ከነጋዴው ጋር የተመከረበት መድረክ

ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም አንድ ተብሎ የተጀመረው የ2017 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ ቀናት ቀርተውታል። ታዲያ አዲስ በጀት ዓመት ሲታሰብ የከረመውን አፈጻጸም መገምገምና ለመጪው ማቀድ የተለመደ ነው። ከሰሞኑ ከንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብ ጋር የተካሔደው ውይይትም እዚሁ ላይ በመመስረት የተፈጸመ ነው። የንግዱን ዘርፍ አላሠራ ያሉ ችግሮችም ሆኑ፤ ቀደም ሲል በመወሰዳቸው እፎይታ ያስገኙ ርምጃዎች እንዲሁም ወደ ፊት ሊሠሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የንግድ ዘርፍ ማህበረሰብ ተወካዮች ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ያደረጉት ውይይት ባሳለፍነው ሳምንት ተካሂዷል።

የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ከሌሎች አካላት ጋር ተወያይተዋል። እንዲሁም አስቀድመው የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። ነጋዴዎቹ የልማት ሥራው ለጸሐይ ሀሩር ባለመሸነፍ፣ ለብርድ እጅ ሳይሰጥ ቀን እና ለሊት ሥራዎች በመሠራታቸው የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ የሥራ ባሕል ለውጥ መምጣቱን እማኝ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በጉብኝቱ ግብር ከፋዩ የከፈለው ገንዘብ ምን ላይ እንደዋለ በተግባር ማየታቸውን በመመስከር አመስግነዋል። የንግድ ፍቃድ እድሳትና መሰል ግንኙነቶች በዲጅታል መጀመራቸው የሚበረታታና ሥራዎችን የሚያቃልል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች በዘርፉ ቢሻሻሉ ያሏቸውን ጉዳዮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል። ነጋዴዎቹ በቀዳሚነት ሕገወጥ ንግድ ሕጋዊ ነጋዴ ላይ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። የነዳጅ አቅርቦት እጥረትና የትርፍ ህዳጉ ቢሻሻል፣ በግንባታ ላይ ያሉ የነዳጅ ማደያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ቢደረግ፤ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ቢፈተሽ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ሕገወጥ ኬላዎች ተዘርግተው የሚጠየቁ ሕገወጥ ክፍያዎች የንግዱ ዘርፍ ራስ ምታት ስለሆኑ ይሠራበት፤ ከክልል ለሚመጡ የኢንዱስትሪ ግብአቶች ደረሰኝ የሚገኝበት ሁኔታ ቢመቻች የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

ኢንዱስትሪውን የሚደግፍ የኢንዱስትሪ ባንክ መኖር እንዳለበት በማስታወስ፤ የባንኮች የማበደር አድማስ ቢሰፋ፣ ባንኮች ለማኑፋክቸሪንግ የሚያበድሩበት ሁኔታ ቢመቻች፣ ቡና ራሱን ችሎ ሚኒስቴር ሊሆን ይገባል፤ ለኢንዱስትሪ የመሥሪያ ቦታ እጥረት ችግር ቢቃለል፤ የመንግሥት ተቋማት የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲጠቀሙ ቢደረግ፣ የመብራት መቆራረጥ ችግር ቢፈታ፣ ለተኪ ምርቶች ድጋፍ ቢደረግ፣ የግብር ትመና አሠራር ቢዘረጋለት፣ የገቢ ደረሰኝ ሕትመት ማተም የሚችሉ ማተሚያ ቤቶች ቁጥር ቢጨምር፣ በፌዴራል የተጀመረው የታክስ ዲጅታል ሲስተም ወደታች ቢወርድ የሚሉ አስተያየቶችም ተሠንዝረዋል።

የኑሮ ውድነትን ሊያባብሱ ከሚችሉ መሠረታዊ ምርቶች ተጨማሪ እሴት ታክስና ተርን ኦቨር ታክስ ቢነሳ፤ ደረሰኝ የመስጠትም ሆነ የመቀበል ባሕልን ለማዳበር የማበረታታ ሥርዓት ተግባራዊ ቢደረግ፤ ከትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተመራቂዎች ለኢንዱስትሪው በሚፈለገው ልክ የተዘጋጁ ባለመሆናቸው የትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች አብረው ቢሠሩ፤ መኖ ላይ ታክስ መጣሉን ተከትሎ የእንስሳት ተዋጽኦ ላይ ዋጋ ጭማሪ ማስከተሉን በማስታወስ ጉዳዩ ቢታይ፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ አምራቾች የከተማውን ገበያ ለማረጋጋት ቶሎ የሚበላሹ ምርቶችን ጭነው ሲመጡ የከተማ መግቢያ ላይ የሰዓት ገደብ በመኖሩ ምርቶች ቆመው እንዳይበላሹ ከያዙት ምርት አንጻር አስተያየት ቢደረግ፤ የኮንስትራክሽን ግብአቶች የጥራት ቁጥጥር ቢደረግ፤ ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶችን መቀበል የሚቻልበት ሁኔታ ቢፈጠርና የሀገሪቱ ምርቶች ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፍ ሸማቾች የሚቀርቡበት የኢኮሜርስ መገበያያ ቢፈጠር የሚሉ አስተያየቶች አቅርበዋል። ሰላምን ከማስፈን አንጻር ምን ታስቧል? የሚል ጥያቄም ተሰንዝሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የቀረቡ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን ተከትሎ ምላሽ ሰጥተዋል። ገበያና ንግድ ለሀገር እድገትም ውድቀትም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ገበያ ለሀገር ሕልውና እንደማቆያ፣ እንደ መሠልጠኛ ብሎም እንደመሸጋገሪያ የሚወሰድ መሆኑን አንስተዋል። ያለገበያ ሀገር ሊጸና አይችልም ያሉ ሲሆን፤ ያም ቢሆን ኢትዮጵያ የከረመና አዲስ ፈተና አለባት። ስለዚህ ያለፈውን መጠገንና ለመጪው መሽቀዳደም ይገባል። አብዛኞቹ ምክክሮች ግን ነገን ታሳቢ ከማድረግ ይልቅ የቅርቡን ታሳቢ የማድረግ ሁኔታ ይስተዋላል። ይህ ሲደረግ ነገ እንዳያመልጥ የብዙ ሀገራት ተሞክሮ ያለው የንግዱ ማህበረሰብ ለቀጣዩ አሻግሮ ማየትን ለሌሎችም የማስተማር ድርሻ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

ለንግዱ ማህበረሰብ በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ለውጥ መኖሩን ያነሱት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ለእዚህም የለውጡ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ወደ 75 በመቶ የሚጠጋው ብድር ይቀርብ የነበረው ለመንግሥት እንደነበር አንስተዋል። “አሁን በተቃራኒው እስከ 85 በመቶ ብድር ለግል ዘርፍ ይሰጣል፡፡” በማለት፤ ይሁንና የግሉ ዘርፍ ሥራውና ፍላጎቱ እየሰፋ በመሄዱ የሚቀርበው ገንዘብ በቂ አይደለም። ለእዚህም ለየዘርፉ የብድር አቅርቦቱ ክፍፍል እንዴት ይሁን? የሚለው ላይ ውይይት መካሔዱን በመጠቆም፤ አሁንም ክፍተት ካለ በጥያቄው መሠረት የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ የባንኮች አሠራርን በተመለከተ ከተወያዮቹ አብዛኞቹ የባንክ ሼር ያላቸው የባንክ ባለቤቶች በመሆናቸው ባንኮችን ማስተካከል የሚችሉት እነሱ ናቸው። ለነጋዴዎቹ ባንኮችን አራጣ አበዳሪና የጥቁር ገበያ ነጋዴ አትሁኑ በማለት ማረቅ ይጠበቅባችኋል። በመንግሥት በኩል ያሉ ክፍተቶች መስተካከል አለባቸው ተብሎ በመታመኑ፤ እስካሁን ለውጭ ዜጎች ዝግ ሆኖ የቆየው የባንክ አገልግሎት ክፍት ተደርጓል። በቀጣይ የሚመደበው ፋይናንስ በየዘርፉ ምን መሆን እንዳለበት የሚጠና ሲሆን፤ የሚሰጠው አገልግሎት ውድድርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ታቅዷል።

አገልግሎት አሰጣጦች ላይ ከሙስና ጋር የተያያዘ ችግር አለ ተብሎ ለቀረበ ጥያቄ ሲመልሱ፤ የማገልገል ባሕሉ አነስተኛ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገልግሎት የሚሰጠው ሰው ብዙ ስለሆነ ችግር መኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል። ለዚህም ምክንያት ቶሎ ሀብታም ለመሆን የገባ ሰው እና አቅም ሳይኖረው በሆነ መልኩ የገባ ሰው መኖሩ ነው። ለእዚህ መፍትሔው ክትትል ነው። “ ባልሰማም ለምን ማታ ማታ ሥራዎችን ታያለህ? ይህ እኮ የጠቅላይ ሚኒስትር ባሕሪ አይደለም” የሚል ብዙ መካሪ እንዳጋጠማቸው ጠቅሰው፤ መደበቅ ትክክል፣ ሥራ ማየት ደግሞ ነውር የሚመስላቸው አሉ ሲሉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ ካልታየ ሥራ አይሠራም ብለዋል። ማገልገል ችግር መሆኑንና ሁሉም ጋር ያለ በሽታ መሆኑን በማንሳት፤ ለእዚህም እንደ መፍትሔ የተወሰደው ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ (የአውቶሜሽን አገልግሎቶችን) ነው ብለዋል።

አብዛኛው ትልልቅ የመንግሥት ተቋማት ሥራዎች ቴክኖሎጂን የተከተለ ማድረግ የጀመሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በመዲናይቱ ካሉ ተቋሞች በተጨማሪ የሀገሪቷ ትላልቅ ከተሞች አገልግሎት የሚሰጡት በዲጅታል እንዲሆን ታቅዷል። ይህ ሁኔታ ሌብነት ይቀንሳል፣ የማገልገል አቅምን ያሳድጋል ሲሉ ተናግረዋል። መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቶቹን ዲጅታላይዝ ቢያደርግ ያሉ አስተያየት ሰጪ በሌላ ጥያቄያቸው መንግሥት ታክስ ቢቀንስ የሚል ጥያቄ መሰንዘራቸው አብሮ የማይሄድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብር ከሌለ ሥራ አይሠራም ብለዋል። አገልግሎትን በዲጅታል መስጠት የሕንጻ፣ የኮምፒውተር ባለሙያዎችን ማሠልጠን ይፈልጋል። ስለዚህ ሥራው ከንግዱ ማህበረሰብና ከሌላው በሚሰበሰብ የሚሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

በአንድ በኩል ገቢ ተሰብስቦ ሳይሰረቅ ሥራ ላይ መዋል አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ሲሆን የዘመነ አገልግሎት መስጠት ይቻላል። ስለዚህ አገልግሎትን በዲጅታል የመስጠት ጅምር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ሌብነት በብዙ ቦታ ያለ ልማድ በመሆኑ የተወሰኑ በመንግሥት ተቋማት ያሉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሌባ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ሃሳብ ላይ እንደሚስማሙ አመልክተው፤ መንግሥታዊ ሌብነት ግን የለም ብለዋል።

“የምንለምናትን፣ የምናገኛትን መቶ በመቶ የምናውለው ኢትዮጵያ ላይ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለእዚህም አዋሬ የተቀየረበት መንገድ በቂ ማስረጃ እንደሆነ ተናግረዋል። 50 በመቶ ሌብነት ያለው የንግዱ ማህበረሰብ ጋር መሆኑን አንስተዋል። ይሄም ሀብታም መሆናችሁ እንዲታወቅና ያለቀጠሮ በር እንዲከፈትላቸው ሌብነት ያልተለማመዱ ወጣቶችን ሳይቀር ሌብነት የሚያለማምዱት እነሱ መሆናቸውን ተናግረዋል። ይህንን ለመከላከል ከገቢዎች ሚኒስቴር በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራና በርካታ ሚኒስትሮችን የያዘ የሚከታተል ኮሚቴ መኖሩን አመላክተዋል፡፡

እንደ ዶክተር ዐቢይ ገለጻ፤ ሙስናን መዋጋት የፈለገ የንግዱ ማህበረሰብ አባል የሚያስቸግረው ሚኒስትርም ሆነ ሌላ ኃላፊ ካለ በማስረጃ ካሳወቀ ርምጃ ይወሰዳል። በመሰል ሁኔታ የተወሰኑ ሰዎች ቢያዙ ሌሎቹ ስለሚፈሩ ሙስናን መቀነስ ይቻላል። ካስፈለገም ቀድሞ መረጃ ከተሰጠ አብሮ መከታተልና መያዝ ይቻላል። በእዚህ ዓይነት ሁኔታ ዓይን ያወጡትን ሌቦች በመያዝ ትንሽ ረገብ ማድረግና አብሮ መሥራት ይቻላል።

በተጨማሪ በኢትዮጵያ በርካታ ሕገ ወጥነት መኖሩን አንስተው፤ በተለይ ከንግዱ ማህበረሰብ የተነሳው የነዳጅ ሕገ ወጥነት ላይ አጽንኦት በመስጠት መንግሥት ከፍተኛ በጀት መድቦ ወደሀገር ውስጥ የሚያስገባው ነዳጅ ወደ ጎረቤት ሀገራት እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል። ማህበረሰቡ ነዳጅ ከመጠቀም ጎን ለጎን ከሀገር እንዳይወጣም ሊከላከል እንደሚገባ በማስታወስ፤ በሂደት ችግሩ መፍትሔ እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።

ቡና ራሱን ችሎ ሚኒስቴር ሊሆን ይገባል በሚል ለቀረበው ሃሳብ ሲመልሱ፤ በየዕለቱ የተሸጠውን ቡና መጠንና የተገኘውን ገቢ መከታተል የዕለት ከዕለት ሥራቸው አንዱ አካል መሆኑን በመጠቆም፤ የቡና ወጪ ንግድ ሪፖርትን በየቀኑ እንደሚከታተሉ ጠቅሰዋል። አደረጃጀት አስፈላጊ ቢሆንም ትኩረት ተሰጥቶት ካልተመራ አይሆንም። ስለዚህ ቡና አሁን ባለበት የመረጃ ክፍተት አለመኖሩንና ለውጥም የመጣው በቅርበት በመመራቱ መሆኑን አንስተዋል። ቡና ሚኒስቴርም ሆነ ኤጀንሲ ወይም አሁን ባለበት ቢሆን ዋናው ነገር ሥራው መሠራቱ ነው ብለዋል። ገቢ ከተወሰደ የወርቅ ገቢ እንደሚበልጥ በማንሳት በገቢ መጠን ከሆነ ወርቅ ቀድሞ ሚኒስቴር ሊሆን ነው ብለዋል። ይሁንና ሁለቱም ሚኒስቴር መሆን እንደማያስፈልጋቸው በማስረዳት፤ ሁለቱም የመንግሥት ራስ ምታት መሆን የለባቸውም፤ የሚሻለው የግል ዘርፍ ቢሆኑ ነው ብለዋል።

ከትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተመራቂዎች ለኢንዱስትሪው በሚፈለገው ልክ የተዘጋጁ አለመሆናቸውን አስመልክቶ ለተሰጠ አስተያየት ምላሽ ሲሰጡ፤ “ከትምህርት ተቋማት የበቁ ሰዎች እንዳትጠብቁ” ያሉት ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ በክፍል ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ብቻውን በቂ ስላልሆነ ተማሪ ከመመረቁ በፊት የተግባር ላይ ልምምድ በማድረግ ማገልገልን እንዲማር ተማሪዎች ሦስተኛና አራተኛ ዓመት ሲደርሱ የግድ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብተው መሥራት አለባቸው በሚል መሠራት መጀመሩንና ይሄ የሚስፋፋ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ በአግባቡ እንዲፈጸም ማገዝ እና ዋነኛ አስተማሪ ሆኖ መገኘት የነጋዴውም ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል። ሰው እናንተ ጋር ለመማር ዝግጁ ሆኖ ከመጣ በኋላ አስተምራችሁ ሰው የምታደርጉት እናንተ ናችሁ ብለዋል።

በተመሳሳይ ሰላምም የጋራ ኃላፊነት እንደሚፈልግ ተናግረዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን የተለያዩ አካላት ሰላምን መንግሥት ቢያስብበት እያሉ የቤት ሥራ እንደሚሰጡ በማንሳት፤ ከኃላፊነት ባይሸሽ መልካም ነው ብለዋል። የኢትዮጵያን ሰላም የሚያናጋው 60 በመቶ የኢትዮጵያ ሀብታም ነው ያሉት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን እያገዙ ሰላም ማለት እንደማይሆን ተናግረዋል። ሰላም የሚፈልግ አካል ጫካ ያሉ አካላትን መርዳት እንደሌለበትና ካስፈለገም መምከር እንደሚቻልና አብሮ መሥራት የሚፈልግ አካል ካለ አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የሀገር ምርትን መጠቀም አስፈላጊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም እንደ ድሮው በአስገዳጅ ሁኔታ ሳይሆን ሰው ተረድቶ አንዱ የአንዱን ምርት የሚጠቀምበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ እንደሚሆን ጠቅሰዋል። ቢታዩ ተብለው የተሰጡ አስተያየቶችም ሆኑ የቀረቡ ጥያቄዎች በምክክሩ ላይ ሚኒስትሮች ስለተገኙና ማስታወሻ ስለተያዘ የተነሱ ጉዳዮች በዝርዝር ይታያሉ። በዘርፉ የታዩና መፈታት ያለባቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚሠራ ሲሆን፤ በጋራ መሥራት ለሀገር ለውጥ እንደሚያመጣ መግባባት ላይ ተደርሷል። ውይይቱ ያስፈለገው ለቀጣይ እቅድ ግብአት ለማሰባሰብ በመሆኑ አብዛኞቹ አስተያየቶች የእቅድ አካል እንደሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አስገንዝበዋል።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You