
የኢራን እና የእሥራኤል ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ እየተካሄደ ያለውን የቡድን 7 ጉባኤ ከመጠናቀቁ በፊት አቋርጠው መመለሳቸው ተገለጸ። ዋይት ሐውስ ‹‹በኢራን እና በእሥራኤል መካከል እየተባባሰ ከመጣው ግጭት ጋር ተያይዞ ፕሬዚዳንቱ ወደ ዋሽንግተን መመለስ አለባቸው›› ሲል አስታውቋል።
ትራምፕ ‹‹ግልጽ በሆኑ ምክንያቶች ቀደም ብዬ መመለስ አለብኝ›› ሲሉ ትራምፕ የተናገሩ ሲሆን፣ የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ ስለማስተላለፋቸውም ተገልጿል። ትራምፕ ወደ ዋሽንግተን የመመለሳቸውን ምክንያት ለትልቅ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ጉባኤው ከመጠናቀቁ በፊት ቀድመው በመሄዳቸው ምክንያት ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ እና ከሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ክላውዲያ ሸይንባውም ጋር ታቅዶ የነበረው ውይይት አይካሄድም። ትራምፕ ጉባኤውን ሳያጠናቅቁ የሚመለሱት የእሥራኤል እና ኢራን እርስ በርስ የሚያደርጉት ጥቃት አምስተኛ ቀኑን በያዘበት ዕለት ነው።
ትራምፕ ቀደም ብለው ‹ትሩዝ ሶሻል› በተሰኘ የሶሻል ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን በቅርቡ በተካሄደው የአሜሪካ እና የኢራን የኒውክሌር ድርድር ላይ ያቀረቡትን ስምምነት መፈረም እንደነበረባት ጽፈዋል። ‹‹ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ሊኖራት አይችልም። ደጋግሜ ተናግሬዋለሁ›› ብለዋል፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ጃፓን የሚገኙበት የቡድን 7 ሀገራት መሪዎች ስብሰባ ትራምፕ ጉባኤውን ሳያጠናቅቁ ቀድመው መሄዳቸውን እንደሚረዱት ገልጸዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ‹‹አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የምታስችል ከሆነ ይህ በጣም ጥሩ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት በበኩላቸው፣ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የመከላከል አቅም ለማሳደግ ወደ ቀጣናው ተጨማሪ መሣሪያ እንደምታሰማራ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አሜሪካ፤ እስራኤል በኢራን ላይ እየፈጸመች ያለችውን የማጥቃት ዘመቻ ልትቀላቀል ትችላለች የሚሉ አስተያየቶችን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ውድቅ አድርገዋል።
ዋይት ሐውስ ትራምፕ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም መካከል የተደረገውን የንግድ ስምምነት ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን በማሳካት በጉባኤው ስኬታማ ቀን እንደነበራቸው ለማጉላት ሞክሯል።
ትራምፕ በተጨማሪም የቴህራን ነዋሪዎች 17 ሚሊዮን ሰዎች ከሚኖሩባት የኢራኗ መዲና በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ብዙም ሳይቆይ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በቴህራን ማክሰኞ ማለዳ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ መነሳቱን ዘግበዋል።
እስራኤል በቀጥታ ስርጭት ላይ በነበረው የኢራን የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ጥቃት አድርሳ ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ ካደረገች ከሰዓታት በኋላ ከበድ ያለ ጥቃት ፈጽማለች። እሥራኤልና ኢራን አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚፈፅሟቸው የአየር ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም