
ጅግጅጋ፦ በሶማሌ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎትን ወደዲጂታል ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ከ10 ሺህ 112 በላይ ዜጎችን መረጃ በዘመናዊ መንገድ ለማደራጀት መቻሉን የሶማሌ ክልሉ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ። በክልሉ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ፈላጊው ማኅበረሰብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን አመለከተ።
የኤጀንሲው ተወካይ የቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አብደላ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች አዲስ ትምህርት ለሚጀምሩ ተማሪዎች፣ በጤና ተቋማት ለሚወለዱ ሕጻናት፣ ንፁሕ የመጠጥ ውሃ አገልግሎትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ይረዳሉ።
ምዝገባው በየዘርፉ ለሚከናወኑ ቀጣይ የልማት ሥራዎች ትክክለኛ ዕቅድ ለማዘጋጀት ጠቃሚ በመሆኑ፤ መረጃዎችን በአግባቡ መመዝገብ እንደሚገባ አመልክተው፤ የወሳኝ ኩነት አገልግሎትን ወደዲጂታል ለማሳደግ በክልሉ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በበጀት ዓመቱ አገልግሎቱን ወደዲጂታል ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ከ10 ሺህ 200 በላይ ዜጎችን መረጃ በዘመናዊ መንገድ ማደራጀት ተችሏል ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በክልሉ አገልግሎቱን ከማዘመን ባሻገር፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን በማጠናከር እና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በስፋት ተሠርቷል። በዲጂታላይዜሽን ምዝገባው ዙሪያ በርካታ ቀበሌዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፤ ሥልጠና ከወሰዱት ቀበሌዎች በ87ቱ አገልግሎቱን እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ፈላጊው ማኅበረሰብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
በክልሉ ከሚገኙ 1 ሺህ 396 ቀበሌዎች ውስጥ በ790 ቀበሌዎች የልደት፣ የሞት፣ የፍቺ እና የጋብቻ ምስክር ወረቀት እየተሰጠ ይገኛል ያሉት አቶ መሐመድ፤ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት ባለፈው ዓመት 30 ሺህ ለሆኑ ዜጎች አገልግሎት መሰጠቱንም በማስታወስ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ባለፉት 11 ወራት በወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት 31 ሺሕ 774 ለሆኑ ዜጎች አገልግሎት ተሰጥቷል። ከአጠቃላይ ቁጥሩም ልደት 25 ሺህ 713 ፣ ሁለት ሺህ 56 ሞት፣ ጋብቻ ሦስት ሺህ 903 እና ፍቺ 102 ሆኖ መመዝገቡን አብራርተዋል።
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች ለማስጠበቅ እና የልማት ፍላጎቶችን ለይቶ ለማሟላት የሚያግዙ መረጃዎች የሚገኝበት መሆኑን የሚናገሩት ተወካይ ኃላፊው፤ የኩነቶች ምዝገባ በየዘርፉ ለሚከናወኑ ቀጣይ የልማት ሥራዎች ትክክለኛ ዕቅድ ለማዘጋጀት ጠቃሚ በመሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል ።
ለአብነትም በጤና ተቋማት በከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ ሆስፒታሎች ጋር በመወያየትና ሠራተኞችን በመመደብ የሚከሰቱ ልደቶች እንዲመዘገቡ እና የልደት የምሥክር ወረቀት በነፃ እንዲሰጧቸው ተደርጓል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ከምዝገባው አፈፃፀም ላይ ያጋጠሙን ችግሮች መኖራቸውን የሚገልጹት ተወካይ የቢሮ ኃላ ፊው፤ በዋናነት ቁልፍ ባለድርሻ አካላት በሚፈለገው ደረጃ ከኤጀንሲው ጋር በቅንጅት አለመሥራት፣ አመራሩ ለወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥራ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ተጠቃሽ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
መረጃ ለማደራጀት የሚያስችል የተሟላ የቢሮ አደረጃጀት በየደረጃው አለመኖር፣ ራሱን የቻለ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መዋቅር በቀበሌ ደረጃ አለመኖር፣ የተከናወነውን የምዝገባ መረጃ በጊዜ አለማድረስ እንዲሁም ኅብረተሰቡ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዙሪያ የተሟላ ግንዛቤ አለመኖር፣ በተለይም ወቅታዊ ምዝገባ ላይ ከሚከሰተው ኩነት አንፃር ሲታይ ከባድ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይ አገልግሎቱን ለማሻሻልና ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ማጠናከርና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የበለጠ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። ወሳኝ ኩነቶችን በሚገባ በመመዝገብ የሚገኘውን መረጃ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል።
በሶማሌ ክልል የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከተመሠረተ ከስድስት ዓመታት በላይ የሆነው ሲሆን በነዚህ ዓመታት 144 ሺህ 274 ዜጎች ወሳኝ ኩነት ምዝገባ መካሄዱ ታውቋል። ምዝገባው በዋናነት ለልደት፣ ፍቺ፣ ጋብቻ፣ ሞት፣ ጉዲፈቻ እና አባትነትን በፍርድ ቤት በማረጋገጥ ምስክር ወረቀት ለመስጠት መቻሉን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም