ ይኖርባቸዋል። በዛሬው ርዕስ ጉዳዬ ላይ በስፋት ልቃኘው የወደድኩት ሀሳብም ይሄው ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተሳሳተ ትርክት፣ በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነት፣ በፍትህ እና በዲሞክራሲ ጉዳዮች ላይ መሰረት አድርገው የሚነሱ አለመግባባቶች መስመር እንዲያገኙና ወደ ሰላም ውይይት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ጉልህ ተፅእኖ መፍጠር ከሚችሉ አደረጃጀቶችና ተቋማት መካከል የሃይማኖት ተቋማት ሕብረት አንዱ ነው።
ሕብረቱ በኢትዮጵያ ሁሉም ቡድኖችና የማኅበረሰቡ ክፍሎች ወደ ሰላማዊ የውይይት መድረኮች እንዲመጡ ግፊት ለማድረግ ከሚችሉት በጣም ጠቃሚ ቡድኖች መካከል አንዱ እንደሆነ አምናለው። ይህንን ኃላፊነቱን እና የተጽእኖ የመፍጠር አቅሙን ተጠቅሞ ልዩነቶች ወደ ጠረጴዛ አንዲመጡና የሰለጠነ ምክክር እና መፍትሄ እንዲያገኙ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት በጣም ጠንካራ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ተቋማቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች አሏቸው። እንደሚታወቀው የሰው ልጆች ከፖለቲካ መሪዎች ይልቅ የሃይማኖት መሪዎችን ተግሳጽና ምክር የመቀበል አዝማሚያ አላቸው። በተለይ ኢትዮጵያውያን ያላቸው ፈሪሀ እግዚአብሄር እና ለዘመናት የቆየው አባቶችን የመስማት እሴት ሰላምና አንድነት ለማምጣት ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው። ካለፉት ልምዶችና ተሞክሮዎቻችን እንደምንገነዘበው በሀገሪቱ በተለያየ ግዜ በሚከሰት ችግርና አለመረጋጋት የሃይማኖት መሪዎች ማኅበረሰቡን የሚያረጋጉ እርምጃዎቸን ሲወስዱ ይታያል።
ኢትዮጵያን ለዘመናት በግጭቶችና በችግሮች አንዳትበገር ምሰሶ ከሆኑ ተቋማት መካከል የሃይማኖት ተቋማት ቀዳሚዎቹ ናቸው። በተለይ አባቶች የእምነቱን ተከታዮቻቸውንም ሆነ ማንኛውንም ሰላም ፈላጊ ዜጋ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለሰላም፣ ለመቻቻል ተገዢ አንዲሆን በማስተማር ይታወቃሉ። ዜጎች የፖለቲካ፣ የሀሳብ ልዩነት ስላላቸው ብቻ ሀገርን ስጋት ላይ የሚጥል ግጭትና መከፋፈል ውስጥ አንዳይገቡ መንፈሳዊ መሪ በመሆን የሚያገለግሉ ናቸው። ኢትዮጵያውያንም የሃይማኖት መሪዎቻቸውን ሲያከብሩ አብዛኛውን ግዜም ተግሳፅን ሰምተው ሲያከብሩ ይታያል። የኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸው ቀናኢ መሆን፣ ባሕልና እሴቶቻቸውን ማክበር የሃይማኖት ተቋማት ቃልና ተግባር ለሰላም ግንባታ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ያሳያል።
የሃይማኖት አባቶችን ተግሳጽ የመስማት እሳቤ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ይስተዋላል። በተለያዩ ሀገራት የተከሰቱ ግጭቶቸን በማርገብና ሰላም በማስፈን እረገድ መልካም ምሳሌዎች አሉ። ለጉዳያችን ቅርብ የሆኑ ምሳሌዎችን ብንመለከት የሃይማኖት ተቋማት በግጭት ወቅት በአንዳንድ ሀገሮች የሰላም አምባሳደር በመሆን አለመግባባቶችን የፈቱ አባቶችና የእምነት ተቋማትን እናገኛለን። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ዘመን እንደ ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። እኚህ አባት የአፓርታይድ አገዛዝ በሰላማዊ መንገድ እንዲያከትም፣ ዜጎች ከበቀል ይልቅ ይቅርታን እንዲማሩ ስለ ፍትህ እና ሰላም ሰብከዋል። ሰዎች የሰላም አማራጭን ዘንግተው ሁከትን አንደ አማራጭ እንዳይጠቀሙ ወትውተዋል።
ዴዝሞን ቱቱ ይቅርታን፣ እውነትን እና ሀገር የማስቀደም ማስተዋል አስፈላጊ መሆኑን መክረዋል። እኚህ አባት እና የሀይማኖት ተቋማት ተሳትፎ ደቡብ አፍሪካ የእውነት እና የእርቅ ኮሚሽን ሂደት እንዲሳካ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው። በሀገሪቱ በግጭቱ ወቅት ስለተፈጠረው ጥፋት ሰዎች በይቅርታ መንፈስ እንዲመካከሩ ረድቷቸዋል። ብዙ የሃይማኖት መሪዎች ይህንን ሥራ ደግፈዋል። የእነሱ ሚና ጥላቻን እንዲቀንስ እና ሀገሪቱ ወደፊት እንድትራመድ ግዙፍ ድርኛ ነበረው።
በተመሳሳይ የሚነሳው ምሳሌ ውስጥ የሀይማኖት አባቶች ሚና ጎልቶ የሚታየው በደቡብ አሜሪካ ውስጥ የምትገኘው ኮሎምቢያ ነው። ሀገሪቱ በመንግሥት እና በአማፂ ቡድኖች መካከል በነበረ የእርስ በርስ ጦርነት ከ50 ዓመታት በላይ ተሠቃይታለች። ይህ ለአምስት አስርት ዓመታት የቆየውን ግጭት ለመፍታት እና የሃይማኖት መሪዎች ሁለቱንም ወገኖች ወደ ጠረጴዛው ለማምጣት ትልቅ ኃላፊነት ወስደዋል። እ.ኤ.አ በ 2016 የሰላም ስምምነቱ በመንግሥት እና በፋአርሲ አማፂያን መካከል ሲፈረም የሃይማኖት መሪዎች የሂደቱ አካል ነበሩ።
በመካከለኛው ምስራቅ የሃይማኖት ተቋማትም ለሰላም ሠርተዋል። በሊባኖስ ብዙ ሃይማኖቶች ጎን ለጎን በሚኖሩባት በሊባኖስ ለሰላም ግንባታ በተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች መካከል ትብብር ተደርጓል። በሀገሪቱ ተነስቶ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅትና ሰላም ከተፈጠረም በኋላ አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች የሰላም ትምህርት ፕሮግራሞችን በመሥራት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ሁሉም ሃይማኖቶች ፍቅርንና ይቅርታን ማኅበረሰቡ አንዲያስቀድም ጥሪ በማድረጋቸው ስኬት አስመዝግበዋል። ይህንን መልእክት በማሰራጨት ግጭትን ምርጫቸው አድርገው በነበሩ ቡድኖች መካከል ያለውን ጥርጣሬ እና ውጥረት ለመቀነስ ረድተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ኢንስቲትዩት በ2020 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው እነዚህ ጥረቶች ዘላቂ ሰላም የመፍጠር እድሎችን ከፍ አድርገዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በበርግሆፍ ፋውንዴሽን የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የሀይማኖት ተቋማትና ሕብረት ሰላምን በማምጣት ሂደት ውስጥ ተዋናይ መሆናቸው በማኅበረሰቡ፣ በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ፍርሃትን የሚቀንስ፣ መተማመንን የሚገነባ አመጽና ነፍጥን ምርጫ ያደረጉ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ሕይወት እንዲቀላቀሉ የሚገፋፋ አንደሆነ ያሳያል። ይህ የጥናት ውጤት እና ከላይ ያነሳናቸው ጥቂት ምሳሌዎች ሰዎች ዓመፅን ለማስወገድ እና በሚኖሩበት ዓለም ላይ ሰላምን ለማስፈን የሃይማኖት ሕብረት እና ተቋማት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ያረጋግጣል።
ኢትዮጵያ በሃይማኖት ብዝሃነት የበለፀገች ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እስልምና፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት እና ትውፊታዊ እምነቶች የሀገሪቱ ባሕልና ታሪክ ናቸው። እነዚህ ተቋማት በተከታዮቻቸው የታመኑ ናቸው። እነሱ በአካባቢው ማኅበረሰቦች ውስጥ ሥር የሰደዱ ናቸው። ይህ ማለት ከብዙ የውጭ ቡድኖች በተሻለ የሕዝቡን ፍላጎት፣ ፍራቻ እና እምነት መረዳት ይችላሉ። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁከት ሲፈጠር የሃይማኖት ተቋማት ቀድመው ግንዛቤና እውቀቱ ይኖራቸዋል። የሰላም ንግግር እንዲሁም ግጭትን የማርገብ ፍላጎት ሲኖር ሁሉንም ወገን ያለ ልዩነት ማናገር፣ ተግሳጽ መስጠት የሚችሉት እነሱ ናቸው። ይህም በሀገራዊ ሰላም ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ሚና በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰላም ለሚደረግ ጥረት ይህ ወቅት በጣም አስፈላጊ ነው። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከተለያዩ ቡድኖች (የፖለቲካና የሀሳብ ልዩነት ካላቸው ወገኖች) አጀንዳዎችን እየሰበሰበ ይገኛል። በዚህ ሂደት የሃይማኖት ተቋማት መሳተፍ አለባቸው። ከማኅበረሰባቸው አጀንዳዎችን በመሰብሰብ፣ የውይይት መነሻ እንዲሆኑ ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር በጋራ በመሥራት፣ የሰላም ጥሪዎችን በተከታታይ በማድረግ መሳተፍ ይኖርባቸዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ከምንግዜውም በላይ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ግጭቶች የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዳንገነባ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዳንፈጥር፣ ሕዝቦች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል። በመሆኑም የሀይማኖት ተቋማት በጋራ በመሆን በመሰረቱት ሕብረት አማካኝነት ሕብረተሰቡ አለኝ የሚለውን ጥያቄና አጀንዳ እንዲደረግለት የሚሻውን ሀሳቦች በማደራጀት፣ ሀሳቦቹን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርብ ግፊት በማድረግ እነዚያን ሃሳቦች ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ ማምጣት ይችላሉ።
የሀይማኖት አባቶች ለማኅበረሰቡ ሀገር የሚለውን እሳቤ እና አብሮ የመኖር ብሂልን ማስተማር ይችላሉ። የሰው ልጆች ባልተስማማንበት ጊዜ እንኳን አብሮ መኖር እንደምንችል ሰዎች እንዲረዱ የሀይማኖት አባቶች ማስተማር ይችላሉ። አንድነት ማለት ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት አስተሳሰብ አለው ማለት አይደለም። የተለያየ ስንሆን እንኳን እርስ በርሳችን ተከባብሮና ተቻችሎ፣ ሕግና ሥርዓትን አስፍኖ መኖር ማለት ነው። ይህንን እሳቤ ለኢትዮጵያውያን ለማስተማር ከሀይማኖት አባቶች በላይ የቀረበ የለም።
ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ሆኖ በተሟላ ሁኔታ ወደፊት እንዲሄድ የሃይማኖት ተቋማትም በጋራ መሥራት አለባቸው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የሙስሊም ሊቃውንት፣ የፕሮቴስታንት ፓስተሮች፣ የካቶሊክ ጳጳሳት፣ የባሕላዊ እምነት መሪዎች በአንድነት፣ በአንድ ድምፅ ጥሪ ሊያደርጉ ይገባል። ይህንን በጋራ ለማከናወን ከዚህ ቀደም የተመሰረተውና ልዩ ልዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ የሚሠራውን የሃይማኖት ተቋማት ሕብረት መጠቀም የችላሉ። ከዚህም አለፍ ካለ ለሰላም ብቻ የሚሠራ አንድነት ያለው የሃይማኖት ምክር ቤት ማቋቋም ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ የተባበረ ድምጽ በጣም ጠንካራ መሆን ይገባዋል። ሰላም የመንግሥት ጥረት ብቻ እንዳልሆነ ለሕዝቡ ማሳየት ይገባል። ሰላም የሁሉም እምነት ተከታዮች እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ እያንዳንዱ ዜጎች ፍላጎት ነው።
ሲጠቃለል የኢትዮጵያ ሰላም ከቃላት በላይ ያስፈልጋታል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ተግባር፣ ጥበብ እና ፍቅር ያስፈልጋል። የሃይማኖት ተቋማት እነዚህ ሁሉ ቁምነገሮች እንዳሏቸው አምናለሁ። ሰዎች ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያስችል ብልሀትና ክብር፣ የማኅበረሰብ አስተዳደር እውቀት እና መንፈሳዊ መሳሪያዎች አሏቸው። በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት ሕብረት በሰላም ግንባታ ማዕከል ልዩ ስፍራ ሊሰጣቸው ይገባል። በከተሞች ውስጥ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች ጀምሮ እስከ ገጠር ያሉ ቅዱሳን ገዳማት፣ መቅደሶች ለሰላም በጨለማ ጊዜ ብርሃን ሊሆን ያስፈልጋል። ይህንን እሳቤ ለማስረጽ አና እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው። ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢትዮጵያን ወደ ሰላም፣ ይቅርታና ብሔራዊ አንድነት መምራት አለባቸው።
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም