ሙሉጌታ ከበደ (ወሎዬው)

ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ናት። በየዘመናቱም ስሟን የሚያስጠሩ እና አርአያ የሚሆኑ ልጆችን የምታፈራ ማህጸነ ለምለም ናት። ኢትዮጵያ የብዙ ስመ ጥር ግለሰቦች ሀገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው:: በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኟቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት የቀሰሙ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደ ነበሩ ታሪክ ይነግረናል።

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም። በውትድርና፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ናቸው።

በሀገር ውስጥም ደምቀው የሚታዩ እና ሥራዎቻቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንም በየዘርፉ ይገኛሉ። ዛሬም ባለውለታነታቸውን ለመዘከር የተነሳነው ዕውቁን የእግር ኳስ ተጫዋች ሙሉጌታ ከበደን ነው።

ኢትዮጵያውያን ለእግር ኳስ ጨዋታ ልዩ ቦታ አላቸው። ነፍሳቸው በሙሉ የተሳሰረው ከእግር ኳስ ጋር ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ ማሳያው ደግሞ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የእግር ኳስ ጨዋታዎች በሙሉ በተመልካች የሚደምቁ እና ስታዲየሞቹም ሁልጊዜ ጢም ብለው መሙላታቸው ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም ቢሆን ለእግር ኳስ ተጫዋቾች ትልቅ ክብር እና አድናቆት አላቸው።

በተለይም እንደ ሙሉጌታ ከበደ ያሉ የልብ የሚያደርሱ ተጫዋቾች በተመልካቹ ልብ ውስጥ ዝንተ ዓለም ሲዘከሩ ይኖራሉ።

በ1959 ዓ.ም በደሴ ከተማ ይህችን ምድር በመቀላቀል ሀገራችን ካፈራቻቸው የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች በቀዳሚነት ስፍራ የተፈረጀ ስለመሆኑ ብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ይስማማሉ። ወላጆቹ ባወጡለት ስም ሙሉጌታ ከበደ ሲባል በኳስ ክህሎቱ ግን የበርካታ ስያሜ ባለቤት ለመሆን ችሏል።

እግር ኳስ መጫወት የጀመረው በትውልድ ሰፈሩ ገና በልጅነት እድሜው ሲሆን በአካባቢው ለሚገኙ የሰፈር ቡድኖች በመጫወት የድንቅ ክህሎት ባለቤት መሆኑን አስመስክሯል። በክለብ ደረጃ ከ1974 ዓ.ም እስከ 1976 ዓ.ም ለወሎው ፔፕሲ ክለብ ከመጫወቱ በላይ በፔፕሲ ውስጥ ባደረገው ምርጥ እንቅስቃሴም የሀገራችን ታላቅ ክለብ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስን የመቀላቀል እድሉን አገኘ። በ1976 ዓ.ም ክረምት ላይ ፈረሰኞቹን ሲቀላቀል ቋሚ የሥራ ዕድል ለማግኘት ከመቻሉ በተጨማሪ በጊዜው ለተጫዋቾች ይከፈል የነበረውን የደመወዝ ክብረወሰን ለመስበር ችሏል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ከ1977 ዓ.ም እስከ 1989 ዓ.ም ተጫውቶ ማሳለፍ የቻለው ሙሉጌታ ከቡድኑ ጋር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሰባት፣ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አንድ፣ በአሸናፊዎች አሸናፊ ስድስት በጥቅሉ 14 ዋንጫዎችን ከቡድኑ ጋር በክብር አንስቷል። ከነዚህ ድሎች በተጨማሪ ሙሉጌታ በግሉ የተለያዩ ስኬቶችን ለማግኘት ችሏል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው ክለቡን ለድል ለማብቃት የበኩሉን አስተዋፅዖ ከማድረጉም በላይ በግሉ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ በኮከብ ተጫዋችነት እና ግብ አግቢነት ለመሸለም የበቃባቸው ዓመታት የሚጠቀሱ ናቸው።

“1975 ዓ.ም ለሙሉጌታ ከበደ ጥሩ ዓመት ነበር:: በዚያኑ ዓመት ለብሔራዊ ቡድን ተመረጠ:: የደሴ ከተማ ነዋሪም በሙሉጌታ መመረጥ ተደሰተ:: በዚያን ዓመት ፔፕሲ የኢትዮጵያ ቻምፒዮናነትን ክብር ተቀዳጀ። የወሎ ምርጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ትቅደም ዋንጫን አነሳ። የማሸነፊያዎቹን ግብ ያስቆጠረውና ለድሉ ማማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ ሙሉጌታ ነበር።

የሀገር ጥሪ ስለመጣለት ለአዲስ አበባው ጉዞ የሽኝት ግብዣ ቤተሰቦቹ አዘጋጁለት:: ጓደኞቹና አድናቂዎቹ እንዲሁም የእናቱ እድርተኞች በተገኙበት ሞቅ ባለ ሁኔታ ተደገሰ:: ምርቃቱም ተዥጎደጎደ…” በማለት የኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ነጋሪው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) በአንድ ወቅት ‹ሰውየው› በሚል ባስነበበው መጣጥፍ የኳሱ ጌታ ታላቅ ተጫዋች የሆነበትን ጉዞ ተርኳል።

ሙሉጌታ ለታላቅ ሀገራዊ ጥሪ መንደሩን ሲሰናበት እናቱ እንዲለያቸው እንዳልፈለጉ የሚነግረን ሊብሮ ታላቁ ተጫዋች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የገጠመውን ፈገግ የሚያረግ ገጠመኝ ብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ያስታውሱታል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን “አሸብር፣ ወለዬው፣ ተንኮሉ” በሚል ቅፅል ስሞቹ ያውቁታል። ከመንግስቱ ወርቁ በኋላ የተፈጠረ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ንጉስ አድርገው የሚመለከቱትም ጥቂት አይደሉም። በርካቶችም “እስካሁን ምትክ ያልተገኘለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ንጉስ” እንደሆነ ይከራከራሉ። “የኳሱ ጌታ” ያሰኘውን ድንቅና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባለተሰጥኦ ተጫዋች መሆኑ ግን ሁሉንም ያስማማል።

ከምንግዜም የኢትዮጵያ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሙሉጌታ ከበደ በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ዓመት ከመጫወቱ በተጨማሪ ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለደሴ ፔፕሲ እና ለወሎ ምርጥ የተጫወተ ሲሆን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሴካፋ ዋንጫን፣ በክለብ እና በግልም በርካታ ሽልማቶችን ማሸነፍ የቻለ ድንቅ ተጫዋች ነበር።

ለአስራ ሦስት ዓመታት አቋሙ ሳይዋዥቅ በወጥ ብቃቱ፣ በድንቅ ችሎታው እንዲሁም በረቂቅ ጥበቡና በተንኮሉ ጭምር ደጋፊዎቹን ብቻ ሣይሆን የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች እንዲሁም እግር ኳስን የሚወዱትን ሁሉ ሲያስቦርቅ፣ ሲያስጨፍር በደስታ ሲያስለቅስ እንደነበር በዘመኑ የነበሩ ሁሉ ይመሰክሩለታል።

በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ በድንቅ ችሎታው የማይነቃነቅ ሀውልት ለመትከል የበቃውና ሁሉም በአንድ ድምፅ “ተተኪ ያልተገኘት የኳሱ ጌታ ነው” በማለት የሚያወድሱት ሙሉጌታ ከበደ፣ በወጥ አቋሙ ለአስራ ሦስት ዓመታት በአንድ ክለብ የፈረሰኞቹን ማልያ ለብሶ በመጫወት ስሙን በወርቅ ቀለም ያፃፈ ተነግረው የማያልቁ አስገራሚ ታሪኮች ያለው ተጫዋችም ነው።

የሙሉጌታን ድንቅ የኳስ ጥበብ “ቃላቶች የመግለፅ አቅም እንኳን የላቸውም፤ እሱ የእግር ኳስ አምላክ ያለ ስስት ለኢትዮጵያ የሰጣት ምትሀተኛ ተጫዋች ነው” በማለት በርካቶች ዛሬም ድረስ ያወድሱታል።

ሙሉጌታ የተወለደው በ1959 ዓ.ም መሆኑን በህይወቱ ዙሪያ የተፃፉ ድርሳናት ያስረዳሉ። የትውልድ ቦታው ደግሞ ደሴ ከተማ ሆጤ ሠፈር ነው። ደሴ ከፍተኛ 2፣ ወሎ ፔፕሲ እና ኒያላ የተጫወተባቸው ክለቦች ክለቦች ቢሆኑም ብዙ ታሪኮችን መሥራት የቻለው ከ1977 እስከ 1989 በተጫወተበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው።

በ1973 ዓም ከወሎ ምርጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተስፋ ቡድን የተመረጠው ሙሉጌታ፣ ሦስት ጊዜ ኮከብ ጎል አግቢና ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው። የኮከብ ግብ አግቢነት ክብር የተቀዳጀው በ1977፣ 1978 እና 1986 ሲሆን፣ የኮከብ ተጫዋችነት ክብር ያገኘው በ1978፣ 1980 እና 1982 ነበር።

በነዚህ ድንቅና ስኬታማ ዓመታት ሰባት ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮናን ዋንጫ፣ ስድስት ጊዜ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ፣ አንድ ጊዜ የጥሎ ማለፍ ዋንጫና አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ትቅደም ዋንጫ አሸናፊ በመሆን በስኬትና በዋንጫ የተንቆጠቆጠ የተጫዋችነት ዘመን አሳልፏል። የኳሱ ጌታ የተጫዋችነት ዘመኑን ከደመደመ በኋላም ወደ አሰልጣኝነት ህይወት ጎራ ብሎ ነበር። ተጫውቶ ባሳለፈበት ኒያላ የኢንስራክተር አብርሃም መብራቱ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ሰርቷል። የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ዋና አሠልጣኝ ሆኖም አገልግሏል።

በግሉ ስኬትን ያስመዘገበባቸው ዓመታት በ1977 ዓ.ም፤ በ1978 ዓ.ም እና በ1986 ዓ.ም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በ1978 ዓ.ም፣ በ1980 ዓ.ም እና በ1982 ዓ.ም ኮከብ ተጫዋች በመሆን በኢትዮጵያ ሻምፒዮናዎች ላይ ለመሸለም በቅቷል። የአዲስ አበባ ኮከብ ተጫዋችና ጎል አስቆጣሪ የሆነባቸው ዓመታቶች ነበሩ።

ከባለቤቱ ከወይዘሮ ዘይቱና አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጅ ያፈራው ታላቁ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋች ሙሉጌታ ከበደ፣ ባደረበት ህመም ሰኔ 04 ቀን 2017 ዓም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ የህልፈተ ሕይወቱ ዜና ተሰምቷል። ሐሙስ ሰኔ 05 ቀን 2017 ዓም የማይረሱ ታሪኮች በሰራበት የአዲስ አበባ ስታዲየም የክብር አስክሬን አሸኛኘት ተደርጎለታል። በእለቱ የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን ጨምሮ የስፖርት ቤተሰቡ፣ ጓደኞቹ፣ አድናቂዎቹና ቤተሰቡ የተገኙ ሲሆን ሥርዓተ ቀብሩ በኮልፌ የሙስሊም መካነ መቃብር ተፈፅሟል።

በዕለቱም በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለስልጣናት፣ የተጫዋቹ ወዳጅ ዘምድ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት የሽኝት ስነስርዓት ተካሂዷል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ የአበባ ጉንጉን ካሳረፉ በኋላ በሰጡት አስተያየት ሙሉጌታ ከበደ “ወሎዬው” ያልሸነፍ ባይነት ምልክት ነው ብለዋል። አያይዘውም ሙሉጌታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ያስጠራ፣ ለተጫዋቾች መልካም ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል። የቀድሞው ኮከብ ሙሉጌታ ከበደ የቀብር ስነስርዓት በኮልፌ የሙስሊም መካነ መቃብር ከቀኑ 7 ሰዓት ተፈጽሟል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ለቀደሞ የክለባችንና የብሔራዊ ቡድን ምርጡ ተጫዋች ለነበረው ሙሉጌታ ከበደ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን መሪር ሀዘን ገልጾ ለቤተሰቦቹና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ለእግር ኳሱ ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል።

እኛም በዚህ ለህዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን የእግር ኳስ ተጫዋች ሙሉጌታ ከበደን ላበረከተው ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አመሰገንን። ሰላም! ነይህንን ጽሁፍ ስናዘጋጅ የተለያዩ ድረገጾችን በምንጭነት ተጠቅመናል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You