“የአካባቢ ብክለትን መከላከል የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል” – ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሑመድ

ጅግጅጋ:- የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ፅዱና ለኑሮ የሚመች አካባቢ መፍጠር የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሑመድ ገለጹ። ንቅናቄው በክልሉ እስከ ታችኛው የመንግሥት እርከን ድረስ ወርዶ የሚከናወን መሆኑም ተጠቆመ።

አቶ ሙስጠፌ ትናንት “ፅዱ ኢትዮጵያ” በሚል የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል የሕዝብ ንቅናቄ በክልል ደረጃ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳመለከቱት፤ የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ፅዱና ለኑሮ የሚመች አካባቢ መፍጠር የሁሉም ኃላፊነት ነው። በክልሉ ያለውን የአካባቢ ብክለት ችግር ለመፍታት የፕላስቲክ አጠቃቀምና አወጋገድን ማዘመን ያስፈልጋል።

በክልሉ እየተስፋፉ ያሉ ከተሞች ላይ በመመሥረት አካባቢ ከብክለት ነፃ እንዲሆን ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በዕቅዳቸው ውስጥ በማካተት እንዲሠሩ ትኩረት እንደሚደረግ የጠቆሙት አቶ ሙስጠፌ፤ በአርብቶ አደር አካባቢ የቤት እንስሳት በፕላስቲክ አወጋገድ ችግር ምክንያት ጉዳት እንደሚደርስባቸው አመልክተዋል። የፕላስቲክ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋልና በዚህም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሊሠራ እንደሚገባም አሳሰበዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ኅብረተሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ኖሮት የድርሻውን እንዲወጣ ለማነሳሳት መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ ከግንዛቤ ማስጨበጡ ጎን ለጎን በዘርፉ የወጡ ሕጎችን በሚተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

በንቅናቄው መድረክ የተገኙት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው፤ የሕዝብ ንቅናቄው የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና የሕግ ተከባሪነትን ለማረጋገጥ የሚካሄድ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ አካል እንደሆነ አመልክተዋል።

የዓለም አካባቢ ቀን ምክንያት በማድረግ ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በንቅናቄው የፕላስቲክ ብክለትን መከላከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፈርና የውሃ ብክለት፤ በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ዙሪያ በተመሳሳይ መንገድ በስፋት እንደሚሠራ ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የአደገኛ ኬሚካል ክምችቶችን በአግባቡ ለማስወገድ ንቅናቄው እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

በከተሞች አካባቢ ያለውን የድምፅ ብክለት ለመከላከል በስፋት እንደሚሠራ ጠቁመው፤ በዚህ ዙሪያ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ገልፀዋል። በንቅናቄው የግንዛቤ ማስጨበጥ፤ የሕግ ተግባራዊነትን ማረጋገጥና መልካም ተሞክሮ ላላቸው አካላት እውቅና መስጠትን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ንቅናቄው የሶማሌ ክልል ጨምሮ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል። በዚህም ከ15 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ብለዋል።

የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና ገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሙህየዲን አብዲ፤ የአካባቢ ብክለት በአካባቢ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል፤ ችግሩን ለመከላከል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት ላይ ትኩረት ተስጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የአካባቢ ብክለትን የመከላከል ንቅናቄው በክልሉ እስከ ታችኛው የመንግሥት እርከን ድረስ በመውረድ  የሚከናወን መሆኑንም ጠቁመው ፤ የንቅናቄው ዓላማ እየተባባሰ የመጣውን የአካባቢ ብክለት በመቀነስ፤ ለቀጣዩ ትውልድ ከብክለት የፀዳ ሀገር የማስረከብ  እሳቤ የያዘ መሆኑን አስታውቀዋል።

ንቅናቄው ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚተገበር መሆኑም በወቅቱ ተነግሯል።

በዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You