ከፍል አንድ
የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን የጉለሌ እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞችን እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደርን መዳረሻው ያደረገ ነው።
«በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘውንና በ1968 ዓ.ም ወላጅ አባቴ ለመንግሥት በአደራ የሰጠውን ቤት አሁን ላይ እንዲመለስልኝ ብጠይቅም የጉለሌ እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር በአደራ የወሰዱትን ቤት ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ስለሆነም በቤቶች አስተዳደር የተፈጸመብኝን በደል የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቶ ይፍረደኝ » ሲሉ አቶ ጌታቸው ከበደ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ እና ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን ማስረጃዎች መርምሮ እንደሚከተለው አቅርቧል፤ መልካም ንባብ።
አቤቱታ አቅራቢው
አቶ ጌታቸው ከበደ ወንድምጊዜ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ነው። ከ2007 ዓ.ም በፊት በተለምዶ አዲሱ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት የቤት ቁጥር 077 ይኖሩ ነበር።
አቤቱታ አቅራቢው እንደሚናገሩት፤ አባታቸው አቶ ከበደ ወንድምጊዜ የኮሪያ ዘማች ነበሩ። ከኮሪያ ዘመቻ መልስ በቀድሞ ስሙ አቃቂ ከተማ አንደኛ ጩሎ ቀበሌ በአሁኑ መጠሪያው ደግሞ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ሦስት አካባቢ የቴሌኮሙኒኬሽን ሠራተኛ በመሆን ተቀጠሩ። ይህ በአንዲህ እንዳለ ለሥራ ቦታቸው ቅርብ አካባቢ በመፈለግ በ1953 ዓ.ም አበበች አባደፋር ከተባሉ ወይዘሮ በ200 ብር 144 ካሬ ሜትር ቦታ ገዙ። ከ1953 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም በቦታው መኖር ቻሉ። በ1967 ዓ.ም በአቃቂ ከተማ ጩሎ ቀበሌ ከሚሠሩበት መስሪያ ቤት ወደ ሱልልታ ሳተላይት እንዲዘዋወሩ ተደረገ። ይህ አጋጣሚ በአቶ ጌታቸው እና ቤተሰባቸው ሕይወት ላይ ሁሉን ቀያሪ ክስተት እንዲፈጠር አደረገ።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ በመንግሥት በተደረገው ምደባ የአባታቸው የአቶ ከበደ ወንድምጊዜ የሥራ ሁኔታ ከአቃቂ ወደ ሱሉልታ ሳተላይት በአዘዋወረበት ወቅት እንደ አሁኑ በቀላሉ የትራንስፖርት አገልግሎት አይቻልም ነበር። በዚህም ምክንያት አቶ ከበደ በቃሊቲ የሚገኘውን ቤታቸውን በማከራየት በተለምዶ አዲሱ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከራይተው እንዲኖሩ ይገደዳሉ።
አዲሱ ገበያ አካባቢ ቤት ተከራይተው እየኖሩ እያለ፤ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ይመጣል። የደርግ ወታደራዊ መንግሥት በትረ መንግሥቱን ይቆጣጠራል። የደርግ መንግሥት ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ 47/67 አዋጅ ታወጀ። በዚህ አዋጅ ትርፍ ቤት ያላቸው ሰዎች እንዲወረሱ ተደረገ። ከዚህም ባሻገር በአዋጁ በተለያዩ ምክንያቶች ዜጎች ይኖሩበት የነበረውን ቤታቸውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ የሚሄዱ ከሆነ ቤታቸውን በአደራ ለመንግሥት መስጠት እንደሚችሉ እና በአደራ በሰጡት ቤት ልክ ደግሞ በሄዱበት አካባቢ መንግሥት በማካካሻነት በነፃ ቤት መስጠት እንደሚገባው በአዋጁ ተደንግጓል።
ይህን አዋጅ የሰሙት አቶ ከበደ ወንድምጊዜ የተባሉ ግለሰብ በሥራ ምክንያት በቀድሞው ስሙ የአቃቂ ከተማ አንደኛ ጩሎ ቀበሌ በአሁኑ መጠሪያው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የሚገኘውን ቤታቸውን ለመንግሥት በ47/67 አዋጅ መሠረት በማስረከብ ለሥራቸው ቅርብ የሆነ የማካካሻ ቤት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። ይህን ጥያቄ ተከትሎ የአቃቂ ከተማ የአንደኛ ጩሎ ቀበሌ በቁጥር 1172777 250 ፅኑ በኅዳር 9 ቀን 1968 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለጉለሌ ወረዳ ቀበሌ በቀድሞ መጠሪያው 01/01/04 የህብረት ሥራ ማህበር ጽሕፈት ቤት፤ በአሁኑ መጠሪው ደግሞ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ደብዳቤ መላካቸውን ሰነዶች ያመላከታሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በቁጥር 4949/ጉ/68 መስከረም 26 ቀን 1968 ዓ.ም ለ10/01/04 የህብረት ሥራ ቀበሌ በተጻፈ ደብዳቤ በቃሊቲ የሚገኘው የአቶ ከበደ ወንድምጊዜ ቤት በ20 ብር እየተከራየ ይገኝ እንደነበረ እና አሁን ላይ በአዋጅ 47/67 ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ያስረከቡ ስለሆነ በጉለሌ ወረዳ የሚኖሩበትን ቤት የሕጉ መንፈስ በሚያዝዘው መሠረት ከኪራይ እንዲድኑ ስለጠየቁ አስፈላጊው ትብብር ይደረግላቸው የሚል ደብዳቤ ለጉለሌ ወረዳ ላከ።
ይህን ተከትሎ በጉለሌ ወረዳ በቀድሞ ስሙ ቀበሌ 04 የቤት ቁጥር 077 በአሁኑ መጠሪያው ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ከኪራይ ነፃ የሆነ ቤት በ1968 ዓ.ም እንዲያገኙ መደረጉን ሰነዶች ያሳያሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ሰነዶች እንደሚያሳዩት፤ የደርግ መንግሥት ወደ ስልጣን እስከመጣበት እና ቤቱን በአደራ ለመንግሥት እስካስረከቡበት ጊዜ ድረስ በአቃቂ ከተማ ይገኝ የነበረው ቤት በአቶ ከበደ ወንድምጊዜ ስር ይተዳደር ነበር።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ አባታቸው አቶ ከበደ ወንድምጊዜ በ1973 ዓ.ም ሕይወታቸው አለፈ። ነገር ግን አቶ ከበደ ወንድምጊዜ ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት ቀደም ብሎ በ1968 ዓ.ም ለመንግሥት በአደራ የሰጡትን ቤታቸው እንዲመለስላቸው ለጉለሌ ወረዳ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ነገር ግን የጠየቁት ጥያቄ ሳይመለስ እና ጥያቄያቸው በሂደት ላይ እያለ ሞት ቀደማቸው።
የዛሬው አቤቱታ አቅራቢ በወቅቱ ሕፃን ስለነበሩ የአባታቸውን ጥያቄ ለማስቀጠል ሳይችሉ ቀሩ። አባታቸው በሕይወት እያሉ ለጉለሌ ወረዳ ጠይቀውት የነበረውን የአደራ ቤት ይመለስልኝ ጥያቄ ሳያነሱ ከጉለሌ ወረዳ በማካካሻነት በተገኘው ቤት ከእናታቸው እና ወንድማቸው ጋር ለበርካታ ዓመታትም ቆዩ።
ቀን ቀንን ሲወልድ የዛሬው አቤቱታ አቅራቢው ለአቅመ አዳም ደረሱ። አባታቸው ከመሞታቸው በፊት አንስተውት የነበረውን የአደራ ቤቱ ይመለስልኝ ጥያቄ እርሳቸውም መልሰው ለማንሳት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ያሉ ባለሙያዎችን ማማከር ይጀምራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ሰነድ አልባ ቤቶች ሰነድ እንዲኖራቸው የሚያስችል መመሪያ አስተላለፈ የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ውሳኔውም ማስታወቂያው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም የመጨረሻ መጠናቀቅ እንዳለበት መመሪያ ተላልፎ እንደነበር ያስረዳሉ። ይህን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ከበደ፣ 2004 ዓ.ም በመጋቢት ወር ላይ አባታቸው ለመንግሥት በአደራ የሰጡትን ቤት ለማስመለስ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 07 የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ማመልከቻ ማስገባታቸውን ያስረዳሉ።
የአቤቱታ አቅራቢውን ማመልከቻ የተቀበሉት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 07 ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎችም ለአቤቱታ አቅራቢው አቶ ጌታቸው በአደራ ለመንግሥት የሰጡትን ወይም በማካካሻነት የወሰዱት ቤት አንዱን በመምረጥ ወደ ግል ይዞታ የመቀየር ሕጋዊ መብት እንዳላቸው እንደነገሯቸው ያስረዳሉ።
ይህን ተከትሎ አቶ ጌታቸው፣ በመመሪያው መሠረት በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 በአደራ ለመንግሥት የተሰጠውን ቤታቸውን ለማስመለስ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 07 ማመልከቻ በማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ያብራራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በ2004 ዓ.ም በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አመራሮች በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ከሚገኙ አመራሮች ጋር የመረጃ ልውውጥ ማድረግ ይጀምራሉ። የመረጃ ልውውጡም ስድስት ወራትን እንደፈጀ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ከመረጃ ልውውጡም በኋላ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 የሚገኘውን በአደራ ለመንግሥት ተሰጥቶ የነበረውን ቤት ይመለስለት ወደሚለው ውሳኔ መደረሱን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ የአቃቂ ክፍለ ከተማ ቤቱን ለመመለስ ቢወስንም በመካከል ግን አንድ ችግር ተፈጠረ። ለተፈጠረው ችግር ዋናው ምክንያት ደግሞ መንግሥት በአቃቂ የሚገኘውን ቤት በ1968 ዓ.ም ከተረከበ በኋላ ኩሽና፣ መጸዳጃ እና እንዲሁም ከዋናው ቤት በተጨማሪ ያሉ ሌሎች በግቢው የነበሩ ክፍሎችን ለእያንዳንዳቸው የቤት ቁጥር ሰጥቷቸዋል። አባታቸው ለመንግሥት ቤቱን ሲያስረክቡ ግን ሁሉንም ቤቶች ያስረከቡት እንደ አንድ ቤት ነበር። አባታቸው በጉለሌ ወረዳ በማካካሻነት የተሰጣቸውን ሦስት ክፍል ቤትም የተረከቡት 077 በሚል አንድ የቤት ቁጥር ብቻ የተመዘገበ ቤትን ነበር። ነገር ግን መንግሥት በአደራ የተቀበለውን ቤት ለመጸዳጃውም፣ ለኩሽናውም፣ ለዋና ቤቱም የተለያዩ ቁጥሮችን ሰጥቷቸዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአደራ የተሰጡት ቤቶች የተለያዩ ቁጥሮች ቢሰጣቸውም እስካሁን ድረስ ቤቶቹ የጋራ መጸዳጃ እና ኩሽና ግን የላቸውም።
በአደራ ለመንግሥት የተሰጡ ቤቶች ለአቶ ጌታቸው እንዲመለሱ በአቃቂ ቃሊቲ እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ስምምነት ላይ ቢደረስም በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 የሚገኘው የቤቶች አስተዳደር በአደራ የተረከበውን ቤት በተለያዩ ቁጥሮች እና ክፍሎች ከፋፍሎ ለተጠቃሚዎች ሰጥቶ ስለነበር ከእነኝህ ከተከፋፈሉ ቤቶች መካከል የትኛውን መመለስ እንዳለበት ስለተቸገረ ጉዳዩን ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ማሳወቁን ያስረዳሉ። በአደራ የተሰጠው ቤት የተለያዩ ቁጥሮች መሰጠታቸውን ተከትሎ ክፍለ ከተማውም እንደወረዳ 03 ጥያቄውን ለመመለስ ይቸገራል። ይህን ተከትሎ ክፍለ ከተማው ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ደብዳቤ ይፅፋል። የቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤትም አቶ ጌታቸው የማግኘት መብት እንዳለቸው ገልጾ ነገር ግን በወቅቱ በነበሩ መመሪያዎች በሙሉ ክፍተቶች አሉባቸው፤ ስለሆነም አሁን ባለው መመሪያ መሠረት የአቶ ጌታቸው ማመልከቻ ሊስተናገድ እንደማይችል ይገለፅላቸዋል።
በአደራ እና በማካካሻነት ከተያዙ ቤቶች ጋር በተያያዘ መመሪያው ክፍትት እንዳለበት የቤቶች ልማት ሥራ አስፈጻሚ ስለነገሯቸው እና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንዲወስዱት አቅጣጫ ስለጠቆሟቸው በ2006 ዓ.ም ጉዳዩን ወደ አቃቂ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመውሰድ የአቃቂ ክፍለ ከተማን እና ወረዳ 03ን ይከሳሉ። ይሁን እንጂ በመዝገብ ቁጥር 3185/05 ሁለቱን ወገኖች ክርክር ሲያስተናግድ የነበረው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ‹‹አቶ ጌታቸው ያነሱት ጥያቄ ተገቢነት የለውም›› ሲል በ22/2/06 በዋለው ችሎት ብይን ሰጠ።
ይህን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ይገባኝ ጠይቀው ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደወሰዱት የሰነድ ማስረጃዎች ያሳያሉ። በከፍተኛው ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር የኮመ/151114 በተከፈተ ፋይል ሁለቱን አካላት ሲያከራክር ከቆየ በኋላ በ1/8/2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቶ ጌታቸው ያነሱትን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ እና የስሩን ፍርድ ቤት ብይን አፅድቀናል የሚል መልስ በመስጠት ፋይሉ መዘጋቱም የሰነድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህን ተከትሎ መፍትሄ ያጡት አቶ ጌታቸው፣ ጉዳያቸውን በፖስታ በማደረግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመላክ ‹‹አቤት›› ይላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ለጉዳዩ አንዳንድ አቅጣጫዎችን ከማሳየት ባለፈ በቀጥታ እጃቸውን በጉዳዩ ውስጥ እንደማያስገቡ ጠቅሰው፤ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍከ ከተማ፣ ወረዳ 03 እና የአዲስ አበባ ቤቶች ውጪ ለሚገኙ ቅሬታ ሰሚዎች ጉዳዩን መውሰድ እንዳለባቸው አቅጣጫ እንደጠቆሟቸው ያስረዳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም በሰጣቸው አቅጣጫ መሠረት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቅሬታ ሰሚ አቤቱታ ማስገባታቸውን ይናገራሉ።
የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቅሬታ ሰሚም ጉዳዩን ከተመለከቱ በኋላ ከአቃቂ ቃሊቲ እና ከጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ባለሙያዎችን ተፈጠረ ስለተባለው ችግር መረጃ እንዲልኩላቸው ጠየቁ።
ከሁለቱ ክፍለ ከተሞች ያሉ መረጃዎች በባለሙያዎች መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ መረጃዎች ወደ ቅሬታ ሰሚው አካል ተላከ። የተላከውን መረጃ መሠረት በማድረግ ቅሬታ ሰሚው አካል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሦስት የሚገኘው ቤት በመንግሥት በአደራ መልኩ ተይዞ የቆየው ቤት እንጂ በአዋጅ አለመወረሱን ፣ ምንም ዓይነት አበል እንደአልተበላበት በመጠቆም ለከንቲባ ቅሬታ ሰሚ ጻፉ።
ይሁን እንጂ ከቅሬታ ሰሚው የደረሰውን ደብዳቤ በፍርድ ቤት ታይቷል የሚል ምላሽ ሰጠ። ይህን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ለቅሬታ ሰሚው ሁለተኛ ጊዜ በመሄድ ቅሬታቸውን አሰሙ። ነገር ግን ቅሬታ ሰሚው ከዚህ በላይ ስለጉዳዩ ማየት እንደማይችል ምላሽ እንደሰጣቸው ያስረዳሉ።
ተስፋ ያልቆረጡት አቶ ጌታቸው ጉዳዩን ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ማስገባታቸውን ይናገራሉ። በወቅቱ ምክትል ከንቲባ የነበሩት አቶ አባተ ስጦታው፣ መረጃዎችን ከተመለከቱ በኋላ ጉዳዩን ለመሬት አስተዳደር መሩት። መሬት አስተዳደርም አቶ ጌታቸውን በመጥራት መረጃቸውን በማየት እና ስለጉዳዩ ጠርተው አነጋገሯቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ መሬት አስተዳደርም ጉዳዩን ለባለሙያዎች መራው። እነዚያ ባለሙያዎች ጉዳዩን ከመረመሩት በኋላ ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ከቤት ቁጥር 395 እስከ 400 ያለውን መረጃ እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት የቤት ቁጥር 077 ያለውን የቤት መረጃዎች አጣርታችሁ ላኩልን ሲሉ አዘዙ። ነገር ግን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ‹‹ጉዳዩ የእኛ ጉዳይ ስለሆነ ለማዘጋጃ ቤቱ መረጃ የምንልክበት ምክንያት አይኖርም›› ሲል መግለጹን አቶ ጌተቻው ያስረዳሉ።
ይህን ተከትሎ አቶ ጌታቸው በአካል ወደ አዲስ አባባ መሬት ልማት ቢሮ በመሄድ ‹‹ለምን የመሬት ማኔጅመንት የጠየቃችሁን መረጃ አትልኩም?›› ሲሉ የመሬት ልማት አስተዳደርን መጠየቃቸውን ይገልጻሉ። የአዲስ አበባ መሬት ልማት አስተዳደርም ጉዳዩን በአግባቡ እንመረምርልሃለን እንዳሏቸው እና አቶ ጌተቻውም እነሱን በማመን ለበርካታ ጊዜያት በተስፋ እንደጠበቁ ያስረዳሉ።
ይህ በእዲህ እንዳለ፤ ጉዳዩን ለመመርመር ከሁለቱ ክፍለ ከተሞች እና ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኮሚቴ ተቋቋመ። የተቋቋመው ኮሚቴም መረጃዎችን ሰብስቦ ሲያይ ቆየ ። ነገር ግን 2007 ዓ.ም አቶ ጌታቸው እና ቤተሰባቸው ይኖርበት የነበረውን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ይገኝ የነበረውን ቤት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ከቤቱ እንዲወጡ ማስታወቂያ ለጠፈ። የተለጠፈው ማስታወቂያም 077 ቤት እየኖራችሁ ላላችሁ ሰዎች ከወረዳው ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ጋር ውል አልተዋዋላችሁም፣ ኪራይም እየከፈላችሁ አይደለም፣ ያለአግባብ የመንግሥት ቤት ይዛችኋል የሚል ማስታወቂያ እንደነበር አቶ ጌታቻው ያስረዳሉ።
አቶ ጌታቸውም በወቅቱ ወረዳ ሰባት ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት በመሄድ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 የሚገኘው ቤት የማካካሻ ቤት ስለሆነ የኪራይ ውል እንዳልተዋዋሉ እና ኪራይ እንደማይከፍሉ ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ መልስ ሊያገኙ አልቻሉም። ይብሱኑ ቤቱ በላያቸው ላይ ታሸገ። በቤታቸው መታሸግ ግራ የተጋቡት አቶ ጌታቸው፣ ጉዳዩን ለወረዳው ፍትህ ቢሮ አቤት አሉ። ይሁን እንጂ አቤቱታቸውን ሊሰማ ፈቃደኛ የነበረ አካል ማጣታቸውን ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ከሁለት አመት በኋላ በ2009 ዓ.ም የወረዳው አስተዳደር አቶ ጌታቸው እና ቤተሰባቸው በሌሉበት የታሸገውን ቤት በመስበር ያለማንም ፈቃድ የቤቱን ዕቃ በማውጣት ቤቱን አከራዩት። የተወሰዱ ሙሉ የቤት ዕቃዎች እስከዛሬ ድረስ የት እንደገቡ እንደማያውቁ አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ።
ማዘጋጃ ቤቱ ለቤቶች ልማት መረጃ ላኩልን ካላቸው እና ቤቶች ልማት ደግሞ ጉዳዩን ኮሚቴ አቋቁመን እኛ እናየዋለን ካሉ ጊዜ ጀምሮ ስለጉዳዩ በየቀኑ እየሄዱ ለቤቶች ልማት ምን ላይ ደረሰ እያሉ ይጠይቁ አንደነበር የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ይሁን እንጂ የተቋቋመው ኮሚቴ እዚህ ግባ የሚባል መፍትሄ እንዳላመጣ ጠቁመዋል።
ተስፋ ያልቆረጡት አቶ ጌታቸው፣ ከአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ጋር በሚሟገቱበት ሰዓት ለውጡን ተከትሎ ከማካካሻ ቤት ጋር ተያይዞ ለቤቶች አስተዳደር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መመሪያ ወረደ። መመሪያውም በማካካሻነት የተሰጣችሁት ቤቱ በእጃቸው እስካለ ድረስ በአደራ የሰጣችሁት ቤት ተመላሽ ይሆናል የሚል ነው። ይሁን እንጂ አቶ ጌታቸው በግድ በማካካሻነት ከተሰጡት ቤት ተባርረው ስለነበር ቤቱ በእጃቸው አልነበረም።
ይሁንና ከማካካሻው ቤት የወጣሁት በግዳጅ ነው ሲሉ አሁንም ለአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር አቤት አሉ። ነገር ግን አዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ቤቱን በግድ እንደነጠቀ እያወቀ ቤቱ በእጅህ ስለሌለ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ይናገራሉ።
ተስፋ መቁረጥን አላውቅም የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ በማካካሻነት የወሰዱት ቤት በእጃቸው እንደሌለ እና ጉዳዩ እንደገና እንዲታይላቸው አዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደርን መጠየቃቸውን ይገልጻሉ። ይህን ተከትሎ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደርም «ኮሚቴ ተቋቁሟል፤ ወረዳ ድረስ ሄደን እናጣራለን» የሚል መልስ እንደሰጧቸው ይገልጻሉ።
በማካካሻነት የተሰጠውን ቤት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 07 ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት በጉልበት ቤቱን ሰብረው እንዳስወጧቸው የሚገልጽ ማስረጃ ለተቋቋመው ኮሚቴ ማቅረባቸውን ያስረዳሉ። የተቋቋመው ኮሚቴም በጉለሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 07 የቤት ቁጥር 077 እናንተ ስለመሆኑና ከ1968 እስከ 2007 ዓ.ም መኖራችሁን የሚያሳይ መረጃ ካለ እሱን እንመረምራለን አለ።
ኮሚቴውም ከብዙ ድካም በኋላ ምርመራውን ጨርሶ ቤቱ ለአቶ ጌታቸው እንደሚገባና ከሁለቱ ቤት አንዱን የመመረጥ መብት አላቸው የሚል ውሳኔ ወሰነ የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ የኮሚቴው በምርመራ የደረሰበትን ለውሳኔ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ለፊርማ ያስገቡታል። ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በአስተዳደር የታየውን ወደ ሕግ ክፍል መሩት ።
ይህን ተከትሎ በአስተዳደር የታየውን ወደ ሕግ ክፍል ተመራ ብለው ለዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አቤቱታ ማቅረባቸውን አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ። ምክንያቱም በአስተዳደሩ ያለቀን ጉዳይ ወደ ሕግ ክፍሉ መመራቱ ጉዳዩን መልሶ ሊያበላሸው እንደሚችል ቀድመው መገንዘባቸውን ያስረዳሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ሃብታሙን ማናገራቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ አቶ ሃብታሙም ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማው ከሕግ ክፍሉ የተሰጠውን ውሳኔ ብቻ እንዲወስዱ እንዳስገደዷቸው ያስረዳሉ።
ይህን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢው አቶ ጌታቸውም መውሰድ ካለብኝ በኮሚቴ የተወሰነው ውሳኔ ጭምር እንጂ የሕግ ክፍሉን ውሳኔ ብቻ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አልወስድም ማለታቸውን ይገልጻሉ። ኮሚቴው የወሰነውን ውሳኔ ከሕግ ክፍሉ ውሳኔ ጋር አንድ ላይ ላኩልኝ እና የአቃቂ ቃሊቲ ከፍለ ከተማ የሚሰጠውን ውሳኔ በጸጋ እቀበላለሁ በማለት አቶ ሃብታሙን ቢጠይቁም ለጠየቁት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዳልሰጧቸው ይናገራሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የኮሚቴውን ውሳኔ ለማግኘት ለአንድ ወር ሙሉ አዲስ አበባ ቢሮ መመላለሳቸውን ያስረዳሉ።
በመጨረሻ ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ ሲሆን የሕግ ክፍሉን ውሳኔ ብቻ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር መውሰዳቸውን የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደርም ለምን ይህን ብቻ የሕግ ክፍሉን ውሳኔ ብቻ ይልኩልናል ? ብለው እንደጠቋቸው እና በሕግ ክፍሉ ውሳኔ ብቻ የጠየቁት የይገባኛል ውሳኔ ሊስተናገድ እንደማይችል ገለጹ።
‹የፈሩት ይደርሳል ፤ የጠሉት ይወርሳል› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የሕግ ክፍሉም ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት የተወሰነ ውሳኔ በኮሚቴ ታይቶ ሊቀለበስ አይገባውም የሚል ውሳኔ ማስተላለፉን ይገልጻሉ።
በሚቀጥለው ክፍል ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የተለያዩ አካላትን ምላሽ እና መመሪያዎች ምን ይላሉ የሚለውን ዘገባ ይዘን እንቀርባለን፤ እስከዚያው ቸር እንሰንብት።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም