ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ያስጀመረው 16ኛው ከተማ አቀፍ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ተገኝቼ ነበር። በፌስቲቫሉ ላይ የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢያዎችን ባህልና ጥበባት የሚያሳዩ ትርዒቶች ሜዳው ላይ ይታያሉ፤ በዓውደ ርዕይ ድንኳኖች ውስጥ ደግሞ የተለያዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ዕቃዎች እና የዕደ ጥበብ የፈጠራ ሥራዎች ይታያሉ፡፡
እየጎበኘሁ ስሄድ ከአንደኛው የድንኳን በር ላይ የቴሌቪዥን ካሜራዎች አነጣጥረው አየሁ፤ ብዙ ወጣቶችም እየተንጠራሩ በስልካቸው ይቀርጻሉ። ጠጋ ብዬ ስመለከት ያ ሁሉ ወጣት ብርቅ የሆነበት አንዲት እናት እንዝርት እያሾሩ ጥጥ ሲፈትሉ ማየት ነው። በዚያች ቀጭን ድር ላይ እንዝርቱን ማሾራቸው ለአንዳንዶች እንደ ሰርከስ ትርዒት ነው፤ ለአንዳንዶችም የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ነው፤ በእርግጥ የምርም የኢንዱስትሪ አይነት ነው! የሴትዮዋ ጥጥ መፍተል በዚያ ልክ ብርቅ የሆነው የአሁኑ ትውልድ ከዚህ ኢንዱስትሪ ጋር የማይተዋወቅ ስለሆነ ነው። ለምን?
በሳይንስና ቴክኖሎጂ በልፅገን ሌላ የረቀቀ ማሽን ላይ ስለደረስን ይሆን? የአሁኑ የተማረ ወጣት የፈጠራ አቅሙ አድጎ እንዝርትን እንደ ጥንት መሣሪያ በማየት እንደ ቅርስ አይቶት ይሆን?
እነዚህን ጥያቄዎች ራሴን ስጠይቅ፤ መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ከዓመታት በፊት በአንድ መድረክ ላይ የተናገሩት ትዝ አለኝ። በቀልድ እያዋዙ የሚናገሩት መጋቢ ሐዲስ ‹‹እኔ የሚገርመኝ ከዩኒቨርሲቲ የመጣ የግብርና ተማሪ የአባቱን ሞፈር ተደግፎ ፎቶ የሚነሳው ነገር ነው›› ብለው ነበር። ፎቶ የሚነሳው ሞፈርና ቀንበር ብርቅ ሆኖበት ነው። በሬ ጠምዶ፣ እርፍ ጨብጦ ፎቶ መነሳት በባህል እንደ መኩራት ወይም ደግሞ የግብርና ሥራው ብርቅ ሆኖበት ነው። የመጋቢ ሐዲስ ትዝብት፤ ይሄ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የግብርና ምሩቅ ለሺህ ዘመናት ያገለገለ ሞፈርና ቀንበር ሳይሆን ትራክተር መሥራት ነበረበት ማለታቸው ነው። አሳዛኙ ነገር ግን እንኳንስ ትራክተር ይቅርና ለሦስት ሺህ ዘመን የቆየውን ሞፈርና ቀንበርም መገጣጠም የማይችል መሆኑ ነው። ሥርዓተ ትምህርታችን ከራሳችንም ከውጭውም እንዳንሆን አድርጎናል።
በነገራችን ላይ ከሴትዮዋ (ጥጥ ፈታይዋ) ጋር በነበረኝ ቆይታ እንደነገሩኝ፤ የጥጥ ፈትል ትኩረት ስላልተሰጠው እንጂ የአሁኖቹ ልጆች ፈጣን እና አዲስ ነገርን ቶሎ የሚቀበሉ ናቸው። ለብዙ ልጆች አሳይተዋቸው ከእናቶች ያላነሰ መፍተል እና እንዝርቱን ማሽከርከር ችለዋል። ስለዚህ ትኩረት ቢሰጠው የአሁኑ ትውልድም መሥራት ይችል ነበር ማለት ነው፡፡
ለምን ትኩረት አልተሰጠውም?
ይህን ጥያቄ የሚጠየቅ አንድ የዘመኑ ወጣት ምናልባትም ሊገረም ይችላል። እንዴት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኋላቀር አሠራር ትኩረት ይሰጠው ይባላል? ሊል ይችላል። ዳሩ ግን የአሁኑ ትውልድ ይህን የማለት ሞራል አለው ወይ? ነው። ይሄ ማለት ‹‹አህያ የሌለው በቅሎ ይንቃል›› እንደሚባለው ማለት ነው። የጥጥ መፍተልን ሥራ ኋላቀር ለማለት ጥጥ ፈትሎ ልብስ መሥራትን በዘመናዊ ረቂቅ ቴክኖሎጂ መተካት ይኖርብናል። ያንን እስካልቻልን ድረስ ግን እናቶቻችን በአካባቢ ከሚገኝ ግብዓት ከተክል እስከ መልበስ ያለውን ሂደት በራሳቸው ፈጠራ መሥራታቸው ሊደነቅ የሚገባው ነው።
በእርግጥ አሁን ላይ የሽመና ሥራ ብዙ ማሻሻያዎች ተደርጎበታል። ሙያው ክብር ተሰጥቶታል። የባህል ልብስም በተገቢው ክብር እንዲያውም በውድ ዋጋ እየተሸጠ ነው። ያም ሆኖ ግን ይህ የሆነው በአዲስ አበባ ውስን ቦታዎች ነው፤ ለዚያውም ከባህላዊ ዕቃዎች ሙሉ በሙሉ ሳይላቀቅ ነው። እንደ መወርወሪያ የመሳሰሉት የሽመና ዕቃዎች አሁንም በሽሮ ሜዳ እና ቀጨኔ አካባቢዎች ይገኛሉ። ስለዚህ አሁንም በአገልግሎት ላይ ያለ ስለሆነ ወጣቶች ቢማሩት ባህልን ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ የገቢ ምንጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ባህላዊ የልብስ አሠራር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ባህልን ለማስቀጠል ብቻ አይደለም፤ ባህል በየዘመኑ ይቀየራል፤ የባህል አብዮት ይፈጠራል። አንድ ነገር ባለበት ብቻ ሊቀጥል አይችልም፤ ድካምን የሚያቀል፣ ጥራትን የሚጨምር የቴክኖሎጂ አሠራር ሲመጣ ነባሩ ባህል አይነቱ ይቀየራል። ባህላዊ የልብስ አሠራር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የምንለው ግን እሱን ሙሉ በሙሉ የሚተካ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ላይ ስላልደረስን ነው። የገቢ ምንጭ ስለሆነ ነው። በዘመናዊ መንገድ ከሚገኘው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ዲግሪ ይልቅ የተሻለ ሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው ስለሆነ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የቀላል ኢንዱስትሪ አይነቶችን ስላልተጠቀምንባቸው ጥሬ ዕቃዎቻችንን ወደ ውጭ እንልካለን፤ የራሳችንን ምርት ወደ ልብስ እና ጫማ ቀይረው ግን በውድ ዋጋ ይሸጡልናል። ተፈላጊ ከሚባሉት የልብስ አይነቶች ውስጥ የጥጥ ልብስ ነው። ነጋዴዎች እንኳን ሲሸጡ ‹‹ኮተን ነው›› እያሉ ነው፤ ምቹ እና እና ጥራቱን የጠበቀ ውድ ልብስ ማለታቸው ነው። ይህ ጥጥ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረት ነበር።
የትኛውም ከባድ ኢንዱስትሪ መነሻው ቀላል ኢንዱስትሪ ነው። ይህን ቀላል ኢንዱስትሪ ለተማሪዎች ማሳየት ለከባድ ኢንዱስትሪ እንዲነሳሱ ያደርጋል። ዓለም አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ የደረሰው ቀላል ነገሮችን በማዳበር ነው። የሰው ልጅ ከድንጋይ መሳሪያዎች መገልገያነት ተነስቶ እዚህ ረቂቅ ቴክኖሎጂ ላይ የደረሰው በፈጠራ ላይ ፈጠራ እየጨመረ ነው። ስለዚህ ተማሪዎች በባህላዊ መንገድ የሚሠራውን የጥጥ ፈትል እንዝርት ቢያዩት ልብስ እንዴት እንደሚሠራ ያውቃሉ፤ ከዚያም ወደ ቴክኖሎጂ የማሳደግ የፈጠራ ሀሳብ ይመጣላቸዋል ማለት ነው። እንዲህ አይነቶችን መነሻዎች ካላዩ ግን አስማት እንደሆነባቸው ይቀራል። ልብስ በፈረንጅ ሀገር ብቻ ተጀምሮ በፈረንጅ ሀገር ብቻ የሚሠራ ይመስላቸዋል። የኢትዮጵያ እናቶች እንዲህ አይነት ፈጠራዎች እንዳሏቸው አያውቁም ነበር ማለት ነው። ከምንም በላይ ግን ዋናው ነገር እንዲህ አይነት ባህላዊ ፈጠራዎች ወደ ዘመናዊ ፈጠራ ለመሄድ መነሻ መሆናቸው ነው።
የሠለጠኑት ሀገራት ረቂቅ ቴክኖሎጂ ላይ የደረሱት ቀላል ኢንዱስትሪዎችን በማሳደግ ነው። የእኛ የኢትዮጵያውያን ደግሞ ችግሩ ከንቀት እና ከማጣጣል ነው የጀመርነው። አህያ የሌለው በቅሎ ይንቃል ነው ያደረግነው። ፈረንጅ የሠራቸውን ዕቃዎች በመተማመን የራሳችንን ነባር ፈጠራዎች አጠፋናቸው። መሠልጠን ማለት ግን የነበረውን ማሻሻል እና ማዘመን እንጂ ማጥፋት አልነበረም! ማጥፋት ካስፈለገም እሱን የሚተካ የራስ ስሪት ሲኖር ነው።
አህያ የሌለው በቅሎ ይንቃል ከምንሆን መጀመሪያ አህያ ይኑረን! ቀላል ኢንዱስትሪዎች ወደ ቴክኖሎጂ ይወስዳሉና ትኩረት ይሰጣቸው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም